Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊወደ ኋላ የቀረው የሠራተኞች ደኅንነት አጠባበቅ

ወደ ኋላ የቀረው የሠራተኞች ደኅንነት አጠባበቅ

ቀን:

በአበበ ፍቅር

ለሠራተኞች የሚሰጠው የደኅንነት ትኩረት አናሳ በመሆኑ በርካታ ዜጎች ለሞትና ለአካል ጉዳት እንዲሁም ለእንግልት ሲረዳጉ ይስተዋላል፡፡ በሥራ ላይ በሚከሰት አደጋ ምክንያትም በዓለም ውስጥ በቀን 6,300 የሚደርሱ ዜጎች ሕይወታቸውን እንደሚያጡ የዓለም ባንክ በሥራ ላይ የሚደርስ አደጋን በተመለከተ ያወጣው ጥናት ያመላክታል፡፡

በዓለም ላይ በሠራተኞች ደኅንነትና ጤንነት አጠባበቅ ዙሪያ የተሻሉ ናቸው በሚባሉት አገሮችም ከ100 ሺሕ ሠራተኞች መካከል ሦስት ዜጎች በዓመት ይሞታሉ፡፡

ኢትዮጵያ ደግሞ ከ100 ሺሕ ሠራተኞች መካከል በዓመት 1,920 ዜጎች በዚህ አደጋ እንደምታጣ መረጃው ያመላክታል፡፡ የሠራተኞች ደኅንነትን ባለመጠበቅ አገሪቱ በዓመት 21 ቢሊዮን ብር እንደምታጣ የዓለም ባንክ መረጃ ያሳያል፡፡ መንግሥትና አሠሪ ተቋማቶች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ካለመወጣትና ለሠራተኞች ስለሥራው በቂ የሆነ ግንዛቤን አለመፍጠር የሚሉት ደግሞ ለአደጋው መስፋፋት እንደ ዋና መንስዔ ናቸው ተብለው ይጠቀሳሉ፡፡

ችግሩ ጎልቶ የሚስተዋለው በታዳጊ አገሮች ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በሠራተኞች ላይ ከሚደርሱ አደጋዎች መካከል በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚከሰቱ አደጋዎች በቀዳሚነት ይነሳሉ፡፡ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት አደረኩት ባለው የዳሰሳ ጥናት ከ85 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ዜጎች በግንባታው ዘርፍ ተሰማርተው እንደሚገኙ አመልክቷል፡፡

ዘርፉ ከትራንስፖርት ቀጥሎ ከፍተኛ የሞትና ከባድ የአካል ጉዳት የሚከሰትበት እንደሆነም በጥናቱ አረጋግጧል፡፡ ዘርፉ በአብዛኛው ከ30 ዓመት በታች ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች የሚሳተፉበት ሲሆን፣ ምቹ የሥራ ሁኔታ ባለመኖሩና ለሠራተኞች ትኩረት ባለመሰጠቱ ብዙዎች በአሠሪዎቻቸው ከፍተኛ እንግልትና ያላግባብ የሆነ የሥራ ጫና እንደሚደረግባቸው በጥናቱ ወቅት ቃላቸውን የሰጡ ሠራተኞች መናገራቸውን ጠቁሟል፡፡

ለስብራት፣ ለወገብ ሕመምና ለመሳሰሉት በሽታዎች እንደሚጋለጡ፣ ከዚህ ባሻገር አሠሪዎች በፈለጉትና ባሻቸው ጊዜ ያለምንም ማስጠንቀቂያና ያለ አገልግሎት ክፍያ ከሥራ እንደሚያሰናብቷቸው፣ የአገልግሎት ክፍያ እንዳይጠየቁ በቀን፣ በሳምንትና በወር እያስፈረሙ ደመወዛቸውን እንደሚሰጧቸው ቃላቸውን ሰጥተዋል ይላል ጥናቱ፡፡

ወጣት ወልደ ተስፋዬ ለበርካታ ዓመታት በኮንስትራክሽን ሥራ እንደቆየ ተናግሯል፡፡ ወጣት ወልደ ከሦስት ዓመታት በፊት አንድ ጓደኛው በሥራ ላይ እያሉም ሕይወቱን ማጣቱን ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡

አደጋው በድርጅቱ የጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ እንደደረሰ የሚያስታውሰው ወጣቱ፣ የመውጫና መውረጃው ሊፍት በመበጠሱ ከሰባተኛ ፎቅ ተነስቶ በመውደቅ ሕይወቱን እንዳጣ ይናገራል፡፡  ‹‹ዛሬን ለመኖር ከአሸዋና ሲሚንቶ ጋር ሲለፋ የነበረ ሰው በድንገት ሕይወቱን ሲያጣ የሚመራው ቤተሰብ እንዳለው እየታወቀ ድርጅቶች የሚከፍሉት ካሳ በጣም አነስተኛ መሆኑ የሚያሳዝን ነው፤›› ብሏል፡፡

ለሚደርሰው የሞትም ሆነ የአካል ጉዳት የሚከፈለው ካሳ እጅግ አናሳ ከመሆኑም ባሻገር ከተጎጂው ጎን ቆሞ የሚከራከርለት አካል ባለመኖሩ ክፍያው በጣም ይዘገያል፣ ተደባብሶና ተለባብሶ ሊቀር የሚችልበት አጋጣሚ እንዳለም ተናግሯል፡፡

በግልም ሆነ በመንግሥት በቋሚነትም ሆነ በጊዜያዊነት ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች ዓመታዊ የእረፍት ፈቃድን ጨምሮ የተለያዩ ጥቅማጥቅሞችን፣ የአካል ደኅንነት እንዲሁም አሠራሩን የተከተለ የደመወዝ ዕድገት ሳያገኙ ይቆያሉ፡፡

እነዚህንና መሰል የሠራተኞችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ደኅንነቶችን ለማስከበር በሚል ከዛሬ 49 ዓመት በፊት በአፍሪካ ደረጃ የሠራተኞች አስተዳደር ማዕከል በሚል ተቋቁሞ ነበር፡፡ ማዕከሉ 19 አባል አገሮችን ያቀፈ ሲሆን፣ በየዓመቱ በሚያደርገው ስብሰባ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ይሳተፋሉ፡፡

ኢትዮጵያም እ.ኤ.አ. ከ1965 ዓ.ም. ጀምሮ የአፍሪካ የሠራተኞች አስተዳደር አባል በመሆን የተለያዩ ተሞክሮዎችን በማምጣት በመተግበር ላይ እንደሆነች የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ አሰግድ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡ መቀመጫውን ዚምባብዌ ያደረገው የቀጣናው አስተዳደር ከሰሞኑ 49ኛውን የአባል አገሮቹን ስብሰባ በአዲስ አበባ አካሂዷል፡፡

በውይይቱም በዓለም ዙሪያ የሠራተኞች አስተዳደር ደኅንነት ገና 45 ከመቶ ላይ እንደሚገኝና አፍሪካ እዚህ ደረጀ ለመድረስ ገና ብዙ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠበቅባት ተነስቷል፡፡ አሁን ካለበት ዝቅተኛ ደረጃ ተነስቶ እንዴት 40 በመቶ ለመድረስ እንደሚቻል ሁሉም የአፍሪካ አገሮች መመካከርና መወያየት ይኖርባቸል ተብሏል፡፡

ወደ 40 በመቶ ለመድረስ ከተቃረቡት የአፍሪካ አገሮች መካከል ደቡብ አፍሪካና ግብፅ በግንባር ቀደምትነት የተጠቀሱ አገሮች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያም በሠራተኞች አስተዳደር ደኅነነት ደረጃ ከአፍሪካ አገሮች ግርጌ ላይ እንደምትገኝ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አሰግድ ተናግረዋል፡፡

ለችግሩ እንደ መንስዔ ያቀረቡት ደግሞ የሠራተኞችን ደኅንነት ከማስጠበቅ አንፃር በየዘርፉ የሠለጠኑና ግንዛቤን ሊፈጥሩ የሚችሉ በቂ የሰው ኃይል አለመኖርን ነው፡፡ ከዚህ በፊት በሠራተኞች ላይ የሚከሰቱ የመብት ጥሰቶች ከዕውቀት ማነስ እንደሚመነጩም አክለዋል፡፡

በተለይ ደግሞ ኮቪድ-19 ከተከሰተ ወዲህ ችግሩ የበለጠ መስፋቱን ተናግረዋል፡፡ በወረርሽኝ ምክንያት በርካታ ሠራተኞች ከሥራቸው መፈናቀላቸውን ያነሱት ሚኒስቴር ዴኤታው፣ ከሥራቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን እንዴት ድጎማ እናድርግላቸው በሚለው ከተለያዩ አገሮች ተሞክሮን በመውሰድ የተለያዩ መመርያዎች እንደሚፀድቁም አብራርተዋል፡፡

የአፍሪካ አገሮች ሠራተኞች አብዛኛዎቹ ችግር ውስጥ ናቸው ደግሞ ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ድርጅት የምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ ዳይሬክተር ጀኒ ሙሳ ባያና ናቸው፡፡

በማኅበራዊ ጥበቃና በሠራተኞች ደኅንነት ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮን ለማስቀረት የማዕከሉ አባል አገሮች በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍና እንደ አፍሪካ የተያዘውን ዕቅድ ግብ እንዲመታ ለማድረግ ኢትዮጵያም ከራሷ ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ከሠራተኛ መብት ከአሠሪና ሠራተኛ መብት አንፃር የተሻሻሉ መመርያዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም ለተለያዩ ለግልና ለመንግሥት አሠሪ ተቋማት በሠራተኞች አያያዝ መብትና ግዴታዎች ዙሪያ የተለያየ የሥልጠናና የማማከር ሥራ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በኩል መሰጠታቸውን ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...