Tuesday, September 26, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጸሙ ጥቃቶችና ግጭቶች የተፈናቀሉ፣ እንዲሁም በድርቅ ሳቢያ ከፍተኛ የምግብ ችግር ያጋጠማቸው ናቸው፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ድርቁ ከቁጥጥር ውጪ ከሆነ ለከፋ ረሃብ የሚጋለጡ ቁጥራቸው ከፍተኛ እንደሚሆን ይነገራል፡፡ ይህ እንግዲህ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች የተጎዱትን ወገኖች የሚመለከት ሲሆን፣ ከኮቪድ-19 ወዲህ ባሉት ሦስት ዓመታት ብቻ በከፍተኛ የኑሮ ውድነት እየተደቆሱ ያሉ ወገኖች ሲጨመሩበት ችግሩ መክፋቱን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ወገኖች ቁጥር 20 ሚሊዮን ያህል እንደሆነ ነበር መረጃዎች የሚያመላክቱት፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህ ቁጥር በከፍተኛ መጠን እንደሚያሻቅብ ነባራዊ ሁኔታዎች በሚገባ ያስረዳሉ፡፡ ወትሮም እንደ ነገሩ ከሆነው የገጠር ማኅበረሰብ ኑሮ በባሰ የከተሜው አስፈሪ እየሆነ፣ በተለይ የዝቅተኛው ማኅበረሰብ ኑሮ ወደ ታች እየዘቀጠ ነው፡፡

አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞችና ገጠር ቀመስ ከተሞች ሳይቀር፣ የሥራ አጥ ወጣቶች ቁጥር በጣም እየጨመረ ነው፡፡ እነዚህ ወጣቶች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወላጆች ላይ ጥገኛ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ ወላጆችም በየቀኑ እየጨመረ ያለውን የምግብ ምርቶች ዋጋ መቋቋም እያቃታቸው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሥራ የሌላቸው ብቻ ሳይሆኑ ሥራ እያላቸው በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ሳይቀሩ ምፅዋት እየለመኑ ነው፡፡ ከምፅዋት ልመና በተጨማሪ ምግብ ቤቶች በመሄድ ተመላሽ ምግብ (ትራፊ) የሚጠይቁ ሰዎች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ዜጎች የሚያገኙት ገቢ እንደ ሰደድ እሳት እየተግለበለበ ያለውን የዋጋ ግሽበት መመከት ባለመቻሉ፣ ዝቅተኛ ገቢ ያለው ማኅበረሰብ ፍፁም ድህነት ውስጥ ሲገባ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ደግሞ ነፍስ ግቢ ነፍስ ውጪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያሉት፡፡ መሠረታዊ ፍላጎት የሚባሉት ምግብ፣ መጠለያና ልብስ ዝቅተኛ ገቢ ላለው ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን፣ መካከለኛ ገቢ ላለው ጭምር የማይቀመሱ ከሆኑ ሰነባብተዋል፡፡ የምግብ ችግሩ ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ ፅኑ እየሆነ ነው፡፡

የምግብ ችግሩ ተባብሶ ሄዶ ቀውስ እንዳይፈጠር የመፍትሔ ያለህ መባል አለበት፡፡ ምግብ ከኢኮኖሚ፣ ከፖለቲካና ከማኅበራዊ ጉዳዮች ጋር ዘርፈ ብዙ ቁርኝት ስላለው፣ በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ትልቅ ትኩረት ካልተሰጠው የሚያስከትለው መዘዝ የከፋ ነው፡፡ በተለይ አገር የሚያስተዳድረው መንግሥትና የሚመለከታቸው ተቋማቱ ይህንን ችግር በቅጡ በመገንዘብ፣ በምግብና ተያያዥ መስኮች ላይ የዳበረ ዕውቀትና ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎችን (ከአገር ውስጥም ሆነ ከዳያስፖራው)፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ አጋሮችን በማስተባበር በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ለመፍትሔ የሚረዱ የፖለሲ ሐሳቦች በፍጥነት እንዲያገኙ ጥረት ያድርጉ፡፡ በምግብ ራሷን ያልቻለች አገር ወደ ውጭ ስንዴ ኤክስፖርት ማድረጓ ጥቅሙና ጉዳቱ በሙያዊ መንገድ መመርመር ሲገባው፣ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች የፖለቲካ ቁርሾ ሒሳብ ማወራረጃ መሆን የለበትም፡፡ ከዚህ ይልቅ የሚታረሰውን መሬት ቁጥር መጨመር፣ በዘመናዊ ግብርና ለመሳተፍ የሚፈልጉ ወገኖችን ማበረታታት፣ ለምርት ዕድገት የሚጠቅሙ ግብዓቶችንና ቴክኖሎጂዎችን በስፋት መጠቀምና በዘርፉ ሊጠቅሙ የሚችሉ ባለሙያዎችን ምክረ ሐሳብ ማዳመጥ ተገቢ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ የውጭ ብድር ጫና ያለባት አገር ናት፡፡ ከኤክስፖርት የሚገኘው ገቢ በሚፈለገው መጠን ካለማደጉም በላይ ውጣ ውረድ ያለበት ነው፡፡ ከብድር፣ ከድጋፍና ከሌሎች የሚገኘውም ቢሆን መጠኑ በጣም ቀንሷል፡፡ በዚህና በሌሎች ምክንያቶች መንግሥት ከትንሽ ምርቶች በስተቀር ድጎማ ማድረግ አቁሟል፡፡ የነዳጅ ድጎማ ከተነሳም ሰንበት ብሏል፡፡ በእነዚህና በሌሎች ተዛማጅ ምክንያቶች ሳቢያ የዋጋ ግሽበቱ ከአቅም በላይ እየሆነ ነው፡፡ በአጠቃላይ በፍጆታ ምርቶች ዋጋ ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ግሽበት በጣም እየጨመረ ሲሆን፣ በተለይ በምግብ ምርቶች ላይ የሚስተዋለው ግን የዜጎችን ምሬት እያከበደው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ፈተና በሚያጋጥምበት ወቅት ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ለሰብዓዊ ፍጡራን በመሆኑ፣ መንግሥትም ቀውስ ከመከሰቱ በፊት የመፍትሔ ዕርምጃዎች ላይ ያተኩር፡፡ ለመፍትሔ የሚረዱ ምክረ ሐሳቦችን ለመስጠት ፈቃደኛ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ዕድሉ ይሰጣቸው፡፡ በርካታ ችግሮች በተደራረቡባት ኢትዮጵያ ውስጥ ፅኑ የምግብ ችግር ሲታከል፣ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው እየተጎዳ ያለውን ሕዝብ መታደግ ነው፡፡

ብዙ ጊዜ እንደሚባለው የምግብ ችግር ወይም ጠኔ ጊዜ አይሰጥም፡፡ በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ ለአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ከተጋለጡት በተጨማሪ፣ ገቢ እያላቸው ምግብ መግዛት ያዳገታቸው ወገኖች ቁጥር በየቀኑ ሲያሻቅብ የሚያስተላልፈው መልዕክት ጥሩ አይደለም፡፡ ከበርካታ ዓመታት በፊት የነበረው ሙግት ኢትዮጵያውያን በቀን ሦስቴ ምግብ ማግኘት እንዳለባቸው፣ በተጨማሪም እንደ ሥጋ፣ ዶሮ፣ ዕንቁላል፣ ወተት፣ ቅቤ፣ ዓይብ፣ ፍራፍሬዎችና የመሳሰሉ ምግቦችን በቀላሉ እንዲያገኙ ምን መደረግ እንዳለበት ነበር፡፡ በተለያዩ የችግር ማዕበሎች ውስጥ የምትንገላታው ኢትዮጵያ ውስጥ ከበቂ በላይ የወጣት ኃይል፣ ክረምት ከበጋ የሚፈሱ የውኃ አካላት፣ ተስማሚ የአየር ፀባዮችና መልክዓ ምድሮች፣ በርካታ ማዕድናት፣ በአፍሪካ ወደር የሌላቸው የቱሪስት መስህቦችና ሌሎች ፀጋዎችን መጠቀም ባለመቻሉ ኢትዮጵያውያን ዛሬም በምግብ ዕጦት ይሰቃያሉ፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ምንድነው ሲባል በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ፖሊሲና ስትራቴጂ መቅረፅ አለመቻል እንደሆነ፣ ለብዙ ጊዜ ሲነገር የነበረና ትውልዶች የተቀያየሩበት አዙሪት ነው፡፡ አሁን ጥያቄው ከዚህ ችግር እንዴት መውጣት ይቻላል የሚለው ነው፡፡

የምግብ ችግር ጉዳይ መፍትሔ ያስፈልገዋል ሲባል በርካታ ተያያዥ ጉዳዮችም ይነሳሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል በጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ለማፍለቅ የባለሙያዎች ዕገዛ አንዱ ነው፡፡ ግብርናውን ጨምሮ በኢኮኖሚው ውስጥ የተሰማሩ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎችና ሠራተኞች ብቁ መሆን አለባቸው፡፡ ተቋማቱም ችግሩን ለመቋቋም መንደፋደፍ ብቻ ሳይሆን የተሻሉ አሠራሮችን ለማመንጨት ብቁ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከማሳ እስከ ሸማቹ ድረስ ያለው የግብይት ሰንሰለት ጤናማ የሚሆነው፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማትና በውስጣቸው ያለው የሰው ኃይል ብቁ ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡ በብልሹ አሠራሮች የተተበተበው የግብይት ሥርዓት መዘመን የሚችለው፣ በሕገወጥ መንገድ ተደራጅተው አፍነው ከያዙት ኃይሎች ነፃ ሲወጣ ነው፡፡ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰገው የዘረፋ ኃይልና ተባባሪዎቹ የሚከስሙት፣ በብቃትና በኃላፊነት ስሜት የሚሠሩ ሹማምንትና ባለሙያዎች ተቋሞቻቸውን ከሕገወጦች መከላከል ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ ሠርቶ ማሠራት ማኩራት ሲገባው አንገት የሚያስደፋ ሲሆን፣ እንኳን መፍትሔ ሊያመነጩ የሚችሉ አጋዦችን ማግኘት ትጉሃን ሠራተኞችንም ማቆየት አይቻልም፡፡ አሁን ግን የምግብ ችግሩ ድህነትን እያባባሰ መሆኑ ይሰመርበት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ በመከረው የመጀመሪያ ጉባዔ ለዲፕሎማቲክና ለትብብር አማራጮች ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ በቀይ ባህር ቀጣና የፀጥታ...

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...

የመጀመርያ ምዕራፉ የተጠናቀቀው አዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ተከላው እንደገና ሊከናወን መሆኑ ተሰማ

እስካሁን የሳር ተከላውን ጨምሮ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ዕድሳቱ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...