Sunday, September 24, 2023

የኑሮ ውድነት ፖለቲካዊ ገጽታዎች በኢትዮጵያ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

እ.ኤ.አ. ሐምሌ 9 ቀን 2022 ዓ.ም. የስሪላንካ መዲና ኮሎምቦ በከባድ ሕዝባዊ ተቃውሞ ተመታች፡፡ ኑሮ መረረን ያሉ የአገሪቱ ዜጎች ፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግሥቱን ወረሩ፡፡ ስሪላንካ በኮሮና ወረርሽኝ ተጎድታ ቆይታለች፡፡ የዩክሬንና የሩሲያ ጦርነት ተጀምሮ የዓለም የሸቀጦች ገበያ የበለጠ ሲናጋ ደግሞ በከባድ የኑሮ ውድነት ታመሰች፡፡

ይህ ብቻውን ግን አልነበረም የስሪላንካ ዜጎችን ወደ ቁጣ የወሰደው፡፡ የፕሬዚዳንት ጋታባይ ራጃክሰን መንግሥት በተለይ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን በተመለከተ የተከተለው ፖሊሲ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በእጅጉ ያቃወሰ መሆኑ ጭምር ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ እ.ኤ.አ. በ2019 ሲመረጡ የአየር ንብረት ለውጥና የተፈጥሮ ጥበቃ ዋና አጀንዳዬ ነው አሉ፡፡ ስሪላንካ የተፈጥሮ ግብርና (ኦርጋኒክ ፋርሚንግ) ዋነኛዋ አገር አደርጋታለሁ አሉ፡፡

እ.ኤ.አ. በ2020 አንዳችም ማዳበሪያም ሆነ ፀረ ተባይ ወደ ስሪላንካ እንዳይገባ ጥብቅ ውሳኔ አሳለፉ፡፡ በዚህ የተነሳ አገሪቱ ከሚታረስ መሬቷ አንድ ሦስተኛው ጥቅም የለሽ ሆነ፡፡

የአገሪቱ የሩዝ ምርት 20 በመቶ አሽቆለቆለ፡፡ ስሪላንካ የምግብ ምርት እጥረቱን ለመሙላት 450 ሚሊዮን ዶላር ለእህል ግዥ ለማዋል ተገደደች፡፡ የዋጋ ግሽበት 50 በመቶ አሻቀበ፡፡ የአገሪቱ የወጪ ንግድ ዋነኛ የገቢ ምንጭ የሆነው የሻይ ቅጠል ምርት በ16 በመቶ ወረደ፡፡ በዚህ የተነሳ 425 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ ታቀፈች፡፡ የተጎዱ አርሶ አደሮችን ለመደጎም መንግሥት 200 ሚሊዮን ዶላር አፈሰሰ፡፡

በዓመት 4.8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኝ የነበረው የስሪላንካ ቱሪዝም በኮሮና ወረርሽኝ የተነሳ በ80 በመቶ አሽቆልቆሎ ነበር፡፡ የአገሪቱ መንግሥት የተከተለው ኦርጋኒክ ግብርና (ተፈጥሯዊ ግብርና) ፖሊሲ ደግሞ ሁለት ሚሊዮን አርሶ አደሮችን ለረሃብ የሚዳርግ ሆነና አረፈው፡፡

ስሪላንካ በዓለም ኢኮኖሚ አለመረጋጋት፣ በሸቀጦች ዋጋ መናርና በኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ብቻ ሳይሆን ብልሹ ፖሊሲ አመጣሽ የኢኮኖሚ መናጋት የገጠማት አገር ተባለች፡፡ ልክ እንደ ስሪላንካ ሁሉ በቅርብ ጊዜያት ኑሮ አስመርሯቸውና የዋጋ ንረት አስከፍቷቸው በተቃውሞ አደባባይ የሚወጡ ዜጎች በበርካታ አገሮች እየታዩ ነው፡፡ በፔሩ በቅርብ ጊዜያት የታየው ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡

አሁን ያለውን የዓለም የዋጋ አለመረጋጋት ችግር የፈተሸው ማርቲን ዎልፍ “Inflation is a political challenge as well as an economic one” ወይም የዋጋ ንረት ኢኮኖሚያዊም ፖለቲካዊም ፈተና ነው በሚል ርዕስ ሰፊ ሀተታ በፋይናንሺያል ታይምስ ላይ አስነብቦ ነበር፡፡

ዎልፍ በርካታ አገሮች እየገጠማቸው ያለው ችግር አዝጋሚ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ግን ያልተቋረጠ የዋጋ ግሽበት ጭማሪ የሚታይበት ኢኮኖሚያዊ ፈተና መሆኑን ያመለክታል፡፡ ይህ ደግሞ በምጣኔ ሀብት ምሁራኑ ስታግፍሌሽን (Stagflation) ተብሎ እንደሚጠራ ያመለከተው ጸሐፊው፣ የዋጋ ንረትን መቅደም በማይችል የኢኮኖሚ ዕድገት መዳከር መሆኑን ያስረዳል፡፡ ይህ ደግሞ ለዓለም ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ ፈተናም መሆኑን ይገልጻል፡፡

ልክ እንደ ሌሎች አገሮች ሁሉ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት በኢትዮጵያም ማሳሰብ ከጀመረ ከራርሟል፡፡ የኑሮ ውድነቱ መነሻ በርካታ መንስዔ ያለው ችግር እንደሆነ ይነገራል፡፡ በመፍትሔነትም በርካታ ጉዳዮች ታሳቢ ሊደረጉ እንደሚገባ ማሳሰቢያ ሲቀርብ ይታያል፡፡ ለረዥም ዓመታት ሳያቋርጥ የቀጠለው የዋጋ ግሽበት የኑሮ ውድነትን እየወለደ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ፣ ውጤቱ ወዴት ያመራል የሚለው ጉዳይ ደግሞ አሳሰቢነቱ የጎላ መሆኑ ተደጋግሞ ይነገራል፡፡

ከሰሞኑ በተለይ በስንዴና በጤፍ ላይ የተፈጠረው የዋጋ ንረትና መናጋት፣ በኢትዮጵያ ያለውን የኑሮ ውድነት ምንጭና ምን ሊደረግ ይገባል ስለሚለው ጉዳይ ብዙ እያወያየ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ የሚታየው የኑሮ ውድነት ወይም የዋጋ ንረት ጤናማ ያልሆነና ኢኮኖሚያዊ መነሻ የሌለው ነው የሚል አስተያየትም ይሰማል፡፡

የዋጋ ንረቱና የኑሮ ውድነቱ ከዚህ ቀደምም ቢሆን በንግድ አሻጥርና በሕገወጥ ግብይት የመጣ ነው የሚል አመክንዮ ሲያሰጥ ቆይቷል፡፡ አሁን አሁን ደግሞ ችግሩ በመንግሥት ሚዛኑን ያልጠበቀና አላስፈላጊ የኢኮኖሚ ጣልቃ ገብነት የመጣ ሊሆን ይችላል የሚል ሙግትም ይሰማል፡፡

ይህን በሚመለከት አስተያየት ከሚሰጡት አንዱ የምጣኔ ሀብትና የፋይናንስ ባለሙያው አቶ ጥላሁን ግርማ፣ በአላስፈላጊ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት የመጣ የዋጋ መረበሽ ችግር መኖሩን ይጠቅሳሉ፡፡

‹‹በዓለም ገበያ ላይ ከሰሞኑ ስንዴ በቶን 400 ዶላር ሲሸጥ አይቻለሁ፡፡ ይህ ምናልባት በኩንታል ከ40 ዶላር የማይዘል ሲሆን እኛ ጋ ካለው የስንዴ ግብይት የማይራራቅ ነው፡፡ ነገር ግን እንደምናየው ገበሬው ከሦስት ሺሕ ብር በማይበልጥ ገንዘብ በኩንታል ካልሸጥክ እየተባለ ዋጋ በመተመን ስንዴ እየሰበሰቡ ወደ ውጭ የመላኩ ጉዳይ፣ ለገጽታ ግንባታ ካልሆነ በስተቀር የኑሮ ውድነቱን የሚያባብስ የፖለቲካ ዕርምጃ ነው፤›› ይላሉ፡፡

በግላቸው ከባሌ ወደ አዳማ እስከ 70 ሺሕ ብር እየተከፈለ ስንዴ በኮንትሮባንድ የማስገባት ሕገወጥ አሠራር መፈጠሩን እንደሰሙ የሚናገሩት አቶ ጥላሁን፣ በዚህ መንገድ የገባ ስንዴ ደግሞ በከፍተኛ ዋጋ ለተጠቃሚዎች መቅረቡ የማይቀር መሆኑን ይገምታሉ፡፡ ‹‹ድንበር አካባቢ ካሉ ቦታዎች የሚገኝ ምርት ደግሞ በኮንትሮባንድ ወደ ውጭ አገሮች እንዲወጣ የሚገፋፋ ነው፤›› የሚሉት አቶ ጥላሁን፣ ያልተጠና የመንግሥት ዕርምጃ የኑሮ ውድነቱን አባባሽ የሆነ ውጤት እንዳለው ያመለክታሉ፡፡

“The Ethiopian Economist View” በሚባለው የፌስቡክ፣ የቴሌግራምና የዩቲዩብ ገጽ ላይ የተለያዩ የኢኮኖሚ ጉዳዮችን በመተንተን የሚታወቁት የምጣኔ ሀብት ባለሙያ አቶ ዋሲሁን በላይም፣ የኑሮ ውድነቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ምንጭ አለው የሚለውን ሐሳብ ይጋሩታል፡፡

‹‹የፖለቲካዊ ለውጦች ፍላጎትን ይጨምራሉ፡፡ ለምሳሌ በግጭትና በጦርነት የተነሳ ሰዎች ይፈናቀላሉ፡፡ እንዲሁም ከአምራችነት ወደ ምርት ፈላጊነት ሕይወታቸው ይቀየራል፡፡ ይህ ደግሞ የምርት ፈላጊ ቁጥርን ስለሚጨምር ዋጋን ያሻቅባል፡፡ የከተሞች ማደግ፣ የመንደሮች መስፋፋትና የመንገድ ትራንስፖርት እንቅስቃሴ መጨመር የባጃጅ ትራንስፖርት አቅርቦትን አስፈላጊ አድርጎታል፡፡ በአንድ ለሊት ተነስተህ ባጃጆች አገልግሎት እንዲያቆሙ የፖለቲካ ውሳኔ ስትወስን፣ በጎን ግን የትራንስፖርት አገልግሎት ፍላጎትን ዋጋ በእጅጉ እንዲያሻቅብ ነው የምታደርገው፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

‹‹ይህም ብቻ አይደለም ቢሮክራሲና የተንዛዛ አሠራር የዋጋ ንረት ምንጭ ይሆናሉ፡፡ በየቦታው፣ በየጉምሩክ መፈተሻ ኬላውና በየወደቡ አላስፈላጊ ቀረጥና ታሪፍ መጨመርም ዋጋን ያንራል፡፡ ዕቃ ከውጭ ለማስገባት ታሪፍና ቢሮክራሲ ሲበዛ ዞሮ ዞሮ ሸማች ላይ ይመጣል፡፡ መሬት፣ መብራት፣ ውኃ፣ መንገድ ለማግኘት አምራቹ ዋጋና ቢሮክራሲ ሲበዛበት ችግሩ ተመልሶ ሸማቹ ላይ ይወድቃል፤›› በማለት ነው አቶ ዋሲሁን ተያያዥ ችግሮችን ያስቀመጡት፡፡

አቶ ዋሲሁን እንደሚሉት፣ ወትሮም 40 በመቶ ላይ ብቻ ተወስኖ የቆየው የኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም፣ በተለያዩ ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች የሚስተጓጎል ከሆነ የምርት አቅርቦት ችግርን የበለጠ ይጎዳል፡፡ አምራቾች የመጨረሻው የሸማች ኅብረተሰብ ላይ የሚያወርዱት ዋጋ የማምረቻ ወጪንና ትርፍን ብቻ ሳይሆን፣ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ጉዳዮችንም ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

የኃይል አቅርቦት፣ የብድር አቅርቦት፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ብቻ ሳይሆኑ የሠለጠነ የሰው ኃይል የማግኘት፣ እንዲሁም የተቀላጠፈ ቢሮክራሲያዊ አሠራር የማግኘት፣ አስተማማኝ የመሠረተ ልማት አቅርቦት ብቻ ሳይሆን አስተማማኝ ፀጥታና የደኅንነት ዋስትና የማግኘት አመቺነትንም ታሳቢ በማድረግ፣ አምራቾችና አቅራቢዎች ሸማቹ ኅብረተሰብ የሚከፍለውን ዋጋ እንደሚተምኑ አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት አረጋ ሹመቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የኑሮ ውድነቱና የዋጋ ንረቱ ፖለቲካዊ መነሻዎች ያሉት መሆኑን እንደሚጋሩ ይናገራሉ፡፡

የየካቲት ወር አጠቃላይ ዋጋ ግሽበት 29.5 መሆኑንና የምግብ ዋጋ ንረት የሚመራው መሆኑን የኢኮኖሚ ባለሙያው ይጠቅሳሉ፡፡ ለአብነት ስንዴን ማሳያ የሚያደርጉት አረጋ (ዶ/ር)፣ ‹‹ባልተጠናና ባልተገባ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ዋጋ ሊንር ይችላል፡፡ የስንዴ ዋጋን መንግሥት መወሰኑ፣ እኔ ወደ ውጭ እልካለሁ ብሎ መነሳቱ፣ ለዩኒየኖች ካልሸጣችሁ ብሎ ማስገደዱ ሳይቀር የስንዴን ዋጋ አናግቶታል፤›› ሲሉ ማሳያ አድርገው ያስረዳሉ፡፡

አገሪቱ ያለችበት ሰላማዊ እንቅስቃሴ ስንዴን ወይም ጤፍን ከቦታ ወደ ቦታ አጓጉዞ ለመሸጥ አመቺ መሆን አለመሆኑም ዋጋውን እንደሚበይን ይናገራሉ፡፡ ምርት አለ ተብሎ በሚታመንበት ወቅት እንኳን ምርት ከገበያ የሚታጣውና ዋጋው የሚንረው በአገሪቱ ሰላምና ፀጥታ ሁኔታ ችግር መሆኑንም ያሰምሩበታል፡፡

‹‹አገሪቱ ባለሁለት አኃዝ የዋጋ ግሽበት ማስተናገድ ከጀመረች 20 ዓመታት አስቆጠረች፡፡ ይህ የዋጋ ግሽበት ደግሞ ከሥራ አጥነት፣ ካልተረጋጋ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ከውጭ ምንዛሪ እጥረትና ከውጭ ንግድ ሚዛን መዛባት ከመሳሰሉ ዓበይት የኢኮኖሚ ቀውሶች ጋር ሲደራረብ ችግሩን ያከፋዋል፤›› በማለት ነው የሚናገሩት፡፡

አረጋ (ዶ/ር) የፋይናንሺያል ታይምስ ጽሑፍ ያነሳውን ‹የስታግፍሌሽን› ጽንሰ ሐሳብ የበለጠ ያጠናክሩታል፡፡ ‹‹ለረዥም ዓመታት ኢኮኖሚ እያደገ ነው እየተባለ ነገር ግን የሥራ አጥነት ችግር እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የዋጋ ግሽበቱ ዘላቂ ከሆነ ‹ኢንፍሌሽን› ሳይሆን ችግሩ ‹ስታግፍሌሽን› ተፈጠረ ነው የሚባለው፤›› በማለትም የኢትዮጵያን የዋጋ ንረት ደረጃ ገልጸውታል፡፡

በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበትን በሚመለከት የሚባለው፣ በመፍትሔነት የሚጠቆመውና ሲደረግ የሚታየው ፍፁም የሚቃረን ነው፡፡ ከሰሞኑ ‹‹እንጀራ መግዛት ስላቃተኝ ተገድጄ ባል ላገባ ነው፤›› የሚል የአንዲት ሴት የኑሮ ውድነት ምሬት በማኅበራዊ ሚዲያዎች ከፍተኛ መነጋገሪያ ፈጥሮ ነበር፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች አንድ እንጀራ ሦስት ቦታ እየተቆረጠ፣ ሰዎች አንድ ቁርጥ እንጀራ በስድስት ብር እየገዙ መሆናቸው ሲነገር ሰንብቷል፡፡

በሌላ አካባቢ ደግሞ በመሥሪያ ቤቶችና በመኖሪያ ሠፈሮች የእንጀራ ዕቁብ ተጀመረ የሚል ወሬ ሲናፈስ ይሰማል፡፡ እነዚህ ሁሉ የኑሮ ውድነት ምሬቶች የተጋነኑ ወይም ከተጨባጩ ሀቅ የራቁ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ የዋጋ ንረቱና የኑሮ ውድነቱ ዛሬ በተጨባጭ የሚታይ ያፈጠጠና ዘርፈ ብዙ ቀውስ ሊፈጥር የሚችል ችግር መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዋሲሁን፣ ‹‹የኑሮ ውድነት የዋጋ ንረትና የሰዎች የመግዛት አቅም መዳከም ተደምረው የሚፈጥሩት ችግር ነው፤›› ይሉታል፡፡ የዋጋ ንረቱ መነሻ በቀጥታ ከፍላጎት መጨመር ጋር የተገናኘ መሆኑን የሚጠቅሱት ባለሙያው፣ የዜጎች ተጨማሪ ገቢ የማግኘት ዕድል የጠበበ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ችግሩ መክፋቱን ያስረዳሉ፡፡

‹‹ለአንዳንዶች የጤፍ በኪሎ ግራም አንድ መቶ ብር መግባትና ብዙም ሳይቀንስ ተሰቅሎ መቅረት ጉዳያቸው ላይሆን ይችላል፡፡ ከጤፍ ይልቅ የሱዙኪ ተሽከርካሪ ዋጋ መውጣትና መውረድ የሚያሳስባቸው አሉ፡፡ ይሁን እንጂ ገበያው በየቀኑ ሰዎችን እየተፋቸው፣ የመኖር ዋስትናን እያናጋ፣ ብዙ ሰውም በረንዳ እየወጣ በየቀኑ እያየን በመሆኑ፣ ችግሩ ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ መፍትሔዎችን የሚሻበት ደረጃ ላይ እንገኛለን፤›› ብለዋል፡፡

የፋይናንስና ኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ጥላሁን በበኩላቸው፣ ‹‹እስካሁን በባንክ ወለድ ጭማሪ የመጣ የዋጋ ንረት ብቻ ነው ያልገጠመን፡፡ መንግሥት ባለው ችግር ላይ ቤንዚን ላለመርጨት በሚል ይመስላል በእንደኛ ባለ ኢኮኖሚ ውስጥ የባንክ ወለድ መጨመር የሚጠበቅ ቢሆንም ይህን ከማድረግ ተቆጥቧል፡፡ ገንዘብ ቆጣቢዎች ግሽበቱ የብራቸውን ዋጋ ሊቀንስባቸው ይችላል፡፡ ሆኖም ወለድ ይጨመር ቢባልና ባንኮች ባበደሩት ብድር ላይ ወለድ ቢጨምሩ ይዞት የሚወርደው ግሽበት ከፍተኛ ነበር የሚሆነው፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያዊያን በሌሎች ምክንያቶች ሊመጡ የሚችሉ የዋጋ ግሽበቶች በሙሉ አግኝተዋቸዋል (ሰለባ ሆነዋል) ሲሉ ነው አቶ ጥላሁን የሚናገሩት፡፡ ‹‹በዓለም የሸቀጦች ዋጋ መናጋት ሊፈጠር የሚችል የዋጋ ንረት ገጥሞናል፡፡ በተለይ በዓለም ነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የሚመጣ ግሽበት ዋና ሰለባ ሆነናል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ እያስከተለ ባለው ግሽበትም ተጠቂ ነን፡፡ አስመጪዎች ከጥቁር ገበያ በውድ ዶላር እየሰበሰቡ ዕቃ ስለሚያቀርቡ ውድ ዋጋ ለመክፈል ተገደናል፡፡ በሌላ በኩል በፀጥታ ችግርና በፖለቲካ ቀውስ በሚፈጠር የገበያ መረበሽ ዋጋ እየከፈልን ነው፡፡ የኢኮኖሚ አሻጥር በሞላበት ገበያ ውስጥ የመንግሥት ያልተጠና ጣልቃ ገብነት መታከሉ ደግሞ ለዋጋ ግሽበቱ ተጨማሪ ራስ ምታት እየሆነ ነው፤›› በማለት የኢትዮጵያን ግብይት እያመሳቀሉ ያሉ ችግሮችን አስቀምጠዋል፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያው አረጋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ምርትን ከተትረፈረፈ ቦታ እጥረት ወዳለበት ቦታ ወስዶ መሸጥ አለመቻል የፈጠረውን ችግር ያወሳሉ፡፡ ‹‹‹ስንዴ ወይም ጤፍ በቂ ምርት ካለበት ቦታ አጓጉዞ ለመሸጥ ጤናማ የሆነ ሁኔታ በአገሪቱ ከሌለ ችግሩ ይባባሳል፤›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡

የኢትዮጵያ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ችግር ግን ከዚህ ያለፈ በጥልቀት ሊጠና የሚገባ እንቆቅልሽ እንዳለውም ነው የሚያስረዱት፡፡

‹‹ለምሳሌ የኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር በቂ ምርት እንዳለ ይናገራል፡፡ ስንዴ 9.8 ሚሊዮን ቶን መመረቱን ይናገራል፡፡ ዓለም አቀፍ ተቋማት ግን አገሪቱ የሚያስፈልጋት ሰባት ሚሊዮን ቶን ስንዴ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ መንግሥት ያስፈልጋል ከሚባለው በላይ ምርት መኖሩን እየተናገረ፣ ነገር ግን በገበያው የስንዴ እጥረት ችግር መታየቱ ሊጠና የሚገባው ነው፤›› ብለዋል፡፡

በኢኮኖሚው ውስጥ መንግሥት ጣልቃ ሊገባ እንደሚችል የሚያስረዱት አረጋ (ዶ/ር)፣ ነገር ግን ጣልቃ ገብነቱ የታሰበውን ዓይነት በጎ ለውጥ ማምጣት እንዳለበት ይመክራሉ፡፡ የብርን የመግዛት አቅም የማዳከም ውሳኔ፣ ከቀረጥ ነፃ መሠረታዊ ሸቀጦችን የማስመጣት፣ እንዲሁም በፍራንኮ ቫሉታ ምርቶችን የማስገባት ዕርምጃዎች የተፈለገውን ዓይነት የዋጋ ንረትን የመቀነስ ግብ ያሳኩ መሆናቸው ሊጠየቅ ይገባዋል ይላሉ፡፡

‹‹መንግሥት ጣልቃ ለመግባት የሚያስችል መዋቅር አለኝ ወይ የሚለውን መጠየቅ አለበት፡፡ የመንግሥት መዋቅር ሙስና፣ ብልሹ አሠራር፣ የሕግ የበላይነት ችግሮች የሞላበት፣ እንዲሁም ግልጽነትና ተጠያቂነት ያልሰፈነበት እስከሆነ ድረስ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት በሚል ጣልቃ መግባቱ መልሶ ያለመረጋጋት ሊያመጣ ይችላል፤›› በማለት ነው አረጋ (ዶ/ር) ያሳሰቡት፡፡

ይህን የሚጋራ አስተያየት የሰጡት አቶ ዋሲሁን፣ ‹‹ኢኮኖሚ የሚረጋጋው ከፖሊሲ በተጨማሪ በጠንካራ ተቋማት ነው፤›› በማለት የተቋማትን አስፈላጊነት አስምረውበታል፡፡

በኢትዮጵያ ለዋጋ ንረቱና ለኑሮ ውድነቱ መንስዔ ብቻ ሳይሆን፣ መፍትሔ እየተባሉ በመንግሥት አካላት የሚሰጡ ምላሾች ብዙ ግራ ሲያጋቡ ይታያሉ፡፡

በቅርቡ አንድ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባለሥልጣን፣ ‹‹ለኑሮ ውድነቱ እኛ ተጠያቂ አይደለንም፤›› የሚል ምላሽ መስጠታቸው ሰፊ መነጋገሪያ ፈጥሮ ነበር፡፡ በተመሳሳይ አንድ የመንግሥት ኃላፊ፣ ‹‹የሸቀጦች የዋጋ ንረት የአመለካከት ችግር ውጤት ነው፤›› ማለታቸው ሲያነጋግር መቆየቱ አይዘነጋም፡፡

በኔዘርላንድስ የሚኖሩት የምጣኔ ሀብት ባለሙያና ጋዜጠኛ አቶ ኤድመንድ ተስፋዬ፣ እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ባለው ደሃ አገር ቀርቶ በአውሮፓም ቢሆን ካፒታሊዝም በሚል ፈሊጥ እንዲህ ባለው ጊዜ መንግሥት ጣልቃ ከመግባት አይታቀብም ይላሉ፡፡

‹‹በአውሮፓም መንግሥታት የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ ጣልቃ እየገቡ ነው፡፡ ለምሳሌ የኢነርጂ ኩባንያዎች ከ250 ዩሮ በላይ በወር ለጋዝ እንዳያስከፍሉ ለአንድ ዓመት ተደጉመዋል፡፡ በኢትዮጵያም የመንግሥት ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ መንግሥት ራሱ የጥቁር ገበያ ተዋናይ ሲሆን መታየቱ ትልቅ እንቅፋት ነው፤›› ብለዋል፡፡

መንግሥት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የኑሮ ውድነቱን ከማርገብ ይልቅ አባባሽ ዕርምጃዎችን ሲወስድ እንደሚታይ የጠቀሱት አቶ ኤድመንድ፣ ‹‹ሪፖርተር በቅርቡ በሠራው ዘገባ መሠረት መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ 100 ቢሊዮን ብር በስድስት ወራት መበደሩ አንዱ ማሳያ ነው፤›› ብለውታል፡፡ የኑሮ ውድነቱ በኢትዮጵያ እጅግ ከፍተኛ የሆነውን የኑሮ ጥገኝነት (Dependency Ratio) የበለጠ እንዳይጨምረው፣ እንዲሁም በጥቂቱ እየተፈጠረ የነበረውን ባለመካከለኛ ገቢ (Middle Income) ማኅበረሰብ ጨርሶ እንዳያጠፋው እንደሚሠጉም ባለሙያው አክለዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -