Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ፈተና

የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ፈተና

ቀን:

በዳግም መርሻ

ይህ ሰሞን የምግብ (የዳቦ) ጉዳይ አገራዊ አነጋጋሪነቱ ጎልቶ የወጣበት ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴን ኤክስፖርት ልናደርግ  ነው ብሎ በይፋ ከማብሰሩ አፍታም ሳይቆይ፣ ቦረናን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የምግብ እህል ተረጂዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ፣ እንደ ስንዴና ጤፍን የመሰሉ መሠረታዊ የሰብል ምርቶች ላይ እጥረት መከሰቱና የመሸጫ ዋጋቸውም ጣሪያ መንካቱ አወዛጋቢና በርካታ ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ሆኖ ሰንብቷል። በርካታ የአገር ውስጥና የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንም፣ ስለስንዴ የተትረፈረፈ ምርት በመንግሥት አካላት የተነገረውን መሬት ላይ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማነፃፀር ሲያነሱና ሲጥሉ የሰነበቱበት ሰሞን ነበር።

ምግብ ከአየር ቀጥሎ ለሰው ልጅ ከሚያስፈልጉት መሠረታዊ ፍላጎቶች መካከል አንዱ እንደሆነ አንድና ሁለት የለውም። የምግብ ጉዳይ ከፖለቲካዊ፣ ከማኅበራዊና ከኢኮኖሚያዊ መስተጋብራችን ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። በአንድ አገር ፈጣን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት ለማምጣትና ዘላቂ የልማት አቅም ለመገንባት ወሳኝ ነው። የምግብ ፍላጎቱና አቅርቦቱ የተሟላለት ሕዝብ  ጤናማ፣ አምራች፣ ረዥም ዕድሜና አስተማማኝ የፈጠራ ብቃት ይኖረዋል። በአንፃሩ የምግብ ፍጆታው ያልተረጋገጠለትና በረሃብ ቸነፈር የሚጠቃ ሕዝብ በአዕምሮና በአካል የበለፀገ አይሆንም፣ አምራች ዜጋም ሊሆን አይችልም። ይህ ደግሞ በአገር ዕድገትና ልማት ላይ የሚያስከትለው ችግር በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡

የምግብ እጥረት ያለባቸው አገሮች ለተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችና ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶች የመጋለጣቸው ሁኔታም የተለመደ ነው። አንጋፋው ፖለቲከኛ  መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) በአንድ ወቅት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነበረ ውይይት የተናገሩትን ንግግር እዚህ ጋ ማስታወስ ይገባል። ‹‹…የሚበላው ያጣ ሕዝብ መሪውን ይበላል›› ነበር ያሉት። ይህን ያሉት ሕዝብ በሕይወት የሚያኖረውን ነገር ሲያጣ ከማማረርና ከማመፅ አልፎ ተጠያቂ ነው ብሎ የሚያስበውን መንግሥት በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ከሥልጣኑ አስገድዶ ለማስወገድ እንደማያመነታ ለማስታወስ ነበር። የብዙ አገሮች ተሞክሮም ይህንኑ ያሳያል።

ለምሳሌ በቅርቡ በሲሪላንካ ሕዝቡ ቤተ መንግሥቱን ጥሶ በመግባት የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ታባያ ራጃፓክሳን ከሥልጣናቸው እንዲነሱ ያደረጉበት መንገድ ከዳቦ ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው። እንዲሁም አሁን እስር ላይ የሚገኙት የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር ከሥልጣን የተወገዱት ሕዝቡ የዳቦ ዋጋ መናርን በመቃወም የጀመረው ሠልፍ እያየለ በመምጣቱ መሆኑም አይዘነጋም። ግብፅም ብትሆን ለዳቦ አመፅ ባይተዋር አይደለችም።

አንዳንድ መንግሥታት የዚህ ችግር ሰለባ እንዳይሆኑ መሠረታዊ የግብርና ምርቶች ወደ ውጭ እንዳይላኩ በማገድ ለአገር ውስጥ ፍጆታ ብቻ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ያደርጋሉ። እንደ ቻይና፣ ሳውዲ ዓረቢያና ሌሎች የፈረጠመ የኢኮኖሚ አቅም ያላቸው  ከበርቴ አገሮች  ደግሞ ከምሥራቅ አውሮፓ፣ ከእስያና ከአፍሪካ አገሮች ለእርሻ ምቹ የሆኑ ሰፋፊ መሬቶችን በመግዛት አልያም በመኮናተር አምርተው ዜጎቻቸውን ለመመገብ ጥረት ያደርጋሉ። በምግብ ራስን አለመቻል ዳፋው ከዚህም አልፎ ሙሉ የኢኮኖሚ ነፃነትና ብሔራዊ ክብርንም ያሳጣል። የምግብ ፍላጎታቸውን ያላሟሉና ሲረዱ የቆዩ አገሮች ለተለያየ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖዎች የመጋለጥ ዕድላቸው እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው። ነፃነቷን ጠብቃ የቆየችው አገራችን የዚህ እውነታ ተጋሪ ናት። የምግብ ዋስትና ጉዳይ ከ1970ዎቹ ጀምሮ የተያዘ ሰፊ ጽንሰ ሐሳብ ነው።

በ1990ዎቹ መጨረሻ ግን ከሚሊኒየሙ ግቦች የመጀመሪያው ከሆነው ረሃብን የማጥፋት ዘመቻ ጋር እንዲያያዝ ተደርጎ በመታሰቡ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ብዙ አገሮች የፖሊሲዎቻቸው አካል ካደረጉት ቆይተዋል። በዓለም የምግብ ድርጅት (FAO) ትርጓሜ መሠረት የምግብ ዋስትና (Food Security) ተረጋገጠ የሚባለው በአንድ አገር ያሉ ሁሉም ሰዎች ንቁና ጤናማ ሕይወት ለመኖር የሚያስፈልጓቸውን በቂ፣ ጤናማና የተመጣጠነ ንጥረ ነገር ያለው የምግብ አማራጭ ለማግኘት የሚችሉበት የኢኮኖሚ አቅምና አቅርቦት ሲኖራቸው ነው፡፡ የምግብ ዋስትና አንድምታው የራስን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የውስጥ ፍጆታን ከማሟላትም የዘለለ ነው፡፡ 

የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ የምርት እጥረትና የዓለም አቀፍ ገበያ ውጣ ውረድ በሚያጋጥምበት ሁኔታም ለዜጎች በቂ የምግብ ምርት ሳያስተጓጉል የሚያቀርብ የምርት፣ የግብይትና የመጠባበቂያ ክምችት ሥርዓት የመዘርጋት፣ እንዲሁም የኢኮኖሚ አቅም ማዳበርንም ያካትታል፡፡ ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከስምንት መቶ ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ በምግብ እጥረት ችግር ወይም የምግብ ዋስትናው ባልተረጋገጠ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ፣ የዓለም የምግብ ድርጅት (World Food Program) ሪፖርት ያመላክታል፡፡ ወደ ሁለት ቢሊዮን የሚገመት ሕዝብ ደግሞ ጠቃሚ ቫይታሚኖችንና ማዕድናትን እንደማያገኝ ይገለጻል። ይህ ሁኔታ የተደበቀ ረሃብ (የምግብ እጥረት) (Hidden Hunger) መከሰቻ ተብሎ ይታወቃል፡፡

በአፍሪካ ደረጃ የምግብ እጥረት የሚፈትነው ሕዝብ ቁጥር በጠቅላላው 21 በመቶ ሲሆን፣ ከሰሃራ አፍሪካ በታች ከሚገኙት ውስጥ ደግሞ ከሕዝቡ 25 በመቶ የሚሆነው በምግብ እጥረት ችግር ዕጦት የሚንገላታ መሆኑን አኃዛዊ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡  ከዚህ በተጨማሪም 13.7 በመቶ የሚሆኑ ጨቅላ ሕፃናት በተመጣጠነ ምግብ ዝቅተኛ ክብደት ያላቸው ሲሆን፣ 30.7 በመቶ የሚሆኑ ከዜሮ እስከ አምስት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሕፃናት ደግሞ የቀነጨሩ መሆናቸው የዓለም አቀፍ የተመጣጠነ ምግብ ሪፖርት ያሳያል።

አፍሪካ ዘጠኝ ቢሊዮን ሕዝብ መመገብ የሚያስችል ለእርሻ ተስማሚ የሆነ መሬት ባለቤት እንደሆነች ቢነገርላትም፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኞቹ አገሮች ይህንን ሀብት በአግባቡ ባለመጠቀማቸው ሕዝቦቻቸውን ከምግብ እጥረት፣ ከተረጂነትና ከድህነት ማላቀቅና የምግብ ዋስትናን በአስተማማኝ ማረጋገጥ ትልቅ ፈተና ሆኖባታል። 

የፓን አፍሪካ ባንክ (The Pan-African Bank) ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፣ አኅጉሪቱ ለእርሻ ተስማሚ የሆነውን 65 በመቶ የሚደርሰውን የተፈጥሮ ሀብቷን በተገቢው ሁኔታ ጥቅም ላይ ማዋል ብትችል እ.ኤ.አ. በ2050 ዘጠኝ ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ የሚገመተውን የዓለም ሕዝብ መቀለብ የሚያስችል ዕምቅ አቅም እንዳላት ያትታል። ሆኖም «ፅድቁ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ» እንደሚሉት ሆኖ አብዛኞቹ በአኅጉሪቱ የሚገኙ አገሮች ዋና መለያቸው ረሃብ፣ የምግብ እጥረት፣ የምግብ ዋስትና ማጣትና የመሳሰሉት ክስተቶች ሆነው ዘመናትን ዘልቋል። ይህም አኅጉሪቱ ጤናው የተጠበቀና አምራች ኅብረተሰብ እንዳይኖራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

አኅጉሪቷ የራሷን የግብርና ምርቶች በዓለም ገበያ በመሸጥ እንደሌሎቹ ሁሉ ተጠቃሚ የመሆን ሰፊ ዕድል ቢኖራትም፣ ዛሬም የምግብ ዋስትናዋ በከፊል የተንጠለጠለው በውጭ ዕርዳታና ተሸምቶ በሚገባ የምግብ እህል ላይ ነው። በዚህም ምክንያት አኅጉሪቱ ካላት ውስን ጥሪት ላይ በዓመት ወደ 75 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በማውጣት ለዚሁ ዓላማ ስታውል እንደቆየች የአፍሪካ ልማት ባንክ (African Development Bank) ሪፖርት ይጠቁማል።

በኢትዮጵያም ተጨባጭ ሁኔታ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደ አገር ካሉ ችግሮች መካከል አንደኛው ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2022 የዓለም የረሃብ ምደባ መሠረት (Global Hunger Index) ኢትዮጵያ ከ121 የዓለም አገሮች ውስጥ 104ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን፣ በአገሪቱ የምግብ ዋስትናቸው ያልተረጋገጠላቸው ዜጎች ቁጥር ወደ 22.3 ሚሊዮን ይደርሳል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ሁሉም ዓይነት ከምግብ ጋር የተያያዙ ችግሮችን እያስተናገደች መሆኑን ይፋ አድርጓል።

ኢትዮጵያ እንደ ስንዴ፣ ሩዝ፣ አተር፣ ምስር፣ ፓስታ፣ ማካሮኒ… ያሉ ምርቶችን ከውጭ ለማስገባት በየዓመቱ ከፍተኛ ወጪ ትከሰክሳለች። ለምሳሌ ስንዴን ከውጭ ለማስገባት በየዓመቱ ከ700 ሚሊዮን ዶላር እስከ አንድ ቢሊዮን፣ ዶላር እንዲሁም ለአተር በአማካይ በየዓመቱ 50 ሚሊዮን ዶላር እንደምታወጣ ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

አገራችን ሰፊና ለም መሬት፣ ተስማሚ ሥነ ምኅዳር፣ ግዙፍ የውኃ ሀብትና በእንስሳት ሀብት የተቸረች ናት። ይሁንና ከ74 ሚሊዮን ሔክታር ሊታረስ የሚችል የመሬት ሀብቷ ያልዘመነ የአስተራረስ ዘዴን በመጠቀም እየታረሰ የሚገኘው 13 ሚሊዮን ሔክታር ብቻ ነው። ይህም በአብዛኛው ሕዝቡ ተጠጋግቶ የሚኖርባቸውን ደጋና የወይና ደጋ አካባቢዎችን አካቶ የያዘ ነው።

በእነዚህ ቦታዎች የሚካሄደው አብዛኛው የግብርና ሥራ አሁንም ድረስ ኋላቀር የአስተራረስና የግብዓት አጠቃቀም ዘዴን የሙጥኝ ያለ ነው። ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ማዳበሪያ የሚጠቀመው አርሶ አደር 62 በመቶ ብቻ ነው። እንዲሁም የምርጥ ዘር አቅርቦታችን 25 በመቶ፣ የሜካናይዜሽን አጠቃቀማችን ስድስት በመቶ፣ በመስመር የመዝራት ባህላችን 28 በመቶ ላይ እንደሚገኝ መረጃው ያመላክታል። በዚህ በኩል የሚታረሰው መሬት የሚሰጠው ምርት በሔክታር አነስተኛ በመሆኑ በምግብ ራሳችንን መቻል ቀርቶ በግብርናው ዘርፍ የተሰማራውን ሰፊውን አርሶ አደር እንኳን በበቂ ሁኔታ መግቦ ማሳደር አልቻለም። በአንፃሩ ከተሞች በአብዛኛው ሊባል በሚችል መልኩ ከገጠር በሚቀርቡ የግብርና ምርቶች ላይ ጥገኛ በመሆናቸው፣ የአብዛኛው ነዋሪም የኢኮኖሚ አቅም ካለው የኑሮ ውድነት አንፃር የማያወላዳ በመሆኑ የምግብ ዋስትና ችግሮችን በመሠረታዊነት ማቃለል አልተቻለም። 

በመሠረታዊ ምግቦች ደረጃ ሲታይ ዜጎች የሚያገኙት የካሎሪ መጠን በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ባለቤት እንደሆንን ቢነገርም፣ “ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ” እንደሚባለው አገራዊ ብሂል ሆኖ ሥጋ፣ ዶሮ፣ ወተት፣ ቅቤ፣ አትክልትና ፍራፍሬ… የመሳሰሉት በማዕድናት የበለፀጉ ምግቦች ለአብዛኛው ዜጋ ብርቅ ወደ መሆን ደረጃ ተሸጋግረዋል። የኑሮ ውድነቱና የገበያው መመሰቃቀል ደግሞ ችግሩን በይበልጥ እንዲከፋ አድርጎታል።

በአንድ አገር የምግብ ዋስትና ተረጋገጠ የሚባለው አብዛኛው ሕዝብ በቂ፣ ጤናማና የተመጣጠነ ምግብ በአስተማማኝ ሁኔታ ማግኘት ሲችልና በየዕለቱ ከ2,100 በላይ የካሎሪ መጠን ሲያገኝ ነው። የምግብ ዋስትና ስለመረጋገጡ ሌላው መመዘኛ  ለተመጣጠነ የምግብ እጥረት የሚጋለጠው ሕዝብ ቁጥር ከጠቅላላው ሕዝብ አምስት በመቶ በታች ሲሆን ነው። በመሆኑም በእነዚህ መመዘኛዎች ሚዛን ሲፈታ፣ በአገራችን የምግብ ዋስትናን ያልተረጋገጠ ከመሆኑ ባለፈ በተለይ በገጠር የሚኖረውን ማኅበረሰብ ከፍተኛ ለሆነ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ ለአካልና ለአዕምሮ ዕድገት ውስንነት (በተለይ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊ ሕፃናት) ተጋላጭ እንደሆነ ጥናቶች ያመላክታሉ። 

ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ቁጥር መካከል አብላጫውን ቁጥር የሚይዘው ማኅበረሰብ (80 በመቶ የሚሆነው) የኑሮው መሠረት ግብርና ነው። የአገሪቱም ኢኮኖሚ በአብዛኛው ግብርናው ላይ የተንጠለጠለ ነው። ግብርና ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት 34.1 በመቶ መያዙና 79 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱን ውጭ ምንዛሪ ገቢም ከዚሁ ዘርፍ የሚገኝ መሆኑ ነው። ያም ሆነ ይህ ሁሉ የሰው ኃይል የተሰማራበት ግብርናችን በምግብ ራሳችንን የመቻል ፍላጎታችንን አላሳካልንም።

ለምሳሌ በእስራኤል በእርሻ የተሰማራው ሕዝብ ከጠቅላላው ሕዝብ ውስጥ 2.5 በመቶ ብቻ ሲሆን፣ ይህን ጥቂት የሰው ኃይል ይዞ የሚካሄደው ግብርና የሚካሄደው ደግሞ 20 በመቶ በሆነው ለም መሬትና 60 በመቶ በሆነው ደረቅ መሬት ላይ ነው።   ከዚህ አኳያ በእርሻ የተሰማራው ሕዝብ ቁጥርና የሚታረሰው የመሬት መጠን ከእኛ ጋር ሲወዳደር እዚ ግባ የሚባል ባይሆንም፣ የእርሻው ምርታማነት ራስን ከመቻል አልፎ የተትረፈረፈ የግብርና ምርት በተለይም የፍራፍሬና የአትክልት ውጤቶችን ኤክስፖርት በማድረግ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት አገሮች ተርታ እንድትሠለፍ አስችሏታል። በዚህም እስራኤል በዓመት 1.3 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ታገኛለች።

እስራኤል በዓለም ላይ ከፍተኛ ወተት ከሚያመርቱ አገሮች አንዷና ዋነኛዋ ናት። በዓመት ከአንድ የወተት ላም በአማካይ እስከ 13,000 ሊትር ወተት ታመርታለች። አብዛኞቹ አገሮች ከአንድ ሔክታር በአማካይ እስከ 500 ኩንታል ቲማቲም የሚያመርቱ ሲሆን፣ እስራኤል ግን በመስኖ ልማት ከአንድ ሔክታር እስከ 3‚000 ኩንታል ቲማቲም የምታመርትበት ደረጃ ላይ ደርሳለች። የእኛ አማካይ ምርት ከ350 እስከ 400 ኩንታል አይዘልም።

በሌላ በኩል በእስራኤል በምርትና በድኅረ ምርት ወቅት ያለው የብክነት መጠን 0.5 በመቶ ብቻ ነው፡፡ የእኛ ግን ከኋላቀር አስተራረስ፣ ዘር መዝራት፣ አጨዳና ውቂያ የግብርና እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ከአጠቃላይ ምርታችን 25 በመቶ የሚሆነው ለብክነት ይዳረጋል። እስራኤልን በግብርናው ውጤታማ እንድትሆን ካደረጓት መሠረታዊ ምክንያቶች አንዱ የመስኖ እርሻን ለማካሄድ የምትጠቀመው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ነው። ለምሳሌ 62 በመቶ የሚሆነው ለመስኖ ጥቅም ላይ የሚውለው ውኃ የሚመረተው የተወገደ ውኃን መልሶ በማጣራት (Waste Water) እና ጨዋማ ውኃን ጨዋማ ወዳልሆነ ውኃ መልሶ በመቀየር (Brackish Water) ነው። 

ከዚህም ባሻገር 75 በመቶ የሚሆነው የመስኖ እርሻ የሚከናወነው የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂን (Drip Irrigation) ሥራ ላይ በማዋል ነው። ከዚሁ ጎን ለጎን በመላ አገሪቱ የሚካሄዱት ዘርፈ ብዙና ተጨባጭነት ያላቸው (Applicable) የጥናትና ምርምር ተግባራት በዓብይነት ይጠቀሳሉ። በእኛ በኩል ምንም እንኳን አሁን አሁን ብዙ መሻሻሎች ቢኖሩም፣ አብዛኛው የግብርና ሥራ ከሳይንሱ በጣም በራቀ ሁኔታ የሚከናወን ነው። ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማካሄድ፣ በማስተዋወቅና በማስፋት በኩልም ብዙ መንገድ ይቀረናል።

ይህ የሚያሳየን ነገር በሰው ሀብትም ሆነ በተፈጥሮ ሀብት ባለፀጋ ብንሆንም፣ የተሰጠንን ሀብት በብቃትና በጥበብ በመጠቀም ባለመቻላችን በሚፈለገው ደረጃ ውጤት ላይ አለመድረሳችን ነው። ይህም በመሆኑ ግብርናችን የተፈጥሮ አደጋን ሆነ፣ ሰው ሠራሽ አደጋን በዘላቂነት መቋቋም እንዳንችል አድርጎናል። በአሁኑ ወቅት ቦረናን ጨምሮ በሶማሌ፣ በደቡብና ሌሎችም አካባቢዎች ከብት በቁም እስከ መሞት ያደረሰው፣ ድርቅና ከድርቁ ጋር ተያይዞ የተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ ለዚህ ጥሩ ማስረጃ ነው። 

ችግሮችን የምናነሳው ከሠራን በግብርናው ዘርፍ ያለውን መጥፎ ታሪክ መለወጥ እንደሚቻል ለማመላከት እንጂ፣ ሒደታችን በሙሉ ጨለማ አድርጎ ለማሳየት አይደለም። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የግብርና ምርትን ለማሳደግ የማይናቅ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ከእነዚህ ጥረቶች መካከል ለማዳበሪያና ለምርጥ ዘር አቅርቦት፣ ለኩታ ገጠም እርሻ፣ ለሜካናይዜሽን አገልግሎት ወዘተ. መስፋፋት የተሰጠው ትኩረት ይጠቀሳል። ከዚህ አንፃር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስንዴ ልማት ላይ እየታየ ያለው የምርትና ምርታማነት እመርታ ይበል የሚያሰኝ ነው። ስንዴ በመኸር ብቻ ሳይሆን፣ በበጋ መስኖም እንዲለማ በማድረግ ውጤት ማምጣት እየተቻለ ነው።

ለምሳሌ የበጋ ስንዴ ልማት ሥራዎች ከተጀመሩ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በዘጠኙ ክልሎች በመስኖ አምራች ያልነበሩ አካባቢዎች ወደ ስንዴ ምርት እንዲገቡ ተደርጎ፣ አመርቂ ውጤት መታየቱን የግብርና ሚኒስቴር ሪፖርት ያመላክታል። በዚህም ኢትዮጵያ በ2015 ዓ.ም. ብቻ በመስኖና በዝናብ ከ160 ሚሊዮን ኩንታል የተሻገረ የስንዴ ምርት ታገኛለች ተብሎ ይጠበቃል። እስካሁን በመኸር ከ112 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት የተገኘ ሲሆን፣ ከበጋ የመስኖ ስንዴ ደግሞ 52 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል ነው የተባለው። ያለውን የገበያ ንረት ከማረጋጋት፣ ከምርት አቅርቦት፣ ወዘተ. ጋር ተያይዘው የሚስተዋሉ ችግሮች እንዳሉ ሆኖ ስንዴ በዚህ መጠን መመረት መቻሉ ለዘመናት ከረሃብተኝነት አባዜ ለመገላገል ጥረት ስታደርግ ለቆየች አገር ትልቅ እመርታና ሰፊ ዕድልም ይዞ የሚመጣ ነው።

ይህ መልካም ውጤት ቀጣይነት እንዲኖረው ከተሠራ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በዋና ዋና የምግብ እህሎች ራሳችንን ከመቻል አልፈን፣ ከውጭ ድጋፍና ተመፅዋችነት ለመላቀቅ ሰፊ ዕድል አለን የሚል እምነት አለኝ። ይሁንና በምግብ ራስን መቻል ብቻውን የምግብ ዋስትና ያረጋግጣል ማለት እንዳልሆነ የዘርፉ ምሁራን ደጋግመው የሚገልጹት እውነታ ነው፡፡ ምክንያቱም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ በተጓዳኝ ሌሎች በርካታ ሥራዎችን መሥራት የሚጠይቅ በመሆኑ ነው። በአገራችን ከሚታየው ፈጣን የሕዝብ ቁጥር ዕድገት፣ የተፈጥሮ ሀብት መመናመን፣ የአየር ንብረት ለውጥ መለዋወጥ፣ ከግብዓት አቅርቦት ውስንነት፣ ወዘተ. አንፃር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ፈተናው ቀላል እንዳልሆነ ግልጽ ነው።

ከዚህ አኳያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት መሠረታዊ ነገሮች ላይ ቅድሚያ ሰጥተን መሥራት እንዳለብን አምናለሁ።

  1. በሁሉም የግብርና ዘርፎች (ዓይነቶች) ምርትና ምርታማነትን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ፣

2 ለእርሻ ሥራ ያልዋሉ አዳዲስ መሬቶችን ወደ ሥራ በማስገባት የተፈጥሮ ሀብታችንን በአግባቡ መጠቀም፣

  1. የምግብ ምርቶች ላይ የሚታዩትን ውስብስብ የገበያ ሥርዓቶችን በየጊዜው እየተፈተሹ መፍትሔ ማበጀት፣
  2. ከእርሻ እስከ ገበያ ድረስ ባሉት ሒደቶች ያለውን የምርት የብክነት መጠን መቀነስ፣
  3. የግብርና ሥራን በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በሜካናይዜሽን አገልግሎት ለማስደገፍ የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል፣
  4. የአካባቢ ጥበቃና የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምን ከግብርና ሥራ ጋር አቀናጅቶ መሥራት፣
  5. ከተለመደው የአመጋገብ ባህላችን ባሻገር አዳዲስ የአመጋገብ ባህሎችን ማበረታታት።

በእኔ እምነት እነዚህ መሠረታዊ ነገሮች ላይ ጊዜ ሳናጠፋ መሥራት እንዳለብንና አገራችንን ከተደቀነባት የምግብ ዋስትና ሥጋት እንውጣ ባይ ነኝ። ይህ ባልሆነበት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አዳጋች ነው ብዬ እሠጋለሁ።

 ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው dagimmersha@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...