Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበድርቅ ለተጠቁ አካባቢዎች ሕይወት አድን ድጋፍ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ ተነገረ

በድርቅ ለተጠቁ አካባቢዎች ሕይወት አድን ድጋፍ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ ተነገረ

ቀን:

በኢትዮጵያ በድርቅ አካባቢ ለሚኖሩ ከ24 ሚሊዮን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሕይወት አድን ድጋፍ ለማቅረብ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባባሪያ ጽሕፈት ቤት (ኦቻ) አስታወቀ፡፡

  ኦቻ እስከ መጋቢት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ያለውን የአገሪቱ የድርቅ ሁኔታ በተመለከተ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው፣ ምሥራቃዊውና ደቡባዊው የኢትዮጵያ ክፍል ለአምስት ተከታታይ ዓመታት በዝናባማ ወቅቶች የሚጠበቀውን ዝናብ ባለማግኘታቸው ድርቁ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡

  እንደ ሪፖርቱ ከሆነ በኢትዮጵያ 24 ሚሊዮን ያህል ዜጎች በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 11 ሚሊዮን የሚሆኑት የዕለት ደራሽ ዕርዳታ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ሰባት ሚሊዮን ያህል እንስሳት መሞታቸው በሪፖርቱ ውስጥ ተካቷል፡፡

  በተለይ በተያዘው የአውሮፓውያን ዓመት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ድርቅን ጨምሮ፣ ሌሎች ተጓዳኝ ውስብስብ ችግሮች በመከሰታቸው የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎቱን እንደሚጨምረው ይጠበቃል ተብሏል፡፡

  በተያዘው ዓመት ለጋሾች 13 ሚሊዮን ያህል የሚደርሱ በድርቅ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችን በተለይም የምግብ፣ የጤናና ሌሎች የሕይወት አድን ድጋፎችን እንዲያገኙ ዕገዛ ያደርጋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህ ዕውን እንዲሆን ደግሞ በአጠቃላይ ከተጠየቀው 3.9 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 2.05 ቢሊዮን ዶላር በአስቸኳይ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡

  የተጠቀሰውን ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚጠበቁት ለጋሾች ቁርጠኛ ሆነው የሚያስፈልገውን ድጋፍ ለማድረግ ርብርብ፣ እንዲሁም የሚሰጡትን የምላሽ መጠን ከፍ ማድረግ እንደሚገባቸው በኦቻ ሪፖርት ተጠቅሷል፡፡

  እ.ኤ.አ. በ2022 ላጋጠመው የድርቅ አደጋ ምላሽ ከሚያስፈልገው 1.6 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ኦቻ ያስተባበራቸውን ጨምሮ ከሌሎችም ምንጮች 928 ሚሊዮን ዶላር ያህል መገኘቱ ታውቋል፡፡ ያም ሆኖ ግን በተለይም ከፍተኛ የድርቅ ጉዳት ተከስቶባቸው ድጋፍ ያፈልጋቸዋል ከተባሉት ዘጠኝ የደቡባዊና የምሥራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች ከሚገኙ ዘጠኝ ክላስተሮች ውስጥ፣ አምስት ያህሉ ሃምሳ በመቶና ከዚያ በታች ድጋፍ የተደረገላቸው መሆኑን፣ በዚህም ምክንያት ለአካባቢዎቹ አፋጣኝ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጿል፡፡

  በተጠናቀቀው የአውሮፓውያን ዓመት በከፍተኛ ሁኔታ በድርቅ በተጠቁት የሶማሌ፣ የኦሮሚያና የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የተሰጠው ድጋፍ (ምላሽ) በቂ አይደለም ተብሏል፡፡

  በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ቢያንስ ለአንድ ጊዜ ያህል የሕይወት አድን ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ተብለው ከታሰቡት 17 ሚሊዮን ዜጎች ውስጥ፣ 11 ሚሊዮን (66 ከመቶ) ለሚሆኑት አጋር አካላት የሚባሉት ድጋፍ ማድረጋቸው ተጠቁሞ፣ ነገር ግን የተቀሩት ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ ወገኖች በፋይናንስ እጥረት፣ በአካባቢ ርቀት፣ ውስን ድጋፍ ብቻ የሚያደርጉ አጋር አካላት በመኖራቸው፣ እንዲሁም እየከፋና ቁጥሩ እየጨመረ ከመጣው የመፈናቀልና ከተባባሰው የድርቅ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ለአንድ ጊዜም ቢሆን ይህንን የሕይወት አድን ድጋፍ ሳያገኙ መቅረታቸው ታውቋል፡፡

  በተለይም ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ከተባሉ ወገኖች ውስጥ 21 በመቶ ያህሉ አስቸኳይ መጠለያና ምግብ ያልሆኑ ድጋፎችን ያላገኙ መሆናቸውን፣ 50 በመቶ ያህሉ ቢያንስ የሚያስፈልጋቸውን የምግብ ድጋፍ ማግኘት እንዳልቻሉ፣ 22 በመቶ የሚደርሱት ደግሞ የተመጣጠነ ምግብ ድጋፍ ለማግኘት አለመቻላቸው ተመላክቷል፡፡

  በአሁኑ ወቅት ወደ 24 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች እንደሚኖሩ፣ ከእነዚህም ውስጥ 13 ሚሊዮን ለሚሆኑ ለአደጋ ተጋላጭ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች አስቸኳይ የሕይወት አድን ዕርዳታ ለማድረግ መታቀዱን የገለጸው ዩኤን ኦቻ፣ በተጠቀሱት አካባቢዎች በምግብ ዋስትና ዕጦትና በተመጣጠነ ምግብ አለመኖር የተጎጂዎች የጤና ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን፣ የተረጂዎቹ የመቋቋም አቅም እየተሸረሸረና ተጋላጭነታቸው እየጨመረ ነው ብሏል።

  ድርቁ ለሰውና ለእንስሳት የሚውለውን ውኃ፣ እንዲሁም ለእንስሳት የሚቀርበውን የግጦሽ ሳር አቅርቦትን መጉዳቱ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ጉዳት በደረሰባቸው ክልሎች ከ6.85 ሚሊዮን በላይ የቤት እንስሳት እ.ኤ.አ. ከ2021 መጨረሻ ጀምሮ እንደ ሞቱ፣ ከደረሰው ጉዳት ውስጥ በኦሮሚያ ክልል (4.64 ሚሊዮን)፣ በሶማሌ ክልል (2.2 ሚሊዮን) እና በደቡብ ክልል ኦሞ ዞን (5,600) መመዝገቡ ታውቋል።

  በኦሮሚያ፣ በሶማሌና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በተከሰተው ድርቅ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ አባወራዎች ከብቶቻቸውን ሊያጡ እንደሚችሉም፣ የግብርና ክላስተርን ጠቅሶ ኦቻ አስታውቋል።

   በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚደረጉ ድጋፎች ዘላቂነት እንዲኖራቸውና በተቀናጀ መንገድ እንዲከናወኑ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከሰሞኑ መጠየቁ ይታወሳል፡፡ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ አበራ ቶላ በኢትዮጵያ በተለይም በዝቅተኛ አካባቢዎች ላይ የሚከሰቱ ተደጋጋሚ የድርቅ አደጋዎች በዘላቂነት እንዲፈቱ የተቀናጀና አገር አቀፍ ርብርብ የሚያስፈልግ መሆኑን፣ ለዚህም መንግሥትና ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...