Sunday, September 24, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ለአገር አይበጅም!

ሰሞኑን የአሜሪካና የኢትዮጵያ መንግሥታት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች መግለጫ ላይ አልተግባቡም፡፡ አለመግባባታቸው የሚጠበቅ በመሆኑ ሊደንቅ አይገባም፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ በተጀመረው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ረቂቅ ውይይት ላይ ለመግባባት ከተቻለ፣ በጦርነቱ ምክንያት የጉዳት ሰለባ የሆኑ ወገኖችን ዕንባ ማበስና ዘላቂ መፍትሔ ማግኘት አያቅትም፡፡ ለዚህ ስኬት ደግሞ አገር በሕግ የበላይነት ጥላ ሥር እንድትተዳደር የሚያስችል ተግባር ያስፈልጋል፡፡ ማንም ሰው በሥልጣኑ ወይም በሀብቱ ምክንያት ከሕግ በላይ እንዳይሆን፣ ኢትዮጵያውያን በሚያራምዱት የፖለቲካ አቋም ምክንያት ለጥቃት እንዳይጋለጡ፣ መሠረታዊ መብቶቻቸው ሙሉ በሙሉ እንዲከበሩ፣ እነሱም በአግባቡ ግዴታቸውን እንዲወጡ፣ ማኅበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍንና በእኩልነት ለመኖር የሚያስችል ከባቢ መፍጠር የግድ መሆን አለበት፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባውም ሆነ አገር ሰላም የምትሆነው የሕግ የበላይነት ሲሰፍን ብቻ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት በሌለበት አምባገነንነትና ፀረ ዴሞክራሲ ድርጊቶች ይበዛሉ፡፡ ግለሰቦች በሕገወጥ መንገድ ከመንገድ እየታገቱ ለጉዳት ይዳረጋሉ፡፡ በሕገወጥ መንገድ ፍላጎታቸውን የሚያስፈጽሙ ከለላ እያገኙ ንፁኃን ይጎዳሉ፡፡ ችግሩን ለመፍታት ግልጽነትና ተጠያቂነት ይስፈን፡፡

በአሁኑ ጊዜ የግልጽነትና የተጠያቂነት ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ በላይ አሳሳቢ እየሆነ ነው፡፡ ሕወሓት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአሸባሪነት መዝገብ እንዲሰረዝ በተጠራው ስብሰባ፣ ከመንግሥት ሚዲያዎች በስተቀር ሌሎች ሚዲያዎች እንዳይገቡ ክልከላ ተደርጓል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች በአገር ጉዳይ ላይ ስብሰባ ሲያደርጉ ለሚዲያ ሲከለከል ተጠያቂው ማነው? የሕዝብ የማወቅ መብት በግላጭ ሲጣስ እንዴት ዝም ይባላል? አገርን የሚጎዱ ድርጊቶች ሲበራከቱ ተጠያቂነት ያለባቸው የሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የተጠያቂነት መርህ እንደ ቀልድ እየታየ ብዙ ነገሮች እየተበላሹ ናቸው፡፡ ሕግ አውጪው፣ ሕግ ተርጓሚውና አስፈጻሚው እርስ በርስ ቁጥጥር ማድረግና ዕርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል አሠራር መፍጠር ሲገባቸው፣ አገር በዘፈቀደ የምትመራ እስክትመስል ድረስ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አይታይም፡፡ በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ የማይመራ የመንግሥት አሠራር፣ ለሕዝብ ሰላምና መረጋጋት ፀር መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ አሁንም በድጋሚ አፅንኦት መሰጠት ያለበት የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነት እንዲኖርበት ነው፡፡ በመንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ ችግሮች ሲከሰቱ ከፈጻሚዎቹ ጀምሮ አስፈጻሚዎቹ ድረስ ተገቢው ሕጋዊ ዕርምጃ ይወሰድ፡፡ 

ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እንቅፋት የሆኑት የግልጽነትና የተጠያቂነት መጥፋት ዜጎችንም አገርንም ዋጋ እያስከፈሉ ነው፡፡ ብልሹ አሠራሮች በዝተው ሕዝብ በየቦታው የሚያለቅሰው ተጠያቂነት በመጥፋቱ ነው፡፡ ፍትሕ በገንዘብ እየተሸጠ ያለው ተጠያቂነት ስለሌለ ነው፡፡ ሙስና አገሪቱን እንደ ሰደድ እሳት የሚለበልበው ተጠያቂነት ባለመታወቁ ነው፡፡ ብዙኃኑ ሕዝብ የድህነት ማጥ ውስጥ ሆኖ ጥቂቶች እሴት ሳይጨምሩ የሚከብሩት ተጠያቂነት በመናቁ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት እየተገፋ ሕገወጥነት የሚስፋፋው ኃላፊነት በመረሳቱ ነው፡፡ መንግሥት ከራሱ ጓዳ ጀምሮ ችግሩን እየቀረፈ መሄድ ካልቻለ፣ ውስጡ የመሸጉትን በድፍረት ካላጋለጠ፣ በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ የተጣለበትን አደራ ካልተወጣ ለራሱ ጭምር አደጋ ይጋብዛል፡፡ ዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብታችንን በመጠቀም ሐሳባችንን ስንገልጽ ጥቃት እየተፈተመብን ነው እያሉ በየዕለቱ ይጮኻሉ፡፡ ለዓመታት ከኖርንበት ቀዬ ማንነታችን እየተለየ ጎጆአችን ፈርሶ ሜዳ ላይ ተጣልን ብለው እሪ ይላሉ፡፡ የተለያዩ መንግሥታዊ አገልግሎቶችና ፍትሕ የተነፈጉ ወገኖች የመንግሥት ያለህ እያሉ ነው፡፡ የዜጎች ጥያቄ ካልተደመጠ የማን ሊደመጥ ነው ታዲያ?

በኢትዮጵያ ከሚስተዋሉ ተጨባጭ ሁኔታዎች በመነሳት የተቋማትንና የአመራሮችን አካሄድ በትኩረት የሚከታተል ማንኛውም ዜጋ የሚጠይቀው፣ መንግሥት ለምን ሕዝቡ በቀጥታ የሚያቀርብለትን ጥያቄ አያዳምጥም የሚለውን  ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥት ካልተደማመጡ ሁሌም ችግር ይኖራል፡፡ መንግሥት የሕዝብ ተጠያቂነትና ኃላፊነት አለብኝ ማለት ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝቡ በትክክል የሚፈልገው ምንድነው ብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ ለዚህ ጥያቄ ትክክለኛ ምላሽ የሚገኘው የፖለቲካ ወገንተኝነት ባላቸው አደረጃጀቶች አይደለም፡፡ የሕዝቡ ትክክለኛ ፍላጎት የሚታወቀው በቀጥታ ከራሱ አንደበት ነው፡፡ በካድሬዎች ተቀባብቶ የሚቀርብ ሐሰተኛ ሪፖርት ዋጋ እንደሌለው በተደጋጋሚ የታየ ነው፡፡ በደካማ ተቋማትና አመራሮች ምክንያት ልቡ የቆሰለ ሕዝብ ግን ሲናገር በትክክል ጥያቄው ይታወቃል፡፡ ምላሹም በዚያ መጠን ይሆናል፡፡ የሕዝብን ችግር ተገንዝቦ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ባለመቻል ምክንያት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው መመሰቃቀልና ትርምስ ከባድ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ አንድ ትውልድ ለአገሩ መክፈል ያለበት መስዋዕትነት እንዳለ ሁሉ፣ የሚያስተዳድረው መንግሥትም መብቱንና ነፃነቱን ማስከበር ይጠበቅበታል፡፡

ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ውስጥ በሚከናወኑ ማናቸውም ጉዳዮች በእኩልነት የመሳተፍ መብት አላቸው፡፡ ቅሬታ ሲኖራቸውም ሆነ ሲከፋቸው በፍትሐዊነት መስተናገድ ይኖርባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን በሁሉም መስኮች በእኩልነትና በፍትሐዊነት መስተናገድ አለባቸው ሲባል፣ ከመንግሥት በተጨማሪ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የግል ኩባንያዎች፣ ማኅበራትና የመሳሰሉት መዋቅሮች ሁሉ ይመለከታቸዋል፡፡ መንግሥት በኃላፊነት ለሚያስተዳድራቸው ዜጎች ከማንም በላይ ተጠያቂነት ሲኖርበት፣ ሌሎች አካላትም ዜጎችን ሳያበላልጡና አድልኦ ሳያደርጉ በእኩልነትና በፍትሐዊነት የማስተዳደርም ሆነ የማስተናገድ ሕጋዊ ግዴታ አለባቸው፡፡ እኩልነትና ፍትሕ በሌለበት ከሰላም ይልቅ ብጥብጥና አለመረጋጋት ይንሰራፋል፡፡ ብዙ ጊዜ በፖለቲካዊ መብቶች ላይ ብቻ በመወሰን የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ በእርግጥም እነዚህ መብቶች ዓለም ያፀደቃቸውና መንግሥታትም በቃል ኪዳን ሰነድነት የተቀበሉዋቸው በመሆናቸውና ተፈጥሮአዊም ስለሆኑ መከበር አለባቸው፡፡ ከእነዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የልማት መብቶችም ጉዳይ አሳሳቢ ነው፡፡ 

ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል እንደሆኑ፣ በመካከላቸውም ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ በሕግ እኩል ጥበቃ እንደሚደረግላቸው በሕግ ተደንግጓል፡፡ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የሆነ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት እንዳላቸው በሕግ የተረጋገጠ ነው፡፡ ከሕግ በተቃራኒ በመንግሥትም ሆነ በማንኛውም ወገን የሚፈጸም ድርጊት ወንጀል ነው፡፡ በአገሪቱ በሁሉም ሥፍራ እከሌ ከእከሌ ሳይባሉ ኢትዮጵያውያን የሕግ ጥበቃና ከለላ አግኝተው፣ በመረጡት የሥራ ዘርፍ ተሰማርተውና እንደፈለጉ ተዘዋውረው ሀብት የማፍራት መብት እንዳላቸው በሕግ ዋስትና አግኝተዋል፡፡ ስለዚህ ሠርተው የመኖር መብታቸው በተግባር መረጋገጥ አለበት፡፡ ለአንዱ የተፈቀደው ለሌላው ሲከለከል፣ አንዱ በሕጋዊ መንገድ ጠይቆ እንቢ ሲባል ሌላው በሕገወጥ መንገድ ሲያገኝ፣ አንዱ ለአገር የሚጠቅም ተግባር እያከናወነ ማግኘት የሚገባውን ሲነፈግ፣ ሌላው አፍራሽ ድርጊት እየፈጸመ መንገዱ አልጋ በአልጋ ሲሆንለት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተስፋፍተው ዓለም አቀፍ ውግዘት ያስከትላሉ፡፡ ከአገር ውስጥ ጀምሮ እስከ ዓለም አቀፍ ተቋማት ድረስ ውግዘት የሚከተለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የመንግሥት አሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት ሲጎድለው ለአገር እንደማይበጅ ይታወቅ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ በመከረው የመጀመሪያ ጉባዔ ለዲፕሎማቲክና ለትብብር አማራጮች ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ በቀይ ባህር ቀጣና የፀጥታ...

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...

የመጀመርያ ምዕራፉ የተጠናቀቀው አዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ተከላው እንደገና ሊከናወን መሆኑ ተሰማ

እስካሁን የሳር ተከላውን ጨምሮ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ዕድሳቱ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...