Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየሊግ ካምፓኒው የክለብ ፈቃድ አሰጣጥን በተመለከተ ያስጠናውን ጥናት ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን...

የሊግ ካምፓኒው የክለብ ፈቃድ አሰጣጥን በተመለከተ ያስጠናውን ጥናት ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታወቀ

ቀን:

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ‹‹ዘርፈ ብዙ የግምገማ ጥናትና የልማት ፍኖተ ካርታ›› በሚል ርዕስ አስጠንቶ ለክለቦችና ለተለያዩ ስፖርት አካላት ይፋ ካደረገ በኋላ፣ ጥናቱን ወደ ተግባር ለመቀየር እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቋል፡፡

በአሜሪካ ታውሰን ዩኒቪርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር እንዲሁም የፌስ ኮርነር አማካሪ ጋሻው አብዛ (ዶ/ር) አማካይነት ለአንድ ዓመት ከመንፈቅ ከተጠና በኋላ፣ ከሊግ ካምፓኒው ጋር መረካከቡ የተገለጸ ሲሆን፣ ለፕሪሚየር ሊግ ክለቦች መከፋፈሉ ተነግሯል፡፡

በቅርቡ ከሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደሚደረግ የተጠቆመ ሲሆን፣ የመውጫ ዕቅድ (Exit Strategy) ተሰናድቶ በአራት ዓበይት ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረቱን አድርጎ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተገልጿል፡፡

በዚህም መሠረት በጥናቱ ውስጥ በቀዳሚነት ከተጠቀሱት መካከል በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበርና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መካከል ያለው የሥራ ድርሻ፣ የክለብ ይዞታነት፣ የተጫዋቾች የደመወዝ አከፋፈል ሥርዓት እንዲሁም የክለብ ፈቃድ አሰጣጥ (Club Licensing) በቀዳሚነት እንደሚታዩ ተጠቁሟል፡፡

በመውጫ ዕቅዱ መሠረትም በተለይ በመንግሥት ይዞታነት የሚተዳደሩ ክለቦች እንዴት ከመንግሥት ይዞታነት ይላቀቁ የሚለው፣ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት  በኢትዮጵያ የሚገኙ ክለቦች እየተከተሉት የሚገኘው መንገድ እንዴት መላቀቅ አለባቸው የሚለው ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡

በፕሪሚየር ሊጉ እየተሳተፉ ከሚገኙ 16 ክለቦች ውስጥ 13ቱ ክለቦች በመንግሥት ይዞታነት የሚተዳደሩ ሲሆን፣ ክለቦችን ከመንግሥት ነፃ ለማድረግ ምን ዓይነት ሒደቶችን መከተል ያስፈልጋል? በስንት ዓመት ተግባራዊ ይደረግ? እንዲሁም ከነበረው አሠራር ወደ ሌላ አሠራር እንዴት እንግባ የሚለው ጉዳይ ሰፊ ምልከታ ይደረግበታል ተብሏል፡፡

በዚህም ማኅበሩ ክለቦች ሕዝባዊ መሠረት እንዲኖራቸውና ከመንግሥት ይዞታነት እንዲላቀቁ ለማድረግ የቀረበው ጥናትና የመውጫ ዕቅድ ጽሑፍ ለክለቦችና ለሚመለከታቸው ባለድርሻ  አካላት መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፣ በቅርቡም ውይይት እንደሚካሄድ የአክሲዮን ማኅበሩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ክፍሌ ሰይፉ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ጥናቱ በዋነኛነት በክለብ ፈቃድ አሰጣጥ የክለብ የባለቤትነት ይዞታና የተጫዋቾች የደመወዝ ክፍያ አስተዳደር ጋር በተያያዘ የሚያጠነጥን እንደሆነ ይፋ መሆኑ ይታወሳል፡፡

ክለቦች በፕሮፌሽናል መንገድ እንዲመሩ ለማስቻል በሊግ ውድድር ውስጥ ለመሳተፍ ሊያሟሉ የሚያስፈልጋቸውን ዝቅተኛ መሥፈርቶች ይዞ የክለብ ፈቃድ አሰጣጥ መመርያ በፊፋ መሰናዳቱ ይታወቃል፡፡

የክለቦች ፈቃድ አሰጣጥ መሥፈርቱ በአነስተኛ ደረጃ ማሟላት ያለባቸው መጠይቆች እንደመሆናቸው፣ በጊዜ ሒደት በሁሉም ዘንድ የመመርያው ተፈጻሚነቱ የግድ እንደሚሆን በጥናቱ መቅረቡ ይታወሳል፡፡

በኢትዮጵያ ተፈጻሚ የሚሆነው መመርያው ካፍ ባሰናዳው ላይ የሚመረኮዝ ሲሆን፣ አምስት መመዘኛዎች ማለትም የስፖርት፣ የመሠረተ ልማት፣ የሰው ኃይል፣ የሕግ፣ የፋይናንስ ጉዳዮች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡

በሌላ ዜና የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር አራተኛ መደበኛና ሁለተኛ አስቸኳይ ጉባዔውን መጋቢት 16 ቀን 2014 ዓ.ም. አከናውኗል፡፡

በጉባዔው አባላት በቀረቡ አጀንዳዎች ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ በዋናነት የመርሐ ግብሩ አካል የሆነው የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ በመሆኑ አዲስ የአመራሮች ምርጫ ተከናውኗል፡፡

በዚህም መሠረት ሰባት የቦርድ አባላት ተመርጠው የሥራ ክፍፍል የተደረገ ሲሆን፣ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ከኢትዮጵያ ቡና የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ፣ ጌቱ ደጉ (ረዳት ፕሮፌሰር) ከወልቂጤ ከተማ የቦርድ ምክትል ሰብሳቢ፣ አቶ አብዮት ብርሃኑ (ከፋሲል ከነማ)፣ አቶ አሰፋ ሆሲሳ (ወላይታ ድቻ)፣ አቶ ልዑል ፈቃዱ (ባህር ዳር ከተማ)፣ አቶ ንዋይ በየነ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) የቦርድ አባል ተደርገው ተመርጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተላቆ ራሱን በራሱ ማስተዳደር ከጀመረ በኋላ በርካታ ለውጦችን እያመጣ ሲሆን፣ ተመራጩ ቦርድ ክለቦች ከመንግሥት ይዞታነት ተላቀው ሕዝባዊ መሠረት እንዲኖራቸው ማድረግ ትልቅ ኃላፊነት ይጠብቀዋል፡፡

በሊጉ እየተሳተፉ የሚገኙ ክለቦች ከመንግሥት ይዞታነት ተላቀው በግላቸው ንብረት በማፍራት የፕሮፌሽናል መንገድ እንዲከተሉ ማድረግ የአክሲዮን ማኅበሩ የቤት ሥራ ያደርገዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...