Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበደብረ ብርሃን ከ30 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮችን ያስጠለሉ ተቋማት ክልሉ እንዲያስለቅቅላቸው ጠየቁ

በደብረ ብርሃን ከ30 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮችን ያስጠለሉ ተቋማት ክልሉ እንዲያስለቅቅላቸው ጠየቁ

ቀን:

በአበበ ፍቅር

በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን በደብረ ብርሃን ከተማ በጊዜያዊነት ተፈናቃዮችን ካስጠለሉ ተቋማት መካከል ሁለቱ ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲመለሱ፣ ከባለ ሀብቶቹ ጥያቄ መቅረቡን የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በከተማው ካሉት ከ30 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች መካከል ከፍተኛውን ቁጥር ይዘው የሚገኙት ቻይና ካምፕና ወይንሸት የወረቀት ማምረቻ ካምፕ የተባሉ ድርጅቶች ሼዶች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ሼዶቹ የተቋቋሙት ለአምራች ኢንዱስትሪ ተብለው እንደነበርና ነገር ግን ባለንብረቶቹ ሥራችን ከዜጎች ችግር አይበልጥም በማለት ላለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ለተፈናቃዮች በመጠለያነት አገልግሎት ሲሰጡ መቆየታቸውን፣ የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፀጋዬ በየነ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት ለመጠለያ ካምፕ ተብሎ ቅድመ ዝግጅት ባለመደረጉ፣ ግለሰቦች ለኢንዱስትሪ ልማት ሊገለገሉበት የነበረውን ሼድ፣ በየጊዜው ከኦሮሚያ ክልል እየተፈናቀሉ ለሚመጡ ዜጎች መጠለያ አድርገው መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡

አሁን ግን ድርጅቶቹ ወደ ማምረት እንቅስቃሴ ሊገቡ መሆናቸውን ገልጸው ተፈናቃዮችን አስለቅቁልን የሚል ጥያቄ እያቀረቡ መሆናቸውን አቶ ፀጋዬ ተናግረዋል፡፡

ከሁለቱ ግዙፍ መጠለያዎች ውጪ ያሉትም የሕዝብ አገልግሎት መስጫ አዳራሾች በመሆናቸው፣ የከተማው ማኅበረሰቦች ዛፍ ሥርና የተለያዩ ሆቴሎችን በመከራየት ሲሰበሰቡ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከችግሩ ስፋት አንፃር ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን ይችላል ባይባልም፣ ከከተማው ሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት በ6.5 ሔክታር መሬት ላይ አዲስ የመጠለያ ጣቢያ እየተገነባ መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

ከአራት ሺሕ እስከ አምስት ሺሕ ተፈናቃዮችን እንደሚይዝ የተነገረለት አዲሱ መጠለያ፣ አሁን እየታየ ካለው የተፈናቃዮች ቁጥር ጋር ፈጽሞ የማይመጣጠን ነው ብለዋል፡፡

የመንግሥትና የለጋሽ ድርጅቶች ድጋፍ በማነሱ የተነሳ ቢሯቸው በተፈናቃዮች ቅሬታና አቤቱታ በመጨናነቁ ወደ ሌሎች የኢንቨስትመንት ልማቶች በሙሉ አቅማቸው መመለስ እንዳልቻሉ የገለጹት አቶ ፀጋዬ፣ ‹‹ሙሉ አቅማችንን ተጠቅመን ወገኖቻችንን ለማገዝ እየሠራን ነው፤›› ብለዋል፡፡

የችግሩ መቋጫ አለመኖርና ከጊዜ ወደ ጊዜ ዜጎች የሚፈናቀሉባቸው አካባቢዎች እየበዙ በመሆናቸው፣ መንግሥት ለችግሩ መፍትሔ የበጎ አድራጊ ድርጅቶችም እየቀነሱ እንደሆነ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በጦርነቱ ወቅት ከሰሜኑ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተፈናቅለው ለነበሩ ዜጎች ከአዲስ አበባ ክፍላተ ከተሞች፣ ከተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ከባለሀብቶች የተለያዩ ድጋፎች ይጎርፉ እንደነበር፣ አሁን ግን በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከኦሮሚያ ክልል በማንነታቸው ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ሁሉም አካላት ዕርዳታን ከመስጠት መቆጠባቸው እንዳሳሰባቸው አክለዋል፡፡

የዓለም ምግብ ድርጅትም እስካሁን ምንም ዓይነት የምግብ ድጋፍ እንዳላደረገ የገለጹት ኃላፊው፣ በተገኘው አጋጣሚ በተለያዩ ሚዲያዎች ጭምር የድረሱልን ጥሪ ማቅረባቸውንና እስካሁን ምንም ዓይነት ምላሽ እንዳልተገኘ ተናግረዋል፡፡

የመንግሥት ዕርዳታ በቂ ካለመሆኑም ባሻገር ወቅቱን ያልጠበቀና ወጥ አለመሆኑን፣ ባሉት ተደራራቢ ችግሮች ሳቢያ ተፈናቃዮች እንደ ሰው እየኖሩ አይደለም ብለዋል፡፡

የደብረ ብርሃን ከተማ የአየር ፀባይ ቀዝቃዛ እንደመሆኑና አሁን ደግሞ ከፍተኛ ዝናብ በመጣል ላይ በመሆኑ ሕፃናት፣ አጥቢና ነፍሰ ጡር እናቶች፣ እንዲሁም እስከ 120 ዓመት ዕድሜ ያላቸው አረጋውያን በአስከፊ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ነገሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ በመሄዳቸው አሁንም ከአዲስ አበባ ዙሪያ ከለገጣፎና ከሱሉልታ አካባቢዎች፣ በሺዎች የሚቆጠሩ አባወራዎች እየመጡ ድጋፍ እንደሚሹ ሪፖርት እያደረጉ ነው ሲሉ አቶ ፀጋዬ አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም መላው የአዲስ አበባ ነዋሪና መላው ኢትዮጵያውያን የተለመደ ቀና ትብብራቸውን እንዲያደርጉልን ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የተለያዩ አልባሳቶችን በማሰባሰብና የምግብ ማብሰያዎችን ጭምር እንዲያበረክቱ ብለዋል፡፡ በአንድ አዳራሽ እስከ አንድ ሺሕ ሰዎች ታጭቀው ለተለያዩ በሽታዎች፣ ሴቶች ደግሞ ለፆታዊ ትንኮሳ መጋለጣቸውን የተናገሩት ደግሞ የደብረ ብርሃን ከተማ ሴቶችና ሕፃናት ማኅበራዊ ጉዳይ መምርያ ኃላፊ ወ/ሮ በለጠች ግርማ ናቸው፡፡

አቅማቸው ለትምህርት ከደረሱት 6,585 ሕፃናት መካከል 1,150 ያህሉ በፕሮጀክት ድጋፍ ትምህርት እንደሚያገኙ የተናገሩት ኃላፊዋ፣ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ክፍል በማስተማርና ቀጣዩን በአቅራቢያቸው ያሉ ትምህርት ቤቶች ተቀብለው እንደሚያስተምሩ ተናግረዋል፡፡

ሕፃናቶችን ማስተማር የተፈለገበት ዋናው ምክንያት ተፈናቅለው ከመጡበት አካባቢ ሲማሩና ሲግባቡበት የነበረው በኦሮሚኛ ቋንቋ ስለነበር፣ አሁን ለመግባባት ያስችላቸው ዘንድ አማርኛ ቋንቋን ጨምሮ ሌሎች መሠረታዊ ትምህርቶች እየተሰጠ እንደሆነ ወ/ሮ በለጡ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በወይንሸት የመጠለያ ካምፕ ተጠልለው የሚገኙ የተወሰኑ ተፈናቃዮች ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ዘርን መሠረት ያደረገ ጥቃት እንደ ደረሰባቸውና በዚህም ከአካባቢያቸው ተሰደው መጥተዋል፡፡

አረጋውያን ከአንድ ዓመት በላይ በሕመም ምክንያት አልጋ ላይ ተኝተው እንደሚገኙ ሪፖርተር በቦታው በመገኘት ለማረጋገጥ ችሏል፡፡

በሌላ በኩል ከአሥር በላይ ቤተሰብ ያሏቸው ወላጆች እንደገለጹት፣ ከአሥራ አምስት ኪሎ ግራም ያልበለጠ ስንዴ አልፎ አልፎ እንደሚሰጡና በጎ አድራጊ ድርጅቶችና ባለሀብቶች በሚያደርጉላቸው ዕገዛ ሕይወታቸውን እንደሚገፉ አስረድተዋል፡፡

ከምዕራብ ሸዋ ዞን ጀባቴ ወረዳ እንደመጡ የተናገሩት አቶ ተስፋዬ በየነ እንዳሉት፣ ስምንት ልጆቻቸውን በትነው ከባለቤታቸው ጋር በመጠለያ ካምፕ ገብተው ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን የሚሰጣቸው ዕርዳታ በቂ ባለመሆኑ የቀን ሥራ ላይ መሰማራታቸውን ገልጸዋል፡፡

በወይንሸት የመጠለያ ካምፕ ለተፈናቃዮች የሕክምና አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩት አቶ ሀብታሙ ተድላ፣ በቀን ለ90 የአዋቂዎች ሕክምና እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ሀብታሙ ገለጻ ከሆነ፣ ከሁሉም በላይ ሰዎች በምግብ እጥረት እየተጎዱ ነው፡፡ ‹‹የሚታዘዘውን መድኃኒት ከምግብ በኋላ ውሰዱ ስንላቸው፣ ምግብ ከየት አግኝተን በማለት የሚመልሱ ታካሚዎች አሉ፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...