የአደንዛዥ ዕፅ፣ የወርቅና የሌሎች የከበሩ ማዕድናት ሕገወጥ ዝውውር ላይ የተሳተፉ 187 የውጭ ዜጎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ፡፡
በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ያለ ምንም ፈቃድ በሕገወጥ መንገድ የአገር ሀብትን ሲያወጡና ወደ ጎረቤት አገሮች ሲያስተላልፉ የተገኙ 83 የውጭ አገሮች ዜጎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን፣ የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ ተናግረዋል፡፡ ምክትል ኮሚሽነሩ ይህንን የተናገሩት ሰኞ መጋቢት 18 ቀን 2015 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በዕረፍታቸው ወቅት ባደረጉት ጉብኝት ከመረጣቸው ሕዝብ ለቀረበ ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጡ ተገኝተው ማብሪሪያ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡
በማዕድናት ሕገወጥ ዝውውር ከተገኙት በተጨማሪ ከ82.8 ኪሎ ግራም በላይ ኮኬይን፣ 9.7 ኪሎ ግራም ካናቢስ፣ 9.2 ኪሎ ግራም ኪሎ ግራም ኦፒየም አደንዛዥ ዕፆች ሲያዘዋውሩ የተገኙና ቁጥራቸው በኮሚሽነሩ ያልተገለጸ የ16 አገሮች ዜጎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቀዋል፡፡
ምክትል ኮሚሽነሩ በቁጥጥር ሥር የዋሉት አደንዛዥ ዕፆች በዓለም ገበያ በሚሸጡበት ዋጋ ሲተመን በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ዋጋ እንዳለው ጠቅሰው፣ ይህንን ድርጊት ከውስጥም ከውጭም ያሉ ሰዎች በሕገወጥ ሰንሰለት የሚሳተፉበት መሆኑን፣ ግለሰቦቹም በፀጥታና በደኅንነት ተቋማት ጥረት በቁጥጥር ሥር የዋሉ ናቸው ብለዋል፡፡
በማዕድናት ቁፋሮ በሕገወጥ መንገድ ተሰማርተው ተገኙ የተባሉት የውጭ ዜጎች የሥራ ፈቃድ የሌላቸው ከመሆናቸውም በላይ፣ በየአገራቸው በተለያዩ ወንጀሎች በፍርድ ቤት የሚፈለጉ ዘራፊዎችና ማፊያዎች መሆናቸውን መረጋገጡን አስታውቀዋል፡፡
የማዕድን ዝርፊያዎች የተፈጸሙት ከኢትዮጵያውያን ጋር በመተባበር መሆኑን አውስተው፣ ‹‹መንግሥት በዓመት ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አገኛለሁ ብሎ ሲጠብቅ በሕገወጥ መንገድ ከምርት ማጓጓዝ ጀምሮ የተሳተፉ ወንጀለኞች በየብስና በአየር ሊወጡ ሲሉ በቁጥጥር ሥር ውለዋል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ በኮንትሮባንድ ሲዘዋወር የነበረ ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ሸቀጥ፣ ወደ መሀል አገር ሊገባ ሲል በቁጥጥር ሥር መዋሉን ጠቁመዋል፡፡
ፌዴራል ፖሊስ ባለፉት ስድስት ወራት ባደረገው ምርመራ ከ45 ቢሊዮን ብር በላይ ከሙስናና ምዝበራ የአገር ሀብትን የማዳን ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡ ላለፉት 20 እና 30 ዓመታት ወደኋላ ተመልሶ ማየት ቢቻል የመንግሥት የመቆጣጠርና የመመርመር አቅም በዚህ ደረጃ እንዳልነበረ ጠቅሰው፣ ‹‹የምርመራ ሥራዎቻችን የዜጎችን የሰብዓዊ መብት ባከበረ መንገድ እየተከወናወኑ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ምክትል ኮሚሽነሩ እንደገለጹት፣ ባለፉት ስድስት ወራት በተፈጸሙ 70 የመንገድ ዝርፊያዎች ላይ ምርመራ ተደርጓል፡፡
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የዝርፊያ ኬላዎች እንዳሉ የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ከ70 የምርመራ ጉዳዮች ውስጥ 28 ዘራፊዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ውስጥ ተመጣጣኝ ሕጋዊ ዕርምጃ የተወሰደባቸው እንዳሉም አክለዋል፡፡
በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሃይማኖትን፣ ማንነትንና የመሳሰሉ መነሻ ያደረጉ 67 ግጭቶች መከሰታቸውን ጠቅሰው፣ በእነዚህ ግጭቶች 644 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስረድተዋል፡፡