Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ፣ ‹‹ከታሪክ የማይማር የታሪክ ማስተማሪያ ይሆናል›› የሚል በደማቅ ቀለማት የተዋበ ጥቅስ ጎላ ብላ ይታያል። ‹‹ምነው አሁንስ አልበዛም እንዴ…›› እያሉ አንዲት እናት ጥቅሱን እያነበቡ ያጉረመርማሉ፡፡ ወግ ሊጀመር በሒደት ላይ ነን ማለት ነው፡፡ ወያላው መጥራት ከመጀመሩ ታክሲው ውስጥ የገባን ተሳፋሪዎች አምስት ነን። በዕለተ እሑድ ተሳፋሪ ጠፍቶ ታክሲው እስኪሞላ ከወዲያ ወዲህ በእግሩ የሚመላለሰውን ለፍቶ አዳሪ ሕዝብ እያየን ነው። የሚታይ ነገር በተመናመነበት ጊዜ አጋጣሚን ተጠቅሞ የሚታይ ነገር መፈለግ በራሱ አንድ የሥራ ፈጠራ ከሆነ ቆይቷል። ከትርምስ መሀል ቁም ነገር መልቀም በዋዛ ፈዛዛ ጊዜን ከመሸኘት በእጅጉ የተሻለ ነው። ለነገሩ ዘንድሮ ‹‹ቀላል›› ከሚባለው ቃል ሌላ ሲጠሩት ለአፍ ቀለል የሚል ነገር እያጣን ነው። ጊዜው የውድድር ነው ካልን ወዲያ ‹‹ከረር›› እንጂ ‹‹ቀለል›› የሚል ነገር መፈለጋችን በራሱ እንዴት ከባድ እንደሆነ ተመልከቱ። ‹‹ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ዋጋና ክብር በሚያሰጥበት በዚህ ዘመን የትናንሽ ነፍሶች ጩኸት ከዜማ አልዘል ብሎ ቀርቶ ይሆን?›› እያሉ እኚያ እናት አሁንም ያጉረመርማሉ፡፡ ነገራችን ሁሉ አልጣማቸውም መሰል!

አሁን የተሳፋርነው ስድስት ገደማ ደርሰናል። አንዲት ወይዘሮ ዘንቢላቸውን ራሳቸው ይዘው አንድ ወጠምሻን ደግሞ መለስተኛ የሶፋ ጠረጴዛ አሸክመው ወደ ታክሲው ተጠጉ። ወያላው ፈንጠር ብሎ ከቆመበት ቦታ ሮጦ መጣ። ዞር ብለው አይተውት፣ ‹‹አንተ ዘንቢል ተሸክሜ ታክሲህን ብሳፈርም ስንት ታሪክ የነበረኝ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ አሁን ለዕቃዬ ቦታ ትሰጥልኛለህ አትሰጥልኝም?›› ሲሉት የሚናገረው ጠፍቶት አተኩሮ ያያቸዋል። ‹‹ድንቄም ታሪክ አሉ፣ አሁን የእርስዎን ታሪክ አይደለም የአገሪቱን ታሪክ ይኸው እንደ ቅርጫ ዕጣ የሚጣጣልበት ትውልድ ተፈጥሮ ምናለበት ዝም ቢሉ…›› እያሉ እኚያ እናት አሁንም አገሩመረሙ፡፡ ‹‹ለመሆኑ እንዲህ በትንሽ ትልቁ ተቃጥለው ይችሉታል?›› ብሎ ጠየቃቸው አጠገባቸው የተቀመጠ ወጣት። ‹‹ምን አባቴ ላድርግ ብለህ ነው? ጋኖች አለቁና ምንቸቶች ጋን ሆኑ ይሉ ነበር የድሮዎቹ ነፍሳቸውን ይማራቸውና፡፡ ታሪክ የማንም መቀለጃ እየሆነ አንጀቴ ለምን አይረር ብለህ ነው ልጄ?›› ብለው ሳግ በሚተናነቀው ድምፅ መልሰው ጠየቁት። ‹‹መቼም ከንዴት ትዕግሥት ይሻላል። ለማንኛውም ረጋ ይበሉ በሽታውም ይደራረባል…›› እያለ ለደቂቃዎች ያህል ምክር ቢጤ ጣል አደረገላቸው። ወጣቱ ተሻለ ማለት ነው!

ታክሲያችን ከተሠለፈበት ተራ ወጥቶ ዋና መስመሩን መያዝ ከመጀመሩ፣ ‹‹ቆይ በፈጠረህ አንዴ ሾፌር አንዴ አንዴ..›› የሚል ድምፅ ከኋላ መቀመጫ ተሰምቶ ታክሲው ቆመ። ሁላችንም ወደ ኋላችን ስንዞር መስኮት ለመክፈት እየታገለ በዓይኑ አንድ መጽሐፍ ሻጭ ተጣራ፡፡ መጻሕፍት የተሸከመው ወጣት ደርሶ ሲቆም፣ ‹‹ከታሪክ ንትርካችን ጀርባ ያለው ሴራ የሚለው መጽሐፍ አለህ…›› እያለ ሲጠይቅ፣ ‹‹ለወደፊት ካልሆነ እስካሁን በዚህ ርዕስ አልታተም…›› ብሎ ሲመልስለት ወያላው ተሳፋሪውን ወረደበት። ‹‹ምነው ለዚህ ከንቱ ቧልት ነው እንዴ የምታስቆመን? የስንት ሰው ጊዜ እኮ ነው እያቃጠልክ ያለኸው?›› አለው ዓይኑን አጉረጥርጦ። ይኼኔ ከኋለኛው መቀመጫ ፊት ላይ ከተቀመጡ ጓደኛማቾች አንደኛው፣ ‹‹ምን ጊዜያችንን ብቻ? ደህና በ7ለ0 ሽንፈት ተቃጥሎ ያበረድነውን ጨጓራችንን ጭምር ነው ያስነሳው እኮ…›› ሲል አንደኛው፣ ‹‹ቱ ቢ ኮንቲኒዩድ ሲባል የምናውቀው ለፊልም ነበር። አሁን ለጨጓራችንም ሠራ…›› አለ። ታክሲውን ያስቆመው ተሳፋሪ መስኮቱን ከመዝጋቱ ሾፌሩ በንዴት ይመስላል ታክሲውን ያከንፈው ጀመር። ‹‹አይ የእኛ ነገር በከንቱ ነገሮች ዕደሜያችንን እየገፋን የት ልንደርስ ነው?›› ሲሉ ዘንቢል ይዘው የተሳፈሩት ወይዘሮዋ፣ ‹‹ምን ይደረግ ብለው ነው… ትውልዱን መንገድ አስተን አሳድገን ይኸው ላያችን ላይ የመከራ ዶፍ እያዘነብን ነው…›› እያሉ እኚያ እናት ተናገሩ፡፡ ውስጣቸው የበገነ ይመስላል!

‹‹ይታይሃል? ይታይሃል ይኼኛው? እርግጠኛ ነኝ የዚህ ሕንፃ ዲዛይን በባለሙያ አይደለም የተሠራው። ተመልከት የፍሳሽ መስመሩን በውጭ በኩል አድርገው እንዴት እንደሠሩት?›› ትለዋለች ቦርሳ አንጋቿ ታዳጊ ለጓደኛዋ። እርሱም ሐሳቡንና ግምቱን መልሶ ይነግራታል። ‹‹እኛ እኮ እንዲያው ነው ተማርን የሚባለው? ዘመኑ ከተራቀቀበት የግንባታ ዕድገት አንፃር ስንታይ አለን ይባላል?›› ቢላት፣ ‹‹ትቀልዳለህ? እዚህ አገር ምንም ነገር ብትችል እንድታስብ የምትገደደው ሌላው ማሰብ እስከቻለበት ደረጃ ብቻ ነው። አለቀ ደቀቀ…›› አለችው። በአነጋገራቸው እየተገረምን ጨዋታቸውን ስናዳምጥ ብዙ ቆየን። ድንገት፣ ‹‹ተመልከት እንግዲህ ገና በዚህ ዕድሜያቸው አቃቂር ማውጣቱን እንዴት እንደሚችሉበት…›› ይላሉ ወይዘሮዋ ደግሞ የታዳጊዎቹ ንግግር አልጣማቸውም መሰል። ‹‹የሕንፃ ግንባታ የዕድገት ጫፍ ይመስል ታዳጊው ሁሉ የሚመለመለው ለዚሁ ሆነ በቃ?›› ብሎ ከሾፌሩ ኋላ የተቀመጠ ወጣት አጠገቡ የተቀመጠችውን ቀዘባ ሲጠይቃት ሰማን። ‹‹ይኼማ ድልድዩንና የባቡር መስመሩን ጭምር የሚዘረጉ ብርቱ ዜጎች ለማግኘት ታስቦ ነበር። ለእንጀራ እንጂ ለሙያ ፍቅር የሚማር እየጠፋ፣ መንግሥትም የጥራቱን ነገር ችላ ብሎት ቻይና ተንሰራፋብን እንጂ…›› ብላ መለሰችለት። ታክሲ ውስጥ አንድ ሐሳብ ተነስቶ ሳይጠናቀቅ ሌላ ይተካና መንገዳችን እያጠረ እንጓዛለን። ይህም ሒደት ነው!

ወያላችን ፊቱን አዙሮ ሒሳብ መሰብሰብ ጀምሯል። ሁሉም ኪሱን እየበረበረ የሚጠበቅበትን ያስረክባል። ወያላው ከሌሎች ሰብስቦ ሲያበቃ ያልታተመ የታሪክ መጽሐፍ ጠያቂው ወጣት ጋ ደረሰና ሒሳብ አለው። አምስት ብር ሰጥቶት ሲያበቃ፣ ‹‹ሁለት ብር ይጎድለዋል አንተ ሙላበት…›› አለው ምንም ሳያፍር። ወያላው፣ ‹‹ዛሬ ደግሞ ሰውን ምን ነክቶታል? ምንድነው የምትለኝ ወንድሜ?›› አለው በፍፁም ትህትና። ‹‹ብሔራዊ ሎተሪ ዲጂታል ሎተሪ ቁረጡ እያለ ደጋግሞ መልዕክት በስልኬ ሲልክልኝ ገንዘቤን በቴክስት ጨረስኩት። ምናለበት የዛሬን ሁለት ብር አንተ ብትሞላልኝ?›› ይለዋል ኮስተር ብሎ። የታክሲው ተሳፋሪዎች በመገረም ያዩታልል። ደፋሩና ኮስታረው ተሳፋሪ ቀጥሏል። ‹‹ኑሮ እኮ አልቻል አለ። በዚህ የሚዋጣው፣ በዚያ የሚበላው፣ በዚህ የሚነበበው ሁሉ ኪስ ያራቁታል…›› እያለ ሊቀጥል ሲል፣ ‹‹እና የታክሲ ሒሳብ ሲሆን አለቀብህ? ወራጅ አለ…›› ብሎ ወያላው ራሱ ታክሲውን አስቆመው። ነገረኛው ተሳፋሪም ያለ ምንም ማቅማማት በፍጥነት ወረደ። ወያላው ‹‹ሳበው!›› ሲል ከቆምንበት በከባድ ማርሽ ተነስተን መንገዳችንን ቀጠልን። ‹‹ይኼ እኮ ነው ያስቸገረን፡፡ ሄድን ስንል የሚያስቆመን፣ ተሻገርን ስንል ከመንገድ የሚመልሰን አናጣም…›› አሉ እኚያ እናት አሁንም በምሬት። ‹‹የዛሬ 49 ዓመት በኢትዮጵያ ምድር የፈነዳው ሕዝባዊ አብዮት ባይቀለበስ ኖሮ ይኼኔ እንዲህ እንደ እርስዎ የሚመረርም ሆነ የሚያስመርር አይኖርም ነበር…› እያለ የታሪካችንን ስብራትአንድ ዛላ መዘዘ፡፡ ሰሚ ግን አልነበረም!!

መዳረሻችን እየተቃረበ ነው። የታክሲው ወሬ ቀጥሏል። ‹‹ዛሬ ሁሉም ነገር በብሔር ሆኗል። ከብሔር ማንነት የሚበልጠው አገራዊ ማንነት እያለ ሁሉም አቁማዳው ውስጥ መወሸቅ ቁምነገር መስሎታል፡፡ እውነቱን እንነገጋር ከተባለ አሜሪካም ሆነ አውሮፓ ግፋ ቢል አፍሪካዊ ካልሆነም በጥቁርነታችን ነው የሚያውቁን፡፡ ወደ እነሱ የሚያስኬደን ጉዳይ ካለም ቡናማውን ፓስፖርት ካልያዝን ቪዛም አይሰጡንም…›› እያለ ጎልማሳው ለወይዘሮዋ ያስረዳል።  እኚያ እናት ደግሞ ከት ብለው እየሳቁ፣ ‹‹ወዳጄ ልፋ ብሎህ ነው እንዲህ ለማስረዳት መከራ የምታየው፡፡ ታሪኩን በሚገባ ያላስጠናነው ትውልድ ይህ የምትለው እኮ የሮኬት ሳይንስ ነው የሚሆንበት…›› ብለው እንደና ሲስቁ፣ ‹‹እናታችን ከሃርቫርድ ወይም ከስታንፎርድ የተመረቁ ይመስላሉ በአነጋገራቸው…›› ብላ አንደኛው ቀይ ቆንጆ አስተያየት ስትሰጥ፣ ‹‹ልጄ እኔ ከሃይስኩል በላይ የተራመደ ዕውቀት የለኝም፡፡ ነገር ግን አገሩ በሙሉ በጥራዝ ነጠቆች ስለተሞላ አንዲት የእንግሊዝኛ ቃል ወይም ሐረግ ወርወር የሚያደርገው እኮ ግራ ተጋብቶ ግራ የሚያጋባችሁ፡፡ እኔ ልሙት ፒኤችዲ ካላቸው ብዙዎቹ የዘመኑ ምሁር ተብዬዎች አንድ አረፍተ ነገር አስተካክሎ የሚናገር የለም…›› ሲሉ ሌላው ወይዘሮ ዘንቢላቸውን ጠበቅ አድርገው ይዘው እየተዘገጃጁ፣ ‹‹ማነህ ወያላው?›› ብለው ጠሩት፡፡ ወያላውም፣ ‹‹አቤት እመቤቴ?›› ሲላቸው፣ ‹‹ከአቅም በላይ ማሰብ ያደርሳል ከሰበብ የሚባለውን የድሮ ጥቅስም እንዳትረሳ…›› ሲሉት ታክሲያችን በሳቅ ተናጋ፡፡ እኚያ እናት እንደገና፣ ‹‹አያችሁ ጥራዝ ነጠቅነት ሲበዛ የደረጀ አቅም ሳይኖር ጡንቻ ያስወጣጥራል፣ የረባ ሐሳብ ሳይኖር ዕቅድ እያስለጠጠ ሀብትም ጉልበትም ያባክናል፡፡ ታሪካችንም በጥራዝ ነጠቆች እየነተበ ያለው በዚህና በመሰል ሌሎች ምክንያት እንደሆነ ለመረዳት ሃርቫርድም ሆነ ስታንፎርድ ድረስ መሄድ አያስፈልግም…›› እያሉ ሲያስደምሙን በዚህ መሀል ግን ወያላው ‹‹መጨረሻ!›› ብሎን አሰናበተን። መልካም ጉዞ!    

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት