Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኮንትሮባንድ ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት እንደሆነ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታወቁ

ኮንትሮባንድ ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት እንደሆነ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታወቁ

ቀን:

  • በሕገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ከ52 ቢሊዮን ብር በላይ በቁጥጥር ሥር ውሏል

በኢትዮጵያ ኮንትሮባንድ ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሆኗል ሲሉ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኰንን አስታወቁ፡፡

አቶ ደመቀ ይህን የተናገሩት ሰኞ መጋቢት 11 ቀን 2015 ዓ.ም. የክልል ፕሬዚዳንቶች፣ ሚኒስትሮች፣ ከንቲባዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በኢንቨስትመንትና በሕገወጥ ንግድ ላይ ያተኮረ ውይይት ሲካሄድ ነው፡፡

‹‹ኮንትሮባንድን ደፈር ብለን ወደ ራሳችን አስጠግተን ካየነው የብሔራዊ ደኅንነት አደጋና አሳባቢ ችግር ነው፤›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡

ከኢትዮጵያ በርካታ ዕቃዎች በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጭ እየወጡ መሆናቸውን ያብራሩት አቶ ደመቀ፣ ‹‹አሁን ምን ቀረን ብለን ስንጠይቅ፣ ሰውን ያህል ነገር በተለይ ወጣቱ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር በደላሎች ከአገር እየወጣ ነው፡፡ ምን ዓይነት ፈተና ውስጥ እንዳለን እናውቃለን፡፡ ሰው በሕገወጥ መንገድ ከወጣ ምን ቀረን ታዲያ? ሰው ዋናው ሀብት ነው እጅግ የሚዘገንን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በብዙ ፈተናዎች መካከል ሆና ከሳዑዲ ዓረቢያ በዚህ ዓመት ብቻ በሕገወጥ መንገድ የሄዱ 102,000 ሺሕ ዜጎች ወደ አገሯ መመለሷን ጠቅሰው ‹‹በሌሎች አገሮች ያላትን ለመመለስ ያለው ጫና ምን ያህል ፈተና እንደሆነና በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ፍዳ እንደ ዜጋ፣ እንደ አገር እጅግ በጣም የሚያሳስብ ነው፡፡ አሁንም በስፋት በሕገወጥነት የሚሄደው እጅግ ይፈትናል፤›› ብለዋል፡፡

በቅርቡ በአንዳንድ አፍሪካ አገሮች በተመሳሳይ አንገት አስደፊ ሁኔታ እንደገጠመ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ሰው በሕገወጥ መንገድ ከሄደ፣ በኢኮኖሚውም ሆነ ለውጭ ገበያ በመላክ ከፍተኛ ውጤት የሚያመጡትና አሉን የሚባሉ የግብርና ምርቶች፣ በኮንትሮባንድ ወደ ውጭ አገር ከወጡ፣ አገሪቱ አላት የሚባለው የእንስሳት ሀብት በኮንትሮባንድ ከወጣ፣ ምን ዋጋ አለው በአፍሪካ ይህን ያህል የመሪነት ሚና ያላት አገር፣ ይህን ህል የእንስሳት ከብቶች ያላት፣ ይህን የመሰለ ማለቱ ምን ይሠራል?›› በማለት ተሳታፊዎችን ጠይቀዋል፡፡

አቶ ደመቀ አክለውም፣ ‹‹የግብርና ምርት፣ እንሰሳት፣ ማዕድናት በሕገወጥ መንገድ ከወጡ አለ የተባለ የኢትዮጵያ ፀጋ ሁሉ ይወጣል፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? ምን ቀረን? የሚለው ጥያቄ በትክክል መታየት አለበት፤›› ብለዋል፡፡ ይህ በጣም አሳሳቢ የሆነ በብሔራዊ ደኅነነት ደረጃ የመጣ፣ አደገኛ የሆነ፣ ሕጋዊ ሥርዓትን እንደ ዋዛ እያሟሟና ሕገወጥ ሥርዓት የበላይነት እየያዘና እየነገሠ የመጣበት ጊዜ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡

  ‹‹ያለፉትን ችግሮች በልክ በልካቸው ተምረንባቸው ወቅሰናቸዋል፡፡ አሁን እኛ በምንመራበት ሰዓት ያለውን ችግር ያንን እንዴት እንደምንፈታ በከፍተኛ ትኩረት ማሰብና መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ታዲያ ምን ቀረን የሚለው ጥያቄ መሪ ጥያቄ ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ በሕወገጥ መንገድ የሚሄዱትና በዓለም ገበያ ዘመናዊ መልክ እየያዙ በየአገሩ ብራንድ እየወጣላቸው እየተሸጡ መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ ይህን ገጽታ አስይዛ እንዴት መጠቀም ትችላለች የሚለው ጉዳይ በደንብ መታየት እንዳለበት አቶ ደመቀ ተናግረዋል፡፡

ችግሩ ካልተቋጨ፣ ‹‹ጉዳዩ ሳናውቀው እያሟሟን፣ እያሟማን ሕገወጥነትን እያነገሠ፣ መንግሥትም ሕጋዊነትን እንዳያሰፍን፣ ሀቀኛ ግብር ከፋይ ተብለው የተሸለሙትም ታዲያ ምን ዋጋ አለው በሚል ተስፋ እየቆረጡ ሕገወጥነት እየሰፋ ይሄዳል፤›› ብለዋል፡፡

 የኮንትሮባንድ መዘዙ በገንዘብ ልኬት ሳይሆን፣ ከዚያ በላይ ግጭትንና አሸባሪነትን የሚፈለፍል፣ አገርን በጠቅላላ አሳልፎ የሚሰጥ የሉዓላዊነት ጉዳይ በመሆኑ በዚህ ደረጃ መመልከት ያስፈልጋል ሲሉ አቶ ደመቀ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

‹‹በእውነት ይህ አገርና ይህ ሕዝብ የማይሸከመው ፍዳ የለም፡፡ ነገር ግን እጅግ ጥልቀት ያለው ሚናና ዋጋ የሚያስከፍል ምዕራፍ ውስጥ እየገባን ስለሆነ ጠንካራ የፀረ ኮንትሮባንድ አገራዊ ንቅናቄ በማካሄድ ሕጋዊ የንግድ ሥርዓትን ማጎልበት ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

ባለፉት ስምንት ወራት በሕገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ከ52 ቢሊዮን ብር በላይ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን፣ የጉምሩክ ኮሚሽን አቶ ደበሌ ቃበታ በመድረኩ ባቀረቡት ጹሑፍ ላይ ተመላክቷል፡፡

ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ላይ የነበረው የፀረ ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ፈተናው ከፍተኛ እየሆነ መጥቷል ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ኮንትሮባንድ በተለይ በትልቁ ውይይት የሚያስፈልገውና መፍትሔ የሚያሻው ጉዳይ ሆኗል ብለዋል፡፡

የገቢ ኮንትሮባንድ መስመሮቹ በሶማሌ ክልል፣ በድሬዳዋ፣ በኦሮሚያ ምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፣ አርሲና ባሌ፣ በአማራ ክልል መተማ፣ ጎንደር፣ ሳንጃና፣ በሲዳማ፣ በደቡብ ብሔራዊ ክልል፣ በአፋር አዋሽ ሰመራ፣ ገዳማይቱ፣ ጋላፊ የኮንትሮባንድ መፈልፈያ ቦታዎች በመሆናቸው በጣም ትልቅ ተግዳሮት እንደሆኑ ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡

ከገቢ ኮንትሮባንድ ዕቃዎች መካከል ኤሌክትሮኒክስ፣ ተሽከርካሪዎች፣ መድኃኒቶችና የጦር መሣሪያዎች ከፍተኛውን ቦታ የሚይዙ መሆኖናቸውን አቶ ደበሌ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ የውጭ ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በሶማሌ ክልል ድሬዳዋን መነሻ አድርጎ የሚደረገው እጅግ በጣም ሰፊ መሆኑን፣ በኦሮሚያ በባሌ፣ በምሥራቅና በምዕራብ ሐረርጌ፣ በአማራ በመተማ፣ በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ዝውውሩ መጨመሩን ገልጸው፣ ወደ ኤርትራና ደቡብ ሱዳን የሚገቡት ሸቀጦች፣ የግብርና ምርቶች፣ የቁም እንስሳትና ማዕድናት ይገኙበታል ተብሏል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ግርማ ብሩ (አምባሳደር) በኬላዎች መብዛት ምክንያት ምርቶች ማለፍ ሲያቅታቸው እንደሚታይ ጠቅሰው፣ ይህን ለመፍታት ኮንትሮባንድን የሚያባብሰው ‹‹መንገብገብ›› ብቻ ሳይሆን የፖሊሲ ችግርም ነጋዴውን ወደ ኮንትሮባንድ እንዲሄድ ሊያደርገው ይችላል ብለዋል፡፡

የኮንትሮባንድ ችግር አገራዊ መሆኑን የተናገሩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ፣ ከጉምሩክ ኬላዎች በስተቀር የክልል ኬላዎችን ማንሳት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡ ‹‹የኬላ መብዛት ክልሎችንም አይጠቅምም፣ የሚጠቅመው ኬላ ላይ የተመደቡ ሰዎችን ነው፡፡ ስለዚህ ያልተነሱ ኬላዎች ከዛሬ ጀምሮ ይነሱ፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...