ሀገር ማለት ልጄ፣ ሀገር ማለት፣
እንዳይመስልሽ የተወለድሽበት ቦታ፣ የተወለድሽበት አፈር፤
እትብትሽ የተቀበረበት፣ ቀድመሽ የተነፈሽው አየር፤
ብቻ እንዳይመስልሽ፡፡
ሀገር ረቂቅ ነው ቃሉ፤
ሀገር ውስብስብ ነው ውሉ፤
ሀገር ማለት ልጄ፣
ሀገር ማለት ምስል ነው፤ በህሊና የምታኖሪው፤
ከማማ ማህጸን ከወጣሽበት ቀን ጀምሮ፤
በጠባሽው ጡት፣ ወይም ጡጦ
በዳህሽበት ደጃፍ፣ በወደቅሽበት ፈፋ፤
በተማርሽበት ትምህርት ቤት፤
በተሻገርሽው ዥረት፤
በተሳልሽበት ታቦት፣ ወይ በተማጸንሽው ከራማ፤
በእውቀትሽና በሕይወትሽ፣
በእውነትሽና በስሜትሽ፣
የምትቀቢው ምስል ነው፣ በህሊናሽ የምታኖሪው፤
ስትወጅ ሰንደቅ ታደርጊው፡፡
ቢያስጠላሽ የማትቀይሪው፡፡
ሀገር ማለት የኔ ልጅ፣
ሀገር ማለት ቋንቋ ነው፣ ባንደበት አይናገሩት፤
በጆሮ አያደምጡት፤
አማርኛ ኦሮምኛ፣ አፋርኛ ቅማንትኛ፤
ጉራግኛ ወይ ትግርኛ፣ ብለው የማይፈርጁት፡፡
የኔ ልጅ
አማራውና አፋሩ፣ ኦሮሞውና ሲዳማው፣ ጉራግኛሽን ባይሰማ፤
ያልገባሽው እንዳይመስልሽ፣ ሀዘን ደስታሽን ያልተጋራ፡፡
የየልቦናችንን ሀቅ፣ ፍንትው አድርጎ እያሳየ፤
ሕዝቦችን ከሰንደቃቸው፣ አስተሳስሮ ያቆየ፡፡
ሀገር ቋንቋ ነው ልጄ፣ የሁለንተናሽ መስተዋት፤
ሲከፋሽ ትሸሸጊበት፣ ሲደላሽ ትኳኳዪበት፡፡
የኔ ልጅ፣
አያት ቅም አያትሽ፣ ሰላም ሲሆን ከወልቂጤ አድማስ ማዶ፣ ሸቅጦ
ሲያቀና ወረቱን፤
ለእኔና ላንቺ መኖሪያ፣ ሲያቀና ቀዬና ቤቱን፤
ሀገር ጠላት ሲደፍራትም፣ ጦሩን ሰብቆ እየፎከረ፤
ከኦሮሞው ከትግሬው፣ ከአፋሩ ከወላይታው፣ … ከሁሉም የጦቢያ ልጆች፣
አጥንቱን እያማገረ፤
ሀገር ይሉት መግባቢያ፣ ሰንደቅ ይሉት መለያ፣ ሲያቆይልሽ፤
በጉራግኛ ማትገልጪው፣ በጎጥ የማትገድቢው፣ ስንት ታሪክ አለ መለሰሽ!
እና የኔ ልጅ፣
ለዚህ ነው ሀገር ይሉት ቋንቋ፣ ላንቺ የሚያስፈልግሽ፤
ከወልቂጤ አድማስ ማዶ፣ ለተሳሰረ ታሪክሽ፤
ከወልቂጤ አድማስ ማዶ፣ ለተወጠነው እድገትሽ፡፡
እና ልብ በይ ልጄ! ሀገር ማለት ቋንቋ ነው፣ ባንደበት አይናገሩት፤
በጆሮ አያደምጡት፡፡
ከሁሉም በላይ የኔ ልጅ፣
ተፈጥሮ ከቸረችው በረከት፣ የላቡን ፍሬ የሚባላ፤
ሀገር ማለት ወገን ነው፣ የእኔ የምትይው ከለላ፡፡
ትመኪበት ጥሪት፣ ትደምቂበት ብርሃንሽ፤
የሰብእናሽ ግማሽ ውል፣ ወገን ነው ማሕተምሽ፡፡
ዜጋው ነው ልጄ ሀገርሽ፡፡
መሬትማ የኔ ልጅ፣
በእምነትሽና እውቀትሽ፣ ከልለሽ ካላበጀሽው፤
ለእድገትሽ ውጥን ካልሆነ፣ ለተስፋሽ ካልተመገብሽው፤
መሬትማ ባዶ ነው፣ ላለማው የሚለማ፤
ለተስማማው የሚስማማ፡፡
ዥረቱም ግድ የለውም፤ ቦይ ለማሰለት ይፈሳል
ተራራውም ደንቆሮ ነው፣ ለቦረቦረው ይበሳል፡፡
መሬቱ አይደለም የኔ ልጅ፣ እድርተኛው ነው ሀገርሽ፤
ስትቸገሪ ታድጎ፣ ስትታመሚ አስታሞ፣ ስትሞቺ አፈር የሚያለብስሽ፡፡
በእጅሽ ያለ ብሩህ ጽጌ፣ ሰው ነው ልጄ ሀገርሽ፡፡
ወገን ነው ልጄ ሀገርሽ፡፡
እና የኔ ልጅ፣
ሀገር ረቂቅ ነው ቃሉ፤
ሀገር ውስብስብ ነው ውሉ፡፡
(በድሉ ዋቅጅራ፤ፍካት ናፋቂዎች፣1999)