Saturday, July 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል ባንኮች ቁጥር ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ውስጥ ከዜሮ ተነስቶ ዛሬ ላይ 29 መድረሱ አንዱ ነው፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ የግል የመድን ተቋማትና የአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ወደ ባንክ የተሸጋገሩትን ሳይጨምር እንደ ቅደም ተከተላቸው 17 እና 36 ደርሰዋል። ከዚህ በተጨማሪ ባለቤትነታቸው ሙሉ በሙሉ የመንግሥት የሆኑ ሁለት ባንኮችና አንድ የመድን ኩባንያ በአገሪቱ የፋይናይስ ዘርፍ ከፍተኛውን የገበያ ድርሻ ይዘው ይገኛሉ፡፡ 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ስድስት የሊዝ ኩባንያዎች የፋይናንስ አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን፣ በተለምዶ በባንኮችና በአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ብቻ ይሰጥ የነበረው የክፍያ አገልግሎት በዲጂታል ዘዴ በኢትዮ ቴሌኮምና ሌሎች የቴክኖሎጂ ተቋማት በመቅረብ ላይ ከመሆኑ ውጪ፣ በአገሪቱ የካፒታል ገበያን የማቋቋም ሒደት ተጀምሯል፡፡ ለውጭ አገር ዜጎችና ተቋማት ዝግ የሆነው የፋይናንስ ዘርፍ እንደሚከፈት የፖሊሲ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ በመሆን በቅርቡ የተሾሙት አቶ ማሞ ምሕረቱ በዋናነት በፋይናንስ ተቋማት ባለቤትነት የተመሠረተው ‹‹ካፒታል የፋይናንስ ልህቀት ማዕከል አክሲዮን ማኅበር›› ሥራ መጀመሩን ይፋ በተደረገበት ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ የተመዘገበውን የኢኮኖሚ ዕድገት የፋይናንስ ዘርፉም ላይ በተመሳሳይ በፍጥነት እየተስፋፋና እየዘመነ ነው ብለዋል፡፡

 መንግሥት የፋይናንስ ሥርዓቱን ለማዘመንና ለማጠናከር የተለያዩ ዕርምጃዎችን እየወሰደ ስለመሆኑ የተናገሩት የባንኩ ገዥ፣ ምንም እንኳ በዘርፉ በንጽጽር የተሻለ የተማረና የሠለጠነ የሰው ኃይል እንዳለ ቢታመንም ከዘመኑ ጋር የዋጀና የላቀ ክህሎት ያላቸው ባለሙያዎች እጥረት አሁንም ከፍተኛ ነው በማለት አስረድተዋል፡፡ ይህንን ክፍተት ለመሙላት የተጠናከረና የተደራጀ፣ በዘርፉ ዕድገት ላይ የሚያተኩር የምርምር፣ የማማከርና የሥልጣና ተቋም አስፈላጊነት ወሳኝ መሆኑን አቶ ማሞ በንግግራቸው አፅንኦት የሰጡት ጉዳይ ነው፡፡

ዜጎች የመረጃና የዲጂታል ዘመን ላይ እንደመገኘታቸው መጠን፣  የፋይናንሰ አገልግሎት ለማግኘት ወደ ፋይናንስ ተቋማት መሄድ የግድ የማይሆንበት ጊዜ ላይ ተደርሷል፡፡

ተገልጋዩ የትምና በማናቸውም ጊዜ የሚፈልገውን የፋይናንስ አገልግሎት ማግኘት በሚችልበት በዚህ ጊዜ  ከፋይናንስ ዘርፉ ፈጣን ዕድገት መሳ ለመሳ የዘርፉ አመራርና ሥራም ይበልጥ ተወዳዳሪና ውስብስብ እየሆነ መምጣቱን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ 

ይህንን የፋይናንስ ዘርፉን ፈጣን ዕድገት ተከትሎ ከዘመኑ ጋር የዋጀ ብዙ የሰው ኃይል ማፍራት እጅግ በጣም አስፈላጊና አገራዊ ተልዕኮም ቢሆንም፣ የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነፃፀር በሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ በቴክኖሎጂና በአሠራር ረገድ ገና ብዙ ርቀት መጓዝ እንዳለበት ይገለፃል፡፡

የጎህ ቤቶች መጨራች የሆኑትና በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ረዥም ዘመን የቸሩት እንዲሁም አዲስ የተመቸረተው ካፒታል የፋይናንስ ልህቀት ማዕከል አክሲዮን ማ‹፤በር ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ጌታሁን ናና ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ ለ30 ዓመታት በተለይም በግሉ ዘርፍ አንቀሳቃሽነት የሠራው የፋይናንስ ኢንዱስትሪ እንደሚታወቀው ለውጭ ተቋማት ዝግ ሆኖ ሲሠራበት ቆይቷል፡፡

ከቴክኖሎጂዎች በፍጥነት መቀያየር ጋር ተያይዞ በተለይ የባንክ፣ የኢንሹራንስ አገልግሎቶች ወደ ዲጂታል እየተቀየሩ ነው፣ ዘርፉ በተለይም በኢትዮጵያ ለውጭ ተሳታፊዎች ዝግ ሆኖ የሚጠብቅበት ጊዜ አብቅቷል፡፡ በሌላ በኩል ከባንክ ውጭ ያሉ የውጭና የአገር ውስጥ ተሳታፊዎች ኢንዱስትሪ ውስጥ ገብተው እንዲሠሩ እየተፈቀደ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ቢሆንም የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ለዚህ ዝግጁ ነው? የሚለው ጥያቄ የሚነሳበት ነው፡፡ ደግሞም ዝግጁ አይደለም እንደ አቶ ጌታሁን ሐሳብ፡፡ ስለሆነም ለውጡ ከሚፈልገው ፍጥነት ጋር የሚሄድ የሰው ኃይል ስለሌለ ያንን ማፍራት አንድ ሥራ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ከለውጡ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ አሠራር መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡

በአገር ውስጥ ባንኮችና ኢንሹራንሶች ለበርካታ ዓመታት በትላልቅ የኃላፊነት ደረጃ የሠሩትና በዚህ ወቅት የማማከር አገልግሎት ላይ የተሰማሩት ወ/ሮ ዘመናይ ክፍሌ እንደሚናገሩት፣ በተለይም የግል የፋይናንስ ተቋሞቹ በዘርፉ ላይ 30 ዓመታት ያስቆጠሩ ቢሆንም፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚፈለገውን የዘርፉን ተፈላጊ ነገሮች ከማሟላት አንፃር ወደ ኋላ ቀርተዋል፡፡

ጊዜው የሚፈልገውን ለማሟላት በቂ አቅም ያለው የሰው ኃይል አለ ወይ? የአመራር አቅማቸውስ ምን ያህል ነው?፣ ሰዎችን እንዴት ነው የሚያስተዳድሩት? ቴክኖሎጂንና ሰውን እንዴት አጣምሮ መሄድ ይቻላል? በቀጣይ የውጭ የፋይናንስ ተቋማት ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ምን ዓይነት ፈተዎች ያጋጥማሉ? የሚለውን በተጠና መንገድ ተገቢው ትንተና ተደርጎ ሰፊ ዕገዛ በሚፈለጉበት ሁኔታ መሠልጠን እንደሚገባቸው ወ/ሮ ዘመናይ ይናገራሉ፡፡

በፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚገኝ አንድ መሪ ለውጥ አስፈላጊ መሆኑን ማመን አለበት፡፡ አንድ ሰው የአንድ ተቋም መሪ ሆነ ማለት ክፍተት የለውም ማለት እንዳልሆነና የአመራር ክህሎት ዓይነቶች እጅግ በርካታ በመሆናቸው ሥልጠና ለበታች ሠራተኛ ብቻ ባለመሆኑ ሁሉም የፋይናስ ዘርፉ ላይ ከታች እስከ ላይ ያለ ባለሙያ በተለያየ መንገድ በዘመናዊ አውታሮች ጭምር የሚሰጥን ሥልጠና እንደሚስፈልገው የፋይናንስ አማካሪዎች ያስረዳሉ፡፡

የአሐዱ ባንክ  አቋቋሚ ፕሬዚዳንት ሆነው ያገለገሉትና የቦርድ አማካሪ ሆነው በማገልገል ያሉት አቶ እሸቱ ፋንታዬ በበኩላቸው፣ የገንዘብ ገበያ፣ የውጭ ምንዛሪ ገበያ፣ የቦንድ ገበያና ሌሎችም አገልግሎቶች በመንግሥት ፍላጎትና እንዲሁም በባንኮች መካከል የሚደረጉትን እነዚህን አገልግሎቶች ለማሳለጥ የሚሆን በቂ ዕውቀት የለም የሚል አስተያየት ያቀርባሉ፡፡ የትምህርት ተቋማት ለእንደዚህ ዓይነት አገልግሎቶች     የሚሆን ሰው እያደራጁና እየፈጠሩ ወደ ገበያ ሲያስገቡ አልነበረም፡፡

ለአብነትም የኢንሹራንስ ዘርፉ የተለየ ዕውቀትና ክህሎት የሚጠይቅ ዘርፍ ቢሆንም፣ ለዘርፉ የሚሆኑ ባለሙያዎችን ወደ ውጭ አገሮች ልኮ የማሠልጠን ልምድም የቀነሰበትና የኢንሹራንስ ዘርፉ ተትቷል የሚባል መሆኑን አቶ እሸቱ ይናገራሉ፡፡

የአገሪቱ የፋይናነስ ተቋማት ካሉባቸው ክፍቶች አንዱ የሆነውን ዘመኑ የደረሰበትን የፋይናንስ ዕድገት የሚመጥን የሠለጠናና ክህሎት ያዳበረ በቂ የሰው ኃይል ክፍተት በመረዳት ዘጠኝ ባንኮች (ንግድ ባንክ፣ ወጋገን፣ ቡና፣ ንብ፣ አዋሽ፣ ዳሽን፣ ደቡብ ግሎባል፣ አዲስ ኢንተርናሽናል፣ ጎሕ ቤቶች)፣ ዘጠኝ የመድን ኩባንያዎች (አፍሪካ፣ ኒያላ፣ ናይል፣ ቡና፣ ንብ፣ ሉሲ፣ ዓባይ፣ አዋሽ፣ ፀሐይ) አንድ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም (ዋሳሳ) ሁለት የፋይናንስ ዘርፍ ማኅበራትና (የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች፣ የኢትዮጵያ አነስተኛ የፋይናነስ ተቋማት ማኅበር) እንዲሁም ግለሰቦች ተሰባስበው ለፋይናንስ ዘርፍ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚችል የተደራጀና የተጠናከረ የምርመራ፣ የማማከርና የሥልጠና አገልግሎቶችን የሚሰጥ ተቋም ‹‹ካፒታል የፋይናንስ ልህቀት ማዕከል አክሲዮን ማኅበር›› በሚል ስያሜ መሥርተው መጋቢት 14 ቀን 2015 ዓ.ም በሒልተን ሆቴል ይፋ አድርገዋል፡፡

አክሲዮን ማኅበሩን ለማቋቋም አስፈላጊው የአዋጪነት ጥናት ተካሂዶ፣ ጥናቱ ላይ ተመሥርቶ የተቋቋመው ካፒታል የፋይናንስ ልህቀት ማዕከል 61.6 ሚሊዮን ብር የተፈረመና 34.8 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ያለው ነው፡፡

 ተቋሙ የፋይናንስ ተቋማት ባለሙያዎች አፈጻጸም ብቃት ለማሻሻል የሚያስችሉ ሥልጠናዎችን ከፍተኛ ዕውቀት ክህሎትና ልምድ ባላቸው የአገርና የውጭ አገር ባለሙያዎች እንደሚሰጥ፣ የሥልጠና ፕሮግራሙን የሚያዘጋጀው በአገልግሎት ፈላጊዎች ፍላጎት ላይ በመመሥረት አስፈላጊውን የዳሰሳ ጥናት በማካሄድ እንደሚሆን በሒልተን ሆቴል በተዘጋጀው መድረክ ላይ ተገልጿል፡፡

የቢዝነስ ተቋማትን የሚቆጣጠሩ ተቋማት በሙሉ የልህቀት ማዕከሉ የሚቆጠጣሩ ሲሆን፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የግብር ሰብሳቢ ሥስሪያ ቤቶች እንዲሁ ሌሎቹ አክሲዮን ማኅበሩን የሚከታተሉ ተቋማት መካከል ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡ ነገር ግን ተቋሙ የትምህርት አካል ስላልሆነ ሥልጠናውን፣ የማማከር፣ የጥናትና ምርምር ሥራውን ለማከናወን በዚህ ወቅት ከትምህርት ሚኒስቴር የሚሰጠው የተለየ ፍቃድ አይኖርም ተብሏል፡፡ የሚሰጣቸውንም የማማከርና የሥልጠና አገልግሎቶች በፋይናንስ ተቋማት ቅፅር ውስጥ የሚሰጥ ይሆናል፡፡

የልህቀት ማዕከሉ ለመነሻ የሚሆኑ የተለያዩ የኮርስ ዝርዝሮችን በዚህ ወቅት ማዘጋጀቱን የሚገልጽ ሲሆን፣ ነገር ግን የት ላይ የፋይናንስ ዘርፉ ምን ይፈልጋል የሚለውን ከዋናዎቹ የኢንዱስትሪ ባለቤቶች ግብዓት ተወስዶ እየተቀረፀና እየተሻሻለ እንደሚሄድ አቶ ጌታሁን ይናገራሉ፡፡

የሥልጠና የማማከርና የምርምር ሥራዎቹን ጥራት ለማረጋገጥና አቅም ለመገንባት በዘርፉ ከተሰማሩ የአገር ውስጥና የውጭ አገሮች ዕውቅ ተቋማት ጋር በትብብር ከመሥራቱ በሻገር፣ በተለይም አሁን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ የፋይናንስ ጥናት ኢንስቲትዩት ጋር በቅርበት ለመሥራት ጥረት እናደሚያደርግ የካፒታል የፋይናንስ ልህቀት ማዕከል አክሲዮን ማኅበሩ አስታውቋል፡፡

ሥራ መጀመሩን ይፋ እንዳደረገው ‹‹የካፒታል የፋይናንስ ልህቀት ማዕከል አክሲዮን ማኅበር›› ዓይነት ተቋማት በአገሪቱ እንዲስፋፉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ያሉት የብሔራዊ ባንክ ገዥው አቶ ማሞ፣ እንዲህ ዓይነት ተቋማት አሁን በዘርፉ ያለውን ከፍተኛ የሆነ የሠለጠነ የተካነ የሰው ኃይል እጥረት በማቃለል፣ በምርምርና በማማከር አልግሎታቸው ዘርፉ ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርስ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ብለዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች