Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከአዲስ አበባና ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ 60 ሺሕ ወገኖች ለከፋ ረሃብ ሊጋለጡ እንደሚችሉ...

ከአዲስ አበባና ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ 60 ሺሕ ወገኖች ለከፋ ረሃብ ሊጋለጡ እንደሚችሉ ተገለጸ

ቀን:

ከአዲስ አበባ ከተማና ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን የተለያዩ መጠለያዎች የሚገኙ ከ60 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች አስቸኳይ ድጋፍ ካልተደረገላቸው በረሃብ ይጠቃሉ የሚል ሥጋት እንዳደረበት የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ገለጸ፡፡

ከኦሮሚያ ክልል በፀጥታው ምክንያት፣ ከአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ቤታቸው ፈርሶባቸው ወደ ደብረ ብርሃን ሄደው መጠለያ ለገቡ ተፈናቃዮች የሚደረገው ድጋፍ አነስተኛ በመሆኑ፣ በረሃብ ይጠቃሉ የሚል ሥጋት እንዳደረባቸው የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና የቅድመ ማስንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪ አቶ ደረጀ ልደቱ ገልጸዋል፡፡

‹‹በጣም የድጋፍ እጥረት አለ፡፡ ድጋፍ እንደሚደረግልን በወረቀት ደረጃ ፀድቆ እንደ ዞን የተላከልን አለ፡፡ ግን አሁንም ያልገባላቸው ወረዳዎች አሉ፡፡ ካለው ከዚያም ከዚያም የክልሉ መጠባበቂያ በጀት የተረፉ ነገሮችን እየሰጠን ነው ያቆየናቸው፤›› ያሉት አቶ ደረጀ፣ ‹‹ይህን ሰሞን ድጋፍ ካልተደረገ የድጋፍ እጥረቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በሁሉም የመጠለያ ጣቢያዎች ድጋፍ ቢያስፈልግም፣ በተለይም በግሸ ወረዳ አጣዬ ከተማ፣ መንዝ ወረዳ ተጀምሮ ቀረ እንጂ ድጋፍ እንዳልተደረገላቸውም ተመላክቷል፡፡ አቶ ደረጄ በይበልጥ የድጋፉ እጥረት ያለባቸውን ቦታዎች ሲገልጹ፣ ‹‹በወንዝ ወረዳ፣ በግሸ ወረዳና በአጣዬ ከተማ ድጋፍ ተጀምሮ ነው የቀረው፡፡ ሁለት ሺሕ ኩንታልና ሦስት ሺሕ ኩንታል የሚያስፈልገው ላይ፣ ከ500 እስከ 700 ኩንታል መስጠት፣ ጀምሮ የመቆም ችግር ይስተዋላል፤›› ብለዋል፡፡

በዚህ ዓመት ውስጥ ምን ያህል ጊዜ ነው ድጋፍ መደረግ የነበረበት፣ ስንት ጊዜስ ድጋፍ ተደርጓል ተብሎ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄም ‹‹በዓመት ውስጥ ሁለት ዙር ብቻ ነው የተሰጠው፡፡ አሁን ሦስተኛው ዙር ነው እየገባ ያለው ብለው መጠለያ ውስጥ ያሉ ሰዎች በየወሩ ማግኘት አለባቸው፡፡ በየወሩ እንኳን በወር በ15 ቀናት ሬሽኑ እየመጣ መከፋፈል ነበረበት፡፡ ግን እየቀረበ አይደለም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ድጋፍ የሚባለው ነገር በራሱ ዘይት፣ ጥራጥሬ አልሚ ምግብን አሟልቶ ፓኬጁን ማሟላት ቢኖርበትም፣ ይህንን ያሟላ አለመሆኑ ሌላው ችግር መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ጥራጥሬና ዘይትን ጨምሮ በአንድ ወር ውስጥ ለአንድ ሰው 15 ኪሎ ግራም ድጋፍ መደረግ የነበረ ቢሆንም፣ መንግሥት በአንድ ወር ውስጥ ድጋፉን አትጠብቁ በማለቱ ለአንድ ወር ውስጥ ሲሰጥ የነበረው ድጋፍ ወደ ወር ከ15 ቀን ከፍ መደረጉ ሌላ ችግር ሆኖ ሳለ፣ በ45 ቀናትም በትክክል አለመድረሱ ረሃብ እንዲከሰት ምክንያት ይሆናል ተብሏል፡፡

ድጋፍ ለመቆራረጡ በተለይም ከኦሮሚያ ክልልና ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ አማራ ክልል ሰሜን ሸዋ የሚፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ በመምጣቱ ‹‹ረሃብ ይከሰታል የሚል ሥጋት አለ፤›› ብለዋል፡፡

ማኅበረሰቡ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለይም በበዓላት ወቅት ተፈናቃዮችን የመረዳትና የመደገፍ ተግባር ሲያከናውን እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፣ አሁን ግን ድርጊቱ ጫና በመፍጠሩ ማኅበረሰቡም ድጋፍን እያቆመ ነው ብለዋል፡፡

ይህንን ተከትሎም የዞኑ አስተዳደር መንግሥት ድጋፍ ካለደረገ ከፍተኛ ረሃብ ሊከሰት እንደሚችል መግለጹን አክለዋል፡፡

ረሃብ እንዳይከሰት ምን የመፍትሔ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄም፣ ‹‹በዕቅድ ደረጃ ድጋፍ ይላካል ተብሎ በወረቀት ፀድቆ ተልኮልናል፡፡ አገባብ ላይ ግን ትልቅ ችግር አለ፡፡ ተፈናቃይ ወደ ረሃብ ደረጃ መድረሱ አይቀርም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ደብረ ብርሃን ስድስት፣ ምንጃር አንድ፣ ሸዋሮቢ አንድ፣ እንዲሁም በመንዝ አንድ መጠለያ የሚገኙ ከ60 በላይ ተፈናቃዮች የተጠለሉባቸው ካምፖች አሉ የተባለ ሲሆን፣ 90 በመቶ የሚሆኑት ተፈናቃዮች ከኦሮሚያ ክልል የመጡ ናቸው ተብሏል፡፡

ከአዲስ አበባ ቤት እየፈረሰባቸው ያሉ ሰዎች በየቀኑ ወደ ዞኑ እየገቡ መሆኑን የገለጹት አቶ ደረጀ፣ መንግሥት ለችግሩ ቋሚ መፍትሔ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...