ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሀብት የማሰባሰብ ግብ ያደረገ የጎዳና ላይ ዱላ ቅብብል ውድድር ቦሌ ክፍለ ከተማ ተከናውኗል፡፡
በቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አማካይነት መጋቢት 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ‹‹ሀብታችንን፣ ዕውቀታችንን፣ ያለ ምንም ስስት የአንድነታችን መገለጫ ለሆነው ለህዳሴ ግድብ ግንባታ›› በሚል መሪ ቃል በተከናወነው ውድድር ከ11 ወረዳዎች የተውጣጡ ተሳታፊዎች መካፈላቸው ተገልጿል፡፡
መነሻውን ከኢትዮጵያ ስፖርት አካዴሚ አድርጎ መድረሻውን በተለምዶ 24 ስታዲየም ባደረገውና ቦሌ ‹‹5150›› የሚል ስያሜን በያዘው በዚህ የሩጫ ውድድር፣ እያንዳንዱ ወረዳ 52 ተወዳዳሪዎችን በመያዝ በአጠቃላይ 572 ተሳታፊዎች ተካፍለውበታል፡፡
በውድድሩ ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ ነጋዴዎች፣ ባለሀብቶች፣ ባንኮች፣ ኢንሹራንሶች፣ ሪል ስቴቶች እንዲሁም ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡
‹‹በክፍለ ከተማችን የሚገኙ የተለያዩ ማኅበራት መላው ነዋሪ ቦንድ በመግዛት የታላቁን ህዳሴ ግድብ ፍፃሜ ዕውን እንዲሆን ለማድረግ ታቅዶ የተዘጋጀ ውድድር ነው፤›› በማለት የቦሌ ክፍለ ከተማ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ታደሰ ገልጸዋል፡፡
በውድድሩ ላይ አቅም ያለው ሁሉ ቦንድ የገዛ ሲሆን፣ በተለይም የተለያዩ ድርጅቶች እንዲሁም ባለሀብቶች ውድድሩን ቦንድ እየገዙ ስፖንሰር ማድረጋቸውን አቶ ተስፋዬ አስረድተዋል፡፡
በዚህም መሠረት የቦሌ ክፍለ ከተማ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 100 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ዓላማን አንግቦ የተነሳ ሲሆን፣ እስካሁን ከ114 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን አቶ ተስፋዬ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ክፍለ ከተማው ‹‹5150›› የተሰኘውን ስያሜ በየዓመቱ በባለቤትነት የሚያካሂደው የሩጫ ውድድር ስያሜ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ይህም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ለመግለጽ የተሰየመ መሆኑን አቶ ተስፋዬ አክለዋል፡፡
ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የፈሰሰበት ከአምስት ሺሕ በላይ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው የታላቁ ህዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ተጠቅሷል፡፡
ግንባታውን ለማጠናቀቅም በመላ አገሪቱ የሀብት ማሰባሰብ መርሐ ግብሮች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡