የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ሩሲያን የጎበኙት ዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) በሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ የእስር ትዕዛዝ ባስተላለፈ ማግሥት ነው፡፡
ሩሲያና ቻይና አባል ያልሆኑበትና የማይዳኙበት አይሲሲ፣ በፑቲን ላይ የእስር ትዕዛዝ ቢያስተላልፍም፣ ዢ ጂንፒንግ ሰሞኑን ይፋ ያደረጉትንና የዩክሬንን ቀውስ ይፈታል ያሉትን ባለ 12 ነጥብ የሰላም ሐሳብ ይዘው ቀርበዋል፡፡
ከሳምንት በፊት፣ ለዓመታት ተቋርጦ የነበረውን የኢራንና የሳዑዲ ዓረቢያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለመመለስ ያደረጉት ጥረት የተሳካላቸው የቻይናው ፕሬዚዳንት፣ ዓመት ያስቆጠረውን የሩሲያንና የዩክሬንን ጦርነት በሰላም ለመቋጨትም ከፑቲን ጋር መክረዋል፡፡
ምዕራባውያን ሩሲያን ከዓለም ለማግለል በሚሠሩበት ወቅት የቻይናና የሩሲያ ግንኙነት መጠናከሩ ለምዕራባውያን መልዕክት ያለው ሲሆን፣ ይህም የቻይናን አዲስ የዲፕሎማሲ ድል የሚያሳይ መሆኑን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
ከሞስኮ ጋር ጠንካራ የኢኮኖሚ ግንኙነት ያላት ቻይና፣ በዩክሬን ሰላም ለማምጣት አቅም እንዳላት እያሳየች መሆኑንም አክሏል፡፡
ከመጋቢት 11 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በሩሲያ የሦስት ቀናት ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ዢ ጂንፒንግ ያቀረቡትን ባለ 12 ነጥብ የመፍትሔ ሐሳብ ፑቲን በአክብሮት ያዩት ሲሆን፣ የሁለቱ አገሮች ዓለም አቀፋዊ ግንኙነትም የዓለምን መሠረታዊ መርሆዎች ለማጠናከርና የኃይል ስብጥር እንዲኖር ያስችላል ተብሏል፡፡
በሞስኮ የፖለቲካ ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ሰርጌይ ማርኮቭን ጠቅሶ አልጀዚራ እንዳለው፣ የዢ ጂንፒንግና የፑቲን ዋና አጀንዳ በሁለቱ አገሮች መካከል የኢኮኖሚ ግንኙነትን ለማጠናከር የሚያስችሉ መሠረተ ልማቶች ላይ መወያየት ነው፡፡
ሩሲያና ቻይና አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት የሚጥሉት ማዕቀብ ጫና የማይፈጥርበት ዓለም አቀፍ አዲስ የንግድ ግንኙነት መገንባት አለባቸውም ብለዋል፡፡
የዢ ጂንፒንግን የሩሲያ ጉብኝት አሜሪካ እንዴት ታየዋለች?
የቻይናና የሩሲያን ግንኙነት ቀድሞውንም በበጎ የማታየው አሜሪካ የአሁኑን ጉብኝትም ተችታዋለች፡፡ ቻይና ወደ ሩሲያ ያቀናችበት ወቅት የዲፕሎማሲ ሽፋን በመስጠት ሩሲያ ተጨማሪ ወንጀል እንድትሠራ ያስችላል ብላለች፡፡
የዩክሬን ቀውስን ለመፍታት ቻይና ያቀረበችው ምክረ ሐሳብ በምዕራባውያን ተቀባይነት ያላገኘ ሲሆን፣ ፑቲን ኃይላቸውን እንዲያሰባሰቡና ከዩክሬን በያዙት መሬት ላይ ተጠናክረው እንዲቀመጡ ጊዜ ለመግዛት ያስችላልም ተብሏል፡፡
የዋይት ሐውስ ብሔራዊ ደኅንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርባይ እንዳሉትም፣ ዢ ጂንፒንግ ፑቲን ጦራቸውን ከዩክሬን እንዲያስወጡ ጫና መፍጠር ያለባቸው ቢሆንም፣ ቤጂንግ ይህንን በማድረግ ፈንታ ተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደርስ የሩሲያ ወታደሮች ዩክሬን እንዲቆዩ ልታደረግ ትችላለች የሚል ሥጋት አለ፡፡
ቃል አቀባዩ ኪርባይ እንደሚሉት፣ ዢ ጂንፒንግ ጦርነቱ በዩክሬን ላይ ስላደረሰው ተፅዕኖ ከዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪና ጋር መወያየት አለባቸው፡፡ የዩክሬንን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን ሩሲያ እንድታከብር እንዲያደርጉም አሜሪካ የምታበታታ ይሆናል፡፡
ቻይና የዩክሬን ቀውስ ለማረጋጋት ያቀረበችው ምክረ ሐሳብ
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በድረ ገጹ እንዳሠፈረው፣ ቻይና በዩክሬን ሰላም እንዲሠፍን የራሷን ሐሰብ አቅርባለች፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የመጀመርያው የሁሉንም አገሮች ሉዓላዊነት ማክበር ነው፡፡ አገሮች ትልቅ ሆኑ ትንሽ፣ ጠንካራ ሆኑ ደካማ፣ ደሃ ሆኑ ሀብታም፣ ሁሉም የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አባል በመሆናቸው እኩል ናቸው ያለችው ቻይና፣ የዩክሬንን ቀውስ ለማስቆም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ሕግ ተግባራዊ መሆን እንዳለበት አሳውቃለች፡፡
በዩክሬንና በሩሲያ ጦርነት ሳቢያ በየአቅጣጫው የሚስተዋሉ የቀዝቃዛ ጦርነት ዕሳቤዎችን ማስቆምና አገሮች ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሌሎች አገሮችን መስዋዕት የሚያደርጉበትን አካሄድ ማቆም አለባቸው የሚለውም ሌላው ያስቀመጠቸው ሐሳብ ነው፡፡
ግጭትና ጦርነት ማንንም የማያተርፍ በመሆኑም፣ ጠላትነትን ማቆምና ሰላም ለማስፈን መፍትሔ የሆነውን የሰላም ውይይት መቀጠልም ከቻይና ምክረ ሐሳቦች ይገኙበታል፡፡
ሰብዓዊ ቀውሱን ፖለቲካዊ ይዘት ከማስያዝ ይልቅ ገለልተኛ ሆኖ የተጎዱ ሰዎች ዕርዳታ የሚያገኙበት፣ ሲቪል ሰዎች የሚረዱበት፣ ግጭት ካሉባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች የመውጫ ኮሪደር የሚያገኙበት፣ አጠቃላይ ሰብዓዊ ቀውሱን መፍታት ያስፈልጋል የሚለውም የምክረ ሐሳብ አካል ነው፡፡
ሲቪሎችንና የጦር እስረኞችን በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ጠብቆ መያዝ፣ ከጥቃት መጠበቅ፣ በግጭት የተጎዱ ሴቶችና ሕፃናትን መጠበቅና መብት ማክበርም ሌላው ምክረ ሐሳብ ነው፡፡
የኑክሌር ጣቢያ ያሉባቸውን ቦታዎች ደኅንነት መጠበቅ፣ ጉዳቶችን መቀነስ፣ ሰብል ወደ ውጭ የሚላክበትን ማመቻቸት፣ ማዕቀብ ማቆም፣ የኢንዱስትሪና የአቅርቦት ሰንሰለትን ማረጋገጥና ከግጭት በኋላ የሚኖር ድጋፍን ማጠናከርም ቻይና ግጭቱን ለማስቆም ያስችላል ካለቻቸው ምክረ ሐሳቦች ውስጥ ናቸው፡፡