በኬንያ የምግብ ዋጋ ማሻቀብን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በያዝነውም ሳምንትም ቀጥሏል፡፡ በተደጋጋሚ ጊዜ ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተወዳድረው ባለማሸነፋቸው ‹‹ምርጫ ተጭበርብሯል›› በሚል ተቃውሞ ሲጠሩና መንግሥትን ሲሞግቱ ዓመታትን ያስቆጠሩት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ራይላ ኦዲንጋ ደግሞ የተቃውሞው ግንባር ቀደም መሪ ሆነዋል፡፡
‹‹በኬንያ የኑሮ ውድነት ቢያይልም፣ መንግሥት መፍትሔ አላመጣም፣ በቅርቡ የተደረገውና ዊልያም ሩቶ ያሸነፉበት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የተጭበረበረ ነው፤›› በማለት ደጋፊዎቻቸው ናይሮቢን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በየሳምንቱ ሰኞና ሐሙስ ተቃውሞ እንዲወጡ መጥራታቸውን ተከትሎም፣ ተቃውሞ በነበሩባቸው ቀናት የናይሮቢ እንቅስቃሴ ተስተጓጉሎ መዋሉን ኤቢሲ ኒውስ ዘግቧል፡፡
መንግሥት የተቃውሞ ሠልፉን ሕገወጥ ነው ቢልም፣ ሰኞ መጋቢት 18 ቀን 2015 ዓ.ም. በናይሮቢ ተቃውሞ የወጡ ሲሆን፣ በሠልፉ የተገኙት ኦዲንጋ የምግብ ዋጋ እንዲቀንስና የምርጫ ፍትሕ እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሚስተር ኦዲንጋና በፓርቲያቸው አዚሞ ላ ኡሞጃ እየተመራ ያለው ተቃውሞ፣ የምግብ ዋጋ በመናሩ ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ ከሥልጣን እንዲለቁም የሚጠይቅ ነው፡፡
ኬንያ እንደ ጎረቤት አገሮቿ በተለያዩ ጊዜያት በተለይ ምርጫን ተከትሎ የተቃውሞ የሚካሄድባት፣ ንብረት የሚወድምባትና ሰዎች የሚገደሉባት ቢሆንም፣ በዚህኛው ተቃውሞ ከዚህ በተጨማሪ ለየት ያለ ክስተት አስተናግዳለች፡፡ በሀብታቸው ለሚታወቁት የኬንያ መሪዎችና ፖለቲከኞች ሥጋት የፈጠረ ክስተትም ነበር፡፡
የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት፣ የተወሰኑ ተቃዋሚዎች በቀድሞ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ቤተሰቦች የእርሻ ልማትን አጥቅተዋል፡፡ ከሥፍራው በጎችን የሰረቁ ሲሆን፣ ዛፎችንም ቆርጠው ወስደዋል፡፡
ጥቃቱ በኬንያታ ቤተሰቦች ንብረት ላይ ብቻ ያነጣጠረ ሳይሆን፣ ተቃውሞውን በመሩት በኦዲንጋ የሲሊንደር ጋዝ ማምረቻ ላይም መፈጸሙን አክለዋል፡፡
ሠልፉ ሕገወጥ ነው ያለው ፖሊስ ተቃዋሚዎችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስና ውኃ የተጠቀመ ሲሆን፣ ሦስት ሰዎች መሞታቸውም ተሰምቷል፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ኦዲንጋ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ተቋም ላይ የደረሰውን ጥቃት አውግዘዋል፡፡
ሆኖም ማናቸውም በተቃዋሚዎች በኩል ለሚሰነዘሩ ውድመቶች ኃላፊነት እንደማይወስዱና ተቃውሞ ሠልፍ መውጣትም ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ጋዜጠኞችን ጭምር ዓላማ ያደረገውን የፖሊስ ዕርምጃም ኮንነዋል፡፡ የፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ የኢኮኖሚ ፖሊሲን በመተቸትም፣ ምንም እንኳን የኑሮ ዋጋ ማሻቀብ ዓለም አቀፍ ችግር ቢሆንም፣ በርካታ አገሮች ዜጎቻቸውን ለመደገፍ ሲሠሩ በኬንያ ቀድመው የነበሩ ድጎማዎች መነሳታቸውን ስህተት ብለውታል፡፡ ድርጊቱ በርካታ ኬንያውያን በኑሮ እንዲሰቃዩ ማድረጉንም ጠቁመዋል፡፡
ዓምና በተደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ መሸነፋቸውን ባለመቀበል ኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረቡት አቤቱታ ማሸነፋቸውን ባያረጋግጥም፣ አሁንም ድረስ የሚሞግቱት ኦዲንጋ፣ ከፕሬዚዳንት ሩቶ ጋር ለመወያየት እንደሚፈልጉ፣ ለዚህ ግን ሁለት ቅደመ ሁኔታዎች መሟላት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
የምርጫ ኤሌክትሮኒክ ሰርቨር ተከፍቶ ዓምና የተደረገው ምርጫ መጭበርበርና አለመጭበርበሩ እንዲጣራ እንዲሁም ለኬንያ ምርጫ ቦርድ ሁሉም ፓርቲዎች የሚሳተፉበት አዲስ ኮሚሽነሮች እንዲመረጡ የሚሉትን ጥያቄዎች በማንሳት ይህ ከተፈጸመ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ለመወያየት ፈቃደኛ እንደሚሆኑ ለቢቢሲ ገልጸዋል፡፡
‹‹በኬንያ የኑሮ ዋጋ እንዲባባስ ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሩቶ ናቸው›› የሚሉት ኦዲንጋ፣ ኬንያውያን በከፍተኛ የግብር ምጣኔ እየተጎዱ መሆኑንም ያነሳሉ፡፡ አሁን ያለው የኬንያ መንግሥት ኬንያውያን ከሚሸከሙት በላይ ግብር እየጣለ፣ የንግድና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን እየገደለ ነውም ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ምንም ዓይነት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተሳትፎ ሳይደረግ፣ የኬንያን ኢንዲፔንደንት ኤሌክቶራልና ባውንደሪ ኮሚሽን ዳግም ማዋቀራቸውንም ይቃወማሉ፡፡
ልውጠ ህያዋን ምግቦች (ጄኔቲካሊ ሞዲፋይድ/ጂኤምኦ) ወደ ኬንያ እንዲገባ በመንግሥት መፈቀዱንም አይቀበሉትም፡፡
ውሳኔው፣ ‹‹የኬንያን የምግብ ቅርጫት ለማውደም ነው፡፡ ኬንያውያንን የአሜሪካ ባለሀብቶች ተገዥ ለማድረግ ያለመ ነው፤›› ብለውታል፡፡
ፕሬዚዳንት ሩቶ አገሪቷን በአንድ ፓርቲ አገዛዝ ሥር ለመጣል አቅደው እየሠሩ መሆኑን፣ ፕሬዚዳንቱ ቀስ በቀስ አምባገነን እየሆኑ መምጣታቸውን፣ የመንግሥት ቢሮና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቅጥር በሁለት ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ጎሳ አባላት እየተተካ መሆኑንና ይህም አገሪቷን ለእርስ በርስ ጦርነት እንደሚያነሳሳም ጠቁመዋል፡፡
የኬንያ ስታትስቲክስ ቢሮ በኬንያ ያለውን ግሽበት 9.2 በመቶ ደርሷል ሲል በቅርቡ ያሳወቀ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንቱ ደግሞ የኬንያ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡