Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአካባቢ ጥበቃ ሳይንቲስቱ ሥርዓተ ቀብር ዛሬ ይፈጸማል

የአካባቢ ጥበቃ ሳይንቲስቱ ሥርዓተ ቀብር ዛሬ ይፈጸማል

ቀን:

የዕውቁ የአካባቢ ጥበቃ ሳይንቲስት ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር) ሥርዓተ ቀብር ዛሬ መጋቢት 13 ቀን 2015 ዓ.ም. በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በዘጠኝ ሰዓት ይፈጸማል፡፡

ብዝኃ ሕይወትና የአርሶ አደሮች የእህል ዘር ባህላዊ መብት እንዲጠበቅ ጽኑ አቋም የነበራቸውና ለዓለም አቀፍ ሽልማቶች የበቁት ተወልደ ብርሃን (ዶ/ር) ያረፉት መጋቢት 11 ቀን ሌሊት መሆኑን ቤተሰቦቻቸው አስታውቀዋል፡፡

የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ የዕፀዋት ሥነ ምህዳር ባለሙያ መሆናቸው የሚነገርላቸው ሳይንቲስቱ፣ ከአካባቢ ጥበቃና ብዝኃ ሕይወት ጋር የተያያዙ ከሠላሳ በላይ ጥናቶችን ማሳተማቸው ገጸ ታሪካቸው ያሳያል፡፡

የዕፀዋት ጄኔቲክ ሀብት ለንግድ ሲባል ፈጽሞ እንዳይለወጥና በተለይም ሠለጠኑ የሚባሉ አገሮች አርሶ አደሩ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈለት ለዘመናት ጠብቆ ያቆያቸውን የዕፀዋት ሀብቶች እንዲጠብቁም በቁርጠኝነት ተሟግተዋል፡፡

የዘረ መል ማሻሻያ የተደረገባቸው ምግቦች ያላቸውን አሉታዊ ተፅዕኖ በተመለከተ ውጤት ያስገኘ ድርድር ማድረጋቸውን ‹‹የምድራችን ጀግና›› በሚል በዘነበ ወላ በተጻፈው ግለ ታሪካቸው ተመልክቷል፡፡

የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በ1955 ዓ.ም. ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ከዌልስ ዩኒቨርሲቲ ያገኙት ተወልደ ብርሃን (ዶ/ር) በ1970ዎቹ መጀመርያ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ፋኩልቲ ዲን የነበሩ ሲሆን፣ ከ1975 እስከ 1983 ዓ.ም. የአስመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆነው ሠርተዋል፡፡

በ1982 ዓ.ም. በኢሕዲሪ መንግሥት ሹም ሽር ሲደረግ የባህል ሚኒስትር የነበሩት ተወልደ ብርሃን (ዶ/ር) በኢፌዴሪ መንግሥት ጡረታ እስከወጡበት ድረስ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዕፀዋት ስያሜ ፕሮጀክት መሥራቹ ሳይንቲስት ካገኟቸው ሽልማቶች መካከል ቀዳሚው፣ እ.ኤ.አ. በ2000 በስዊድን ስቶክሆልም ከተማ በአካባቢ ጥበቃ ላበረከቱት ላቅ ያለ ተግባር አማራጭ የኖቤል ሽልማት ነው፡፡ ሌላኛው በ2006 በሲንጋፖር ‹‹ሻምፒዮን ኦቭ ዘ ኸርዝ›› ከመንግሥታቱ ድርጅት ተቀብለዋል፡፡

ከአባታቸው ከቄስ ገብረ እግዚአብሔር ዮሐንስና ከእናታቸው ወ/ሮ መዓዛ ተወልደ መድኅን በትግራይ ዓድዋ ርባ ገረድ የካቲት 12 ቀን 1932 ዓ.ም. የተወለዱት ተወልደ ብርሃን፣ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን በንግሥተ ሳባ፣ ሁለተኛ ደረጃን በጄኔራል ዊንጌት ተከታትለዋል፡፡

ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በ83 ዓመታቸው ያረፉት ነፍስ ኄር ተወልደ ብርሃን የሦስት ልጆች አባት የነበሩ ሲሆን፣ ከስድሳ በላይ ልጆችን ማሳደጋቸው በዜና ሕይወታቸው ተመልክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...