Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹ኢትዮጵያን ሊያፈርስ የሚችል ኃይል እንኳን በኢትዮጵያ በሌላም ቦታም አለ ብለን አናስብም›› ...

‹‹ኢትዮጵያን ሊያፈርስ የሚችል ኃይል እንኳን በኢትዮጵያ በሌላም ቦታም አለ ብለን አናስብም›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

ቀን:

‹‹አሁን ባለው ሁኔታ የዜጎች ደኅንነትና የአገር ሉዓላዊነት የሥጋት ምንጭ ራሱ መንግሥት ነው››

አቶ ክርስቲያን ተደለ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአብን ተወካይ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከእንግዲህ ኢትዮጵያን ሊያፈርስ የሚችል ኃይል እንኳን በኢትዮጵያ ውስጥ ከኢትዮጵያ ውጭም አለ ብለው እንደማያስቡ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ማክሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው 11ኛው መደበኛ ስብሰባና ከ325 በላይ አባላት በተገኙበት፣ የመንግሥታቸውን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም አስመልክተው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡

ከምክር ቤት አባላት መካከል አቶ ጀምበርነህ አያልነህ የተባሉ አባል፣ በብልፅግና የሚመራው መንግሥት አገሪቱን ለማፍረስ አቅዶ እየሠራ ነው በሚል ወቀሳ እየቀረበ ስለመሆኑ ስለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ ‹‹በጥያቄ ደረጃ የተከበረ ጥያቄ ነው፣ ነገር ግን የዓመቱ ምርጥ ቀልድ አድርጌ ነው የምወስደው፣ ከዚህ ባለፈ ግምት አልሰጠውም፤›› የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡

‹‹ይህ ምክር ቤት ዘንግቶት ቢሆንም ድፍን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያውቀው ነው፣ የኢትዮጵያን ክብር አላስደፍርም ብሎ የቆመን መንግሥት ሊያፈርስ ነው የሚሠራው ብሎ መጠየቅ፣ ጥሩ ቀልድ ከመሆን ባለፈ ትርጉም አይሰጥም›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጥለውም፣ ልትገነቡ ልታንጹ ሞክራችሁ ያልቻላችሁት ነገር አለ እናግዛችሁ አስተካክሉ፣ አርቁ ከሆነ፣ ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን አስባችሁ ልታፈርሱ ነው፣ ከሆነ ግን ማነው የሚያቆመን ታዲያ፣ እኛ አገር ለማፍረስ የምንሠራ ከሆነ ማነው አገርን ለማቆም የሚከለክለን ኃይል ሲሉ አባለቱን ጠይቀዋል፡፡

የፀጥታና የአስፈጻሚ አካላትን ለአብነትም፣ የአገር መከላከያ፣ ደኅንነትና ፖሊስ ተቋማትን የገነባንበት መንገድ አገር ለማጽናት ያለንን ተነሳሽነት የሚያሳይ ነው ያሉት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ በማይታወቀው ልክ፣ በቁጥጥርም በጥራትም፣ በቴክኖሎጂም ብዙ የአፍሪካ አገሮች የሚቀኑባቸው ተቋማት መገንባታቸውና ያን እያደረጉ ያሉት ደግሞ ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ የመፍረስ ሥጋት አልፏል፣ እንደዚህ ዓይነት ሥጋት እኛ የለብንም፣ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚነሳ ኃይል ካለ ኢትዮጵያን ለማጽናት የሚቻል የተሻለ ኃይል ስለገነባን ከእንግዲህ ሥጋት የለብንም፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ሥጋት ነበረብን፣ ምክንያቱም እንደዚህ አድርገን ስላልገነባን፣ አሁን ግን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚቻል ኃይል እንኳ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሌላም ቦታ ይምጣል ብለን አናስብም፣ ብዙ ሥጋት አያስፈልግም›› በማለት ለአባላቱ ተናግረዋል፡፡

ዴሞክራሲን ለመገንባት ጥረት እያደረጉ መሆኑንና ነፃ ሚዲያ፣ ነፃ ሐሳብና ነፃ ምርጫ ሙከራ እየተደረገ ስለመሆኑ አብራርተው፣ ይህን ዴሞክራሲን ለመገንባት የሚደረገው ጥረት በቀና መንገድ በማሰብ፣ ‹‹በሐሳብ ገበያ ተወዳድሮ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመተካካት የማንሠራ ከሆነ፣ የመንግሥት መንገድ የሚሆነው ፈላጭ ቆራጭ እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡ በዚህም ዴሞክራሲ ካልተገነባ ፈላጭ ቆራጭ ሥርዓት እንደሚገነባ፣ ፈላጭ ቆራጭ ሥርዓት ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ በፊት ተሞክሮ ባለመሳከቱ ቢተገበር የሚመጣው መበታተን በመሆኑ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም ሲባል ዴሞክራሲን ከእነ እንከኑ ማስቀጠል እንደሚሻል ገልጸዋል፡፡

በኃይልና በሴራ የሚታሰበው ነገር ያው የተሻለ ኃይል ያለው መንግሥት ስለሆነ ወደ ጉልበት ይሄዳል በዚያም ጥፋት ይፈጠራል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አባል አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ ‹‹አሁን ባለው ተጨበጭ ሁኔታ የዜጎች ደኅንነትና የአገር ሉዓላዊነት ዋነኛ የሥጋት ምንጭ ሆኖ የምናየው ራሱ መንግሥት ነው፡፡ የበርካታ አገሮች መሪዎች ኃላፊነትን በወጉ ሳይወጥኑ ሲቀሩ ሕዝብን ይቅርታ ጠይቀው ሥልጣናቸውን እንደሚለቁት ሁሉ እርስዎስ ሥልጣንዎን በመልቀቅ የመፍትሔ አካል ለመሆን አላሰቡም ወይ?›› በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው፣ ነገር ግን ጥሩ ጥያቄ የሚሆነው ሥልጣንን ብንለቅ ቢሉ ነው፣ ምክንያቱም መንግሥት ማለት አስፈጻሚ ማለት አይደለም፣ ሕግ አውጭውንም፣ አስፈጻሚውንም ተርጓሚውም መንግሥት በመሆኑና እኛ እዚህ ውስጥ ያለን ሰዎች የመንግሥት ባለሥልጣን በመሆናችን፣ ይልቁንም አቶ ክርስቲያን የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆናቸውና በጋራ ብንለቅ የሚሉ ቢሆን የተሻለ ነው ብለዋል፡፡ ምክንያቱም የሁሉም ችግር ምንጭና ባለቤት እኔ ብቻ ልሆን አልችልም፣ ኃላፊነት ከወሰድንም በጋራ ቢሆን ጥሩ ነው ብለዋል፡፡

ሥልጣን በሚመለከት የሥልጣን ባለቤት ሕዝብ ነው፣ ሥልጣን ሰጪም ነፋጊም ሕዝብ ነው፣ መሆን ያለበት የተሻለ ሐሳብ ይዞ ወደ ሕዝብ መቅረብና የእኔን ሐሳብ ምረጡልኝ ብሎ በሰጪው መመረጥ እንጂ፣ በምክር ቤት ውስጥ ስጠኝ ልቀቀኝ በሚል አይሆንም ብለዋል፡፡

በመሆኑም ‹‹ሥልጣን በኮሮጆ እንጂ በመናጆ አይያዝም››ና ለምርጫ ሦስት ዓመት ይቀራል፣ በውጪም ‹‹የኦሮሞ መንግሥት፣ የኦሮሞ መንግሥት›› እያሉ የሚዘፍኑ ዘፋኞች አሉ፣ እነሱን ጨምሮ ሰብሰብ ብሎ ሐሳብ አጠናክሮ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማቅረብ የተሻለ ስመሆኑ ገልጸዋል፡፡

‹‹እኛ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የገባንው ቃል ካልመለስን የኢትዮጵ ሕዝብ በእኛ አስተዳደር ካልረካ፣ በምርጫ ከጣለን በተደጋጋሚ እንዳልነው ሥልጣንን በደስታ እናስረክባለን፣ ፓርቲዎች መዘጋጀት ያለባቸው ሐሳብ ይዘው መምጣት ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ሐሳብ የለም፣ ሰብሰብ ብሎ ሐሳብ ይዞ ያንም ወደ ሕዝብ አቅርቦ ለመመረጥና ለማሸነፍ የሚደረግ ጥረት ለሁሉም ስለሚጠቅም በዚህ አግባብ ቢታይ ይሻላል ብለዋል፡፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው የገቡ የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎችን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ደቡብ ሱዳን የሰው አገር ለመውረር የሚያስችል ቁመናም ፍላጎትም እንደሌላት ጠቅሰው፣ በወረራ መንገድ ባይገለጽ ጥሩ እንደሚሆን ለአባላቱ አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ድንበራችን የሚያሠጋ ነገር አይፈጠርም፣ በአርብቶ አደር መካከል ከደቡብ ሱዳንም፣ ከኬንያም አልፎ አልፎ የሚያጋጥም ችግር ነው ብለዋል፡፡ ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ጋር በመወያየት ችግሩን በጋራ ለመፍታት መግባባት ላይ የተደረሰበት ጉዳይ ስለመሆኑ አክለው ገልጸዋል፡፡

በመንግሥት ኦነግ ‹‹ሸኔ›› እየተባለ የሚጠራውን ኃይል በተመለከተ የብልፅግና ማዕከላዊ ኮሚቴ ተወይቶ በፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት የሚመራ የሰላም ኮሚቴ መቋቋሙን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

ከቤኒሻንጉል፣ ጋምቤላ፣ ቅማንት ጋር የተሻሉ ውጤቶች መገኘታቸውን አብራርተው፣ ኦነግ ሸኔን በሚመለከት ባለፉት ሁለት ወራት ገደማ ከአሥር በላይ ሙከራዎች ተደርገው እንደነበር፣ ነገር ግን አንድ የተሰባሰበ ኃይል ባለመኖሩ የምንነጋገራቸው ኃይሎች የተለያየ አቋምና ፍላጎት ይዘው ስለሚመጡ አስቸጋሪ ሁኔታ ስለመፈጠሩ አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ያቀረበው የሰላም ጥሪ የሚባለው የኦሮሚያ መንግሥት ያቀረበው ሳይሆን እንደ ፓርቲ ውይይት ተደርጎና ተወስኖ፣ በምክትል የፓርቲው ፕሬዚዳንት የሚመራው ኮሚቴ ተቀጥያ፣ በኦሮሚያ ስለመጀመሩ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጠቃላይ የአገሪቱን የሰላም ሁኔታ አስመልክተው ማብራሪያ ሲሰጡ፣ አሁን ላይ የሚታየው ሰላም እጅግ የተሻለና የዛሬ ስድስት ወር በፊት ከነበረው የተሻለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይሁንና ሰላም ሲባል አንፃራዊ መሆኑን ለአባላቱ በመግለጽ፣ ይሁን እንጂ የጦርነት ነጋሪት የሚጎስሙ በርካታ ዜጎች ያሉበት አገር ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

እንደ ጦርነት ጊዜ ሁሉ በሰላም ጊዜም ጀግንነት እንደሚያሰፈልግ ጠቀሰው፣ ጦርነት የሚጎስሙ ኃይሎች ጦርነትን በቅርበት የማያውቁ፣ በርቀት ሆነው ግጭትን በስፋት የሚሰብኩና ሰው የሰላም መንፈስ እንዲይኖረው የሚያደርጉ ስለመሆናቸው እንስተዋል፡፡ እነዚህ የጦር ነጋሪት ጎሳሚ ኃይሎች ግጭት እንደሚፈበርኩ፣ ቀድመው እንደሚያቅዱ፣ አብዝተው በስፋት እንደሚዘግቡና ገለው ሞተ እንደሚሉ አስረድተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የሰላም አየር በተሟላ መንገድ ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስፈን ፈተና ሲሆን ቆይቷል ብለዋል፡፡

ላለፉት 50 እና 60 ዓመታት እንደ ኃጢያት ሆኖ በኢትዮጵያ የዘለቀው ፖለቲካ የመጠላለፍ፤ የሴራ ፖለቲካ እንዲሁም የጉልበት ፖለቲካ እንጂ በሐሳብ ልዕልና፣ በንግግርና በውይይት ፍላጎትን ማረጋገጥ ሳይሆን ወይም ጉልበት ለመፈጸም እንደሚኬድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡ በዚህም ጉልበት ከሌለ ሴራ እንደሚሆን፣ በሴራ ፖለቲካ በንፁኃን ደም የሚሸቀጥና ከዚያ ሲያልፍ መጠላለፍና ሰላምን እንደሌለ አድርጎ መስበክ የተለመደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹ስትዋጋ ሰላም አምጡ የሚሉ ኃይሎች፣ ሰላም ሲመጣ ደግሞ እንዴት ሰላም ይመጣል ይላሉ፣ ይህ ደግሞ የሴራ ፖለቲካ ውጤት አካል ነው፤›› ብለዋል፡፡

የሚዲያ ተቋማትን በተመለከተ ሲያብራሩ፣ በርካታ ሚዲያዎች መርዝ ወደ ሕዝቡ ስለሚረጩ ሕዝቡ መርጦ ያድምጥ ብለዋል፡፡ ይህም አድማጩ ኃላፊነት እንዳለበት ማሳያ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ሰፊ ችግር እንዳለባቸው ጠቅሰው፣ ራሳቸውን በስፋት መፈተሽ እንዳለባቸው የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አንደኛ የሌለ ግጭት ይፈጥራሉ፣ ያልሞተ ሰው ገለው ይዘግባሉ፡፡ ስለዚህ ሕዝብ ፈቅዶ መስማት እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡ አክለውም ‹‹ያጋጫሉ፣ ይገላሉ፣ ይሾማሉ፣ ይሽራሉ፣ በመሆኑም እንደ እነዚህ ዓይነት የጥፋት ሚዲያዎች ራሳቸውን በደንብ ማየት አለባቸው፣ አድማጩም እየነጠለ መትፋት አለበት፣ ብለዋል፡፡

ሚዲዎች ግጭት መፍጠር ብቻ ሳይሆን ግጭት ያበዛሉ፣ አንድ ሰው ከሞተ 50 ይላሉ፣ 50 ከሞተ 100 ይላሉ፡፡ ግጭት ካጡ ደግሞ ታሪክ ይመዛሉ፣ የዛሬ 50 ዓመት እኮ በሚል ታሪክ እንደሚመዙ አስረድተዋል፡፡

 በመሆኑም እነዚህ ሚዲያዎች ‹‹ከአንገት ላይ ሀብል ለመውሰድ አንገት የሚቆርጡ ሚዲያዎች ናቸው ›› ብለዋቸዋል፡፡ ሀብሉን መቁረጥ ወይም መፍታት ሳይሆን አንገት ቆርጠው ሀብል መውሰድ የሚሹ ስለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡

ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ መዘዋወርን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲያብራሩ፣ በነፃ መዘዋወር መብት ነው፣ ማንም ሰው ከአንድ ሥፍራ ወደ ሌላ ሥፍራ ሕጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሠርቶ ማደር መብቱ ነው፡፡ ይህ መብቱ እንዲከበርም አብዝተን መሥራት ይኖርብናል ብለዋል፡፡ ነገር ግን በዚህ ሁለት ዓመት ውስጥ ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው ፍልሰት ቀላል አለመሆኑን ጠቅሰው፣ ለምሳሌ በሁለት ዓመት ወደ አዲስ አበባ የተደረገው ፍልሰት ቁጥር አምስትና ስድስት ዓመት ከነበረው እንደሚበልጥ አስረድተዋል፡፡

‹‹መንገድ ተዘጋ ሲባል እንቅስቃሴ አልቆመም›› ያሉት ዓብይ (ዶ/ር)፣ በቅርቡ በተደረገ ጥናት አዲስ አበባ አካባቢ ሕገወጥ በሆነ መንገድ ገብተው ከሚኖሩት ዜጎች መከካል 96 በመቶ የሚሆነው የአዲስ አበባ ነዋሪ አይደለም ብለዋል፡፡

‹‹አዲስ አበባን የብጥብጥ ማዕከል ማድረግ አለብን፣ አዲስ አበባ ውስጥ ሁከት ካላስነሳን በስተቀር በቀላሉ መንግሥትን መነቅነቅና ሥልጣን መያዝ አንችልም›› በሚል በአገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኃይሎች በተቀናጀ መንገድ በርካታ ሙከራዎች ሲያካሂዱ እንደነበር አንስተዋል፡፡

በመሆኑም ይህንን ለመከላከል ሰፊ ሥራ መሠራቱንና ውጤት ማምጣቱን አውስተው፣ ምንም መርጃ ሳይኖር የተሠራ ሥራ የለም ብለዋል፡፡ ከዚህ በመነሳት ግጭት ለማስቀረት በሚደረጉ ሥራዎች ሥጋት እንደሚገታ፣ ነገር ግን መጉላላት የሌለባቸው ዜጎች እንደሚጉላሉ አንስተው ይህ መታረም እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ ሲደረጉ ከነበሩ ጉዞዎች በአንድ ቀን፣ በአንድ ቀበሌ፣ በአንድ ሰው ፊርማ፣ አንድ ሙሉ ባስ በወረቀት ተልኮ ቀድሞ መረጃ ስለደረሰን በቁጥጥር ሥር አውለን እናውቃለን ብለዋል፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የክልልነትን ጥያቄ በተመለከተ ሲያብራሩ የፖለቲካ ሰዎች ክልል እንሁን ሲሉ፣ መንገድ ይሠራልሃል፣ ልማት ይመጣልሃል፣ ችግር የለውም ብለው እንደሚቀሰቅሱና ቅስቀሳው ተደርጎ ክልል ሲፈጠር ወዲያው ዞን፣ ወረዳ እየተባለ ሲስፋፋ የሚፈጠረውን የበጀት ችግር አንስተዋል፡፡

ደርግ ወድቆ ኢሕአዴግ ሲገባ 230,000 ያህል የመንግሥት ሠራተኛ እንደነበሩ የጠቀሱት ዓብይ (ዶ/ር)፣ አሁን ላይ ይህ ቁጥር አድጎ 2.6 ሚሊዮን መድረሱን አንስተዋል፡፡

አዲስ ክልል ከተመሠረተ በኋላ የሚታየው ደስታ አንድ ሳምንት እንደማይቆይና ርቆ ሳይሄድ የደመወዝ መክፈል ጥያቄ ችግር እየተነሳ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢኮኖሚው ዘርፍ ባለፉት ስድስት ወራት የነበረውን አፈጻጸም ሲያብራሩ፣ የኢትዮጵያን ዕድገት እየተገዳደሩ ያሉ መሰናክሎች ያሏቸው፣ አገሪቱ የተበደረችው የውስጥና የውጭ ብድር ጫና፣ የዋጋ ንረት፣ የመሠረተ ልማቶች ክፍተት እንዲሁም የፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም የሚሉትን አንስተዋል፡፡

የዋጋ ንረቱ የተባባሰው ለ20 ዓመታት የቀጠለው የሸቀጦች ግሽበት፣ በአምራችና ሸማች መካከል የፍላጎት ልዩነት፣ ከውጭ የሚገባ የዋጋ ንረት፣ ድርቅ፣ ጦርነት እንዲሁም ወደ ከተማ በሚደረግ ፍልሰት የተነሳ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

መንግሥት የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የምርት አቅርቦትን ማሳደግ፣ በጀት ሲመደብ አመዛኙን ተገንዘቦ ድህነት ቅነሳ ላይ እንዲያተኩር ማድረግ፣ ከተሞች ላይ የመመገቢያ ማዕከላት መገንባት፣ የዳቦ ፋብሪካዎች ግንባታና የማዕድ ማጋራት መጀመር መልካም ጅማሮዎች ስለመሆነናቸው ተናግረዋል፡፡

በስምንት ወራት ውስጥ መንግሥት ለነዳጅ ድጎማ 58 ቢሊዮን ብር ማውጣቱን፣ በዚህም 133 ሺሕ ተሽከርካሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን፣ በተያዘው ዓመት ለማዳበሪያ 21 ቢሊዮን ብር ድጎማ እያደረገ መሆኑን፣ ለስኳርና ዘይት በፍራንኮ ቫሉታ አሥር ቢሊዮን ብር በሚያወጣ ገንዘብ መደጎሙን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ባለፉት ሰባት ወራት የተጣራ ታክስ 210 ቢሊዮን ብር ማስገባቱንና አጠቃላይ ወጪው ደግሞ 376 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስረድተዋል፡፡

ወደ ውጭ መላክ የነበረበት ወርቅና ጫት በሕገወጥ መንገድ እየወጣ መሆኑን የገለጹት ዓብይ (ዶ/ር)፣ በ2014 ዓ.ም. ከአሶሳ 20 ኩንታል ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም፣ በተያዘው ዓመት ግን ሦስት ኩንታል ወርቅ ብቻ ነው የቀረበው፡፡ በተመሳሳይ በጉጂ የሚመረተው ታንታለም በሕገወጥ መንገድ እየተላከ፣ የማያመርቱ የጎረቤት አገሮች ኢትዮጵያ ከምታገኘው በላይ ወደ ውጭ ገበያ እንደሚልኩ አንስተዋል፡፡

ወደ ውጭ ከተላከ አገልግሎት 4.3 ቢሊዮን ዶላር፣ ከውጭ ኢንቨስትመንት 2.2 ቢሊዮን ዶላር አገሪቱ ማግኘት የቻለች ቢሆንም፣ የገቢ ንግዱ 9.1 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡

የፋይናንስ ተቋማት ባለፉት ሰባት ወራት 311 ቢሊዮን ብር ያበደሩ ሲሆን፣ ካበደሩት የሰበሱቡት ደግሞ 172 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

በመሠረተ ልማት ግንባታ በተለይም በሥራ ላይ ላሉ ከ320 በላይ የመንገድ ፕሮጀክቶች አንድ ትሪሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ አንስተዋል፡፡ በመንገድና ሌሎች መሠረተ ልማት ዘርፎች የሚጠየቅ የካሳ ክፍያ ግብር የተከፈለበት ሕገወጥ ንግድ ሆኗል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፡፡

በቱሪዝም ዘርፍ መንግሥት ገበታ ለትውልድ በሚል አዲስ ፕሮጀክት መጀመሩን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህም እስከ ሰባት ቢሊዮን ብር ይገኛል በሚል ከአንድ ወር በፊት ዕቅድ የወጣ ቢሆንም፣ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አምስት ቢሊዮን ብር አልፈናል ብለዋል፡፡

በዚህ ገበታ ለትውልድ በተሰኘ የፕሮጀክት ላይ በሚገኘው ገንዘብ ስምንት ፕሮጀክቶች የሚገነቡት መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም በትግራይ ገራአልታ ሪዞርት፣ በአማራ ሐይቅ ዳርቻ ላይ፣ በጂማ፣ በአፋር፣ በአርባ ምንጭና በሶማሌ ክልል የሚገነቡ ሪዞርቶች መታሰባቸውን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...