Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናጉራጌን በክላስተር ለመጨፍለቅ የሚደረገውን ጥረት እንደሚቃወም ጎጎት ፓርቲ አስታወቀ

ጉራጌን በክላስተር ለመጨፍለቅ የሚደረገውን ጥረት እንደሚቃወም ጎጎት ፓርቲ አስታወቀ

ቀን:

ለጉራጌ ሕዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እንደሚታገል የሚናገረው አዲሱ ጎጎት (ለጉራጌ አንድነትና ፍትሕ ፓርቲ) የጉራጌ ሕዝብን ክላስተር በሚባል ክልል አወቃቀር የመጨፍለቅ ጥረት እንደሚቃወም ተናገረ፡፡

ፓርቲው የደቡብ ክልል ምክር ቤት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲሁም ብልፅግና መራሹ መንግሥት ከተከበረው የጉራጌ ሕዝብና ዞን ምክር ቤት ፍላጎት ውጪ የሚያካሂዱትን፣ ሕዝቡን በክላስተር ክልል የመጨፍለቅ ሙከራ ኢ ሕገ መንግሥታዊ ነው ሲል በመግለጫ አውግዞታል፡፡

የጉራጌ ዞን ሕዝብ ፖለቲካዊ ውክልና ያጣ፣ እንዲሁም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የተነፈገ ሆኗል ያለው ፓርቲው የጉራጌ ዞን ሕዝብ ያቀረበው ራሱን ችሎ በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንዲመለስ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ፓርቲው ምሥረታውን ለማካሄድ ፔቲሽን (ፊርማ) ከማሰባሰብ ጊዜ ጀምሮ መሥራች ጠቅላላ ጉባዔ ሲያካሂድና አሁን እስካለበት ደረጃ በመንግሥት አካላት መዋከብና እስራት እየገጠመው መሆኑን ተናግሯል፡፡

በዋቢ ሸበሌ ሆቴል መጋቢት 3 ቀን 2015 ዓ.ም. መሥራች ጠቅላላ ጉባዔውን በስኬት ቢያካሂድም፣ ከ12 ያላነሱ አባላቱ ከእነ ጠቅላላ ጉባዔ ሰነዶቹ በፖሊስ መታሰራቸውን ፓርቲው ጠቅሷል፡፡

በርካታ የፓርቲው ደጋፊዎችና አባላት አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኙ የገለጸው ፓርቲው ይህ ደግሞ የጉራጌ ዞን ሕዝብን ድምፅ አልባ ለማድረግ የተወጠነ ነው ብሎታል፡፡

ትናንት ቅዳሜ ወደ ጉራጌ ዞን ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ረቡዕ መጋቢት 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ደግሞ በጽሕፈት ቤታቸው የጉራጌ ተወላጅ ነጋዴዎችን ሰብስበው እንደነበር የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ መሀመድ አብራር ይናገራሉ፡፡

ስብሰባው ‹‹በደንብ ተጠንቶና የተመረጡ ሰዎች ብቻ ተወክለው የተካሄደ ነበር›› ሲሉ የገለጹት አቶ መሀመድ ‹‹ክልል መሆን የሚጠቅማችሁ ቢሆን ኖሮ በአምስት ደቂቃ እሰጣችሁ ነበር፡፡ ነገር ግን ክልል መሆን ስለማይጠቅማችሁ አልሰጣችሁም፤›› የሚል አንድምታ ያለው ንግግር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መናገራቸው ፍጹም እንዳስከፋቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹የጎጎት ዋና ግብ የጉራጌ ዞን ሕዝብ የራሱ ክልል እንዲኖረው ከማድረግ ባለፈ፣ ዴሞክራሲያዊ ወንድማማችነት የሰፈነባት ኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያ ስትፈጠር ማዬት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሊቀመንበሩ አቶ መሀመድ አብራር ፓርቲያቸው ለዚህ ዓላማ ዕውን መሆን ከብልፅግናም ሆነ ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በሚያግባቡ ጉዳዮች ተቀራርቦ እንደሚሠራ አመልክተዋል፡፡

የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ መላኩ ሳህሌ በበኩላቸው፣ ከፓርቲ አባላት ደጋፊዎች በተጨማሪ የጉራጌ ሚዲያ ኔትወርክ ጋዜጠኞች ጭምር እየታሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መላው የጉራጌ ዞን ማኅበረሰብ አፈና ውስጥ እንዳለ በማከል የክልልነት ጥያቄውን ላለመመለስ የተለያዩ አሻጥሮች እየተካሄዱባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ፓርቲያችን ፍፁም አንድነትና ፍፁም መለያየት ከሚያቀነቅኑ ሁለት አፍራሽ የፅንፈኝነት ኃይሎች ጋረ አይተባበርም›› ያሉት አቶ መላኩ፣ ዓላማቸው በኢትዮጵያ እውነተኛ ኅብረ ብሔራዊ ዴሞክራሲ ሲፈጠር ማየት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹ጎጎት› የሚለው ስያሜ የመጣው በ18ተኛው ክፍለ ዘመን ቤተ ጉራጌዎች ለአንድነትና ለነፃነት ለመታገል ከተሰባሰቡበት ጎጎት ተራራ ስያሜ መሆኑንም አቶ መላኩ አመልክተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...