Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ፅናት!

ሰላም! ሰላም! ይኼውላችሁ ባለፈው ሰሞን ለተወሰኑ ቀናት ሠፈራችን መብራትና ውኃ ተያይዘው ጠፍተው ጉድ ሲባል ሰነበተ። ውኃና መብራት ሲጠፋ ግድ የሚለንን ያህል አገር አስፈሪ ሁኔታ ውስጥ ስትገባ ግን ጉድ የማንል አለን። እናም ስንት አገሩን የዘነጋ በአቋራጭ ከብሮ ከሹም ጋር አበልጅ የሆነ እያለ፣ ስንት ሥራችሁ ያውጣችሁ ብሎ እንደ ሰደድ እሳት ለሚጋረፈው ከባድ የኑሮ ውድነት የዳረገን ሹም እያለ፣ ስንት በሹመኛ ጥላቻ ብቻ አገሩ ላይ ጀርባውን ያዞረ እያለ ውኃና መብራት ጠፋ ብለን ስንነፋረቅ ይነደኛል፡፡ ውኃውም ሆነ መብራቱ በአስተማማኝነት የሚገኘው አገር ስትኖር ነው የሚለውን ቁምነገር በቅጥ ከሚያዳምጥ ይልቅ፣ ምንጩ ከየት እንደሆነ በማይታወቅ ትልቅ ገንዘብ በገዛው አይፎን ወይም ሳምሰንግ ጋላክሲ ጌም ላይ የሚመሰጥ መብዛቱ ድንቅ ይለኛል፡፡ ኧረ ጉድ ነው ዘንድሮስ፡፡ ስንት የወዳደቀ ነገራችንን ሳናነሳና ሳናስተካክል በማይረባ ጉዳይ የምናጠፋው ገንዘብ፣ ጊዜና ጉልበት ያሳዝነኛል። ውሎ ሳያድር ደግሞ አዛውንቱ ባሻዬ የውኃና የመብራት ችግሩን በተመለከተ የተጠራውን የመንደር ስብሰባ እንዲመሩ የቀረበላቸውን ጥያቄ ውድቅ አደረጉ ተባለ። ‹እኔ በመንግሥት ሥራ አልገባም› አሉ ተብሎ ተዋራ። ገሚሱ ‹ደግ አደረጉ!› ሲላቸው ገሚሱ፣ ‹ችግራችን እንዴት አያሳስባቸውም?› ብሎ ተቀየማቸው ተባለ። ይኼ ለድጋፍና ለተቃውሞ መጣደፍ የሚለቀን ግን መቼ ይሆን? እንጃ!

ስለስብሰባው የሰሙ ዲግሪ ጭነዋል የተባሉ ወጣቶች ደግሞ ሥራ ፈልግልን እያሉ አላስቆም አላስቀምጥ ብለውኛል፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ ደግሞ ሕገወጥ ደላላ ሊሉኝ እኮ ነው፡፡ ‹ውኃንም ሆነ መብራትን እኮ አምላክ አይቆጣጠረውም… በአገረ መንግሥት ግንባታ ደካማ በመሆናችን… ቅብጥርሶ…› ብለው ኧረ የት ሄደን ተግባር ላይ እናውለው እያሉ የሚንገዋለሉበትን የዕውቀት ጫና ባሻዬ ላይ ለማራገፍ መጣጣራቸው ተሰማ። ‘ዕውቀት ሲበዛ አመድ ዱቄት ነው ያስብላል’ ያለው ማን ነበር? ጠፋኝ ብቻ። ተብሎ ተብሎ የስብሰባውን ‘ሪፖርት’ በአጭሩ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ሲያጫውተኝ ቧልተኞች ተናገሩት የተባለው ቀልቤን ስቦት ነበር። ምን አሉ አትሉም? ‹በየቦታው እህል ከተማ እንዳይገባ መንገድ እየተዘጋበት ነው የሚል ወሬ በየአቅጣጫው የሚሰማበት ሰሞን ስለሆነ እስኪ ትንሽ እንታገስ? መንገድ ዘጊዎችም ልቦና አግኝተው ሲሰክኑ ይሆናል…› አሉ ብሎ አጫወተኝ። ጆሮአችን ከተደገነ እኮ ወሬ በሽ ነው!

ወዲያው የስብሰባው አጀንዳ ፖለቲካዊ ሆነ አሉ። ገሚሱ፣ ‹ተው እንጂ እናንተ፣ ደግሞ እንደ ፈረንጅ ልታደርጉን ነው እንዴ ልትሉ ነው? ኧረ በሰላም እንኑርበት…› እያለ ሲርበተበት ሌላው፣ ‹እኛ ሳንሰማ ሁሉም ነገር የመንግሥት ሆነ እንዴ?› እያለ ተንሾካሾከ። በበኩሌ ከሁሉ ከሁሉ የሚገርመኝ ይኼ ‘አንዳንድ’ የሚባሉ ነዋሪዎች ትልም ነው። ቴሌቪዥኑም እነዚህን አንዳንድ ነዋሪዎች የሚያጠምድበት ዘዴና በአንድ ዓይነት ልሳን እንዲያወሩ የት እንደሚያሠለጥናቸው የሚጠቀምበት ሥልት ይገርማል ይባባሉ። በተቸገርንባቸው ነገሮች መፍትሔ የምንለውን ከማቅረብ ደግሞ ፎክሮና ተመፃድቆ የመለያየት አባዜያችን፣ እንደ አንዳንድ ባለምጡቅ ዓይነት ‘ጂኒየስ’ ዜጎች በዝተውልን ችግራችንን ሊፈቱልን እንደሚችሉ አያወያየንም። መቼም ይኼ ምሳሌ ይገባችኋል፡፡ ወድጄ አይደለም የምሙለጨለጭባችሁ፡፡ ተግባባን አይደል!

ነገርን ነገር ያነሳዋል። ለነገረኛም ነገረኛ ያዝለታል። አላዝልን እያለ የተቸገርነው በበሽታችን ልክ መድኃኒት ብቻ ነው። ‹‹በሽተኛው በዛ መድኃኒት አነሰው…›› ያለው ዘፋኙ ወዶ መሰላችሁ? ‘ማንም የወደደውን ያገባና የዘፈነ የለም’ እንዳትሉኝና እንዳልስቅ። ውዷ ማንጠግቦሽ ሰሞኑን በገባች በወጣች ቁጥር፣ ‹‹አንተ ሰውዬ በዚህ ኑሮው እንደ እሳት በሚጋረፍበት ጊዜ ወሬህን ትተህ ሥራህ ላይ አተኩር…›› ስትለኝ እኔ ደግሞ ‘ይህ ማሳሰቢያ መልዕክት ይኖረው ይሆን? ያለንበት ጊዜ እያስፈራት እየነገረችኝ ይሆን?’ እያልኩ መጨነቅ። በዚህ የተነሳም በወጣሁ በገባሁ ቁጥር የባንክ ደብተሬ ወጪና ገቢ ላይ ማፍጠጥ። ግን ለምንድነው ዘንድሮ የወር ቀለብም ሆነ የዓመት ልብስ ሲታሰብ ከፍተኛ ድካም የሚተርፈን? የኢኮኖሚው መዝቀጥ ማሳያ ይሆን እንዴ? ቢጨንቀኝ እኮ ነው የምጠይቃችሁ። በኋላ ታዲያ አስቤ አስቤ ሲደክመኝ ምሁሩን የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ምን አባቴ ባደርግ ይሻለኛል?›› ብዬ ማማከር። ምን ይለኛል፣ ‹‹ቆይ ትንሽ ታገስ ማንጠግቦሽ ብቻ አይደለችም ይህ ሥጋት የሚንጣት። ችግሩ የአገሩ ሁሉ ነው…›› አለኝ። እውነት ነው፣ ሁሉም ሰው ፊት ላይ የሚነበበው ችግር ነው፡፡ ያስፈራል!

አገር የምታድገው በወሬ አይደለም ሲባል በተደጋጋሚ ሰምተናል፡፡ እኔ የዋሁ በቃ ነዳጅ ነው የሚያስፈልገን ብዬ ምሁሩን የባሻዬ ልጅን፣ ‹‹ታዲያ ምነው ነዳጃችንን በቶሎ አውጥተን በሀብት የማንንበሸበሸው?›› ስለው፣ ‹‹ከነዳጅ በላይ ብዙ ሀብት አለን፡፡ ከሠራንበት በቱሪዝም ብቻ የትና የት መድረስ እንችላለን፡፡ ማዕድናቶቻችን ተዝቀው አያልቁም፡፡ ውኃ ብትል መሬት፣ ወጣት ብትል ታዳጊ ሞልቶናል፡፡ የጎደለን አርቆ ማሰብ ነው…›› አይለኝ መሰላችሁ? ጉድ እኮ ነው እናንተ፡፡ ‹‹እኔ እኮ በነዳጅ ብቻ የምንከብር መስሎኝ ነው…›› እለዋለሁ፣ ‹‹ተው እንጂ አዕምሮህን አሠራው…›› ብሎ ተቆጣኝ። ኧረ እንዴት ነው ነገሩ? ይኼ ዓለም እያደር የህልም ሆነ እኮ ጎበዝ፡፡ እኔማ እጄ ላይ ያለውን ገንዘብ ስለመቆጠብ እንጂ፣ ሠርቼበት የበለጠ ለማትረፍና ሥራ ለመፍጠር አስቤበት አለማወቄ ቆጨኝ፡፡ እኛ ደግሞ ካጠፋን በኋላ ሲቆጨን እንጂ ሌሎች የፈጸሙትን ስህተት ላለመድገም አንጠነቀቅም፡፡ እኔም ራሴን እወቅሳለሁ፡፡ ‹‹አምስት ሺሕ ብር ያለው ቁጠባ የሚጀምረው አምስት ብር ሲቀረው ነው…›› የሚሉኝን ባሻዬን እያሰብኩ ራስን መውቀስ መልካም መሰለኝ፡፡ ምን ይደረግ ታዲያ!

ከሥራ የሚበልጥ የለም ብዬ ሁሉንም ነገር ትቼ እንደ ወትሮዬ ወደ ድለላዬ ሮጥኩ። አንድ ደንበኛዬ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ መኪኖች አስመጪ ጋር እንዳገናኘው ስለጠየቀኝ ወዲያው ደዋውዬ አገናኘኋቸው። ስለሚጫኑት የመኪና ዓይነቶች ለቀናት በፅሞና ተነጋገሩ። ያው ዘመኑ የሚሊዮኖች ነውና የምትሰሙዋቸው ቁጥሮች በጠቅላላ ባለሰባት ‘ዲጂት’ ናቸው። እኔን የሚገርመኝ ታዲያ ውስን ግለሰቦች ሰባት ‘ዲጂት’ እያገላበጡ ሥራ ሲሠሩ፣ እኛ ብዙኃኑ ደግሞ ከወሬው ቀንሰን ገንዘብ ማሳደዱን መልመድ አለመቻላችን ይገርመኛል። እውነቴን እኮ ነው። አንድ ወዳጄን እንዲህ ስለው፣ ‹‹ሀብታሞችና ባለሥልጣናት እየተናበቡ የሚሠሩበት ሥራ ውስጥ ማን ያስደርስሃል…›› አለኝ። ስለህልውናችን ለመፈላሰፍ ከተፈለገ እኮ እኛም እንብሳለን። በአንድ ወቅት አንዱ፣ ‹‹አንበርብር ምንተስኖት በሚባለው ስምህ ብትታወቅም፣ ማንጠግቦሽ የምትባል ቆንጆ ሚስት ብትኖርህም፣ ባሻዬ የሚባሉ የተከበሩ አዛውንት ጎረቤትህ ቡና ቢያጣጡህም፣ ከምሁሩ ልጃቸው ጋር ቅርበትህ እስከ ግሮሰሪ ቢዘልቅም ለሀብታሞቹ ኢምንት ነህ…›› ብሎ ጭር ካደረገኝ በኋላ በሰው ተስፋ ቆርጫለሁ ብዬ አስብና እተወዋለሁ፡፡ መተው ይሻላል፡፡

ሌላው ወዳጄ የምለው ደግሞ የተለየ አባዜ ነው ያለበት፡፡ ብዙ ጊዜ ይህንን ሰው ስታዘብ ይገርማችኋል ታላላቅ አገራዊ ጉዳዮች ተነስቶ እየተወራ፣ ነገር ማብራራት የሚቀናው በሥጋና ምግብ ነክ በሆኑ ቅመማ ቅመሞች ነው። የአማልክት ስም ጠርቶ ምፅዋት ከሚጠይቀው የእኔ ብጤ ይልቅ፣ ‘ፍየሎቼ አልቀው፣ በሬዎቼ ሞተው ተሰድጄ ነው’ ላለው መዥረጥ አድርጎ ባለሁለት መቶውን ብር በጭብጥ ይመፀውታል። አንዳንዴ የምናውቀውን ሰው በሌለበት ስንሸረድድ፣ ‹‹ቁርጥ አትቁረጡና ከሰው ተቆራረጡ…›› ብሎ ያፌዝብናል። ግን መቆራረጥ ከአፈጣጠራችን ሳይሆን ከምናዘወትረው አመጋገብ የተነሳ ይሆን እንዴ? አለመተማመን፣ ለራስ ወገን ማድላት፣ አገርንና ሕዝብን በንብረቱና በጥቅሙ መበደል ምንጩ ከምንጎርሳት ጉርሻ አቀማመም ጋር ግንኙነት እንዳለውስ? በሚሊዮን እየተጫወትን ዝርዝር ሳንቲም ብቻ ኪሳቸው ውስጥ ያለውን ችላ የምንልበት ምክንያቱም እኮ ከጉርሻችን ጋር አብሮ መጠናት አለበት። አይደለም እንዴ? ‘ኤግዛክትሊ!’ በሉ እንጂ፡፡ እንዲህም እንኖራለን ለማለት ነው!

እናላችሁ በቅርቡ የኤሌክትሪክ መኪኖች አስመጥቶ ከሚሸጠው ደንበኛዬ ጠቀም ያለ ‘ኮሚሽን’ እጄ እንደሚገባ እያሰብኩ፣ ራሴን በተመለከተ አንዳንድ የ‹ሪፎርም› ዕቅድ መተለም ጀመርኩ። ካፖርቴ ስለነተበ ቅያሪ ያስፈልገዋል። የጫማዎቼ ሶሎች አልቀዋል። እግሬ እስኪቀጥን እየተጓዝኩ ዳሩ ቀድሞኝ የሚያልቀው ጫማዬ እየሆነ ተቸግሬያለሁ። ለሁሉም ‘ሾፒንግ’ ያስፈልገኛል። እናም አንድ የልብስና የጫማ ሱቅ ዘው ብዬ ገባሁ። ‹‹ይኼ ጫማ ዋጋው ስንት ነው?›› ብዬ ከመጠየቄ ደንበኛ ለማስተናገድ ሳይሆን ደመኛ ለማፍራት የተቀጠረች የምትመስል ገጿን አጨፍግጋ፣ ‹‹አሥራ ሁለት ሺሕ…›› አለችኝ። ‹‹አቤት?›› የምር አልሰማኋትም። አንዳንዴ እኮ አይሰማችሁም። ‹‹አሥራ ሁለት ሺሕ አልኩህ እኮ…›› ተነጫነጨች። የንጭንጯ ሰበቡ ገባኝ። በቀን አሥራ ሁለት ሺሕ ጊዜ ይኼን ጥሪ እየጠራች አንድም ሰው ሳይገዛት ስለሚሄድ መሆን አለበት አልኩ። ‹‹ቅያሪ አለው ማለት ነው?›› ታዲያ ምን ልበላት? ‹‹የምን ቅያሪ ጥንዱን ነው እንጂ፣ ከገዛህ መግዛት ነው…›› ብላ ፊቷን አዞረችብኝ። ሳለ ፈጣሪ የእሷ ፊት ምን ተዳዬ!

‹‹እሺ የስንት ዓመት ‘ጋራቲን’ አለው?›› ልላት ብዬ የስንትስ ዓመት ቢኖረው? አሁን ይኼን ጫማ አድርጌ የሠፈር ሰው ቢያየኝ ሠርቶ ገዛው ብሎ ያምነኛል ብዬ ተውኩት። በቃ ባዶዬን ከምወጣ ካልሲ ምናምን ልግዛ ብዬ ካልሲ ስጠይቃት አንድ ካልሲ 550 ብር ገብቷል። እንዲህ የሚረባውም የማይረባውም እየጨመረማ እኛም ብልጠት ሳንጨምር ‘ጉድ እያሉ መኖር’ አያዋጣንም አልኩና ስከንፍ መርካቶ ሄጄ ክርና ኪሮሽ ገዛሁ። አንገቷ ላይ ያለቀች ካፖርቴን አስገልብጬ ለማሰፋት ወስኜ ለሰፊ አቀበልኳት። ክርና ኪሮሹን ደግሞ ለማንጠግቦሽ ወስጄ ሰጠሁና ጊዜ ስታገኝ ካልሲ እንድትሠራልኝ ነገርኳት። ታዲያ በዚህ ኑሮ ላይ ‘ኢምፖርትድ’ ዕቃዎች እየሸመትን ‘ኤክስፖርት’ ለመደረግ ሳንበቃ ‘ኤክስፓየርድ’ እንሁን እንዴ? ከዚህ የተሻለ የ‘ሪፎርም’ ዕቅድ ያለው ሐሳቡን ‘ሼር’ ማድረግ ነው። ‘ፌስቡክን’ም ስንሰዳደብበት ከምንውል ለ‘ሪፎርም’ ዕቅዳችን መሳካት ብንጠቀምበት ጥሩ ነው። የእናንተን ባላውቅም እኔን ግን መስሎኛል፡፡ ኑሮ ተወደደ ብሎ ማማረር ብቻ ሳይሆን ወገብን ጠበቅ አድርጎ ለመጋፈጥ መዘጋጀት የግድ ነው፡፡ አለበለዚያ ማንም ሊታደገን ፈቃደኛ አይደለም፡፡ እውነቴን ነው!

በሉ እንሰነባበት። የሰሞኑ የበልግ ብርድ እየጨመረ ነው። ከብርዱ የኑሮ ውድነቱ ነገር ትዝ ብሎኝ ውስጤ እያረረ ፈገግ ስል ባሻዬ መንገድ ላይ አገኙኝ። ‹‹አንተንም ጀመረህ?›› አሉኝ ለሰላምታ እጃቸውን ዘርግተው። ‹‹ምኑ?›› አልኳቸው። ‹‹ለብቻ በሐሳብ መዋለሉ…›› ብለው ተራቸውን ፈገግ አሉ። እንዳልገባኝ ስነግራቸው፣ ‹‹እስኪ ወደ ቤቴ እየሸኘኸኝ እነግርሃለሁ…›› ብለውኝ አብረን መጓዝ ጀመርን። ‹‹እንዲያው ሕመሙና የጋራ ጥያቄው ሁሉ የወል፣ ማግኘቱና ማጣቱ፣ መታፈኑና መተንፈሱ፣ መጨነቅና መባዘኑ የሁላችንም የሕይወት አካል ሆኖ ሰው ብቻውን ሲተክዝ፣ ብቻውን ሲያወራ፣ ብቻውን ሲያብድ ሆኗል የማየው። አንተም እንደዚያው የሆንክ ስለመሰለኝ እኮ ነው…›› ሲሉኝ ያስፈገገኝን ነገር አጫወትኳቸው። አዛውንቱ ባሻዬ ከወትሮው በተለየ ከትከሻቸው ጎብጠው በረጂሙ ተንፍሰው፣ ‹‹አንበርብር?!›› አሉኝ። ‹‹አቤት!›› አልኳቸው። ‹‹ምን እንደ ሰለቸኝ ታውቃለህ?›› ሲሉኝ፣ ‹‹ምን ይሆን ባሻዬ?›› ስጓጓ እያዩኝ ጥቂት በሐሳብ ተጉዘው ቆይተው፣ ‹‹በማያንገዋልለው የሚንገዋለለው፣ በማይቸግረው የሚቸገረው ሰው ብዛት። እንዴ ምንድነው እንደዚህ ነገር ሰንጣቂው የበዛው? እንጨት እየሰነጠቁና እየላጉ ጎጆ የሚያጠብቅ ማገር መሥራት አይሻልም? በነፈሰው ሁሉ ሆ፣ በየቀኑ ጭፈራ፣ በየቀኑ ስላቅ፣ በየቀኑ ቧልት አይሰለችም እንዴ? ይህም አልዘልቅ ብሎ እርስ በርስ መጠማመድና መተናነቅ…›› ብለው ሳይጨርሱ ቤታቸው ደርሰን ነበር። ድንገት ቆም ብለው፣ ‹‹አደራ ለራስህም እያወቅክበት። ቁም ነገር ተረስቷል። ቢተች የማይሰለቸው፣ ቢዝት የማይደክመው ሰው በዝቷል። ሰውን ሰው ያደረገው ግን ሥራና ቁምነገር ነበር። ደህና እደር…›› ብለውኝ ቤታቸው ገቡ። ይሻላል!

እኔም ተለይቻቸው ስሄድ ሰውን በእርግጥ ሰው ስለሚያስብለው ነገር እያሰብኩ ነበር። የማሰብ መብታችንን ሳንጠቀምበት ለምን ለአፍ ወለምታ እንደምንቸኩልም ማሰብ ስለፈለግኩ ቶሎ ብዬ ወደ ቤቴ ስገባ ማንጠግቦሽ ኪሮሿን ይዛ ተቀምጣለች። ‹‹እንዲህ ነው እንጂ ሪፎርም!›› ስላት፣ ‹‹ገና ኤክስፖርት እናደርጋለን እባክህ፣ ይልቁንስ ሰው ለመሆን ከፈለግክ ሰውን ሰው ያደረገው ምን እንደሆነ ዕወቅ…›› ስትለኝ ግጥምጥሞሹ አስገረመኝ፡፡ ውኃ ልኩ ጠፋ እንጂ ይኼ መቼ ይጠፋናል? ከግጥምጥሞሹ ይልቅ እውነታው ላይ ብናተኩር ይበጀናል፡፡ እውነት ነፃ ያወጣል፣ ትውልድ ያንፃል፣ አገር ያሳድጋል፣ መግባባት ይፈጥራል፡፡ ከአገር በፊት ኖረው የማያውቁ እኛ ከሌለን አለቀላት ብለው ሲሳለቁ እረፉ መባል ነበረበት፡፡ ምክንያቱም ውሸታሞች ስለነበሩ፡፡ የጋራ ታሪክን ወደ ጎን ብለው ወገንን የሚያምሱ የግጭት ነጋዴዎችንም ማስቆም የምንችለው እውነትን ይዘን ነው፡፡ አገር አዋራጅ ሐሰተኞችን የምናሳፍረው በእውነት ነው፡፡ አገርን የማያከብር አክባሪ የለውም እንዲሉ፣ ለአገር ክብር ስንል በፅናት መቆምን ብንለማመድ ይሻለናል፣ ይበጀናልም፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት