Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

ቀን:

በኢተፋ ቀጀላ​​

 ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣ አንድም የኦሮሞ ድርጅት በራሱ ድርጅትና የድርጅት ኃይሉ ለኦሮሞ ሕዝብ አስገኘሁ የሚለው አንድም ነገር የለውም። በ1966 ዓ.ም. በአብዮቱ ዘመን ለምሳሌ አንድም ሌላ የኦሮሞ ድርጅት ለመሬት ለአራሹ በሥራ መተርጎም አልታገለም። በ1967 ዓ.ም.  የተመሠረተው ኦነግ እንደሚታወቀው በዚያን የኦሮሞ ሕዝብ ለመሬት ለአራሹ በሚታገልበት ወቅት፣  “ፋሽስቱን ደርግ” በመሣከያ ለመታገል ጫካ ገብቶ ነበር። የኢሕአዴግ አባል የሆነው የአባዱላ  “ድርጅት”  ከሽግግር መንግሥቱ ውስጥ የገባውም፣ በሕወሓት ተፈጥሮ በአንቀልባ ታዝሎ ነበር። ኦሕዴድ አፒዲኦ የኦሮሞ ድርጅት ተብሎ ለ27 ዓመታት የሰነበተውም፣ በሕወሓት  ፈቃድ  የተሰጠውን ሥፍራና ሀብት ይዞና በሕወሓት ሞግዚትነት ነበር።

ኦነግ ከዓመታት በኋላ በ2010 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት የቻለውም፣ በዓብይ (ዶ/ር) እና በአቶ ለማ መገርሳ ይሁንታና ፈቃድ ነበር። በዚህ መሀል አንድ ራሱን ችሎ የተንቀሳቀሰ የኦሮሞ ድርጅት በመረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) የሚመራው ኦፌኮ ነበር። እሱም በጃዋር መሐመድና በበቀለ ገርባ ቡድንና ከሚኒሶታ በሚጎርፍለት ፋይናንስ ተጠልፎ አበቃ።  

 የ1960ዎቹ ዋና ዋና ጥያቄዎች የመሬት ይዞታ፣ የብሔሮችና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄዎች ነበሩ። ለጥያቄዎቹ የታገሉላቸው በብሔርና በቋንቋ አጥር ያልተከፋፈሉት የኢትዮጵያ ተማሪዎች፣ ምሁራን፣ ተራማጆች፣ የቀድሞ የመሬት ባለቤት፣ የአርሶ አደር፣ የአርብቶ አደርና የነፍጠኛ ልጆች ነበሩ። የመሬት ይዞታ ለውጥ  ከኢጭአት በስተቀር አንድም ሌላ የኦሮሞ ድርጅት ሳይሳተፍበት በ1967 ዓ.ም.  ከሞላ ጎደል ተመለሰ። የብሔሮች ጥያቄም በ1983 ዓ.ም. በሕወሓትና በአንዳንድ በሽግግር መንግሥቱ ውስጥ በሕወሓትና በሻዕቢያ አንቀልባ ታዝለው በገቡ የሕወሓት ፍልፍል የብሔር ድርጅቶች ከእነ ጉድለቱ  ተመለሰ። የዛሬዎቹ ጽንፈኛ የኦሮሞ ድርጅቶች ይህንን የሃምሳ ዓመት ታሪክ ለተከታዮቻቸው ቢያሳውቁና ቢያስተምሩ፣ እርግጠኛ ነኝ የማታገያ ትርክታቸው ይናዳል። 

 ከ1983 ዓ.ም.  በኋላ ያሉት ሁለት ዋና ዋና የፖለቲካ ጥያቄዎች አንደኛው፣ በመሬት ይዞታና በብሔር ጥያቄዎች ረገድ የጎደለውን የማሟላትና የተሰነካከለውን የማረም ጥያቄ ነው። ሁለተኛው የመጀመሪያ ደርጃ መልስ እንኳን ላላገኙት  የዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት ጥያቄዎች መታገል ነው። ሦስተኛው የሕገ መንግሥቱና የአስተዳደር መዋቅሩ መሻሻል ነው። የኦሮሞ ሕዝብ ትግል በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ ቢያተኩር  የቱን ያህል በተጠቀመ ነበር? የኦሮሞ ሕዝብ  በሰላምና በደኅንነት  እየኖረ የቱን ያህል ወደ ዕድገትና ብልፅግና በተጓዘ ነበር?

 ለኦሮሞ ሕዝብ እንታገላለን ለሚሉት ጽንፈኞች ግን የኦሮሞ ሕዝብ  በኢትዮጵያ ውስጥ  ሰላም፣ ዕድገትና ብልፅግና  አግኝቶና  ደኅንነቱ ተጠብቆ  የመኖሩ ጉዳይ  ጉዳያቸው  አይደለም። ጉዳያቸው  በኦሮሞ ሕዝብ ታጋይነት ስም ሥልጣንና  ሀብት ማካበት ነው። በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የበላይ  ሆነው የበለጠ ሥልጣንንና ሀብትን ለማካበት ነው። ለዚህም ብቻ ነው የኦሮሞን ሕዝብ ለእነሱ የሥልጣንና የሀብት ማካበቻ ግብ መሣሪያቸው አድርገው የሚገለገሉበት። የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ  ያልሆኑትን  ጥያቄዎች  ነው በየዕለቱ እየፈጠሩ  ለኦሮሞ ሕዝብ መብትና ጥቅም እንታገላለን የሚሉት። የኦሮሞን ሕዝብ በዙሪያው ካለው ሕዝብ ጋራ ሁሉ በማቋሰልና በማጋጨት ሴራ ተደመጠው የሚገኙት። ፀጥ ያሉት የኦሮሞ ልሂቃንና ሕዝብ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለራሳቸው በማቅረብ ጥያቄዎቹ በእውነት የኦሮሞ ሕዝብ የመብትና የጥቅም ጥያቄዎች መሆናቸውን እንዲመረምሩ ያስፈልጋል። 

➢  በሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎችን በብሔራቸውና በቋንቋ ማንነታቸው እየለዩ መግደል፣ ማገት፣  መዝረፍና ማፈናቀል እውነተኛ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ነውን?

➢  የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መዲና የሆኑትን አዲስ አበባንና ድሬዳዋን የኦሮሞ ግዛት ለማደረግ መሻት እውነተኛ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ነውን?

➢  አዲስ አበባን በኦሮሞ ተወላጆች ቀበቶ ማጠር እውነተኛ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ነውን?

➢  ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ ዜጎችን በየኬላው ማገትና ከየግል ጉዳያቸው ማሰነካከል  እውነተኛ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ነውን?

➢  የእህል ምርት ወደ አዲስ አበባ እንዳይገባ በማገድ የከተማውን መካከለኛ፣ ዝቅተኛና ደሃ ዜጋ ለረሃብና ለችጋር መዳረግ እውነተኛ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ነውን?

➢  ሊሎቹን ኅብረ ብሔር ከተሞች  ነገና ተነገ ወዲያ  በኦሮሞ  ተወላጆች  ቀበቶዎች ማጠር እውነተኛ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ነውን?

➢  ቋንቋችን ተጨቁኗል የሚል  የኦሮሞ ሕዝብ  ትግል እንዳልነበር ሁሉ፣ የኦሮሞን ቋንቋ  በሌሎች ላይ  በግዴታ መጫን  እውነተኛ  የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ነውን?

➢  የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሔራዊ መዝሙር እንደሌለ ሁሉ፣ የኦሮሞ አስተዳደር መዝሙርን በሌሎች ላይ በግዴታ መጫን እውነተኛ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ነውን?

➢  አንድ የተዋሕዶ ሲኖዶስ እያለ የኦሮሞን ብቸኛ ሲኖዶስ ለማቋቋም መነሳሳት እውነተኛ  የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ነውን?

➢ የሃይማኖት አባቶችን ማሰርና በጥፊ ማጮል እውነተኛ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ነውን?

➢ የዜጎችን  መኖሪያ  ቤቶችንና ሠፈሮችን  በብሔርና በቋንቋ እየለዩ በቡልዶዘር ማፈራረስና ማፈናቀል እውነተኛ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ነውን?

➢ ጋዜጠኞችንና አስተያየት ሰጪዎችን እያገቱ መደብደብ እውነተኛ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ነውን?

➢ ሕጋዊ የሚዲያ ቢሮዎችን እየሰበሩ ሕጋዊ የሥራ መሣሪያቸውን መዝረፍ  እውነተኛ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ነውን?

➢ ስንት መቶ ሺሕ የኦሮሞ ልጆች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ተሸክመው በስንት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ነፃነትና የሉዓላዊነት ጦርነቶች እንዳልተዋደቁ ሁሉ፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ማንቋሸሽና ማራከስ እውነተኛ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ነውን?

➢ የኦሮሞን ሕዝብ የረጅም ዘመን ታሪክ በተበዳይነት ትርክት ወስኖ ማሳወቅና ማስተማር የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ ማሳነስና ማጉደፍ አይደለምን?

 ጽንፈኞች ግን የኦሮሞ መሪዎችና ልሂቃን ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በኢትዮጵያ መንግሥት ግንባታና ሒደት ውስጥ የነበራቸውን ሥፍራና ሚና ለተከታዮቻቸው አያሳውቁም፣ አያስተምሩም። የኦሮሞን ሕዝብ  ታሪክ የሚያስጀምሯቸውና የሚያስጨርሷቸው አንደኛ በ19ኛው ክፍለ ዘመን  በአፄ  ምኒልክ  የደቡብ ዘመቻ ወቅት  ስለደረሰው በደል  በማተት  ነው።  ሁለተኛ  ተበዳይነትን አጉልቶ በማጫወት ለቂምና ለቁርሾ አወራራጅ  ትግል በማነሳሳት ነው። ሦስተኛ ፈራርሶ ያበቃለትን የገዳ ሥርዓት አብዝቶ በመዘመር ነው። አራተኛ  አሁን አሁን ደግሞ፣ “ከእጃችን  የገባው ሥልጣን  እንዳያመልጠን”  በሚል  በመቀስቀስና የዓብይን (ዶ/ር) ተክለ ሰውነት ለመገንባት በመጣር ነው። አምስተኛና በመጨረሻም ትርክታቸውንና አካሄዳቸውን የማይቀበለውን የእኔ ዓይነቱን ኦሮሞ በብሔር ከሃዲነት በመፈረጅ፣  በማግለልና ዓይን ባወጣ  ማስፈራራት  ነው።  የዚህን የመጨረሻውን ጉዳይ ምንነት ለማያውቁት ለማሳወቅ፣ ብዙኃኑ ኦሮሞ ፀጥ ብሎ የሚገኘው ጽንፈኞቹን ስለሚደግፍ አይደለም፣ ጽንፈኞቹን ስለሚፈራ ነው። 

 ሀቁ ግን  አንደኛ  ኦሮሞ በ16ኛው  ክፍለ ዘመን ከባሌ እስከ ጎንደርና ትግራይ የዘለቀው አገላብጦ እየሳመ አይደለም። እየወጋ፣ እየገደለ፣ እየዘረፈና በወረራ የያዛቸውን ሕዝቦች በሞጋሳና በጉዲፈቻ እየዋጠ (Assimilate) እና እያስገበረ ነው። በጊቤ የነበሩትን  ቀደምት መንግሥታትንም አፈራርሶና በአባ ሞቲዎች ንጉሣዊ አገዛዝ ተክቶ ነው።  ሁለተኛ የ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ የአፄ ምኒልክ የደቡብ ዘመቻና የደረሰው በደል  የተመራው፣ የተካሄደውና የተፈጸመውም በታወቁ የኦሮሞ መሪዎችና ሠራዊት ጭምር  ነው። የዛሬዎቹ ጽንፈኛ ኦሮሞዎች ይህንን ታሪክ ለተከታዮቻቸው ቢያሳውቁና ቢያስተምሩ፣ እርግጠኛ ነኝ የማታገያ ትርክታቸው ይናዳል።

 ሦስተኛ የገዳ ሥርዓት ከቦረና አንዳንድ አካባቢ በስተቀር በ16ኛው ክፍለ ዘመን የኦሮሞ ሰሜን ፍልሰት ወቅት ፈራርሶ በአባ ሞቲዎች፣ አባ ዱላዎች፣ ወዘተ ከተተካ  500 ዓመታት አልፈዋል። የገዳ ሥርዓት የፈራረሰውም በጎሳ ደረጃ እንጂ ከዚያ ውጪ  ላሉ ማኅበራዊ ዕድገቶችና አወቃቀሮች የሚሠራ ስላልነበር ነው። ስለዚህም ነበር ገና በ18ኛው ክፍለ ዘመን በጎንደሩ በንጉሥ በካፋ ጊዜ የኦሮሞ ጦር መሪዎች ቀኛዝማች፣ ደጃዝማች፣ ወዘተ እየተባሉ ሲዘምቱ የኖሩት። የጊቤ መንግሥታትን ነገሥታት በአባ ሞቲዎች፣ በአባ ቦጊቢዎች፣ በአባ ዱላዎችና በአባ አፍካላዎች እየተኩ ሲገዙ የኖሩት። የዛሬዎቹ ጽንፈኞች ይህንን የአምስት መቶ ዓመት የኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ  ለተከታዮቻቸው ቢያሳውቁና ቢያስተምሩ፣ እርግጠኛ ነኝ የማታገያ ትርክታቸው ይናዳል።

አራተኛ  የአሮሞ መሪዎች፣ ልሂቃንና ሕዝብ ከዓድዋው አፄ ምኒልክ አንስቶ እስከ ትናንትናው የሰሜኑ ጦርነት ድረስ፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ነፃነትና አገረ መንግሥት ግንባታ ያበረከቱትን ከፍተኛ አስተዋጽኦና ተጋድሎ ቢያውቁና ቢቀበሉ፣ ለተከታዮቻቸው ቢያሳውቁና ቢያስተምሩ፣ እርግጠኛ ነኝ የማታገያ ትርክታቸው ይናዳል።

 ለኦሮሞ ሕዝብ እንታገላለን የሚሉ ጽንፈኞች እንደለመዱት ሌሎች አጀንዳዎችን በየዕለቱ ሊፈጥሩ ይችላሉ። ከላይ ከተዘረዘሩት 15 ነጥቦች የሚለያዩ ግን አይሆኑም። ለኦሮሞ ሕዝብ አስገኘን የሚሏቸውም “ድሎች” ለእነሱ ሥልጣንና ሀብት ከሚጠቅሙት “ድሎች” ውጪ አይሆኑም።  ፀጥ ያሉት የኦሮሞ ልሂቃንና የኦሮሞ ሕዝብ  እስከ መቼ ድረስ ነው የራሳቸውን፣ የልጆቻቸውንና የልጅ ልጆቻቸውን የዛሬና የወደፊት ዕድል ለጽንፈኞች አስረክበው ፀጥ የሚሉት?

 “ከየት እንደመጣ የማያውቅ ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም” ይባላል። የዛሬዎቹ ጽንፈኞች ከየት እንደመጡ ስለማያውቁ የኦሮሞን ሕዝብ ወዴት እንደሚወስዱት አያውቁም። ስለዚህም የኦሮሞን ሕዝብ ይዘው ወደ ጥፋት እየወሰዱት ናቸው። ፀጥ ያሉት የኦሮሞ ልሂቃንና የኦሮሞ ሕዝብ ይህንን የጽንፈኞች አካሄድ ሊፈቅዱ አይገባም። በፍርኃት ተውጠውና በጉልበት ታፍነው የዳር ተመልካች የሆኑበት  ጊዜ ማብቃት አለበት። ድምፃቸውን በተደራጀ መንገድ ማሰማት መጀመር አለባቸው። የኦሮሞ ሕዝብ  እውነተኛ ታሪኩን ማስመለስ አለበት። 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው itefaqj@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...