Saturday, July 20, 2024

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጉብኝትና የሁለቱ አገሮች ግንኙነት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የገጠማቸው፣ የአፍሪካ ዜና አውታሮች የወሬ ማሟሻ ሆኖ ነው የሰነበተው፡፡ ከጋቦን ጉብኝታቸውን የጀመሩት ማክሮን፣ በአንጎላና በኮንጎ ብራዛቪል ዞረው ወደ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አመሩ፡፡ ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጋር ተገናኝተው ለጋዜጠኞች መግለጫ ወደ የሚሰጡበት መድረክ ብቅ አሉ፡፡

የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ሺሴኪዴ በመግለጫው ላይ ጠንካራ ቃላትን ማዝነብ ጀመሩ፡፡

‹‹አውሮፓም ሆነ ፈረንሣይ እኛን የምትመለከቱበትን መነጽርም ሆነ ከእኛ ጋር ያላችሁን ግንኙነት ቀይሩ፡፡ ልታከብሩን ይገባል፡፡ ሁሌም እናንተ የምትሉት ትክክል የእኛ ግን ስህተት ተብሎ መቅረብ የለበትም፡፡ ስለእኛ አፍሪካውያን የምትናገሩትን አስተካክሉ፤›› በማለት ነበር ሺሴኪዴ ማክሮንን የገሰፁት፡፡

ማክሮን በበኩላቸው ተቆጥተው፣ ‹‹አንድ ጋዜጠኛ ስለአፍሪካ የሰጠው አስተያየት የፈረንሣይ አቋም ነው ተብሎ ሊወሰድ አይገባም፤›› በማለት ሲናገሩ ተደመጡ፡፡

ቪሴኪዴ ግን አላስጨረሷቸውም፣ ‹‹ጋዜጠኛ የተናገረውን አይደለም የጠቀስኩት፣ የፈረንሣይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተናገሩትን ነው፤›› ሲሉ ኩም አደረጓቸው፡፡

ሺሴኪዴ በድፍረት ነው ማክሮንን የተጋፈጧቸው፡፡ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ሩዋንዳ የሰላም ስምምነት ላይ ካልደረሱ፣ በማዕቀብ እንቀጣለን የሚል የፉከራ መግለጫ እየሰጡ ኪንሻሳ ለረገጡት ማክሮን ሺሴኪዴ ግን አልተበገሩላቸውም ነበር፡፡

‹‹ፍራንኮፎን ያለፈበት ታሪክ ነው፡፡ በተለየ መንገድ ልትመለከቱን ይገባል፡፡ እንደ ትክክለኛ አጋር ቁጠሩን፡፡ እንደ ወላጅ እኛን እንወቅላችሁ አትበሉን፡፡ ልታከብሩን ካልቻላችሁ ሌሎች የግንኙነት አማራጮቻችን ልናማትር እንገደዳለን፤›› የሚል ጠንካራ መልዕክት አስተላለፉ፡፡

የአፍሪካ አገሮች ከምዕራባዊያን አገሮች ጋር ግንኙነት ለማጠናከር ከሚቸገሩባቸው ምክንያቶች አንዱ የአቻ አጋርነት መሻት መሆኑ ይነገራል፡፡ በሁለቱ መካከል ባለው ግንኙነት ሁሌም የምዕራባዊያኑ ፍላጎት ያጋደለ እንዲሆን መደረጉ፣ አፍሪካዊያንን ሲያበሳጭ የኖረ ጉዳይ ነው፡፡ ልክ እንደ ሼሴኪዴ ግን ይህን ብሶት ለምዕራባውያን አገሮች ባለሥልጣናት በድፍረት የሚናገር የአፍሪካ መሪ እምብዛም አይታይም፡፡

ከሰሞኑ የልዕለ ኃያሏ አገር አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ወደ ኢትዮጵያና ኒጀር መጥተው ነበር፡፡ በዚህ ጉብኝት ወቅት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ኢትዮጵያ ሊጠበቅላት ስለሚገቡ ጥቅሞችና ፍላጎቶች ለአንቶኒ ብሊንከን በቅጡ አስረድተዋል ወይ የሚለው ጉዳይ የሰሞኑ ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡ አንቶኒ ብሊንከን ወደ አፍሪካ ለሁለተኛ ጊዜ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ በእሳቸው ደረጃ የሚገኝ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣን ለኢትዮጵያ ቅድሚያ ሰጥቶ ጉብኝት የሚያደርገው ደግሞ፣ ቡና ጠምቶት ወይም የሸገር ፓርክ ሽርሽር አምሮት እንዳልሆነ ነው የፖለቲካ ተንታኞች የሚናገሩት፡፡

ይፋዊ በሆኑ መረጃዎች መሠረት የብሊንከን የኢትዮጵያ ጉብኝት ዋና ዓላማዎች የሕወሓትና የፌዴራል መንግሥትን ሰላም ስምምነት ትግበራ ለመመልከት፣ እንዲሁም በሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ለመምከር የሚሉ ማብራሪያዎች ሲሰጥበት ነበር፡፡

እንደተጠበቀውም ብሊንከን በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጀምሮ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን፣ እንዲሁም ከገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ጋር ተገናኝተው ነበር፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያን ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የተለያዩ የሲቪክ ማኅበራት አመራሮችን አግኝተው ነበር፡፡

አንቶኒ ብሊንከን በተጨማሪም የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማኅመትን ከማግኘታቸውም በላይ የመንግሥትና የሕወሓት ዋና ተደራዳሪ የሆኑትን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) እና አቶ ጌታቸው ረዳን በጋራ አግኝተው መወያየታቸውም ታውቋል፡፡

ሁሉንም አካል ለማዳረስ የሞከረው የብሊንከን ቆይታ በይፋም በዝግም ውይይቶች የተደረጉበት ነበር፡፡ ከእነዚህ ግንኙነቶችና ምክክሮች መካከል ደግሞ አንዳንዱ በይፋ መግለጫ ሲሰጥበት ገብስ ገብሱ ተነግሮ ያለፈም ነበረበት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ ‹‹ለረዥም ጊዜ የዘለቀውን ግንኙነታችንን የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል ቁርጠኝነታችንን አረጋግጠናል፤›› የሚል መግለጫ ከብሊንከን ጋር ከተነጋገሩ በኋላ አውጥተዋል፡፡ ብሊንከን በበኩላቸው ኢትዮጵያ በሰላም ስምምነት ትግበራ ትክክለኛውን መንገድ እየተከተለች ስለመሆኑ ለጋዜጠኞች መናገራቸው ጎልቶ ሲወሳ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በአደባባይ ከተነገረውም ሆነ በዝግ ከተካሄደው ምክክር በላይ፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ከፍተኛው ባለሥልጣን የአንቶኒ ብሊንከን የኢትዮጵያ ጉብኝት ምን ለውጦችን ይዞ ይመጣል የሚለው ጥያቄ በስፋት እያነጋገረ ነው፡፡

ብሊንከን ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በዋናነት በሕወሓትና በፌዴራል መንግሥት የሰላም ስምምነት ጉዳይ ደስታቸውን ለመግለጽ? ወይስ የሁለቱን አገሮች ሁለንተናዊ ግንኙነት ዳግሞ ለማጠናከር? የሚለው ጉዳይ እያነጋገረ ይገኛል፡፡

ይህን በተመለከተ ማብራሪያ የሚሰጡት ጋዜጠኛና የውጭ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ፍትሕአወቅ የወንድወሰን፣ ‹‹የሰላም ስምምነቱንም ሆነ አተገባበሩን በጉዳዩ ቀጥተኛ ተሳትፎ ባለው የምሥራቅ አፍሪካ ተወካያቸው በኩል ይከታተሉታል፡፡ የብሊንከን በአካል ኢትዮጵያ መገኘት ግን ከዚያ የሰፋ አንድምታ ያለው ነው፤›› ይላሉ፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ዋና መቀመጫ ወደ ሆነችው አዲስ አበባ እስካሁን ብሊንከን ሳይመጡ መቆየታቸው የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ላልቶ መቆየት ጠቋሚ እንደሆነ አቶ ፍትሕአወቅ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ብሊንከን አሁን መምጣታቸው ይህን የሚለውጥና የሁለቱ አገሮች ግንኙነትን የሚያሻሽል ነው፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡

በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ አየነው ብርሃኑ (ዶ/ር)፣ በተመሳሳይ ጉብኝቱ ብዙ አንድምታ ያለው መሆኑን ያወሳሉ፡፡

‹‹አሜሪካ ለምሥራቅ አፍሪካ በተለይም ለኢትዮጵያ ጉዳይ ልዩ ትኩረት የሰጠች መሆኑን ጉብኝቱ ያሳያል፡፡ አሁን በዓለማችን አሜሪካ ልዩ ትኩረት የምትሰጣቸው የዩክሬን፣ የሩሲያና የቻይና ጉዳዮች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ እያሉ ወደ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣን መላኳ ለኢትየጵያ ጉዳይ የሰጠችውን ሥፍራ የሚያሳይ ነው፤›› በማለትም አየነው (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡

ብሊንከን ከሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) እና ከአቶ ጌታቸው ረዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ የሕወሓት ታጣቂዎችን ትጥቅ ስለማስፈታትና መልሶ ስለማቋቋም ትኩረት ሰጥተው መነጋገራቸውን፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህመት ጋር ባደረጉት ውይይት ደግሞ የኅብረቱ በቡድን 20 አገሮች ማኅበር ቋሚ መቀመጫ የማግኘት፣ እንዲሁም በተመድ ፀጥታው ምክር ቤት የኅብረቱ ተደማጭነት ከፍ ስለሚልበት ጉዳይ ማንሳታቸው ነው የተነገረው፡፡

ብሊንከን ከአፍሪካ ኅብረት ባለሥልጣናት ጋር ይህንን ብቻም ሳይሆን፣ የአሜሪካና የአፍሪካ አገሮች የንግድ፣ የኢንቨስትመንት፣ የፀጥታ፣ የሰላምና የምግብ ዋስትና ጉዳዮች ላይ በሰፊው መነጋገራቸው ነው የተነገረው፡፡

ይሁን እንጂ አሜሪካ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት እንዲጠናከር የምትፈልገው፣ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ሺሴኬዲ ለፈረንሣዩ ማክሮን እንደነገሯቸው አዛዥና ታዛዥነትን ባሰፈነ መንገድ? ወይስ አቻ አጋርነትን በተከተለ ሁኔታ? የሚለው ጥያቄ ለውይይት የሚጋብዝ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ ደግሞ በኢትዮጵያና በአሜሪካ ግንኙነት ዙሪያም ሊነሳ የሚችል መሆኑን ተንታኞች ይጠቅሳሉ፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ካላት አቀማመጥ አንፃር፣ ከሕዝብ ብዛትና ተፅዕኖ የመፍጠር አቅም አኳያ በአፍሪካ ቀንድም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላት አገር መሆኗን አሜሪካኖቹ በቅጡ ተረድተውታል፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ የአሜሪካ ጉዳይ እንደሆነ የተረዱት ይመስላል፤›› በማለት ነው አየነው (ዶ/ር) የሚያስረዱት፡፡

በአፍሪካ ቀንድ ቻይና፣ ቱርክ፣ ሩሲያና የዓረብ አገሮችን ጨምሮ የበርካታ አገሮች የኃይል አሠላለፍ እንደሚታይ የተናገሩት የፖለቲካ ተንታኙ፣ አሜሪካኖቹ ኢትዮጵያን ባማከለ መንገድ ይህን የኃይል አሠላለፍ በበላይነት ለመወጣት ማሰባቸው ግልጽ እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ ሐሳብ ያስተጋቡት አቶ ፍትሕአወቅ በበኩላቸው፣ ብሊንከን ከምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ጋር መነጋገራቸው ጉዟቸው ቀጣናዊ ጉዳዮችንም ታሳቢ ያደረገ መሆኑን እንደ አንድ ማሳያ ያቀርቡታል፡፡

‹‹በሶማሊያና በሶማሌላንድ አካባቢ በቅርብ ጊዜያት እየተፈጠሩ ባሉ ክስተቶች አሜሪካኖች ኢትዮጵያ ሚና እንዲኖራት የፈለጉ ይመስላል፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ ከሰሞኑ ተለዋዋጭ የፖለቲካ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ደቡብ ሱዳን ሲጓዙ፣ የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ደግሞ ከሱዳንና ከሶማሊያ መሪዎች ጋር በተከታታይ ሲገናኙ ታይቷል፡፡ ለረዥም ጊዜ በተረጋጋችው ሶማሌላንድ ደግሞ አሳሳቢ ግጭት እያገረሸ ነው፡፡ በዚህ ተለዋዋጭ ቀጣናዊ ፖለቲካ ላይ ደግሞ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር በአጋርነት የራሷን ሚና ለመጫወት መፈለጋቸው እየተንፀባረቀ ይገኛል፤›› በማለት ነው የጉብኝቱን ጂኦ ፖለቲካዊ አንድምታ ያብራሩት፡፡

የብሊንከን ኢትዮጵያ መምጣት አኅጉራዊና ቀጣናዊ ገጽታ ያለው ስለመሆኑ ከሚነገረው ጎን ለጎን፣ ጉብኝቱ በዋናነት የሻከረውን የሁለቱን አገሮች የሚያሻሽል ነው የሚል ተስፋ እየተስተጋባ ይገኛል፡፡ ብሊንከን ኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ የ331 ሚሊዮን ዶላር የሰብዓዊ ዕርዳታ ድጋፍ ይፋ ማድረጋቸውም ሆነ ከገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ጋር መምከራቸው፣ አሜሪካ ሻክሮ የቆየውን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማደስ መፈለጓን ማሳያ ሆኖ ሲቀርብ ቆይቷል፡፡

ይሁን እንጂ ብሊንከን ገና ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸው እንደተነገረ አስተያየት የተጠየቁት የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊዋ ሞሊ ፊ፣ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት መሻሻል በወሳኝ ቅድመ ሁኔታዎች የታጠረ መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡

‹‹ግንኙነታችንን ለማሻሻል ከተፈለገ ከኢትዮጵያ በኩል ብሔርን መሠረት ካደረገ የግጭት አዙሪት እንድትላቀቅ እንፈልጋለን፤›› በማለት ነው ያስረዱት፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስም ቢሆኑ ይህን ሐሳብ በሌላ መንገድ አስተጋብተውታል፡፡ ‹‹ብሊንከን በጦርነቱ ወቅት ለተፈጸሙ ጭፍጨፋዎች ተጠያቂ አካል እንዲኖር ሁሉንም አካታችና የተሟላ የሽግግር ጊዜ ፍትሕ እንዲረጋገጥ አሜሪካ እንደምትፈልግ ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ግልጽ አድርገዋል፤›› በማለት ነው፣ አሜሪካ ለግንኙነቱ መታደስ የሰብዓዊ ጉዳዮችን እንደምታስቀድም የተናገሩት፡፡

ብሊንከንም ቢሆኑ በተለይ ከሰብዓዊ መብትና ከሲቪክ ማኅበራት ተቋማት ወኪሎች ጋር ባደረጉት ቆይታ ይህንኑ ጉዳይ በጉልህ ማንሳታቸው ታውቋል፡፡ ‹‹የሰብዓዊ መብቶችና የዴሞክራሲ ጉዳዮች የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ የልብ ትርታዎች ናቸው፤›› በማለት ነበር ለግንኙነቱ መታደስ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች የማይታለፉ ነጥቦች መሆናቸውን የተናገሩት፡፡

በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በኩል ከአሜሪካ ጋር ሻክሮ የቆየው ግንኙነት እንዲጠገን ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩ ሲንፀባረቅ ታይቷል፡፡ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ያቀረቡት የሰብዓዊ ረድኤት ጥያቄም ይህን ጠቋሚ ሆኖ ነው የታየው፡፡ የአሜሪካን የስንዴ ዕርዳታ የማጣጣል የቅርብ ጊዜ ትርክት መለወጡን፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ ተጨማሪ ዕርዳታ አድርጉልን የሚል ጥያቄ በጉልህ ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያ የሰብዓዊ ረድኤት ጉዳይ ብቻም ሳይሆን ከግንኙነቱ መታደስ ብዙ ጥቅሞችን ለማግኘት እንደፈለገች ነው የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አስተያየቶች የሚጠቁሙት፡፡ የአጎዋ ንግድ ዕድል ዳግም ተጠቃሚ የመሆን፣ እንዲሁም የውጭ ብድር ዕዳ ሽግሽግ ጥያቄዎች፣ የተለያዩ ማዕቀቦችና ዕገዳዎች የመነሳት ጉዳይ ኢትዮጵያ በግንኙነቱ መሻሻል ልታገኝ የምትሻቸው ጥቅሞች መሆናቸው በሰፊው እየተነገረ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -