Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቡና ላኪዎች የኮንቴይነር እጥረት እንደገጠማቸው ተጠቆመ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎች በማነሳቸው የቡና ላኪዎች፣ ከሌላው ጊዜ በተለየ የኮንቴይነር እጥረት እየገጠማቸው እንደሆነ ታወቀ፡፡

በኮቪድ-19 ወረርሽኝን ወቅት በተወሰነ ደረጃ ቡና ላኪዎች የኮንቴይነር እጥረት ይገጥማቸው እንደነበረ የሚታወስ ነው፡፡ አሁንም ይህ ችግር ሲንከባለል መጥቶ በአሁኑ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ገቢ ዕቃዎች በማነሳቸው፣ ቡና ለመላክ የኮንቴይነር እጥረት እየገጠመ እንደሆነ ሪፖርተር የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር ለመረዳት ችሏል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍም ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ያሉበት ኮሚቴ በማዋቀር እየተሠራ ሲሆን፣ ኮሚቴውን የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን እየመራው ነው፡፡ የጉምሩክ ኮሚሽን፣ የአንድ መስኮት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት፣ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የምርት ገበያና የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የኮሚቴው አባላት ናቸው፡፡

ሌብነትን ጨምሮ በቡና ንግድ ላይ በርካታ ፈተናዎች እንደበዙ የሚናገሩት ቡና ላኪ ነጋዴ የሆኑት አቶ ታምሩ ታደሰ፣ የኮንቴይነር እጥረቱ ግን በዚህ ዓመት እንደባሰበት አስረድተዋል፡፡

‹‹ከፍተኛው የቡና መላኪያ ወቅት ሳይደርስ ነው በዚህ ዓመትም የኮንቴይነር እጥረት የገጠመን፤›› ሲሉ የገለጹት አቶ ታምሩ፣ ቡና በከፍተኛ መጠን ወደ ውጭ የመላኪያ ወቅት ሲመጣ ችግሩ የባሰ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣንን በመወከል በተዋቀረው ኮሚቴ ውስጥ እየሠሩ ያሉት አቶ ኤርጋና ቡቼ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኮንቴይነር እጥረት አጋጥሟል፡፡ ምክንያቱም ገቢ ዕቃዎች የሚመጣባቸው ኮንቴይነሮች ቁጥር በመቀነሱ ነው፡፡

ወደ አገር ውስጥ እየገባ ያለው ኮንቴይነር ያለ ምንም ችግር በቅድሚያ ለላኪዎች እንዲሰጥ የመፍትሔ ሥርዓት መዘርጋቱን አቶ ኤርጋና ገልጸው፣ ላኪዎችም ኮንቴይነር ወደ አገር ውስጥ ሲገባ በተጠየቀው ፍጥነት ለመስጠት ሙከራ እያደረጉ መሆኑን አክለዋል፡፡

ኮሚቴው በየሁለት ሳምንቱ ስብሰባ በማድረግ አፈጻጸሙን እንደሚከታተል የገለጹት አቶ ኤርጋና፣ ችግር የገጠመው ላኪም ካለ ሪፖርት እየተቀበሉ በሪፖርቱ መሠረት ዕርምት እንደሚወሰድ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ከአንድ ሳምንት በፊት ነው ስብሰባ ያደረግነው፣ ከዚያ ወዲህ ችግር ገጥሞናል በሚል የቀረበ ሪፖርት የለም፡፡ ይህ ማለት ኮንቴይነሮች እየገቡ ስለሆኑ ጥሩ ምልከት ነው፤›› ብለዋል፡፡

የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ዑመር፣ ችግሩ ከበፊቱ የበለጠ እንደሆነና መሥሪያ ቤታቸው ይህንን ለመቅረፍ በትብብር እየሠራ እንደሆነ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹እጥረቱ አለ የሚካድ አይደለም፡፡ እሱንም በየሁለት ሳምንቱ  እየገመገምን ነው ያለነው፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ ሻፊ፣ እሳቸውም ወደ አገር ውስጥ የሚገባው ኮንቴይነር ማነሱ ለችግሩ መንስዔ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች