የፋይናንስ ተቋማት ከዓመታዊ መደበኛ ወጪያቸው ሁለት በመቶ የሚሆነውን ለሥልጠናና ለአቅም ግንባታ እንዲያውሉ ቢገደዱም፣ ብዙዎቹ ይህንን ግዴታ በአግባቡ እየተወጡ አለመሆኑ ተገለጸ፡፡
ከፋይናንስ ተቋማት የአስተዳደር ውጪ ሁለት በመቶ ለሥልጠናና ለሰው ኃይል ልማት እንዲውል አስገዳጅ የሆነው፣ የቦርድ ዳይሬክተሮች ወጪ ቁጠባ ላይ ትኩረት ስለሚያደርጉና ‹‹የሰው ኃይል ኢንቨስትመንት›› እንደ ወጪ ስለሚወሰድ፣ ያንን ለማስገደድ የወጣ መሆኑን የብሔራዊ ባንክ የኢንሹራንስ ሱፐርቪዥን ዳይሬክተር አቶ በላይ ቱሉ ገልጸዋል፡፡
‹‹ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ ለዚህ የሚመደበውን ገንዘብ አገልግሎት የሚሰጥ ጠንካራ ተቋም ስለሌለ ዳይሬክተሮች ዱባይ ይሄዱበታል፣ 50 በመቶ ለዚህ የሚሆነው በጀት ጥቂት ሰዎች በሚሠለጥኑበት ወጪ ያልቃል፤›› ሲሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
የኢንሹራንስ ሱፐርቪዥን ዳይሬክተሩ ይህንን የተናገሩት፣ ከሰሞኑ የካፒታል የፋይናንስ ልህቀት ማዕከል አክሲዮን ማኅበር በይፋ በተመሠረተበት፣ ‹‹የፋይናንስ ዘርፉ የሰው ኃይል ማብቃት ፍላጎቶች፣ ተግዳሮቶችና መፃዒ ዕድሎች›› በሚል ርዕስ በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ ነው፡፡
በአገር ውስጥ ባንኮችና በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለበርካታ ዓመታት በትልልቅ የኃላፊነት ደረጃ የሠሩትና በአሁኑ ጊዜ በማማከር አገልግሎት ላይ የተሰማሩት ወ/ሮ ዘመናይ ክፍሌ በበኩላቸው፣ ብሔራዊ ባንክ ለሥልጠና ትልቅ ትኩረት እንደሰጠና ለአብነትም ከፋይናንስ ተቋማት መደበኛ ወጪ ሁለት በመቶ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡
‹‹ይኼ ጥሩ ሆኖ፣ ያንን በጀት በትክክል ለተፈለገው ልማት እየዋለ ነው ወይ ተብሎ እያንዳንዱ ባንክ፣ ኢንሹራንስና ማይክሮ ፋይናንስ ቢጠየቅ የሚገኘው መልስ የተዘበራራቀ ነው፤›› ያሉት ወ/ሮ ዘመናይ፣ በጀት መጠቀም በራሱ ሥራ አለመሆኑንና በትክክል ሊሸፍን የሚገባው የሥልጠናና የሰው ኃይል ብቃት ርዕሰ ጉዳይ ተለይቷል ወይ የሚለውን መረዳት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የብሔራዊ ባንክ ሪፖርትን በማጣቀስ በፋይናንስ ተቋማት ያለው የሰው ኃይል ልማት ኢንዴክስ 4.89 በመቶ መሆኑን፣ ይህም ከ195 የዓለም አገሮች ጋር ሲወዳደር ኢትዮጵያ 175ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ወ/ሮ ዘመናይ አስረድተዋል፡፡ ይህም የሰው ኃይል ብቃትን ማሳደግ በኢትዮጵያ ምን ያህል አናሳ ግንዛቤ ያለው መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል፡፡
በተለይ በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ያለው የሰው ኃይል በሥልጠና አቅም እንዲያገኝ ሲደረግ የቆየው የእሳት ማጥፊያ በሚመስል አሠራር እንደነበር፣ የሰው ኃይል ሥልጠና በአግባቡ እንዲሰጥ የፋይናንስ ተቋማት ኃላፊዎች ራሳቸው የአመለካከት ለውጥ ሊኖራቸው እንደሚገባ በውይይት መድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡
ወ/ሮ ዘመናይ በፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚገኝ አንድ መሪ ለውጥ አስፈላጊ መሆኑን ማመን አለበት ብለዋል፡፡ አንድ ሰው የአንድ ተቋም መሪ ሆነ ማለት ክፍተት የለውም ማለት እንዳልሆነና የአመራር ክህሎት ዓይነቶች እጅግ በርካታ በመሆናቸው ሥልጠና ለበታች ሠራተኛ ብቻ ባለመሆኑ፣ በፋይናንስ ዘርፍ ከታች እስከ ላይ ያለ ሁሉም ባለሙያ ዘመናዊ ሥልጠና እንደሚያስፈልገው የፋይናንስ አማካሪዋ አስረድተዋል፡፡
መሪዎች የሚሰጡዋቸውን ሥልጠናዎች ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን የሚያገኙትን ዕውቀት የማካፈል፣ ዕውቀትና ክህሎቱን የተቋሙ ንብረት (ሀብት) ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው በተወያዮች ተገልጿል፡፡
‹‹ለፋይናንስ ዘርፉ የሚያስፈልጉ ሰዎች በበቂ ደረጃ ቢዘጋጁ ኖሮ ተቋማት የሰው ኃይል መነጣጠቅ ውስጥ እንዳይገቡ ማድረግ ይቻል ነበር፤›› ያሉት ወ/ሮ ዘመናይ፣ በቂ ኃይል የሌለው ከተማረ ሰው እጥረት ሳይሆን፣ ችግሩ የበቃ ሰው ከማግኘት ጋር የሚያያዝ እንደሆነና ተቋማትም ይህንን ክፍተት ለይተው የሚሠሩበት ወቅት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ሥራ አስኪያጆች ከአንድ ተቋም ወደ ሌላ ተቋም የሚያደርጉት የፈጠነ እንቅስቃሴ የተፈጠረው ከእጥረት የተነሳ እንደሆነና ይህም በቂ ሰው ባለመሠልጠኑ መሆኑን፣ የበቃ ሰው ለማፍራት አለመቻል ከሚነሱ ምክንያቶች ውስጥ አንድም ድርጅቱ ወይም የበላይ ኃላፊዎች በማሻሻያው ባለማመናቸው፣ ወይም የሚሰጡ ሥልጠናዎች ሪፖርት ለማሟላት የሚደረጉ በመሆናቸው ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የአሀዱ ባንክ መሥራች ፕሬዚዳንት ሆነው ያገለገሉትና የቦርድ አማካሪ ሆነው በማገልገል ያሉት አቶ እሸቱ ፋንታዬ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የባንክ አስተዳደር ሥርዓት ብዙ መሻሻልና ለውጥ የሚፈልግ ነው የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
‹‹ከላይ ከብሔራዊ ባንክ ጀምሮ በመሀል ያሉት ቦርዶችና የባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ግንኙነት በጣም ብልኃት ባለው መንገድ መሻሻል አለበት፤›› ያሉት አቶ እሸቱ ቦርዶች፣ ብሔራዊ ባንክና የባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች እንደፈለጉ የሚያደርጉበት አሠራር መወገድ አለበት ብለዋል፡፡
‹‹ባንኮች ሕዝቡ የሚፈልጋቸውን አገልግሎቶች ካልሰጡ ብሔራዊ ባንክ ጣልቃ መግባት አለበት፡፡ የቦርድ ራዕይና የአስፈጻሚዎች ራዕይ ሳይገጣጠም ሲቀር አስፈጻሚዎቹ የቦርዱን ራዕይ መጋፈጥ መቻል አለባቸው፤›› ያሉት አቶ እሸቱ፣ ይህ ጊዜ የሚጠይቅ ጉዳይ ቢሆንም፣ በአብዛኛው የገንዘብ ሥርዓት ውስጥ ያሉ ተዋንያን በሙሉ ካተኮሩበት ባለአክሲዮኖችን ብቻ ተጠያቂ ከማድረግ በመውጣት ሌሎች ተገልጋዮች፣ ተበዳሪዎች፣ የኢንሹራንስ ዋስትና ለሚፈልጉ ሳይቀር አግባብ ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ የሚችሉበትን አሠረር እያሰቡ መተግበር ያለባቸው ጊዜ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡
የፋይናንስ ዘርፉ ተዋንያን በቀጣይ የሚገጥማቸውን ውድድርና ፈተና ለመቋቋም በቂ ሰው አለ ወይ? ሰው ብቻም ሳይሆን ተወዳዳሪ የሆነ በቂ ተሰጥዖ አለ ወይ? የሚለው ሊታይ እንደሚገባ በመድረኩ አፅንኦት ተሰጥቶ ተገልጿል፡፡
ከዚህ ቀደም ብሔራዊ ባንክ ከአስተዳደራዊ ወጪዎች ሁለት በመቶ የሚሆነውን ለሠራተኞች የሥልጠናና የሙያ ማሻሻያ ተግባራት ላይ በትክክል አላዋሉም ባላቸው ባንኮች ላይ የገንዘብ ቅጣቶች ማስተላለፉ የሚታወስ ሲሆን፣ ባንኩ ከሰባት ዓመታት በፊት በመመርያ ያሳለፈው ውሳኔ ዋነኛ ዓላው በተለይም በኢንዱትሪው ውስጥ ያለውን የባለሙያዎች መነጣጠቅ በመቀነስ ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎች ለማፍራት የሚለው ዋነኛ ጉዳይ ነው፡፡