Tuesday, September 26, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የሰላም ዕጦትና የኑሮ ውድነት አሁንም የአገር ፈተና ናቸው!

ማክሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በርካታ ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡ ጥያቄዎቹ በአመዛኙ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ ነበሩ፡፡ ምንም እንኳ የምክር ቤት አባላት በአመዛኙ የልማት ችግርን ከፍተኛ ትኩረት ቢሰጡትም፣ መሬት ላይ ከሚታየው ምስቅልቅል አኳያ ለሰላም ዕጦትና ለኑሮ ውድነት ያሳዩት ፍላጎት አነስተኛ ነበር፡፡ የገዥው ፓርቲም ሆኑ ቁጥራቸው በጣም አነስተኛ የሆነው የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች፣ መሠረታዊ በሚባሉ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በመካከላቸው ያለው ርቀት በጣም ሰፊ እንደሆነም ተስተውሏል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከምንም ነገር በላይ ለሕጉ፣ ለወከላቸው ሕዝብና ለህሊናቸው ተገዥ ነበሩ ወይ ከማለት ይልቅ፣ ለፖለቲካዊ ውግንና የሰጡት ሥፍራ ከፍ ያለ በመሆኑ የፓርላማው ውሎ ያን ያህል ነበር ማለት ይቀላል፡፡ የፓርላማ አባላት ተወክለው የመጡበትን አካባቢ ልማት በተመለከተ ጥያቄዎችን ማዥጎድጎዳቸው ተገቢ ቢሆንም፣ የአገርን ህልውና እየተፈታተኑ ያሉትን የሰላም ዕጦትና የኑሮ ውድነት ለማቃለል የሚረዱ መፍትሔዎች እንዲገኙ ግፊት አለማድረጋቸው ደግሞ አስገራሚ ነው፡፡  

በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ የብዙዎች ፍላጎት ከምንም ነገር በላይ ሰላም ሰፍኖ የኑሮ ውድነቱ እንዲረጋጋ ነው፡፡ ሰላም እንዲሰፍን የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ ከኃይል ድርጊቶች በመላቀቅ፣ በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆናቸውን ሊያሳዩ ይገባል፡፡ አሁን የተሟላ ሰላም ሰፍኖ ሕዝባችን ያለ ሥጋት ሥራውን ሊያከናውን የሚችለው፣ በመጀመሪያ አንፃራዊ ሰላም ለማስፈን የሚያስችል መደላድል ለመፍጠር የጋራ ትብብር ሲኖር ነው፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ የተከሰቱ ጥቃቶች፣ ግጭቶችና በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደው አውዳሚ ጦርነት ከፍተኛ ጠባሳ ጥለው ያለፉ በመሆናቸው ከፍተኛ የሆነ ማኅበረሰባዊ ሕክምና ያስፈልጋል፡፡ የኑሮ ውድነቱን በተመለከተም ከችግሩ ስፋትና ጥልቀት አኳያ ቆም ብሎ በሰከነ መንገድ በጋራ መፍትሔ መፈለግ አንዱ ዋነኛ ጥያቄ መሆን አለበት፡፡ በግራና በቀኝ ጎራዎች የተሠለፉ ኃይሎች ከሴራ ፖለቲካ ተላቀው አብረው ለመሥራት ፈቃደኛ ሲሆኑ፣ የፓርላማው ውይይትም ሆነ በተለያዩ መድረኮች የሚኖሩ ንግግሮች የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ ለሚረዱ ሐሳቦች በር ይከፍታሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፓርላማ አባላትም ሆነ ከሌሎች ፖለቲከኞች የሚጠብቀው የኑሮ ጫናው እንዲቃለልለት ተግተው እንዲሠሩ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘመናትን አብሮ እየተሻገረ እዚህ የደረሰው፣ ከዘመኑ ፖለቲከኞች ለየት ባለ ብልኃትና አርቆ አሳቢነት እንደነበረ ነጋሪ አያሻውም፡፡ በዚህም ምክንያት የብሔርና የሃይማኖት ልዩነቶች ሳይገድቡት ተጋብቶና ተዋልዶ ከመኖር ባለፈ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተቀባበላቸው የጋራ ማኅበራዊ እሴቶችን ገንብቷል፡፡ እነዚህ አኩሪ እሴቶች አገርን መውደድ፣ ሕግ ማክበር፣ ሌብነትን መፀየፍ፣ እርስ በርስ በተለያዩ መንገዶች መረዳዳትና መተባበር፣ ከፋፋይ ጥላቻዎችንና ክፋቶችን በጋራ ማስወገድና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ይህንን የመሰለ ታሪክ ያለውን ሕዝብ በመናኛ ጉዳዮች በመጥመድ በሴራ ፖለቲካ ጭንቅላቱን ማዞር፣ ግጭት በመቀስቀስ ለዕልቂትና ለውድመት መዳረግ፣ አንዱን ብሔር ወይም እምነት የሌላው ታሪካዊ ጠላት አድርጎ ማቅረብ፣ በኑሮ ውድነት አቅሉን ማሳጣት፣ በሥራ አጥነት ማሰቃየትና ሌሎች አስከፊ ድርጊቶችን መፈጸም የዚህ ዘመን ፖለቲከኞች ሒሳብ ማወራረጃ ነው፡፡ ይህ ኩሩና ጨዋ ሕዝብ ሰላም ሰፍኖለት በአገሩ በነፃነትና በእኩልነት እንዲኖር ጥረት ማድረግ ነበር የሚሻለው፡፡

በኢትዮጵያ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚወሳው የአገር ህልውና ጉዳይ ወደ ጎን እየተባለ፣ ለፖለቲካ ሥልጣን ብቻ የሚደረገው ኃላፊነት የጎደለው አጉል ሽኩቻ ነው፡፡ በወጉ መነጋገርንና መደማመጥን እርም ያለውና ምክንያታዊነት የጎደለው ሽኩቻ፣ ለአገር ህልውና የሥጋት አደጋ ደቅኗል፡፡ ዴሞክራሲ ከሌለ ሰላም የለም፣ ሰብዓዊ መብት ካልተከበረ መረጋጋት አይታሰብም፡፡ መነጋገርና መደማመጥ ከሌለ ጉልበተኞች ይበዙና ለዕልቂት የሚዳርግ ቀውስ ይከተላል፡፡ በዚህ ላይ ብሔርን፣ የፖለቲካ አመለካከትን፣ ሃይማኖትንና መሰል ልዩነቶችን በመንተራስ ኃላፊነት በጎደለው መንገድ የጥላቻ ንግግሮች ይሠራጫሉ፡፡ ጥላቻ ሌላ ጥላቻ እየወለደ ለአገርና ለሕዝብ ምንም ዓይነት ፋይዳ የሌላቸው የጥፋት ድግሶች ይፈበረካሉ፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ ከንቱ ነገር ውስጥ መውጣት ካልተቻለ ልማትም ሆነ ዕድገት አይታሰቡም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች ያሏት አገሩን አልምቶ፣ ከድንቁርናና ከድህነት ውስጥ የሚያወጡት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ያስፈልጉታል፡፡ የዓለም ኢኮኖሚና ታዋቂ የፋይናንስ ተቋማት እየተሽመደመዱ በዋዛ ፈዛዛ ቆሞ ማየት የማይጋፈጡት መከራ ማስከተሉ አይቀሬ ነው፡፡

ዘወትር እንደምንለው የሕግ የበላይነት መኖር ዋነኛው ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ሲኖር የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ይከበራሉ፡፡ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና ተጠቃሚነት ይኖራል፡፡ ቅሬታዎች ሲኖሩ የሚፈቱበት ሕጋዊ አሠራር ይሰፍናል፡፡ መልካም አስተዳደር ዕውን ይሆናል፡፡ ፍትሕ ለሁሉም ተደራሽ ይሆናል፡፡ ሙስና አከርካሪው ይሰበራል፡፡ ሕገወጥነት አደብ ይገዛል፡፡ ለአሉባልታና ለሐሜት የሚዳርጉ እኩይ አሠራሮች ይወገዳሉ፡፡ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅር፣ ከሽኩቻ ይልቅ መነጋገር፣ ከኩርፊያ ይልቅ መደማመጥ፣ ከጠባብ ፍላጎቶች ይልቅ የአገር የጋራ ጥቅሞች ይቀድማሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ የተቀደሱ ተግባራት ይረጋገጡ ዘንድ የፓርላማ አባላትም ሆኑ ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች በአንድነት ድምፃቸውን ያሰሙ፡፡ በአገራዊ የምክክር ኮሚሽን አማካይነት እየተደረገ ያለው ዝግጅት እስኪጠናቀቅ፣ በተገኙ አጋጣሚዎች ሁሉ ለአገር ሰላምና ለኢኮኖሚው ዕድገት የሚረዱ ተግባራት ላይ ይተኮር፡፡ በምግብ ዕጦት የሚሰቃዩ በርካታ ሚሊዮኖች ያሉባት ኢትዮጵያ ውስጥ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከትና በመሳሰሉት ልዩነትን እያገነኑ ግጭት መቀስቀስ ነውር ነው፡፡ ለዘመኑ በማይመጥን የፖለቲካ ዕይታ ሕዝብ መከፋፈል የለየለት ዕብደት ነው፡፡

ኢትዮጵያን ወደ ብተና፣ ሕዝቡን ደግሞ ወደ ዕልቂትና ስደት የሚያመቻቹ አጓጉል ድርጊቶች በሁሉም ወገኖች መወገዝ አለባቸው፡፡ ሥልጣን ለማጠባበቅም ሆነ በአቋራጭ ለማግኘት ሲባል ወደ ቀውስ የሚያንደረድሩ አላስፈላጊ ድርጊቶች ይቁሙ፡፡ በተለይ ብሔርንና መሰል ልዩነቶችን እያቀነቀኑ ለዘመናት አብሮ የኖረን ሕዝብ ለማለያየት፣ ኢትዮጵያንም ቀውስ ውስጥ ለመክተት እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩ ወገኖች ከድርጊታቸው ይቆጠቡ፡፡ ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች በአገር ባለቤትነት ስሜት ተንቀሳቅሰው፣ እሳት ለማቀጣጠል የሚፈልጉ ወገኖችን መገሰጽ አለባቸው፡፡ የሕዝብ ጥያቄም በአግባቡ ተሰምቶ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኝ መትጋት ይኖርባቸዋል፡፡ ዜጎች ቅሬታ ሲያቀርቡ እንዲደመጡና ምላሽ እንዲያገኙ፣ ምላሽ የሚሰጠው አካልም በሕጉ መሠረት ኃላፊነቱን እንደወጣ መደረግ አለበት፡፡ ሰላማዊና ሕጋዊ ጥያቄዎች ኃላፊነት በማይሰማቸው ወገኖች እየተጠለፉና አቅጣጫቸውን እየሳቱ ደም መፍሰስ የለበትም፡፡ ሕዝባችንም ፋይዳ በሌላቸው ድርጊቶች ምክንያት ሕይወቱ አይመሰቃቀል፡፡ በቀን አንድ ጊዜ ምግብ ማግኘት ብርቅ በሆነባት ኢትዮጵያ ሰላም አደፍራሽነት ለማንም አይጠቅምም፡፡ የሰላም ዕጦትና የኑሮ ውድነት አሁንም የአገር ፈተና መሆናቸው ይታወቅ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ በመከረው የመጀመሪያ ጉባዔ ለዲፕሎማቲክና ለትብብር አማራጮች ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ በቀይ ባህር ቀጣና የፀጥታ...

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...

የመጀመርያ ምዕራፉ የተጠናቀቀው አዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ተከላው እንደገና ሊከናወን መሆኑ ተሰማ

እስካሁን የሳር ተከላውን ጨምሮ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ዕድሳቱ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...