Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉለውጡንና አገርን ስናስባቸው

ለውጡንና አገርን ስናስባቸው

ቀን:

በምሥጋናው ገለታ

መጋቢትና 24ኛዋ ቀን

በኢትዮጵያ መጋቢት የካቲትን የሆነበት ታሪክን ባለፉት 12 ዓመታት መመዝገብ ጀምሯል። የመጀመርያው የ2004 ዓ.ም. የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሠረት ድንጋይ የተቀመጠበት ነው። ሁለተኛው የለውጡ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አገሪቱን የመምራት ኃላፊነት የተቀበሉበት ወር ሆኗል። ሁለቱም ድርጊቶች ወሩ በገባ በ24ኛው ቀን መዋላቸው ደግሞ ወሩን ብቻ ሳይሆን፣ የቀኑን ታሪካዊነት ያጎሉታል። ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የግድቡን የመሠረት ድንጋይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ወረዳ ባስቀመጡ ከስድስት ዓመታት በኋላ፣ ሌላኛው ጠቅላይ ሚኒስትር የአገር መሪ ሆነው ሰላማዊ የሥልጣን ርክክብ አድርገዋል። መጋቢት አንደ የካቲት ወር ባይበዙም ሌላ ታሪካዊ ግጥምጥሞሽ ያለው፣ ለየት ያለና ድርብርብ ቀን እንድናስብ አድርጎናል።

ግድቡ

ዓባይን ለልማት ያስገበረው የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ባይጠናቀቅም እየተገነባ፣ እየተጓተተ፣ አደረጃጀቱ ዳግም እየተዋቀረ፣ ኃይል እያመነጨ ግንባታው ወደ 90 በመቶ ደርሷል። የዘመናት ቁጭትና የልማት ጥያቄ መመለሻ በመሆኑም፣ የሕዝብ ተሳትፎ ያልተለየው ግድብ ሆኖ ለግንባታው ድጋፍ እየተደረገለት ነው። ቢያንስ ለሁለት ዓመታት እየተገነባ ከፍፃሜው ይደርሳል ተብሎም ይጠበቃል።

በዚህ ላይ በተለይ ግብፅ ግድቡ ‘’የውኃ ድርሻዬን ይቀንሳል’’፣ “ህልውናዬን ያጠፋል’’ እያለች መንግሥታትን፣ ዓለም አቀፍና አኅጉራዊ መድረኮችን ማጨናነቋን እንደቀጠለች ዘመናትን አስቆጥራለች። በውስጥና በውጭ ተፅዕኖዎች ያልተበገረው ግንባታ ቀጥሎ እነሆ 11ኛ ዓመቱን አስቆጥሯል።

ዓብዩ ዓብይ

አገሪቱ ከገባችበት አረንቋ ለማውጣት ሥልጣን የተረከበ፣ ከችግሮቿ ለማውጣት የተፈጠረ ሙሴ ወይም ነብይ ያደረጓቸው ነበሩ። መነሻውና መድረሻው የኢትዮጵያ አንድነት፣ ኅብረ ብሔራዊነትና እኩልነት መሆኑን ያመለከተ መሪም ሆነው ተከስተዋል። በውስጥም በውጭም ያሉትን ኢትዮጵያውያንን በአገራቸው እንዲኮሩ ያደረጉ መሪ ሆነው ብቅ ብለዋል። ቢያንስ በሦስት ዓመታት ውስጥ ውስጡን ሲደረግ የነበረው ትግል በለውጥ መንገድ ለመመለስ የተደረገውን ሙከራ ለመምራት ከፊት ተሠልፈዋል። ወጣቱ የኢትዮጵያ መሪ ባለፉት አምስት ዓመታት የኖቤል የሰላም ሜዳሊያ ተሸላሚ በመሆናቸው ያገኙትን ስምና ክብር፣ በአገሪቱ ውስጥ በነበረው ጦርነት በወሰዱት ዕርምጃ እስከ ሰላም የማይሹ ሕዝብ ጨራሽ መሪ ተደርገው ስማቸውን ያጠፉም ነበሩ። በማኅበራዊ ዘርፍ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኘውን ኅብረተሰብ ሕይወት ለማሻሻል በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ግንባር ቀደም ሆነው በአርዓያነት እንደ መሠለፋቸው፣ የኑሮ ውድነት በልቶ ማደር ፈተና እስኪሆን አድርገዋል የሚሉ ወገኖችም አሉ። እስቲ ዘርዘር አድርገን እንየው፡፡

ፖለቲካዊ

የለውጡ መሪ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ እውነተኛ እንዲሆን ጥረዋል። በውጭ በስደትና በትጥቅ ትግል የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ወደ አገራቸው አስገብተዋል። ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ቦርዱን እንደገና በማዋቀር ምርጫ እንዲካሄድ ሠርተዋል። ዴሞክራሲያዊና የሰብዓዊ መብት ተቋማትን በነፃነት ለማዋቀር ጥረትም አድርገዋል። በስደት የነበሩ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የሕዝብ አንደበት ሆነው እንዲቀጥሉ ወደ አገር ውስጥ አስገብተዋል። የተዘጉና የተከለከሉ ድረ ገጾች እንዲከፈቱ በማድረግ የሐሳብ ነፃነት እንዲንሸራሸር በር ከፍተዋል። የማንነት ጥያቄዎችን ለመመለስ አዳዲስ ክልሎች እንዲፈጠሩም ሠርተዋል። ነገም ሌሎች ክልሎችን ለመፍጠር ሒደት ውስጥ የገቡ አሉ።

ኢኮኖሚያዊ

በአገሪቱ ነፃ የገበያ ሥርዓትን ለመክፈት ሙከራ ተደርጓል። መንግሥት ነባሩን የንግድ ሕግም አሻሽሏል። አገሪቱ ወደ አኅጉራዊና ዓለም ንግድ ሥርዓት እንድትገባ መንገድ ተጠርጎለታል። በግብርናው መስክ በተለይ የስንዴ ልማትን በማስፋፋት በተለይ የበጋ ስንዴ ልማትን ከስንዴ አስገቢነት ወደ ስንዴ ላኪነት ለመሸጋገር ጥረት ተደርጓል። በአረንጓዴ አሻራ የልማት ንቅናቄ በተለይ የደን ልማት እንዲስፋፋም የተሠራው ሥራ በመልካምነቱ የሚጠቀስ ነው። በኢንዱስትሪ ዘርፍ ‘’ኢትዮጵያ ታምርት’’ በሚል ንቅናቄ  መፈጠሩ፣ የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጣና በመክፈት ዘርፉ እንዲነቃቃ የተጀመረው እንቅስቃሴ ጥሩ ነው። የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ የለውጡ መንግሥት የሁለትዮሽ፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ለማሳደግ ሞክሯል።

በተለይ ከጎረቤትና ከመካከለኛው ምሥራቅ አንዳንድ አገሮች፣ እንዲሁም ከቻይና ጋር የሚደረገው ግንኙነት በአርዓያነት ይጠቀሳል። በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር ‘‹‹ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ›› በህዳሴው ግድብና ከሕወሓት ጋር ለተደረሰው ስምምነት በአርዓያነት ለመንቀሳቀስ የተደረገው ጥረት በአመርቂነቱ መጠቀስ ይቻላል። የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ክብር ለማስከበር የተደረገው ጥረት፣ ተሰሚነትና ተቀባይነቷን ለማሳደግ ተሞክሯል። ሽብርተኝነት ከአገር አልፎ በጎረቤት አገሮች በመታገል የተመዘገበው ውጤት ኢትዮጵያ የክፍለ አኅጉሩ አገሮች በሞዴልነት የሚወስዱት የደኅንነትና የፀጥታ ተቋማት ያሏት አገር መሆኗን ያስመሰከረ ተግባር ሆኗል።

ማኅበራዊ

ነባሩን የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል ለማጠናከር ከሠሩ የኢትዮጵያ መንግሥታት ይኼኛው ቀዳሚ ነው ማለት ይቻላል። በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተከናወኑና በመከናወን ላይ የሚገኙ ተግባራት አስመሥጋኝ ናቸው። አቅመ ደካሞች፣ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች፣ ጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ተፈናቃዮች፣ ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች በተለያዩ መልኮች ድጋፍ የተደረገላቸው ዜጎች ሆነዋል። በተለይ ለአረጋውያንና ለአቅመ ደካሞች የመኖሪያ ቤቶች ግንባታና ዕድሳትም የመሪውን ማንነትና ባህሪ በጉልህ ያሳየ ተግባር ነው። በመላ አገሪቱ 9.5 ሚሊዮን ተማሪዎች የምገባ መርሐ ግብርም ቢሆን ሆድ ከመሙላት በላይ ነው። ተማሪዎች በተረጋጋ ሁኔታ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ከማድረግ ባለፈ፣ የትምህርት አቋራጮችን ቁጥር ቀንሷል።

ሰላምና ፀጥታ

ባለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ከነበሩት ነገሮች ሁሉ የከፋው በሰላምና በፀጥታ ዘርፍ የነበረው ችግር ነው። ዜጎች ‹‹መንግሥት የተቋቋመው የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ለማስከበር ነው›› እያሉ ደጋግመው እስከሚናገሩ ድረስ። መንግሥት የዜጎችን ህልውና ለማስከበር ሲቸገር ታይቷል። በተለይም በምዕራብ ኢትዮጵያ በሚገኙ ክልሎች። የለውጡ መንግሥት እስከ ታችኛው የሥልጣን መዋቅር በአግባቡ አለመዋቀር፣ ያለውም ኃይል ለውጡን አለ መቀበል ለመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት ችግር ሆነው ቆይተዋል ማለት ይቻል ይሆናል፡፡ ሽግግርን ላይ ስለነበርን። ከዚያ በኋላስ? ክልልን እንደ መከለል አድርጎ በመንቀሳቀስ፣ ኢትዮጵያውያን አገራቸው እንደሚያስቡት እንደ ልብ የሚንቀሳቀሱበት አለመሆኑ ሲነገራቸው ቆይቷል። በዚህም ብሔር ተኮር ጥቃት በተለይ በኦሮሚያ፣ በአማራና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ሕጋዊ ነው የተባለ እስኪመስል ተካሂዷል። በትግራይ ቀጥሎም በአማራና በአፋር ክልሎች የነበሩት ግጭቶችም ዜጎችን ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለሥነ ልቡና ጉዳት ዳርገዋቸዋል።

የንብረት ጥፋትም ደርሷል። መቻቻልና መከባበር መለያው የነበረው ሕዝብ የተጨካከነበት የሞት ዓይነቶች የተቆጠሩባቸው ዓመታትም አሳልፈናል። በአገራችን ከሁሉም በላይ የከፋው ለውጡን የመከራ ያስመሰለው በዚህ ዘርፍ የነበረው ችግር ነው። በአንዳንድ የአገሪቱ ክልሎች ወጥቶ መግባትን አዲስ ክስተት ያስመሰለ። የለውጡ ዓመታት አንዳንዶች ‘’የኢሕአዴግን አገዛዝ የሚያስናፍቅ ዘመን’’ የተባለውም ያለ ነገር አይደለም። ቢያንስ በዚያን ዘመን ወጥቶ መግባት አስቸጋሪ አልነበረም።

ችግሮች

በፖለቲካው ዘርፍ ኢሕአዴግን የተካው ብልፅግና ፓርቲ ለመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲ በሩን ገርበብ አድርጎ በመክፈት የአባቱን ሥራ አስቀጥሏል። ምንም እንኳን ተቃዋሚዎችን በየደረጃው ባሉት የመንግሥት መዋቅሮች ለማካተት ጥሩ የሚባል ባህል እያስለመደ ቢሆንም፣ ማንነት ማለት ክልልነት ሆኖ በመታየቱ በዜጎች ህልውና ያስከተለው ጉዳት ቀላል አልነበረም። በተለይ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሚቀርቡ ጥያቄዎች ታፍነዋል የሚሉ ወገኖች እንዳሉ ሁሉ፣ አዳዲስ ክልሎች መፈጠራቸው መልካም መሆኑን የሚገልጹ አልታጡም። በእነዚህ ዓመታት ኢትዮጵያዊነትን ከለላ አድርገው የብሔረሰብ/ብሔር ማንነትን የበላይነት ለማሳየት የሚጥሩ ፖለቲከኞች የአገሪቱን የለውጥ ሒደት ፈተና ውስጥ ከትተውታል።

ፖለቲካው ወደ እምነትም ዘልቆ በመግባት የማይደፈረውን ነካክቷል። የሃይማኖት አባቶችን እንደ ፖለቲካ ካድሬዎች ለመመደብ ሲሞከርም ተስተውሏል። አጃኢብ! በኢኮኖሚው ዘርፍ የገጠሙት ችግሮች ህልውናን ተፈታትነዋል። የኑሮ ውድነቱን ተባብሶ በልቶ ማደር ብርቅ የሆነበት ጊዜ ውስጥ ገብተናል፡፡ በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች። የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ ሕገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ኢኮኖሚው ሰንገው ይዘውታል። በዚህ ላይ ያልተከፈለ የውጭ ዕዳ ሲታከልበት ሕይወትን አክብዶታል። ሙስናና የመልካም አስተዳደር ጉድለቶችም ሕዝብን አማረዋል። በመንግሥትና በሕዝብ ተቋማት ዘረፋና ሌብነት ደግሞ በሕግ የተፈቀዱ መስለዋል። በዲፕሎማሲው መስክ የሕወሓትና የሎቢስቶች በላይነት የታየበት ዘመን አልፎ፣ የአገሪቱ ተሰሚነትና ተቀባይነት ከፈተና ውስጥ መውጣት አልቻለም። በውጭ በተለይም በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የሚኖሩ ዜጎችን መብት ለማስከበር፣ የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የሚደረገው ጥረት ውስንነት ታይቶበታል።

ሲጠቃለል

ያለፉት አምስት ዓመታት በተስፋና በሥጋት ውስጥ አልፋለች፡፡ ዛሬም በተስፋና በችግሮቿ መካከል ህልውናዋን አስቀጥላለች፡፡ ሆኖም በታሪኳና በህልውናዋ ከገጠሟት ሁኔታዎች ሁሉ በባሰ ችግር ገጥሟታል። በሰላምና ፀጥታ ረገድ ያሉት ችግሮች ሳይቃለሉ፣ በኢኮኖሚው ዘርፍ ያሉት ሥር የሰደዱ ችግሮች ሳይፈቱ እየተኖረ ነው። በብሔር/ብሔረሰብ ስም አኩሪው ኢትዮጵያዊት እየተገፋ የታሪክ ጠባሳዎችን፣ ጥቃቶችንና በደሎችን እየቆጠረ፣ ማንነትን መሠረት ያደረገ ተረኝነት መሰል የገዥነት ባህሪ መታየት ጀምሯል። የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሌሎች ችግሮች ለመፍታት ቀን ከሌት የሚተጋ አመራር በሚያሻበት በዚህ ወቅት፣ ብሔር ለይቶ መጠዛጠዝ በገዥው ፓርቲ ውስጥ መታየቱ እንደ አገር ለመቀጠል ሥጋት ሆኗልና ሃይ ሊባል ይገባዋል። ከአምስት ዓመታት በፊት ተስፋ ሰጥቶ ወደ ላቀ ደረጃ ሊያሸጋግረን ሥልጣንና ኃላፊነት የወሰደው መሪና አመራር ኢትዮጵያን የሚያድንበት፣ የሚያገለግልበትና ቃሉን በተግባር የሚያውልበት አሁን ነው።

የምናምነውና የምንተማመንበት መሪና አመራር እንጂ፣ የማናምነውና የምንጠራጠረው መሪና አመራር እንደ ሌለ ዛሬም ተስፋ አለን። ያልተፈለገና የማይገባ ጥርጣሬ እየፈጠሩም አገርን ማስቀጠል አይቻልምም፣ አይገባም። “ኢትዮጵያ ማለት እኔ ነኝ፣ እናንተ አይደላችሁም’’ በሚል አጉል የብልጣ ብልጥ የሚመስል አስተሳሰብና አካሄድ የራሱን ሥርወ መንግሥት ለማቋቋም የሚውተረተር እንቅስቃሴ ብቅ ማለት ይዟል፡፡ አገሪቱ የግል ርስቱ ትመስል። ጽሑፌን ከማጠናቀቄ በፊት ሰሞኑን በአልጄዚራ ቴሌቪዥን ጣቢያ ኢራቅ ውስጥ በነበረ ታሪካዊ ክስተት የተመለከትኩትን አንድ ነገር ላካፍላችሁ፡፡ አገሪቱ ከ20 ዓመታት በፊት በአሜሪካ ተወራ በነበረችበት ወቅት ሕዝብ ተቃውሞውን ይገልጽ ነበር፡፡ ታዲያ ሕዝቡ ወረራውን የተቃወመበት የአንድነት መንፈስ ያስቀና ነበር። ምንም እንኳን ኢትዮጵያውያን ስለአንድነታችን ከሌሎች የምንማር ባንሆንም።

      የሠልፈኞቹ አስተባባሪ፣ “አሜሪካዊ ናችሁ?’’

    “አይደለንም’’

  “ኢራናዊ ናችሁ?’’

   “አይደለንም’’

   “እንግሊዛዊ ናችሁ?’’

    “አይደለንም’’ ነበር መልሳቸው።

ከዚያ ወረድ ብሎ “ሱና ናችሁ?’’ ወይስ “ሺዓ ናቸሁ?’’ በማለት በእስልምና እምነት ውስጥ በዋነኝነት የሚጠሩትን መለያዎች ይጠራል። አሁንም ይህ ልዩነት እንደማይለያያቸው ለማስታወቅ “አይደለንም’’ በማለት በአንድ ድምፅ ይመልሳሉ። የአስተባባሪው የመጨረሻው ይሁንታ ያስገኘ፣ ሁሉንም ያግባባና ጭብጨባና ሆታ ያስከተለ ደግሞ ይኸኛው ነበር፡፡

   “ኢራቃዊ ናችሁ?’’

   “አዎን!’’ ብለው ዜጎች በአገራቸው መኩራታቸውን ደስታና ጭፈራ

    አክለውበት ገለጹ።

ወራሪው ኃይል ጠብመንጃው ደግኖ አጠገባቸው ቢሆንም፣ ቢያንስ እንዲያፍር አደረጉ። በዜግነታቸው እንደሚኮሩም በአደባባይ በኩራት መሰከሩ። እኛም በኢትዮጵያዊነታችን ሳንደራደር ለመቀጠል የሌሎች አገሮችን ስም፣ ብሔር፣ ነገድና ጎሳ ሊጠሩብን አይገባም። ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድ ሆነው አንድ አድርገው የሚያስተዳድሩን መሪዎች እንሻለን። ኢትዮጵያን የሚሉ መሪዎች ካገኘን ምርጥ ኢትዮጵያውያን ነን። ዓለም የሚያውቀንና የሚያደንቀን የኩሩና የብርቱ አገር ዜጎች ነበርን፣ ነንም፣ ሆነንም እንድንቀጥል አድርጉን።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...