Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት የበይነ መረብ ሥነ ምግባር ደንብ ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት የበይነ መረብ ሥነ ምግባር ደንብ ይፋ አደረገ

ቀን:

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ያዘጋጀውን የበይነ መረብ ጋዜጠኝነት የሥነ ምግባር ደንብ ይፋ አደረገ፡፡ በሥነ ምግባር ደንቡ ላይም ከሚዲያ ባለሙያዎች ጋር ውይይት አድርጓል።

ይፋ በተደረገው የሥነ ምግባር ደንብ ላይ ባለፈው ሳምንት ከሚዲያ ባለሙያዎች ጋር ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ በወቅቱም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት የሥራ አስፈጻሚ ሰብሳቢ አቶ አማረ አረጋዊ፣ የተዘጋጀው ደንብ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አማራጭ የመረጃ ማሠራጫ ዘዴ ሆኖ በመጣው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚሠሩ ጋዜጠኞች፣ የሙያውን ሥነ ምግባር አክብረው ለኅብረተሰቡ መረጃዎችን ማሠራጨት እንዲችሉ እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።

በአሁኑ ጊዜ የዲጂታል ሚዲያ ተደራሽነት እየጨመረ ነው ያሉት አቶ አማረ፣ በዚሁ ልክ በዲጂታል ሚዲያው በሚሠራጩ የሐሰት መረጃዎች፣ የጥላቻ፣ የብሔርና ሃይማኖት ተኮር ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶች መበራከታቸውን ገልጸዋል።

‹‹ሁሉም የበይነ መረብ ጋዜጠኞች ሐሰተኛ መረጃዎችንና ከፋፋይ መልዕክቶችን እያስፋፉ ነው ለማለት ባይቻልም፣ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የበይነ መረብ ጋዜጠኞች ከጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር በተቃራኒ መረጃዎችን ያሠራጫሉ፤›› ሲሉ አቶ አማረ ተናግረዋል።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችንና የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ የበይነ መረብ የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ደንብ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በበይነ መረብ ጋዜጠኝነት የሥነ ምግባር ደንብ ላይ ጽሑፍ ያቀረቡት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታምራት ኃይሉ፣ በአብዛኛው በዲጂታል ሚዲያው እየተሳተፈ ያለው ከጋዜጠኝነት ሙያ ውጪ መሆኑን ጠቁመው፣ የበይነ መረብ የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ደንቡ የሚመለከተው በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ሆነው በዲጂታል ሚዲያ ተሳትፎ ያላቸውን ነው ብለዋል።

በዲጂታል ሚዲያ የሐሰት መረጃ፣ የጥላቻና የግጭት ጉሰማ መልዕክት የሚያስተላልፉት በሙያው ዕውቀቱና ሥነ ምግባሩ የሌላቸው ግለሰቦች መሆናቸውን ለኅብረተሰቡ ማሳወቅና ማስገንዘብ እንደሚገባ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ግዛው ተስፋዬ በበኩላቸው፣ ባለሥልጣኑ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን የጀመረውን የእርስ በርስ ቁጥጥር ሥርዓት እንደሚደግፍ ገልጸዋል። አክለውም ባለሥልጣኑ በዲጂታል ሚዲያዎች የሚንቀሳቀሱ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ዕውቅና የሚያገኙበት አሠራር መዘርጋቱን ጠቁመዋል።

ምክር ቤቱ ያዘጋጀው የሥነ ምግባር ደንብ ከያዛቸው ድንጋጌዎች መካከልም፣ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች የተዛባ መረጃ ከማሠራጨት ራሳቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው፣ ራሳቸው ያላዘጋጁትንና ኃላፊነት መውሰድ የማይችሉበትን ከአንድ ወደ ሌላው የሚተላለፍ መረጃን በመቀነስ ወይም በመጨመር ማጋራት እንደሌለባቸው፣ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ጋዜጠኞች ጥቅሶችን ወይም ተቆርጠው የተወሰዱ ድምፆችንና ምሥሎችን ሲጠቀሙ ጉዳዩ መጀመርያ የቀረበበትን ዓውድ መጠበቅና የመጀመርያውን ቃና ሳይለውጥ ለማስተላለፍ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ይገኝበታል።

በተጨማሪም የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ጋዜጠኞች ሐሰተኛ፣ አሳሳች፣ የተዛቡና የጥላቻ ንግግሮች በሌሎች ቻናሎች ስለመታተሙ ወይም ስለመሠራጨቱ ሲታወቅ የተሠራውን ስህተት ማጋለጥና ትክክለኛውን መረጃ በተቻለ ፍጥነት ማቅረብ እንዳለባቸው፣ እንዲሁም የበይነ መረብ አዘጋጆች ተጠቃሚዎች ለሚያቀርቡት ቅሬታ ምላሽ መስጠትና በገጻቸው ላይ ማተም እንዳለባቸው ደንቡ ያመለክታል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...