Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየ‹ደብረ ዘይት› በዓል ከትግራይዋ ናዝሬት እስከ ምንጃርዋ ሳማ

የ‹ደብረ ዘይት› በዓል ከትግራይዋ ናዝሬት እስከ ምንጃርዋ ሳማ

ቀን:

ከቱሪዝም ልዩ ልዩ ዘርፎች መካከል ሃይማኖታዊ ቱሪዝም ተጠቃሽ ነው። ይኼው ዘርፍ መንፈሳዊ ቱሪዝም፣ የተቀደሰ ቱሪዝም ወይም የእምነት ቱሪዝም በመባልእንደሚጠራ፣ ሁለት ዓይነቶችም እንዳሉት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

አንደኛው ለሃይማኖታዊ ወይም ለመንፈሳዊ ዓላማ የሚደረግ ጉዞ (ንግደት/ሒያጅ/ሐጅ) ሲሆን፣ ሌላኛው የጉብኝት ቅርንጫፍ ሃይማኖታዊ ኪነ ሕንፃዎችንና ቅርሶችን መመልከት ነው። ሰዎች በግላቸው ሃይማኖተኛ ቢሆኑም ባይሆኑም የተቀደሱ ቦታዎችን ለመጎብኘት አይሰንፉም።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ታዋቂ ሃይማኖታዊ ቦታዎች ከሃይማኖታዊ ጠቀሜታቸው ባሻገር ከታሪካዊና አርኪኦሎጂያዊ ጠቀሜታቸው አንፃር በብዛት በመጎብኘት በዓለም ተዋውቀዋል። ለምሳሌ አክሱምና ላሊበላ፣ የመስቀልና ጥምቀት፣ ዓረፋና መውሊድ ያሉ ሃይማኖታዊ በዓላት ለሃይማኖታዊ ቱሪዝም ጠቀሜታቸው ጉልህ ነው።

በኦርቶዶክሳዊቷ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሚከበሩት በዓላት መካከል የጥምቀትና የመስቀል ክብረ በዓላት በመንግሥታቱ የባህል ድርጅት ዩኔስኮ የዓለም የሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ተብለው መመዝገባቸው ለመንፈሳዊው ቱሪዝም ልዕልና የራሱ የሆነ አስተዋጽዖ አለው፡፡

ለሃይማኖታዊ ቱሪዝም ማሳያነት ለምሳሌ ከብዙው በጥቂቱ አክሱም ከኅዳር ጽዮንና ሆሣዕና፣ ላሊበላ ከልደት፣ ጎንደር ከጥምቀት፣ አዲስ አበባ ከመስቀል ደመራ፣ ቁልቢና ሐዋሳ ከታኅሣሥ ገብርኤል እንጅባራ ከመርቆሬዎስ፣ ክብረ በዓላት ጋር ተያይዘው ይነሳሉ፡፡ እነዚህ በዓላት ፀሓያዊውን አቆጣጠር ስለሚከተሉ በቋሚ ቀናቸው ሁሌም ይከበራሉ፡፡

ዛሬ እሑድ መጋቢት 10 ቀን 2015 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን እያከበሩ ያሉት ‹ደብረ ዘይት› ተብሎ የሚታወቀው በዓል ነው፡፡ ይህም ከፋሲካ ጋር ስለሚያያዝ ቋሚ ቀን ሳይሆን ተንቀሳቃሽ ቀን ነው ያለው፡፡ የሚከተለውም የፀሓይና የጨረቃ ጥምር አቆጣጠር ነው፡፡

ኦርቶዶክሳውያኑ በየካቲት አጋማሽ የጀመሩት ታላቁን የሃምሳ አምስት ቀናት ጾማቸውን ዛሬ፣ ተእኩሌታው አድርሰውታል፡፡ ‹ዓቢይ ጾም› ተብሎ በኦርቶዶክሳዊቷ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት በባህረ ሐሳቧ አቆጣጠር መሠረት፣ ካሉት ስምንት እሑዶች አምስተኛው በ‹ደብረ ዘይት› ተሰይሟል፡፡

ደብረ ዘይት ትርጉሙ የወይራ ዛፍ ያለበት ተራራ ሲሆን፣ በእስራኤል መዲና ከኢየሩሳሌም በምሥራቅ አቅጣጫ የሚገኝ ነው። ስለዓለም ፍፃሜ/ ዳግም ምጽአት እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ ያስተማረበት በመሆኑ ዕለቱ ይታሰባል፡፡ ይህንን ዕለት በስድስተኛው ምታመት የኖረው ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ስለ ዳግም ምጽአት መዝሙር ደርሷል።

ደብረ ዘይት በምሥራቅ ኢየሩሳሌም የሚገኝ ኮረብታማ ሥፍራ ሲሆን፣ ስሙን ያገኘው ከሥፍራው በብዛት ከሚበቅለው የወይራ ዛፍ ነው፡፡ መጻሕፍት እንደሚነግሩን፣ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ የፀለየበት፣ ቅድስት ማርያም የተቀበረችበት፣ ጌቴሰማኒ የተባለውም የአትክልት ቦታ በዚህ ሥር ነው የሚገኘው፡፡ የደብረ ዘይት እሑድ የሚያስታውሰው እግዚእ በቦታው ስለዳግም ምጽአቱ ለጴጥሮስ፣ ለያዕቆብና ለዮሐንስ ያስተማረውን ነው፡፡

የእኩለ ጾም እሑድን ‹‹ደብረ ዘይት›› ብሎ የሰየመው የ6ኛ ክፍለ ዘመኑ ቅዱስ ያሬድ ሲሆን፣ የመዝሙሩ ርዕስም ‹‹እንዘ ይነብር እግዚእነ ውስተ ደብረ ዘይት›› (ጌታችን በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ) ነው፡፡

የዛሬው የደብረ ዘይት በዓል ከአገር ቤት እስከ በመላው ዓለም በሚገኙ የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያን የሚከበር ቢሆንም፣ በተለይ እንደ ሌሎች ተለይተው ከሚታወቁት የበዓላት ማክበሪያ ቦታዎችም ጉልህ ሥፍራ ያላቸው አሉ፡፡
‹በሰንበት ላይ ደብረ ዘይት› እንዲሉ በክብረ በዓሉ ላይ ለመገኘት ንግደት (መንፈሳዊ ጉዞ) ከሚደረግባቸው ቦታዎች መካከል በሰሜን ኢትዮጵያ የትግራይዋ ናዝሬት (ማርያም ናዝረ) እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ የምንጃርዋ ሳማ ሰንበት ይጠቀሳሉ፡፡

ስለሳማ ሰንበት የሚያወሳ አንድ መጽሔት እንደገለጸው፣ ሦስት መቶ ዓመታትን ያስቆጠረው ገዳሙ ከአዲስ አበባ በስተ ደቡብ ምሥራቅ 110 ኪሎ ሜትር ርቀት በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ዋና ከተማ ከአረርቲ 21 ኪሎ ሜትር ርቀት ሳማ ቀበሌ ይገኛል፡፡ በክብረ በዓሉ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን ይገኙበታል፡፡ ሳማ ሰንበት ከክብረ በዓሉ ባሻገር  ርካታ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶችን  ይዟል፡፡

ወረዳው በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳስታወቀው፣ ሳማ ሰንበት ከክብረ በዓሉ በተጨማሪ ብዙ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶችን አምቆ የያዘ ቦታ ነው፡፡ ከዚህ ገዳም በተጨማሪ በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ባልጪ አማኑኤል፣ ሸንኮራ ዮሐንስ፣ ዶፋ ሚካኤል፣

አረርቲ ደብረ ገነት ቅድስት ማሪያም፣ ጉራምባ ማሪያም ወዘተን የመሳሰሉ ሌሎች የቱሪስት መስህብ ቦታዎችም ይገኛሉ። ‹‹ማርያም ናዝረ›› የደብረ ዘይት በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው ቦታዎች አንዱ ከአንድ ሺሕ ዓመታት በላይ  ባስቆጠረችው ማርያም ናዝሬት ነው።

ማርያም ናዝረ (ናዝሬትን የአካባቢው ሰው የሚጠራበት) በደቡብ ምሥራቅ ትግራይ በህንጣሎ ዋጀራት ወረዳ ከማይ ነብሪ ከተማ በስተምሥራቅ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። ሩቅ በሆነው በዓዲ አቡን መንደር ውስጥ ጥንታዊው ቤተ ክርስቲያን ይገኛል። ቤተ ክርስቲያኒቱ በ14ኛው ክፍለ ዘመን በአፄ ዓምደ ጽዮን የተሠራች ናት።

የዘመነ አክሱም ኪነ ሕንፃዎች አሻራ ያቀፈው የማርያም ናዝሬት፣ በላስታ ላሊበላው የዛጉዌ ሥርወ መንግሥት ዘመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ጵጵስና የኮፕቲክ/ግብፅ ሊቃነ ጳጳሳት መቀመጫ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ቦታው ‹‹ዓዲ አቡን›› ተብሎ የሚጠራው፡፡

መሓሪ ሰሎሞን የአገርሽ ማግሌዎችን ጠቅሶ እንደ ጻፈው፣ ናዝረ የሚለው ቃል “ናዝሬት” ከሚባል ቃል የተገኘ ነው፡፡ አሰያየሙም ከአፄ ላሊበላ የሚያያዝ ታሪክ አለው፡፡ ላሊበላ ከመንገሡ በፊት ታላቅ ወንድሙ ሃርቤ ንጉሥ ነበረ። ከርሱ ጋር ባለመግባባቱ ላሊበላ ከባለቤቱ መስቀል ክብራ ጋር ሆኖ ዛሬ ዓዲ አቡን ተብሎ በሚታወቅ ከባቢ ይቀመጣሉ፡፡ ላሊባላ ወደ ኢየሩሳሌም ከመሄዱ በፊት ታማ የነበረችው መስቀል ክብራን እዚያው ትቷት ይሄዳል፡፡

ከረዥም ጊዜ በኋላ ሲመለስ ባለቤቱ በሕይወት ከቆየችው ፀበል እንዲሆናት፣ ከሞተችም ከመቃብሯ ላይ የሚበትነው አፈር ከጎሎጎታ፣ የሚያፈሰው ውኃ ከዮርዳኖስ ይዞ ይመጣል፡፡ ከአገሩ እንደደረሰ ግን ባለቤቱ በሰላም መቆየቷን እንዳወቀ ያመጣውነ አፈር ከዓዲ አቡን በሰሜን አቅጣጫ ሦስት ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ቦታ ይበትነዋል፡፡ የጎሎጎታን አፈር የበተነበት አካባቢ ደግሞ ‹‹ጎሎጎታ›› የሚል መጠሪያ ስም ያገኛል፡፡ ያመጣውን ውኃ ደግሞ ከማርያም ናዝረ አጠገብ በሚገኝ ወንዝ ያፈሰዋል። በመጨረሻም ባለቤቱ ተጠብቃ የቆየችበትን ቦታ ‹‹ሁለተኛዋ ናዝሬት›› ብሎ ይሰይማታል፡፡ ከጊዜ በኋላም ቦታው በተለምዶ ናዝረ እየተባለ መጠራት ጀመረ ይላሉ የአካባቢው ቀሳውስትና ሽማግሌዎች፡፡

‹‹ንዑ እዚ ድንቂ ነገር ረአዩ” (ኑ ይህን ድንቅ ነገር እዩ) በሚል መሪ ቃል ደብረ ዘይትን በማርያም ናዝረ ምዕመናን እንዲያከብሩ ጥሪ ያስተላለፉ በመቐለ የሚገኙ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡ በንግደቱ የሚጎበኙት 1,000 ዓመት ያስቆጠረ ያለ ስሚንቶ የተገነባ ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን፣ ትንቢት የተነገረለት ዳዕሮ (ዋርካ)፣ የአክሱማውያን የሥልጣኔ መገለጫ የሆኑ ጥንታዊያን ትኩል ድንጋዮችና ሌሎች ቅርሶች መሆናቸው ተመልክቷል።

የዕለቱ ልዩ ምግብ ‹‹በቆልት›› ዛሬ እኩለ ጾም ነው፡፡ ደብረ ዘይት ይባላል፡፡ ከትውፊት እንዳገኘነው፣ ዛሬ ከቁርስ በፊት የሚቀመሰው በቆልት ነው፡፡ ሰሞኑን በውኃ ውስጥ ተዘፍዝፎ የቆየው ባቄላ መብቀሉ ከተረጋገጠ በኋላ በአዋዜና በሰናፍጭ ተቀላቅሎ ለማዕድ የሚቀርብበት ነው፡፡ ተምሳሌታዊ ፍችው የባቄላው መብቀል ዳግም ምጽአትን የሚያሳስብ ነው፡፡ በዕለተ ምጽአት ሙታን የሚነሡበትና የሚለዩበትን ያመለክታል፡፡ የበቀለው ባቄላ ‹‹ያባቴ ቡሩካን›› የተባሉትን በቀኝ በኩል የሚሆኑትን ሲወክል፣ የማይበቅለውና ደረቁ ባቄላ በግራ በኩል የሚሆኑትን ይወክላል፡፡ ‹‹በጎቹን በቀኝ ፍየሎቹን በግራ. . .›› እንዲል፡፡

spot_img
Previous article
Next article
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...