Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበደራ ወረዳ ከ100 በላይ ሰዎች በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መታገታቸው ተገለጸ

በደራ ወረዳ ከ100 በላይ ሰዎች በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መታገታቸው ተገለጸ

ቀን:

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ከ100 በላይ ሰዎች የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ማገታቸውን፣ የታጋቾች ቤተሰቦችና ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የታጋቾች ቤተሰቦች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ታጣቂዎቹ ነዋሪዎችን ማገትና ማፈናቀል ከጀመሩ ረዥም ጊዜያት ቢቆጠሩም፣ በ2015 ዓ.ም. ግን ለተወሰኑ ወራት ፋታ አግኝቶ እንደነበር፣ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ እንደ አዲስ እንደተቀሰቀሰና በዚህም ነዋሪዎቹ እየታገቱ፣ እየተፈናቀሉና ቤት እየተቃጠለ ነው፡፡

በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር የነበሩ የደራ ወረዳ ሰባት ቀበሌዎችን ከሁለት ወራት በፊት በተደረገ ዘመቻ ነፃ ማድረግ ተችሎ እንደነበር ያስረዱት ነዋሪዎቹ፣ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ግን ጥቃት ማገርሸቱን አክለው ገልጸዋል፡፡

‹‹እኔ የማውቃቸው እንኳ ከ30 በላይ ሰዎች ታግተዋል›› ያሉት አቶ አራርሳ አብዱ የተባሉ የባቦ ደሬ ነዋሪ፣ ‹‹በአጠቃላይ ከ100 በላይ ሰዎች ቢታገቱም የተወሰደ ዕርምጃ የለም፡፡ ፌዴራል ፖሊስ ግን ባቡ ደሬ ካምፕ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ግን ዕርምጃ እየወሰደ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

ሪፖርተር በስልክ ያነጋገራቸው አምስት የወረዳው ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ የአካባቢው ነዋሪዎች በታጣቂ ቡድኑ እየተሰቃዩ መሆናቸውን፣ በርካታ ሰዎች በየቀኑ እየታገቱና እየተፈናቀሉ እንደሆኑ፣ የታገቱ ሰዎችን ለማስመለስም የሸኔ ታጣቂዎች እስከ 200 ሺሕ ብር እየጠየቁ ስለሆነ በዚህ ኑሮ ውድነት ማግኘት አልተቻለም ሲሉ በምሬት ተናግርዋል፡፡

ታጣቂ ቡድኑ ጥቃት እያደረሰ ያለው በወረዳው በሚገኙ ባቡ ደሬ፣ ማንቃታ፣ ጅሩ፣ አድዓ መልኬ፣ ከሩ ሲባ በተባሉ ቀበሌዎች መሆኑን ነዋሪዎቹ አስረድተዋል፡፡

ተቀስቅሷል የተባለውን ጥቃት በተመለከተ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው የደራ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሺበሺ አያሌው፣ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ሰሞኑን ነዋሪዎችን በማገት ጥቃት እያደረሱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሰኞ መጋቢት 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ሦስት ሰዎች በታጣቂ ቡድኑ ታግተው የነበረ ቢሆንም፣ በተደረገ ክትትልና ዕርምጃ ጅማ በር ተብሎ ከሚጠራ ሥፍራ ሲደርሱ ማስመለስ እንደተቻለ የገለጹት አቶ ሺበሺ፣ ‹‹ንፁኃን ሰዎች በታጣቂዎች ሲታገቱ ወዲያው ከሰማን ለማስመለስ እንሠራለን፡፡ ካልሰማን ግን ምንም ማድረግ አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡

ታጣቂዎቹ ሰዎችን አግተው አቦቴ የሚባል ጫካ ውስጥ እንደሚያስቀምጧቸው ያስረዱት የወረዳ አስተዳዳሪው፣ ታጣቂ ቡድኑ የሚያደርሰውን ጥቃት ለማስቆም የግድ ኃይል መጨመርና ዕርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ፣ ይህን ለማድረግም የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ነዋሪዎቹ ባቡ ደሬ ቀበሌ የፌዴራል ፖሊስ ቢኖርም ታጣቂዎች የሚያደርሱት ጥቃት መከላከል አልቻለም ሲሉ የወቀሱ ሲሆን፣ አቶ ሺበሺ በበኩላቸው ከማክሰኞ መጋቢት 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ዕርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል፡፡

የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋና የተለያዩ ዞኖች ጥቃት እንደሚያደርሱ ይታወቃል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ትናንት መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎችን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹መንግሥት ከሸኔ ጋር ለመደራደር ባለፉት ጊዜያት ከአሥር ጊዜ በላይ ሙከራ አድርጓል፡፡ ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...