በንጉሥ ወዳጅነው
ሰሞኑን በሥራ አጋጣሚ ወደ ደቡቦቹ ሐዋሳና አርባ ምንጭ ከተሞች ጎራ የማለት ዕድል ገጥሞኝ ነበር፡፡ እግረ መንገዴንም የማውቃቸውን ሰዎችና ዘመዶቼን የማነጋገር ዕድል አግኝቼም ነበር፡፡ በከተሞቹ ከፍተኛ የሥራ አጥ ቁጥር መመልከት ብቻ ሳይሆን፣ አካባቢዎቹ ከዚህ ቀደም ከሚታወቁበት ገጽታ በተለየ ሁኔታ በርካታ ወጣቶችና አቅመ ደካሞች በጠራራ ፀሐይ የዕለት ጉርስ ሲለምኑ መመልከት ችያለሁ፡፡ ሁኔታው ረሃብ/ጠኔ ምን ቀን ምንስ ቀልብ ይሰጣል ያሰኛል፡፡
አልባብ አልባብ ትሸት በነበረችውና በእንቅስቃሴ ትሞላ በነበረችው ሐዋሳ ከተማ ባረፍኩበት አንድ ሆቴል ባለማቋረጥ የውጪ በር እያንኳኩ “ፍርፋሪ አለ ወይ…” የሚሉ ዜጎች ሁኔታ ቅስምን የሚሰብር ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በውቧ ከተማ የንግድና የቱሪዝም እንቅስቃሴ መዳከሙ ከመዳከሙም በላይ፣ ሆቴሎችን በመሰሉ ከፍተኛ የሥራ ዕድል በሚፈጥሩና ገቢ በሚያስገኙ የንግድ ማዕከላት የታዘብኩት ነገርም የምጣኔ ሀብቱንና የአጠቃላይ እንቅስቃሴውን መዳከም የሚያሳብቅ ፍዘት ነው፡፡
ለነገሩ የቅርብ ምልከታዬ ላይ አተኮርኩ እንጂ በመዲናችን አዲስ አበባና በዙሪያዋ፣ በርከት ባሉ የኦሮሚያና የአማራ ክልል ከተሞችም አየሩ በችግር፣ በኑሮ ውድነትና በደኅንነት ሥጋት ብሎም የመጠራጠርና ዋስትና በማጣት ስሜት እየተሞላ ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ ትኩረት የሆነውን ገበያና የኑሮ ጉዳይ ለተመለከተውም ከፍተኛ የገበያ መዋዥቅ፣ የምርት እጥረት፣ የትራንስፖርት መቆራረጥና በፀጥታና በደኅንነት ሥጋት፣ እንዲሁም በአሻጥርና በፖለቲካ ብልሽት ገበያን የማናወጥ ክስረት እያጋጠመ ነው፡፡
ይህ ሁኔታም ሕዝቡን ከጊዜ ወደ ጊዜ ለከፋ ችግር ከማጋለጡም ባሻገር፣ በተለይ ዝቅተኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ለረሃብና ለተረጂነት እያጋለጠ መምጣቱ እንደማይቀር እያሠጋ ነው፡፡ ቀደም ሲል በሲሚንቶና በሌሎች የግንባታ ግብዓቶች ላይ የተስተዋለው የገበያ አሻጥር በመጠኑም ቢሆን መሻሻል አሳየ ሲባል፣ አሁን ደግሞ ጤፍን ጨምሮ በብዙዎቹ ምርቶች፣ ቅመማ ቅመምና አትክልቶች ላይ የሚታየው እጥረትና የዋጋ ግሽበት እጅግ አስደንጋጭ ሆኗል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በዋናነት የፖለቲካ አሻጥር፣ አለመደማመጥና በነፃነት መንቀሳቀስ አለመቻል መሆኑ ወዴት እየሄድን ነው እያስባለ ነው፡፡
እውነት ለመናገር የሕዝቡ ጫና ውስጥ መውደቅ ብቻ ሳይሆን፣ አሁን ያለው ሕጋዊ ነጋዴ ወይም ባለሀብትስ ቢሆን በነፃነት የመንቀሳቀስ ዋስትናና በሥርዓት የመመራት ሥነ ልቦና አለ ወይ ብሎ መጠየቅም የሚያስፈልግበት ፈታኝ ወቅት ላይ መገኘታችንን ነው ብዙዎች እየገለጹ ያሉት፡፡ ለዚህ ችግር መባባስ ደግሞ መንግሥትን ጨምሮ፣ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎችና ራሱ ሕዝቡም የየራሳቸውን አሉታዊ ድርሻ መጫወታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ፅንፈኛ ብሔርተኞችና አማፂያን የገበያ ፍሰቱን ክፉኛ እያደናቀፉ መሆኑን ተገንዘቦ ነገሮች በጥሞና መመርመርና የጋራ መፍትሔ መፈለግ ያስፈልጋል፡፡
“ግርግር ለሌባ ይመቻል” እንደሚባለው ደግሞ አሁን የተፈጠረውን በለውጥ ስም ያጋጠመ የሥርዓት መፈላቀቅ፣ የመንግሥታዊ ሥርዓት ውህደት ማጣትና የሕግ የበላይነት መላላት ተንተርሶ የግል ስግብግብ ፍላጎትን በሕገወጥ መንገድ ጭምር ማሳደድ እየበረከተ ነው፡፡ ከአገራችን ነጋዴዎች ብዙዎቹ ክፉና ሥነ ምግባር የጎደላቸው ለመሆኑ ማሳያው የገዙትን ምርት እየደበቁ በብዙ እጥፍና ከዚያ በላይ ሲሸጡ፣ ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅለው በግፍ ሲቸበችቡ ወይም ገቢያቸውን ሳያሳውቁ ግብር ሲያጭበረብሩና በወገናቸው ላይ ያለ ርህራሔ ሲጨክኑ የሚስተዋሉ በመሆናቸው ነው፡፡ ይህንን ሕገወጥነት እንደ ፖለቲካ አሻጥር ቆጥሮ መታገል የግድ አስፈላጊ ነው፡፡
ብዙዎቹ ነጋዴዎች እንኳንስ ሸማቾችን በደንበኝነት ሊያበረታቱ ይቅርና ሸማቹ ሕዝብ ስለሚገዛቸው ምርት ወይም ዕቃ መረጃ እንኳን በወጉ አይሰጡም፡፡ ማን እንዳወጣውና መቼ በሥራ ላይ እንደዋለ በማይታወቅ ያልተጻፈ ሕግ የተጭበረበረና የተሳሳተ መረጃ ይሰጣሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ለይቶላቸው የሕገወጥ ደረሰኝ ንግድ ላይ ተሰማርተው ከመንግሥት፣ ከመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ከግል ተቋማት ሌቦች ጋር እየተመሳጠሩ ዘረፋ ላይ ተሰማርተዋል፡፡ መንግሥት በግብይት ወቅት ሊያገኝ የሚገባውን ታክስ በመቀራመት አገር እያደኸዩ ነው፡፡
በሁለቱም የአገራችን ታላላቅ እምነቶች (ክርስትናና እስልምና) እንዲሁም በአገሪቱ የንግድ ሕግ የተከለከለና የሚያስቀጣ መሆኑን እያወቀ አብዛኛው ነገዴ ሚዛን ይቀሽባል፣ ከዳቦ ላይና ከሌሎች መሠረታዊ ምርቶች ላይ ጭምር በመቀናነስ ነውሩ ደርቷል፡፡ በብዙዎቹ ግብይቶች ስለዕቃው ጥራት መጠየቅ አይቻልም፡፡ ዋጋ መከራከር የማይቻልበት ሁኔታ ቀስ በቀስ እየተፈጠረ መጥቷል፡፡ አማርጦ መግዛትማ ቅንጦት መስሏል፡፡
የንግድ ፈቃዱንና የሸቀጦቹን ዋጋ በግልጽ በሚታይ ሥፍራ መለጠፍም ግዴታ መሆኑን የሚዘነጋው በዝቷል፡፡ የተበላሸ ዕቃ አይመልስም፣ ደረሰኝ አይሰጥም፣ ዛሬ የገባ ስኳር፣ ዘይት፣ ጤፍ፣ የስንዴ ዱቄት ‹‹የለም›› ይባላል፡፡ ፖሊስ ወይም ደንብ አስከባሪ ይዘህ ብትሄድ ‹‹ከእኔ ላይ አልገዛም›› ብሎ ይክድሃል፡፡ ነጋዴ ተብዬ ተብሎ የተሰየመው አከፋፋይ ወይም ቸርቻሪ የንግድ ፈቃዱ በስሙ ቢሆንም፣ ከበስተጀርባው ያሉ ዘራፊዎችን ገንዘብ እያንቀሳቀሰ የእነሱን ወንጀል ያስፈጽማል፡፡
ሌላው ቀርቶ በሸማቾች ማኅበራት ሱቆች ውስጥ ወግና ሥርዓት ያለው የሬሽን አሠራር መተግበር ሲያቅት ይታያል፡፡ በዚህ አካሄድ ተራ ሸቀጥ ከሱቅ ለመግዛት ምስክር ይዞ መሄድ እያስፈለገ ነው፡፡ ነጋዴው በተለይ ከሸማቹ ሕዝብ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ቸርቻሪ ለሥራው ያለበትን ግዴታ አልተረዳም፡፡ አብዛኛው ልኩን አላወቀም፡፡
ሸማቹም መብትና ግዴታውን አለማወቁ ወይም ቸል ማለቱ ብቻ ሳይሆን፣ ዘወትር የሚሸምተው በአካባቢው ካለው መደብር/ኅብረት ሱቅ ስለሆነ ንዴቱን በሆዱ ይዞ ‹‹ጊዜ ይፍታው›› ብሎ የተጠየቀውን ከፍሎ ይሄዳል፡፡ በየቤቱ ሆኖ ችግሩን ከአቅሙ በላይ ተሸክሞ እነሱ (ነጋዴዎቹ) ምን ያድርጉ! ሃይ የሚላቸው መንግሥት የለም! ‹‹ሕግ ወጣ›› ይባላል እንጂ የሚያከብረውና የሚያስከብረው የለም እያለ ያንጎራጉራል፡፡ ቢያንስ የፖለቲካ አሻጥሩና ውንብድናውን በጋራ ለመታገል ሲንቀሳቀስም ዓይታይም፡፡
ደንብ አስከባሪዎች ወይም የበታች የዘርፉ አስፈጻሚዎች አንድ ሰሞን ሽር ብትን ይሉና ከዚያ ወዲያ የት እንደገቡ አይታወቅም፡፡ በመንገድ ላይ እንኳ አይታዩም፡፡ ሃያ ኩንታል፣ አርባ ኩንታል ደብቆ ወደ ሌላ ቦታ ሲያስተላልፍ በተያዘ “ሕገወጥ” ነጋዴ ላይ የሚወሰደው ዕርምጃም ከማስጠንቀቂያና ከጥቂት ወራት እስራትና ከተወሰነ ብር ቅጣት የሚያልፍ አለመሆኑ (አንዳንዱም በጉቦና በአሻጥር ሕግን እየጣሰ መሻገር የሚችል በመሆኑ)፣ ሕግን መፍራት ቸል መባል ጀምሯል፡፡ ከተመን በላይ በመሸጡ ወይም ሸቀጦችን/ምርቶችን ደብቆ በመገኘቱ የንግድ ፈቃዱን የተነጠቀ ነጋዴ የለም ወይም አልሰማንም የሚሉ ብዙ ናቸው፡፡
አሁን አሁን እየታየ እንዳለው ደግሞ ራሳቸው በማዕከላዊ መንግሥት ወይም በክልሎች ወይም በሕገወጥ መንገድ የተደራጁ አካላት የእህል ምርት ሳይቀር ከቦታ ቦታ እንዳይዘዋወር፣ እንዲሁም በገበያ ውስጥ እንዳይገኝ እያደረጉ ነው ሲባል ይደመጣል፡፡ ለአብነት ያህል ስንዴን መንግሥት ከአርሶ አደሩ ገዝቶ በውጭ ምንዛሪ ሒሳብ በመሸጡ የዱቄት እጥረት በመፈጠሩ የዳቦ ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱ ሳያንስ፣ ምክንያቱ በውል ባልታወቀ ሁኔታ የጤፍ ምርት ከገበያ መጥፋቱ ለሸማቹ ሌላ ፈተና ሆኗል፡፡ ግን እስከ መቼ፡፡
በተጨማሪም ሕገወጦች፣ ሸማቂዎችም ይባሉ አማፅያን የንግድና የገበያ ሥራውን በሚያደናቅፍ ብቻ ሳይሆን አጠቃላዩን የአገር ሰላምና ደኅንነት በሚያውክ ደረጃ መንቀሳቀሳቸው ነገሩን በቦሃ ላይ ቆረቆር እንደሚባለው እያደረጉት ነው፡፡ በእርግጥ ስለመንግሥት በተለይ ስለልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት (ብልፅግናም ቢሆን በገቢር ከኢሕአዴግ የተቀየረ ነገር እምብዛም ያላሳየ በመሆኑ) አቋም በመጠኑም ቢሆን ካነበብነውና ከሰማነው መጠነኛ ግንዛቤ አናጣም፡፡ ማንኛውም ‹‹ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ነኝ›› ወይም በካፒታሊስቱ ዓለም ለሚመላለስ መንግሥት ቁልፍ ጉዳይ የገበያ መር ኢኮኖሚ ወይም ‹‹ነፃ ገበያ›› የሚባለው ነው፡፡ ይህን አካሄድ ያውም በደሃ አገር ካለ በቂ የሕግ ልጓምና ጥበቃ ላስቀጥል ማለት ደግሞ በደሃው ላይ ሰማይ እንዲደፋ እያደረገ ነው፡፡
በዚህ ሁኔታ ደግሞ ያለ ነፃ ገበያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ልማት አይመጣም ብሎ በጭፍን መንቀሳቀስ ብቻውን ውጤት ሊያመጣ እንደማይችል መታመን አለበት፡፡ ደሃ ሕዝብ በዛበት አገር የገበያውን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ (ያለ በቂ ቁጥጥርና የተጠያቂነት አካሄድ) በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መሠረት ከመንግሥት እጅ አውጥቶ ለመዳከር መሞከር የባሰ ችግር መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ በልቶና ሳይቸገር መኖር ለማይችል ብዙኃኑ ሕዝብ ስለብልፅግናም ሆነ ስለዴሞክራሲ መናገርም ጉንጭ አልፋ መሆኑ አይቀርም፡፡
እውነት ለመናገር አሁን ነዳጅ፣ ዳቦ፣ ስኳር፣ ዘይትና ከመሳሰሉት ወሳኝ መሠረታዊ ፍጆታዎች በስተቀር የገበያ ሥርዓቱ ሙሉ በሙሉ ልቅ ነው፡፡ እነዚህም ቢሆኑ የተከሰቱ ቀውሶችን ለማስተካከል መንግሥት ባለበት ኃላፊነት ምክንያት ተገድዶ የገባባቸው ችግሮች ናቸው እንጂ ቀስ በቀስ ድጎማና ቁጥጥራቸው እየቀረ መስሏል፡፡ ለአብነት ያህል የነዳጅ ሁኔታን ብንመለከት መንግሥት ቀስ በቀስ ድጎማውን በማንሳቱ በአሥር ቢሊዮን ብሮች የሚገመት ሀብት እያዳነ ስለመሆኑ ይናገራል፡፡
የድጎማው መነሳት ግን በሕዝቡ ላይ የኑሮ ጫና ለማሳደሩ ወቅታዊውን ገበያ ብቻ ማየት ብዙ ያስረዳል (ድጎማ እየተደረገላቸው ያሉ የብዙኃን ትራንስፖርት ተዋናዮችም በአሻጥር የሚሞዳሞዱበት ነገር እየበዛ መሆኑ ነው የሚደመጠው)፡፡ እንደ አዲስ አበባ አስተዳደር ያሉት የማኅበር ሱቆችንና የሰንበት ገበያዎችን ከአምራቾች ጋር በቀጥታ በማስተሳሰር ለኑሮ ውድነት ማረጋጊያ የጀመሩት ጥረት ይበል የሚሰኝ ቢሆንም፣ በቂ መሆን እንዳልቻለ ግን ተጨባጩ አብነት ራሱ ገበያውና ሸማቹ ነው፡፡
አሁን “ገበያው በመንግሥት አይመራም” ስንል ምን እያልን ነው? በማን እየተመራ ነው? ማንም ይምራው ማን ገበያው ግን በነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ሕግ እየተመራ አይደለም፡፡ ገበያው በፖለቲካ አሻጥረኛው፣ በሕገወጡ ኮንትሮባንዲስቱና በደላላው፣ ብሎም ኃላፊነቱን በማይወጣው ነጋዴ ተብዬው አንዳንዱ አካል መጫወቻ ሆኗል፡፡ እናም እንደ ሕዝብ ነፃ ገበያ የሚባለው አሠራር ይህንን ያህል ልቅና ሕዝብ መበደያ እስኪሆን ድረስ ዕድል ሊሰጠው አይገባም ብለን ግፊት ማድረግ አለብን፡፡
መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ቁጥጥር የሚያደርጉበት፣ ጠበቅ ያለ ዕርምጃ የሚወስዱበት፣ እሽሩሩ የማይሉበት ሆኖ በተቀናጀና በተሳለጠ አግባብ እንዲመሩት ግፊት ማድረግም የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡ የመንግሥት በየደረጃው ያለው መዋቅር በተለይም የንግድ፣ የፋይናንስና የገበያ ሥርዓቱን የሚመሩ አካላትም ከዚህ በላይ ወቅታዊና አንገብጋቢ አጀንዳ እንደሌለ አውቀው ሕዝብ ስለመታደግ ሊጨነቁ ግድ ነው፡፡ ካልሆነ ግን ነገሮች መክፋታቸው የማይቀር ነው፡፡
በእርግጥ መንግሥት በኢንቨስትመንት ይሳተፋል፣ አቅጣጫ ያስቀምጣል፣ ዕቅድ ያወጣል፣ ፀጥታ ለማስከበር ይሞክራል፡፡ ይህን ከማድረግ ውጪ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ውስጥ ጣልቃ ገብቶ ማነቆ አይሆንም፡፡ እኛም ይህንን እንደግፋለን፡፡ መንግሥት ብዛት ያላቸው ባለሀብቶችን ወይም ካፒታሊስቶችን ማፍራት ይፈልጋል፣ ማፍራትም አለበት፡፡ እስከዚህ ድረስ ችግር የለብንም፡፡ ችግሩ ያለው በማን ወጪ? በማን ኪሳራ? የሚለው ላይ ነው፡፡ ሕዝብ እየተጎዳ ሥራዎች ውጤታማ መሆን ካልቻሉ መንግሥት መጠየቅ አለበት፡፡ ሀብት ቢሰበሰብም ሆነ የድጎማ ወጪ ቢቀንስ ደሃውን ሕዝብ ካልታደገ ትርጉሙ ምኑ ላይ ነው ይባል፡፡ ለዚያውም በከፍተኛ መጠን የተሰበሰበ የሕዝብ ገንዝብ በራሱ ለሙስናና ለብልሹ አሠራርም የመጋለጥ ዕድል ያለው መሆኑ እየታወቀ፡፡
ከዚህ አንፃር የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች፣ ‹‹ነፃ ገበያው የሚያድገውና ካፒታሊስቶች የሚፈጠሩት ግዙፍ አቅም ወይም የመንግሥት ካፒታል ዕድገት በሸማቹ ግብር ከፋይ ሕዝብ ኪሳራ መሆን የለበትም፤›› የሚሉትን ምክረ ሐሳብ ማጤን ይገባል፡፡ እንደ ማንኛውም ልማታዊ ወይም ዴሞክራሲያዊ መንግሥትም ይባል፣ ብሔራዊ ዕድገት እንዲመጣና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር እንደ ሚመኝ ሰው የነፃ ገበያ ሥርዓቱም ሆነ እየተውረገረገ ያለው የገበያ ሥርዓት ፈር እንዲይዝ መመኘት ብቻ ሳይሆን መትጋት ከሁሉም ይጠበቃል እላለሁ፡፡
በመሠረቱ ከእያንዳንዱ የልማት ውጤት ቀጥተኛ ተጠቃሚ መሆን የማይፈልግ የለም፡፡ ለምሳሌ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትም ሆነ በገበያ ሥርዓት ማቃናት ላይ ብዙ ቢሊዮን ብር ወጪ ሆኖ ሊሆን ይችላል፡፡ ከግብርና ከቀረጥ ወይም ከውስጥም ሆነ ከውጭ በብድር የተገኘ ገንዘብ ቢሆንም፣ የሕዝብ ገንዘብ ሥራ ላይ እንደሚውል የታወቀ ነው፡፡ መንገዶችን የመገንባት ዓላማ ብዙ ቢሆንም አንዱና ዋነኛው ግን አምራቹንና ሸማቹን ማገናኘት ነው፡፡ ሰላምና በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት በተሟላ መንገድ ሊተገበር ካልቻለ ግን ሁሉም መና ይቀራል፡፡
ምርቶችን በተፋጠነ ጊዜና በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ ማቅረብ የሚቻለው ምርት ስለበዛ ብቻ ሳይሆን፣ በነፃነት መዘዋወርና ሠርቶ መኖርም ሲቻል ነው፡፡ እኛ ባለመታደላችን በማንነትና በፖለቲካ ትርክት ታጥረን እየተወናበድን እንጂ፣ በዓለም ወይም በአኅጉር ደረጃ ዕውን ማድረግ የሚፈልገው ነፃ እንቅስቃሴን ነው፡፡ በአገራችን በየትኛውም አቅጣጫ የሚመረተው የእህል፣ የአትክልት ምርትም ሆነ የግንባታ ግብዓቶች በፍትሐዊነትና በገበያ መር በሆነ መንገድ ያለ አሻጥር እንዲዘዋወር ማድረግ ካልተቻለ ችግሩ ከሰብዓዊነትም ጋር የሚጣረስ መሆኑን መርሳት አይገባም፡፡
በአጠቃላይ የተጠቃቀሱት ማጠንጠኛዎችና የገበያ ተግዳሮቶች ሁሉ የሚያሳዩት፣ የነፃ ገበያውን የፖሊሲ አቅጣጫም ሆነ ተለምዶአዊውን የአምራችና የሸማች መስተጋብር እያወከው ያለው የፖለቲካ አሻጥረኛውና ሕገወጡ ነጋዴ ጠልፎ ለራሱ ጥቅም እያዋለው በመሆኑ ነው፡፡ በንግድ አሠራሩና ሥርዓቱ፣ በገበያተኛው፣ በመንግሥትም ሆነ በሕዝቡ በራሱ እየተመራ አለመሆኑ ጥብቅ እርምት ይሻል፡፡ ገበያውን እንደፈለገ የሚያሽከረክረውና የሚያጦዘው አካል ሁሉ አደብ እንዲይዝም ሕግ መከበር አለበት፡፡ ከወሮበላ በማይተናነሱ አጥፊዎች መተራመስም ሊያበቃ ይገባል፡፡
የመንግሥት አንዳንድ የገበያ ማስተካከያ ጥረቶች ቢኖሩም የቅንጅት ማነስ፣ ያለመናበብ ችግር፣ የሕዝብ ጫናን ያለ ማጤን ፈተና እየታየባቸው መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ “በቂ አይደለም” ካልተባለ በቀር ሕዝቡ ከሥርዓቱ ጋር በመቆም ብልሹ አሠራሮችን ለመዋጋትም መፍጨርጨሩ አልቀረም፡፡ በሒደቱ በቂ ውጤት ካልመጣና ነገሮች ከድጡ ወደ ማጡ መሄድ ከጀመሩ ግን ውድቀት መከተሉ አይቀሬ ነው፡፡ ስለሆነም ሁላችንም የመፍትሔው አካል ለመሆን መሥራትና መረባረብ ይገባናል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው nwodaj@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡