Sunday, March 3, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ ኃላፊነት ኃላፊነት ተሰጥቶት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በመጀመሪያው ምዕራፍ ውጥኑ ሰባት ሺሕ ኪሎ ሜትር የባቡር መሠረተ ልማት ለመዘርጋት ወጥን ይዞ ነበር።

በዚህም ቁልፍ የሚባሉ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ከባቢዎችን በባቡር ለማስተሳሰርና አገሪቱን ከተለያዩ የባህር ወደብ አማራጮች ለመገናኘት አልሞ ቅድሚያ የተሰጣቸውን የአዲስ አበባ ቀላል ባቡርና የአዲስ አበባ ጂቡቲ አገር አቋራጭ የባቡር መሠረተ ልማት አጠናቋል።

በመቀጠልም የአዋሽ ወልዲያ መቀሌ የባቡር መሠረተ ልማት ግንባታን ጀምሮ በከፍተኛ የዕዳ ጫና ወገቡን ተመቶ መላወስ እንዳስቃተው መረጃዎች ያመለክታሉ።

ኮርፖሬሽኑ የአዲስ አበባ ጂቡቲ የባቡር መሠረተ ልማትና የኢዲስ አበባ ቀላል ባቡር መስመርን ለመገንባት ከቻይና መንግሥት ያገኘው ከሁለት ቢሊዮን ዶላር ብድር መክፈል የጀመረ ሲሆን፣ ግንባታው ያልተጠናቀቀው የአዋሽ ወልዲያ መቀሌ ባቡር ፕሮጀክትን ለመግንባት ከአውሮፓ አበዳሪዎች የወሰደው 1.7 ቢሊዮን ዶላር ብደርም ገና በሁለቱ እግሩ ሳይቆም የመክፈል ግዴታ ወስጥ ገብቷል። 

ኮርፖሬሽኑ ገንብቶ ያስረከባቸው የባቡር መሠረተ ልማቶች የተፈለገውን ያህል ገቢ ባያስገቡም እንደ ሀብት የሚቆጠሩ ናቸው። ነገር ግን ኮርፖሬሽኑ የተቋቋመበት ካፒታል ከተሰጠው ግዙፍ ተልዕኮ ጋር የማይመጣጠን በመሆኑ ተጨማሪ ብድር ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ አበዳሪዎች ለማግኘት አልቻለም።

ግዙፍ ተልዕኮ የተሰጠው ይህ ኮርፖሬሽን የተቋቋመው በ39.9 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በተለያዩ ጊዜያት የተወሰኑ ማሻሻያዎች ተደርገው መጠነኛ ጭማሪ ቢደረግለትም ይህም ከተልዕኮው ጋር የሚመጣጠንና ተጨማሪ ብድር ለማግኘት የሚያስችለው እንዳልሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። በስተመጨረሻ ላይ ግን መንግሥት የኮርፖሬሽኑን የረዥም ጊዜ ውትወታ ሰምቶ ሰሞኑን ምላሽ ሰጥቷል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት መጋቢት 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ ደንብ ያሻሻለ ሲሆን፣ በዚህም የኮርፖሬሽኑ ማቋቋሚያ ካፒታል በብዙ እጅ እንዲያድግ ወስኗል።

ምክር ቤቱ አሻሽሎ ባፀደቀው ማቋቋሚያ ደንብ መሠረት የኮርፖሬሽኑ የተፈቀደ ካፒታል 221 ቢሊዮን ብር ሆኗል። በጥሬ ገንዘብና በዓይነት የተከፈለ ካፒታሉ ደግሞ 120 ቢሊዮን ብር ሆኖ ማቋቋሚያ ደንቡ መሻሻሉን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ያወጣው መግለጫ ያመለክታል።

የኮርፖሬሽኑ ማቋቋሚያ ካፒታል በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ መወሰኑ የሚኖረው ፋይዳ በተመለከተ ያነጋገርናቸው የኮርፖሬሽኑ የፋይናንስና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሥዩም ገዙ ውሳኔው የተቋሙን ክፍተቶች እንደሚሞላ አስረድተዋል።

ኮርፖሬሽኑ ያሉበትን ክፍተቶች ለመሙላት ዕገዛ ይፈልግ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሥዩም፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅና አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙትን ደግሞ ያላቸውን አቅም ለማጠናከር በእጅጉ ያስፈልግ ነበር ብለዋል።

የባቡር አገልግሎት ውጤታማነትን ለማሻሻልና የንድፍ ማሻሻያ በማዘመን፣ ያለባቸውን ውዝፍ ዕዳ ለመክፈል እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡ 

እነዚህን ሥራዎች ለመሥራትም ኮርፖሬሽኑ መንግሥትን በጠየቀው መሠረት የተፈቀደ ካፒታል ማሻሻያና የተከፈለ ካፒታል ከፍ እንዲል መወሰኑን ገልጸዋል፡፡ 

እስካሁን ድረስ መንግሥት በካፒታል ኢንጄክሽን ለኮርፖሬሽኑ ሲያስተላልፍ እንደነበር አስታውሰው፣ የተፈቀደ ካፒታል ደግሞ ከላይ ይሠራሉ ተብሎ የተዘረዘሩትን ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ የሚያግዙ ናቸው ብለዋል፡፡ 

የኮርፖሬሽኑ ራሱ አትራፊ ሳይሆን በአገሪቱ ሌሎች ሴክተሮችን በመደገፍ ኢኮኖሚውን ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና ያለው ነው፡፡  እንደ አቶ ሥዩም ገለጻ፣ በባቡር ትራንስፖርት በባህሪው ግዙፍ ክምችትን ለማንቀሳቀስ በዝቅተኛ ወጪ የሚከወን ነው፡፡ በዚህም ኮርፖሬሽኑን ከጎረቤት አገሮች ጋር የሚደረገውን የትኛውም ግብይት በቀላሉና በአነስተኛ ዋጋ አገልግሎት በመስጠት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል፡፡ 

ይህም ለግብርና፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለንግድና በሌሎች ዘርፎች ላይ ያለው አዎንታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ እንደሆነም ያብራራሉ፡፡  እስካሁን ዘርፉ ለራሱ ትርፋማ ባይሆንም ሌሎች ዘርፎች እንዲያድጉ የማድረግ አቅሙ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 

በምሳሌነት ያነሱትም፣ አንድ ባቡር ጂቡቲ እስከ አዲስ አበባ 3,500 ቶን ዕቃ የማጓጓዝ አቅም እንዳለው፣ ከመኪና ለማጓጓዝ ቢሞከር እስከ ሰባት ከባድ አሽከርካሪዎች የሚይዘው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 

ይህም ገንዘብና ጊዜን ከመቆጠብ አኳያ ከሌሎች የትራንስፖርት ዘርፍ በይበልጥ፣ ተመራጭ የሚሆነው የባቡር አገልግሎት መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ 

ይህንንም አገልግሎት በይበልጥ ለማሳለጥ የተጀመሩ የባቡር ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በመጨረስና አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙትን ደግሞ አቅማቸውን ማሳደግ ግድ እንደሚል አስረድተዋል፡፡ 

መንግሥት በሁሉም ዘርፍ ሪፎርም እያደረገ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ሥዩም፣ ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ይጠቀሳል ብለዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ የባህር ወደብ እንደሌላት ገልጸው፣ የተለያዩ ወደቦችን ለመጠቀም የባቡር መሠረተ ልማት ለወደፊቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡  

አሁን ባለው ሁኔታ ለጂቡቲ የበርበራ፣ ሊሙ፣ ወደቦች ላይ ፓርት ላይ የሚሠሩ ሥራዎች የሚደግፈው፣ የባቡር አገልግሎት መሆኑን አብራርተዋል፡፡ 

በተለይም በቅርቡ መንግሥት የፈቀደው የተፈቀደ ካፒታል ማሻሻያና የተከፈለ ካፒታል በዋናነት የሚጠቅመው የመለዋወጫ ችግሮችን ለመቅረፍ፣ ወደብ ለመገንባት፣ የሎጂስቲክ መገልገያዎችን (መጫኛና ማራገፊያ ፍጥነት እንዲኖረው) የኮርፖሬሽኑ ገቢ ከፍ እንዲል የሚያግዙ ናቸው ብለዋል፡፡ 

ከዚህ ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም ሁለትና ሦስት ጊዜ የማመላለስ አቅም ያለው ባቡር በስድስትና በሰባት ምልልስ ፍጥነት እንዲኖረው (እንዲጨምር) ለማድረግ የሚደግፍ ነው ብለዋል፡፡ 

አክለውም ለወደፊቱ ኢኮኖሚው እያደገ ሲሄድ ኢኮኖሚውን የሚመጥን አቅም የሚኖረው ባቡር መሠረተ ልማት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

 

 

 
     

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች