«የአፍሪካ አገሮችን አስተባብረው የተሟገቱ ተሟግተውም ያሸነፉ፣ በመጨረሻም አፍሪካ የራስዋን ብዝኃ ሕይወት እንድትጠብቅ ያደረጉ ሰው ናቸው፤ በኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ላይ ብዙ ሕጎች እንዲወጡ፣ በአየር ለውጥ ኢትዮጵያ ታዋቂ ሆና አቅሟ እንዲጎለብት ያደረጉ ትልቅ ሰው ነበሩ፡፡»
ይህን ዓቢይ ኃይለ ቃል በምስክርነት ለሥነ አካባቢ ሳይንቲስቱ ነፍስ ኄር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር) የሰጡት የጄኔቲክስ ፕሮፌሰሩ እንዳሻው በቀለ ናቸው፡፡ ‹‹ተቋምን ብቻ ሳይሆን አብረው ሰውን የመሠረቱና ያፈሩ ትልቅ ሰው፣ በአገራችን ይሁን በአህጉር ደረጃ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ናቸው፤›› ሲሉ በሥርዓተ ቀብራቸው ዕለት ማስተጋባታቸውን ዲደብሊው አስተጋብቶታል፡፡

ማክሰኞ የካቲት 12 ቀን 1932 ዓ.ም. ተወልደው፣ ማክሰኞ መጋቢት 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ያረፉት የብዝኃ ሕይወት ሳይንቲስቱ ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር)፣ ሥርዓተ ቀብራቸው ረቡዕ መጋቢት 13 ቀን 2015 ዓ.ም. በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሲፈጸም በተነበበው ገጸ ታሪካቸው እንደተገለጸው፣ ተወልደ ብርሃን (ዶ/ር) በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ በብዝኃ ሕይወት ሀብት፣ በደኅንነተ ሕይወት ጭምርና በማኅበረሰብ የፈጠራ መብት ባለቤትነት በመልማት ላይ የሚገኙ አገሮችን በማስተባበር ዋና ተደራዳሪ ሆነው አፍሪካውያን በዚህ ረገድ ግንዛቤ እንዲጨብጡ በማድረግ ያገለገሉ ታላቅ ምሁር ናቸው። ከስድስት በላይ ዓለም አቀፍ ድርድሮች ላይ አገራቸውን፣ አፍሪካንና በመልማት ላይ የሚገኙ 77 አገሮችን ወክለዋል። በእነዚህና በሌሎች ዓለም አቀፍ አስተዋፅኦዎቻቸው በ1993 ዓ.ም. የአማራጭ ኖቤል ሽልማት ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ በ1998 ዓ.ም. የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ መርሐ ግብር /ዩኔፕ/ ‹‹የምድራችን ጀግና›› (Champions of the Earth) የሚል ሽልማት ሰጥቶአቸው በሲንጋፖር ተገኝተው ተቀብለዋል።
ዘጋርዲያን (The Guardian) የተባለው ዕድሜ ጠገብ አንጋፋ ጋዜጣ እ.ኤ.አ 2008 ዓ.ም. የዓለማችን 50 ምርጥ ሰዎች ብሎ እውቅና ከሰጣቸው ሰዎች መካከል አንዱ ዶ/ር ተወልደብርሃን ነበሩ፡፡
በፈረንሣይ የሞንትፐልዬ (Montpelier) ከተማ የሌሮ (L’Herault) አውራጃም የክብር አምባሳደር አድርጎ ሾሟቸዋል፡፡
ኦርጋኒክስ ኢንተርናሽናል (Organics International) ከተባለ ተቋም ጋር በመተባበር በመላው ዓለም በሰላም፣ በፍትሕና የተፈጥሮ ሀብትን በመንከባከብ አስተዋፅኦ ላደረጉ ሁሉ ዕውቅና የሚሰጠው ዋን ወርልድ አዋርድ (One World Award) ተቋም፣ ባልና ሚስቱን ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር) እና ወ/ሮ ሱ ኤድዋርድ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ በማለት እንደ እ.ኤ.አ. 2017 በጀርመን አገር ባለትዳሮቹ ተገኝተው እንዲቀበሉ አድርጓል፡፡
በ1996 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ተሸልመዋል። በኢትዮጵያ ሚሊኒየም የአካባቢ ተቆርቋሪ መድረክ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ካዘጋጀው ሽልማት ላይ ከወቅቱ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ‹‹የአረንጓዴ ጀግና›› ሽልማት ተቀብለዋል፡፡ በመንግሥት ሥራ ላይ ላደረጉት አስተዋፅኦ የ2008 ዓ.ም. የበጎ ሰው ተሸላሚ በመሆን በተወካያቸው አማካይነት ተቀብለዋል፡፡
ሳይንቲስቱ በአገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከአምስት ዓመት በፊት ያረፉት ባለቤታቸው ወ/ሮ ሱ ኤድዋርድስ አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደነበር ይወሳል፡፡ የቤተሰቡን ደኅንነት ከመጠበቅ በተጨማሪ እንግሊዝ አገር ተወካዮች ምክር ቤት ሳይንቲስቱን ወክለው ንግግር አድርገዋል፡፡ ወ/ሮ ሱ፣ ባለቤታቸው ዓለም አቀፍ ድርድር በሰላም አድርገው ውጤታማ ከሆኑ በኋላ ሲጨዋወቱ ‹‹አንድ ቀን ይጨክኑብሀል ብዬ እፈራ ነበር ይህ ፍርኃቴ ዕውን ባለመሆኑ በጣም ደስተኛ ነኝ፣ እንኳን ለቤትህ አበቃህ›› ብለዋቸው ነበር፡፡ ለእውነት ፍለጋም ሆነ ለእውነት መቆም የሚከራከሩት ሕይወትንም እንደሚያካትት በመረዳት፡፡
ነፍስ ኄር ተወልደ ብርሃን፣ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን አገራቸውን በማገልገል ላይ እያሉ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በጡረታ ተሰናብተው የግል ጥናትና ምርምራቸውን ሲያካሂዱ መቆየት ብቻ ሳይሆን የሚሰማቸውን ለመግለጽ ወደ ኋላ የማይሉ ነበሩ፡፡ አንዱ ማሳያ ከሦስት ዓመት በፊት ለኢትዮጵያ መንግሥት ግልጽ ደብዳቤ መጻፋቸው ነበር፡፡ ደብዳቤውም መንግሥት በኢትዮጵያ ልውጥ ህያዋን የሆኑ አዝርዕት እንዲመረቱ መፍቀዱን መገለጹ አሳስቧቸው ሚያዝያ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. የጻፉት ነበር፡፡
በከፊል እንዲህ ይላል፡- ‹‹አሁን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት በኢትዮጵያ ልውጥ ህያዋን የሆኑ አዝርዕቶች እንዲመረቱ መፍቀዱን በዜና አነበብሁ፥ ሰማሁ። ብዙ ነገሮች ያሳስቡኛል። ከሚያሳስቡኝ ነገሮች መካከልም 130 ሄክታር የሚሸፍነው የዘረ መል ጥናት በሌሎች አጎራባች ከባቢዎች ላይ አደጋ የማይደቅን ጥብቅ እርሻ የመሆን ያለመሆኑ ጉዳይና እነዚህ ጉዳዮች የደኅንነተ ሕይወትን ዓለም አቀፍ ፕሮቶኮል ባማከለ ሁኔታ እንዴት እየተሄደባቸው ነው የሚሉት ይገኙባቸዋል። ፕሮቶኮሉ በአገራችንም የፀደቀና ዝርዝር አሠራሮቹም በኢትዮጵያ የደኅንነተ ሕይወት ማዕቀፍ በአካባቢ ጉዳዮች፥ በደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ሕግ፥ ፖሊሲና መስፈርቶች የካቲት 2011 ዓ.ም. የተቀረፀለት ነው።
እነዚህ የሕግ ሒደቶች ካልተተገበሩ አሁን በሚደረገው የልውጥ ህያዋን ምርት ዙሪያ እጃቸውን ያስገቡት አካላት የካቲት 2011 ዓ.ም. የወጣውን ፕሮቶኮልና በአዋጅ ቁጥር 655/2009 በነጋሪት ጋዜጣ ወጥቶ በቁጥር 896/2015 የተሻሻለውን ሕግ እየተላለፉ ነው። ይህም ኢትዮጵያ ይፋዊ ባልሆነ ሁኔታ ከካርታኼናው የደኅንነተ ሕይወት ፕሮቶኮል ራስዋን እንዳገለለች ሊያስቆጥራት ይችላል።
እኔ እስከማውቀው እስከአሁን ድረስ ኢትዮጵያ ሕግጋቱን ጠብቃ ቆይታለች፤ አስፈላጊ ሆና ባገኘችውም ጊዜ ሕጎችዋን አሻሽላለች እንጂ በይፋ ከካርቴሄናው የደኅንነተ ሕይወት ፕሮቶኮል አልወጣችም።
ጡረተኛ እንደመሆኔና 80 ዓመት እንዳለፈው አንድ አረጋዊ ከኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግሥት ጋር የቀጥታ ግንኙነት የለኝም። ስለሆነም ኢትዮጵያ የካርቴሄናውን የደኅንነተ ሕይወት ፕሮቶኮልን ሕጋዊ ትግበራ ገሸሽ እያደረገችው ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጉዳይ የማጣራበት መንገድ የለኝም።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግሥት የካርታኼናውን የደኅንነተ ሕይወት ፕሮቶኮል ሕጋዊ ትግበራ ገሸሽ እያደረገው ከሆነ፤ አገሪቱ ዓለምአቀፍ ስምምነትን እየጣሰች መሆኑ ግልፅ ይሆናል። ይህ እንዲሆን ሊፈቀድለት አይገባም። እናም የትውልዱ ወጣቶች በሚችሉት መንገድ ሁሉ ተቃውሟቸውን ያሰሙ ዘንድ አሳስባለሁ። ይህን የምልበት ምክንያትም የካርታኼናውን የደኅንነተ ሕይወት ስምምነት ጨምሮ የፀደቁትን ዓለምአቀፋዊ ሕጎች በይፋ ወጥቼባቸዋለሁ ሳይሉ መጣስ በመሆኑ ነው። በአገራችንም ሆነ በአፍሪካ አህጉር ብሎም የማያሚ ቡድን ከሚባለውና አምስት ሀገራትን ብቻ ካቀፈው ተቃዋሚ ቡድን በቀር በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የሕጋዊነት መሠረት ማናጋትም በመሆኑ ነው።
በመጨረሻም የየሀገራቸው መንግሥታት የደኅንነተ ሕይወት ስምምነቶችን ጨምሮ ዓለምአቀፍ ሕግጋትን በዓለም ዙሪያ አክብረው መተግበራቸውን እንዲቀጥሉ ይወተውቱ ዘንድ፤ የአፍሪካን እና የቀሪውን ዓለም ወጣቶች አበክሬ አሳስባለሁ።››
ከአባታቸው ከመምሬ ገብረ እግዚአብሔር ገብረ ዮሐንስና ከእናታቸው ወ/ሮ መአዛ ተወልደ መድኅን በትግራይ ጠቅላይ ግዛት በዓድዋ ከተማ አቅራቢያ በምትገኝ ርባ ገረድ በተባለች መንደር የካቲት 12 ቀን 1932 ዓ.ም የተወለዱት ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር)፣ ከቤተሰባቸው ግዕዝን፣ አማርኛንና የአፍ መፍቻ ቋንቋቸውን ትግርኛን ተምረዋል፡፡ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን በንግሥተ ሳባ፣ ሁለተኛ ደረጃን በጄኔራል ዊንጌት ተከታትለዋል፡፡ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በ1955 ዓ.ም. ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ከዌልስ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡
በኢኮሎጂ (ሥነ ምኅዳር) የዶክትሬት ትምህርታቸውን ሲጨርሱ በዌልስ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ምረቃ የዘጠኝ ወር ጊዜ ይቀረው ስለነበር ቆይተው በምረቃ በዓል እንዲሳተፉ የተጠየቁት የ27 ዓመቱ ወጣት ዶክተር ተወልደ ብርሃን፣ ‹‹እኔን ግብር ከፍሎ ያስተማረኝ የኢትዮጵያ ገበሬ ነው፣ እስከ ምርቃቱ ቀን ድረስ እዚህ አልቆይም፣ ዲግሪዬን በፖስታ ቤት ላኩልኝ›› ማለታቸው ይወሳል፡፡
በ1960ዎቹ መጀመርያ ከመምህርነት እስከ 1970ዎቹ መጀመርያ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ፋኩልቲ ዲን ነበሩ፡፡ ከ1978 እስከ 1983 ዓ.ም. የአስመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆነው ሠርተዋል፡፡
ቀጥሎም ለኢትዮጵያ የአካባቢ እንክብካቤ አዲስ ሥርዓት ዘርግተው በርካታ የምርምር ውጤቶቻቸው በአገር ውስጥና በውጪ አገር ጆርናሎችና በተለያየ የመጻሕፍት ምዕራፎች ታትመዋል።
ለብዙ የዕፀዋትና የአካባቢ ምርምር መሠረት የሆነውን የዕፀዋት የጄኔቲካል ባንክ በ1968 ዓ.ም. ሲመሠረት የካውንስል አባል ሆነው ሠርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ የዕፀዋት ሥርጭትና ስያሜ ጥናትን በተመለከተ መሪ በመሆን በርካታ ብቁ ተማሪዎቻቸውን በማሠልጠን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትልቅ የዕፀዋት ቤተመዘክር (National Herbarium) ተቋም በመገንባት ተማሪዎቻቸውን ፍለጋቸውን ይዘው እንዲመሩትና እንዲያሳድጉት አድርገዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት መስፋፋትና መጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ ከማኖራቸውም በላይ ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን የሳይንስን ቃላት ወደ አማርኛ በመተርጐምና ተገቢ ፍቺን በማስቀመጥ የራሳቸውን አሻራ አኑረዋል፡፡
በ1982 ዓ.ም. በኢሕዲሪ መንግሥት ሹም ሽር ሲደረግ የባህል ሚኒስትር የነበሩት ተወልደ ብርሃን (ዶ/ር) በኢፌዴሪ መንግሥት ጡረታ እስከወጡበት ድረስ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል፡፡
በ83 ዓመታቸው ያረፉትን ሳይንቲስቱን፣ የመሬቲቱ ሻምፒዮኑን፣ ዘተወልደ ብዝኃ ሕይወቱን የሦስት ልጆች አባቱን ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔርን ለመሸኘት በሺዎች የሚቆጠሩ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዓውደ ምሕረት የተገኙ ሲሆን፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን መንግሥታቸውን ወክለው ተገኝተዋል፡፡ አስክሬናቸውም ከአምስት ዓመት በፊት ካረፉት ባለቤታቸው ወ/ሮ ሱ ኤድዋርድስ አጠገብ በክብር አርፏል፡፡
‹‹የምድራችን ጀግና›› ደራሲ እንዲህ ከተበ፡–
ድርሳን ከታቢው፣ ዜና ሕይወት ዘካሪው፣ ዜናዊው ዘነበ ወላ የታላቁን ኢትዮጵያዊ ሳይንቲስት የተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔርን ዓውደ ሕይወት የምድራችን ጀግና አተረፈልን፡፡ ዜና ዕረፍታቸውን ተከትሎም ‹‹አፈር ነህና…!›› በሚል ርዕስ ይህን ከተበ፡፡
ሕይወትና ሞት ስለመጽደቅና መኰነን እንዲሁም ገነትም ስለመግባት አንስቼበት ያለኝን ምንጊዜም አልረሳውም። ከጠየቅኩት በሺሕ ከሚቆጠሩ ጥያቄዎች መካከል ይህቺ አንዷ ነበረች። ‹‹አይ ወንድሜ እኔስ ዕዳዬን ነው የምከፍለው!›› ነበር ያለኝ። የምን ዕዳ አለበት? ስል ማብሰልሰል ጀመርኩ። ምላሹን ፍለጋ ወደ ሙያው ላይ አተኮርኩ። የዕፀዋት ሳይንቲስት ነው። ጠዋት ተነስቶ በሶ ተበስብሶ በተነጠረ ቅቤ ተዋዝቶ ይቀርብለታል። በትኩስ ሻይ ፉት እያለ ይበላል። ያንን በሶ ለማዘጋጀት ስንት የገብስ ፍሬዎች ታምሰው፣ ተሽክሽከው፣ ተቆልተው እና ተፈጭተው ነው በሶ የሆኑት? የተነጠረው ቅቤውን አክሉበት … ሻይ ቅጠሉስ ስንቷ ቅጠል ተሸምጣ ነው ሻይ ቅጠል የሆነችው? ማጣፈጫ ስኳሩን ለመሥራት ስንት አገዳ ተጨምቋል? አስቡት። እነዚህ ሁሉ ህያዋን ነበሩ ሞት ተፈርዶባቸው ለሰው ልጅ ምግብ ሆነዋል። እነሱ ሞተው ለሰው ልጅ ሕይወት ይዘራሉ። ይህ ዕዳ ነው። ምሳ እራት ጨምሩበት። በምድር ላይ የኖርነውን ዓመት አስሉት? ዕዳው እየተቆለለብን ይሄድና ስንሞት አፈር በመሆን ምድሪቱን እናዳብራለን። እንዲህ ነው ‹‹አፈር ነህና ወደ አፈርም ትመለሳለህ›› የገባኝ።