Friday, March 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊዜጎች የተፈተኑበት የኑሮ ውድነት

ዜጎች የተፈተኑበት የኑሮ ውድነት

ቀን:

በኢትዮጵያ በየጊዜው እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት የበርካታ ዜጎችን አቅም እያሳጣ ነው፡፡ በተለይ በምግብ ነክ ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ በየጊዜው የሚደረገው የዋጋ ጭማሪ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች እየፈተነ ይገኛል፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ ከመሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች እስከ ሌሎች ቁሳቁሶች ድረስ የዋጋ ግሽበቱ በየጊዜው እየጨረ ቢሆንም፣ የአብዛኛው ኅብረተሰብ ገቢ ወይም የመግዛት አቅም ከዋጋ ግሽበቱ ጋር የሚጣጣም አለመሆኑ የማኅበረሰቡን ህልውና ፈትኖታል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሸማቹን እየፈተነ ያለውን የኑሮ ውድነት አባብሰውታል ተብለው ከሚጠቀሱ ምክንያቶች፣ ብልሹ የሆነ የግብይት ሥርዓትና ሥነ ምግባር የሌለው የንግድ አሠራርና ጣልቃ ገብነት እንደሆነም ምሁራን በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡

በተለይ በቅርቡ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ዘይት፣ ፓስታ፣ መኮሮኒ፣ ስኳር፣ ዳቦ፣ አትክልትና ሌሎች መሰል ምግቦች ላይ ጭማሪ መታየቱ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብን እያማረረ ለመሆኑ ብዙ ማሳያዎች አሉ፡፡

በከተማዋ ለስርቆት፣ አለመግባባት፣ ለተለያዩ ወንጀሎችም ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ይታመናል፡፡  ለጦርነት፣ ለድርቅ፣ ለውጭ ተፅዕኖና ለተለያዩ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ባለመበጀቱ፣ የኑሮ ውድነቱ ቅጥ ያጣ፣ መቆሚያ የሌለውና አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ከማድረጉም በላይ፣ ዜጎች ወደ ጎዳና እንዲወጡ እያደረገ ነው፡፡ በእነዚህ ችግሮች ገፈት ቀማሽ የሆኑት አነስተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች ናቸው፡፡

የኑሮ ውድነት ለስቃይ ከዳረጋቸው መካከል ወ/ሮ ጌጤ ገብረ ማርያም ይገኙበታል፡፡ ወ/ሮ ጌጤ በአዲስ ሠፈር አካባቢ ከሌሊት 7፡00 ሰዓት ጀምሮ ፓስቲ (ቆቀር)፣ አምባሻና ሻይ ለታክሲ ሾፌሮችና ለሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች በመሸጥ መኖር ከጀመሩ ሰባት ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡

ከባለቤታቸው አምስት ልጆችን ያፈሩት ወ/ሮ ጌጤ፣ የልጆቻቸውን የዕለት ጉርስ ለመሙላት ደፋ ቀና ቢሉም፣ አሁን ላይ እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት አንገታቸውን እንዳስደፋ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡  

ከዚህ በፊት ፓስቲ፣ አምባሻና ሻይ ሸጠው በሚያገኙት ገንዘብ ከዕለት ጉርስ ውጪ በመጠኑም ቢሆን የልጆቻቸውን ቀዳዳ እንደሚሸፍኑ የሚናገሩት እኚህ እናት፣ በአሁኑ ወቅት ባለቤታቸው ሥራ ፈትቶ ቁጭ በማለቱ የተነሳ የቤት ኪራይ ለመክፈል እንኳን እንደሚቸገሩ ይናገራሉ፡፡

በተለይ ብርድና ፀሐይ ተፈራርቆባቸው የሚያመጡት ገንዘብ ዋጋ ቢስ እንደሆነባቸው፣ ባለቤታቸውም ከዚህ ቀደም መንገድ ላይ ሸራ ዘርግተው የወንዶችና የሴቶች ልብሶችን ይሸጥ ስለነበር በተወሰነ መልኩ ያግዛቸው እንደነበር፣ ሆኖም አሁን ላይ ሕገወጥ ተብለው እንደማይሠሩ አስታውሰዋል፡፡

ባለቤታቸው መንገድ ላይ ነግደው የሚያገኘውን ገንዘብ ጨማምረው ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ ሽሮና ሌሎች ምግብ ነክ የሆኑ አስቤዛዎችን በመሸመት ኑሯቸውን ይገፉ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት አምስቱም ልጆቻቸው ተማሪዎች መሆናቸውን፣ ለመማሪያ የሚሆናቸውን ግብዓት መንግሥት ቢሸፍንላቸውም፣ ለምግብና አልፎ አልፎ ሚቀይሩትን ብጣሽ ጨርቅ ለመግዛት መቸገራቸውን ወ/ሮ ጌጤ ያስረዳሉ፡፡

‹‹የኑሮ ውድነቱ በዚህ ከቀጠለ አብዛኛው ሰው ጎዳና ለመውጣት ይገደዳል፤›› የሚሉት እኚህ እናት፣ መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ችግሩን ማስቆም ይኖርበታ ይላሉ፡፡ በተለይ የዚህ ችግር ገፈት ቀማሽ የሆኑት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች መሆናቸው ችግሩን ይበልጥ አጉልቶታል ሲሉ ይናገራሉ፡፡

ከዚህ በፊት ሃምሳ ኪሎ ጤፍ፣ ሃምሳ ኪሎ ስንዴ አስፈጭተው ወሩን ሙሉ አብቃቅተው እንደሚጠቀሙ፣ አሁን ላይ ግን ነገሩ ሁሉ የተገላቢጦሽ እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ በቀን መቶ ፓስቲ፣ አምባሻና ቆቆር ሸጠው እንደሚጨርሱና ከእያንዳንዱ ሁለት ብር ትርፍ እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡ ባገኙትም ትርፍ የልጆቻቸውን የዕለት ጉርስ እንደሚሸፍኑ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜም እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት ለከፋ ችግር እንዳያጋልጣቸው ሥጋት እንዳደረባቸው ለሪፖርተር ያስረዳሉ፡፡

ሌላዋ የጡረታ አበል እየጠበቁ ኑሯቸውን እየገፉ ያሉት ወ/ሮ እቴነሽ ዓለሙ እንደሚሉት፣ በተለያዩ ጊዜያት እየጨመረ የመጣው የኑሮ ውድነት የነዋሪዎችን አቅል አስቷል፡፡   

3,000 የጡረታ አበል እየተከፈላቸው መኖር ከጀመሩ ረዥም ጊዜ ሆኗቸዋል፡፡ በየወሩም የሚከፈላቸው ገንዘብ ሁለት ልጆቻቸውን ለማሳደግ ቀርቶ፣ የእሳቸውን ፍላጎት እንኳን በቅጡ እንደማያሟላላቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጤፍ፣ በስንዴ፣ በፓስታ፣ በመኮሮኒ፣ በዘይትና በሌሎች ግብዓቶች ላይ የተደረገው ጭማሪ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሰዎች ፈተና ሆኗል ይላሉ፡፡

ከዚህ በፊት የተሻለ የሚባል ኑሮ ይኖሩ እንደነበር፣ ባለቤታቸውን በሞት ካጡ በኋላ ግን ሁለት ልጆቻቸውን ለማሳደግ መከራ ማየታቸውን ይናገራሉ፡፡ ከምንም በላይ በቀበሌ ቤት ውስጥ መኖራቸው በተወሰነ መልኩ የኑሮ ሁኔታቸውን የተሻለ ቢያደርገውም፣ የልጆቻቸውን የዕለት ጉርስ ለመሙላት ግን መጠለያ ብቻ በቂ አይደለም በማለት ያስረዳሉ፡፡

በየወሩ በሚያገኙት 3,000 ብር አንዱን ከአንዱ ሲያደርጉ ገንዘቡ  እንደሚያልቅ፣ ከዚህ በፊትም ከእነ ልጆቻቸው ጭምር የሚላስ የሚቀመስ ነገር አጥተው ልመና መውጣታቸውን ይናገራሉ፡፡

በአሁኑ ወቅትም እየታየ ያለውን የኑሮ ውድነት ተደምሮበት ችግር ላይ መውደቃቸውን፣ አንዱ ልጃቸውም ትምህርቱን አቋርጦ ተባራሪ ሥራ እየሠራ መሆኑን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

እሳቸውም ተሯሩጠው እንዳይሠሩ የደም ግፊትና የስኳር በሽታ ተጠቂ መሆናቸውን የሚናገሩት እኚህ እናት፣ መንግሥት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ችግሮቻቸውን በመረዳት መታደግ ይኖርበታል ይላሉ፡፡

በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚበዛው ሥራ አጥና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኝ የማኅበረሰብ ክፍል መሆኑ ችግሩን እንዳባባሰው ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በፊት አብዛኛውን ጊዜ የኑሮ ውድነትን የሚያባብሱ ነገሮች ሲፈጠሩ መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሰጥ፣ ይህም በሌሎች ዓለም አገሮች ላይ የተለመደ መሆኑን ወ/ሮ እቴነሽ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት በዚሁ ከቀጠለ አብዛኛው ሰው ለከፋ ችግር እንደሚጋለጥና ጎዳና ወጥቶ መለመንን አማራጭ እንደሚያደርግ ያስረዳሉ፡፡

በተመሳሳይ ዱባና ወይራ በመሸጥ አንድ ልጃቸውን የሚያሳድጉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ እናት እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለምግብነት የሚውሉ ግብዓቶች ላይ የሚጨመረው ዋጋ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ያማከለ አይደለም፡፡

ከባለቤታቸው ጋር ተፋተው መኖር ከጀመሩ ሰባት ዓመታት ያስቆጠሩት እኚህ እናት፣ የኑሮ ውድነቱ በዚሁ ከቀጠለ አንድ ልጃቸውን ይዘው ወደ ቤተሰባቸው ለመቀላቀል ዕቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ከባለቤታቸው ጋር እያሉ ሦስት ልጆችን አፍርተው ሁለቱ እንደሞቱባቸው፣ አሁን ላይ አብሯቸው አንድ ሴት ልጅ ብቻ እንደቀረቻቸውና እሷንም ለማሳደግ ቀኑን ሙሉ ወይራና ዱባ ለመሸጥ ገበያ እንደሚውሉ ይናገራሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት እየሸጡ በሚያገኙት ገንዘብ የልጃቸውንና የእሳቸውን የዕለት ጉርስ ከመሙላት ባለፈ፣ ለልጃቸው መሠረታዊ የሚባል ፍላጎቷን እንኳን እያሟሉ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

በተለይም ምግብ ነክ የሆኑ ነገሮች ላይ እየታየ ያለው ጭማሪ ምሬት ውስጥ እንደከተታቸው፣ አንዳንድ ጊዜም ልጃቸውን አስቀምጠው መጥፋት እንደሚመኙ ይናገራሉ፡፡ ‹‹አሁን ላይ ለሰው ልጆች የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮችን መመገብ ቅንጦት ከሆነ ሰነባብቷል፤›› የሚሉት እኚህ እናት፣ በዚህ የተነሳ ‹‹መንግሥት አገር ውስጥ አለ ብዬ እንዳላምን አድርጎኛል፤›› ብለዋል፡፡    

የስታትስቲክስ አገልግሎት ይፋ ባደረገው ሪፖርት፣ በጥር 2015 ዓ.ም. በአንዳንድ እህሎች ማለትም ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስና ማሽላ ላይ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል፡፡ ቀይ ሽንኩርት፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ጥቅል ጎመን፣ ቲማቲምና ከውጭ የሚገባው የምግብ ዘይት፣ ቡናና ለስላሳ መጠጦች ላይ መጠነኛ ቅናሽ አሳይቶ ነበር፡፡

በ2015 ዓ.ም. በየካቲት ወር ከምግብ ምርቶች በተጨማሪ ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች ማለትም ልብስና ጫማ፣ የቤት ጥገና ዕቃዎች፣ ነዳጅ፣ ጫትና የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ጭማሪ እንዳሳዩና የምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር የዋጋ ግሽበቱ ጭማሪዎች የተስተዋሉበት ሆኗል፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ በሚሰጡት ምክረ ሐሳብ መሠረት፣ በአገሪቱ አኃዙን እየጨመረ የመጣውን የዋጋ ግሽበትና መዘዞቹን ለማስወገድ በአምራቹና በሸማቹ መካከል የአቅርቦት ሰንሰለቶችን ማጥበብ ዋነኛው ዘዴ ነው፡፡

ይሁን እንጂ የስታቲስቲክስ አገልግሎት ሪፖርት ከወጣ በኋላ፣ በአገሪቱ እህል ነክ በሆኑ ነገሮች ላይም ሆነ በሸቀጣ ሸቀጦች ላይ ጭማሪ መታየቱን ሪፖርተር መመልከት ችሏል፡፡

እስከ 45.00 ብር ይሸጥ የነበረ አንድ ፓስታ (500) ግራም ከ65.00 እስከ 70.00 ብር፣ መኮሮኒ በኪሎ ከ90.00 እስከ 100.00 ብር፣ ነጭ ሽንኩርት በኪሎ 260.00 ብር፣ ካሮት፣ ድንችና ጥቅል ጎመን ከ35.00 እስከ 40.00 ብር በኪሎ፣ ጤፍ መንግሥት በኅብረት ሥራ ሸማቾች በኩል በኪሎ ከ55.00 እስከ 65.00 ብር አቅርቤያለሁ ቢልም፣ በወፍጮ ቤቶችና ጤፍ በተሻለ ሁኔታ በሚገኝባቸው ገበያዎች በኪሎ እስከ 90.00 ብር ስንዴ በኪሎ 60.00 ብር፣ ከጤፍ ጋር ተቀላቅሎ የሚፈጭ ሩዝ ከ70.00 እስከ 75.00 ብር በኪሎ፣ በቆሎ በኪሎ 40.00 ብር መሆኑን መታዘብ ችለናል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...