በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ አካባቢዎች በአሁን ጊዜ የተከሰቱት ድርቅ፣ የሥነ ምግብ እጥረት የኮሌራ፣ የፖሊዮና የኮቪድ-19 በሽታዎች የኅብረተሰቡ የጤና አደጋዎች ሆነው ተጠቅሰዋል፡፡
ከ2013 ዓ.ም. ወዲህ ለአምስት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች ዝናብ ባለመዝነቡ በኦሮሚያ (8 ዞኖች)፣ በሶማሌ (9 ዞኖች)፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ (3 ዞኖች) እና በደቡብ (7 ዞኖች) ክልሎች ለድርቅ ተጋልጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ እንደገለጸው፣ በኦሮሚያ ክልል ቦረና፣ በሶማሌ ክልል አፍዴርና ሌሎችም ትኩረት የሚሹ ዞኖችን በመለየት የሥነ ምግብ እጥረት ልየታ በተጠናከረ መልኩ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በዚህም በከፍተኛ የምግብ እጥረት የተጎዱ ሰዎች በማገገሚያ ማዕከላት ተኝተው፣ መካከለኛ የምግብ ጉዳት ያለባቸው ደግሞ በተመላላሽ እየታከሙ መሆኑን አስረድቷል፡፡
ልየታ ከተደረገላቸው ከ853 ሺሕ በላይ ሕፃናት መካከል ከ136 ሺሕ በላይ ሕፃናት በምግብ እጥረት ተጠቅተዋል፡፡ ጥቃቱንም የማኅበረሰብ የሥነ ምግብ እጥረት ደረጃ አመላካች ውጤት መጠንን (ግሎባል አኪዩት ማልኒውትሪሽን ሬት) 16 በመቶ ያደረገው ሲሆን፣ ይህም በኢትዮጵያ ከተቀመጠው 15 በመቶ ስታንዳርድ በላይ በመሆኑ ድጋፍ የሚሹ መሆኑን ከኢንስቲትዩቱ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍና ለነፃ ሕክምና የሚውሉ 230 ሚሊዮን ብር አካባቢ የሚያወጡ 547 የድንገተኛ መድኃኒት ኪት፣ 18.2 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ መድኃኒቶችና የተለያዩ ግብዓቶች፣ በቤተሰብ ደረጃ የውኃ ማከሚያ ኬሚካልን በተመለከተ 2.5 ሚሊዮን ብር የሚገመት እንክብል ተሠራጭቷል፡፡
የሥነ ምግብ ልየታና ሕክምናን ለመደገፍም 9.2 ሚሊዮን ብር በመመደብ እየተሠራ ሲሆን፣ ተጨማሪ ዕቅድ በማዘጋጀት በጀት የማፈላለግ፣ የድንገተኛ ሥነ ምግብ ምላሽና ወረርሽኞችን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራዎችን ለማጠናከር እየተሠራ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡
እንደ ኢንስቲትዩቱ፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በሚገኙ 13 ወረዳዎች የኮሌራ ወረርሽኝ ከተከሰተበት ከነሐሴ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ የካቲት 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ በድምሩ 1541 ሰዎች ሲታመሙ 37 ሰዎች ደግሞ ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል፡፡
የኮሌራ ወረርሽኝ በተከሰተባቸው አምስት (ባሌ፣ ጉጂ፣ ምዕራብ አርሲ፣ ምሥራቅ ባሌ፣ ሊበን) ወረዳዎች 19 ጊዜያዊ የኮሌራ ማከሚያ ማዕከላት እንደተቋቋሙ፣ የሕክምና ግብዓቶችም የማሠራጨት አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝም አክሏል፡፡ ኮሌራን በመከላከሉ ረገድ ቀጣይነት ያለው የግልና የአካባቢ ንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስና የሕክምና ግብዓት በወቅቱ የማሠራጨት፣ የጤና ትምህርትና ለባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠናና አፋጣኝ የሕክምና አገልግሎት የመስጠት ተግባር እየተከናወነ መሆኑ ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዳስታወቀው፣ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የኮሌራ ወረርሽኝ ለመቀነስ የሚያስችል የተለያዩ ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የስምንት ዓመት የኮሌራ ማጥፊያ ፍኖተ ካርታ ሰነድ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ ምዕራፍ እያመራ ነው፡፡
ይህ ፍኖተ ካርታ በ2023 ኮሌራን 90 በመቶ ለመቀነስና ለማጥፋት ያለመ ነው ተብሏል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ የፖሊዮ በሽታን ለመከላከል የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከጥቅምት 2014 ዓ.ም. ጀምሮ እየተካሄደ መሆኑን ኢንስቲትዩቱ ገልጿል፡፡ በመጀመርያው ዙር የክትባት ዘመቻ 17.1 ሚሊዮን በሁለተኛው ዙር የክትባት ዘመቻ ከ18 ሚሊዮን በላይ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን መክተብ ተችሏል፡፡
በሌላ በኩል የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ እስከ የካቲት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ በአጠቃላይ ሚሊዮን የላቦራቶሪ ምርመራዎች የተከናወኑ ሲሆን ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ናሙናዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡ ይህም ማለት አጠቃላይ ከተመረመሩት ሰዎች 9.11 በመቶ የሚሆኑት በኮቪድ-19 ቫይረስ በሽታ የተያዙ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ እስካሁን ድረስ በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች መካከል 7,572 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ይህም 1.5 በመቶ የሞት ምጣኔ እንዳለው ኢንስቲትዩቱ ጠቁሟል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ 44,285,561 ሰዎች የኮቪድ-19 ክትባትን የወሰዱ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 377,796,736 የሚሆኑት የተጠናቀቀ ተከታታይ ክትባትን ወስደዋል፡፡ ክትባቱን ከወሰዱት ጠቅላላ ሰዎች ውስጥ 3,058,233 የሚሆኑት ደግሞ፣ ሦስተኛውን ዙር (ቡስተር ዶዝ) ክትባት ወስደው መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡