Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከአፋርና ሶማሌ ክልሎች ለተፈናቀሉ አስቸኳይ ዕርዳታ እየቀረበ አለመሆኑ ተገለጸ

ከአፋርና ሶማሌ ክልሎች ለተፈናቀሉ አስቸኳይ ዕርዳታ እየቀረበ አለመሆኑ ተገለጸ

ቀን:

በአፋርና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠሩ ተደጋጋሚ የወሰን ግጭቶች ለተፈናቀሉና ቁጥራቸው እየጨመረ ላሉ ዜጎች፣ በቂ ዕርዳታ እየቀረበ አለመሆኑ ተነገረ፡፡ ከ13 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች የተጠለሉበት የሶማሌ ክልል ኤረር ወረዳ፣ ተፈናቃዮቹ ከዝናብና ከፀሐይ መጠለያ ላስቲክ ጭምር እየተቸገሩ መሆኑን አስታውቋል፡፡

አስካ፣ አስቡሊና ኤረር ከተማ ባሉ በሦስት መጠለያዎች በርካታ ሕፃናትና ሴቶችን ጨምሮ ከ13 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች እንደሚኖሩ ወረዳው ገልጿል፡፡ እስካሁን ከፌዴራል መንግሥት ዕርዳታ እየቀረበ አለመሆኑን የጠቀሰው ወረዳው፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራምና የሶማሌ ክልል መንግሥት ብቻ እየተረባረቡ መሆኑን አክሏል፡፡

የተፈናቃዮቹ ቁጥር እየጨመረ መሆኑንና ከዝናብና ከብርድ የሚጠለሉበት ላስቲክ እንኳ መቸገራቸውን፣ የኤረር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባስ ዩሱፍ ተናግረዋል፡፡ በአካባቢው በአሁኑ ጊዜ ከባድ ዝናብ እየጣለ መሆኑን ገልጸው፣ አጣዳፊ ዕርዳታ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

‹‹ተፈናቃዮች ወደ ወረዳችን መስፈር ከጀመሩ ዓመት አልፏቸዋል፡፡ ከሁለት ሳምንታት በፊት የመጡ አሉ፡፡ ክልሉ በራሱ አቅም ዕርዳታ ለማቅረብ እየሞከረ ነው፡፡ የዓለም ምግብ ፕሮግራምም የስንዴ ዕርዳታ ያቀርባል፡፡ ሆኖም የሚቀርበው ዕርዳታ ቁጥራቸው እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር የሚጣጣም አይደለም፡፡ የዝናብ ወቅት መምጣቱ ደግሞ ሁኔታውን አክብዶታል፤›› ሲሉ ነው ተፈናቃዮቹ ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ የገለጹት፡፡

የአፋርና የሶማሌ ክልሎች የወሰን አካባቢ ግጭቶች በየጊዜው እንደሚያገረሹ አስተዳዳሪው አቶ አባስ ይናገራሉ፡፡ የሁለቱ ክልሎች ኃይሎች ከሚጋጩባቸው አጨቃጫቂ አካባቢዎች እስከ 20 ኪሎ ሜትር ወደኋላ ተመልሰው እንዲቆሙ በፌዴራል መንግሥቱ ታዞ ዕርቅ የወረደ ቢሆንም፣ ከስምምነቱ በኋላም በየጊዜው ግጭቶች መፈጠራቸውን ገልጸዋል፡፡

በኤረር ወረዳ ቤት ንብረታቸውን በግጭት አጥተው ከተጠለሉት መካከል፣ እስከ ሰባት ልጆች ያሏቸው እናቶች መኖራቸውን አቶ አባስ አስረድተዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥቱና የሚመለከታቸው ወገኖች አጣዳፊ የሰብዓዊ ረድኤቶችን እንዲያቀርቡ የጠየቁት አስተዳዳሪው፣ በዘላቂነት ደግሞ ግጭቱን በማስቆም ወደ መደበኛ መኖሪያቸው በመመለስ እንዲቋቋሙ እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡

የአፋርና የሶማሌ ክልሎች በሚዋስኗቸው አካባቢዎች በቅርብ ዓመታት ተደጋጋሚ ግጭቶች የተከሰቱ ሲሆን፣ በፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ገብነት ግጭቶቹን ለማርገብ ተደጋጋሚ ጥረቶች መደረጋቸው ይታወሳል፡፡

ሁለቱ ክልሎች በዋናነት አዳይቱ፣ ገዋኔና ገዳማይቱ በሚባሉ የወሰን አካባቢዎች ይገባኛል የተነሳ ግጭት ውስጥ መግባታቸው አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...