Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መንግሥት የአገሪቱን ገበያ እያረጋጋ መስሎት እያመሰ አለመሆኑን ያረጋግጥ!

በህብስት አበበ 

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ከሚስተዋለው የሰላም ዕጦት ባሻገር የዋጋ ንረት በአሁኑ ወቅት ‹‹በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› ሆኖ ኅብረተሰቡን በእጅጉ እየፈተነ ይገኛል፡፡

መሽቶ በነጋ ቁጥር የምርቶች ዋጋ በሁለትና በሦስት ጨምሮ ማደሩ የተለመደ ሆኗል፡፡ በዚህም በልቶ ማደር ፈተና መሆን ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡

በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ነገ ይኼንን ምርት እገሸምታለሁ ብሎ ማቀድ ከንቱ ምኞት እየሆነ መጥቷል፡፡ ገበያውን አጥለቅልቆት የከረመ ምርት በማግሥቱ በአንዳች ምትሐታዊ ኃይል እንደተሰወረ ሁሉ ሙሉ ለሙሉ ሊጠፋ ይችላል፡፡

ለዚህም ማሳያ በወራቶች ልዩነት ሰማይ የነካውን ወይም በሦስት አኃዝ ያደገው የዘይት ገበያ ማስታወስ ብቻ በቂ ነው፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት የዘይት ዋጋ የጨመረበት ሁኔታም ይህንኑ ልጓም ያጣው የገበያ ሒደት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ ከዘይት ባለፈ ሌሎችም ምርቶች በዚሁ ሁኔታ ቅጥ ያጣ የዋጋ ንረት ምክንያት የዜጎችን ኑሮ መቀመቅ እያስገባ ይገኛል፡፡

በሁሉም የምርት ዓይነት ለሚስተዋለው የዋጋ ንረት መፍትሔ ተብሎ በመንግሥት የሚሰጠው ምላሽ ደግሞ በእሳት ላይ ቤንዚል ማርከፍከፍ እየሆነ ነገሩን አባብሶታል።

ችግሩን ለይቶ መፍትሔና ሥርዓት ከመዘርጋት ይልቅ፣ በንግዱ ሥርዓት ውስጥ በመግባት የነጋዴነት ሚና መጫወቱ ችግሩን አባብሶታል፡፡ መንግሥት ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት እየሄደበት ያለው መንገድ ትክክል አለመሆኑም የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እየፈጠረ ባለው የዋጋ ንረት መባባስ ውስጥ በግልጽ የሚታይ ነው፡፡ 

ይህንኑ መንገድ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ምርቶች ሞክሮት ለውጥ ማምጣት አልቻለም፡፡ ለዚህ ማሳያ መንግሥት የሲሚንቶ ዋጋን ለማረጋጋት የዋጋ ተመን ከማውጣት ጀምሮ በንግድ ሰንሰለት ውስጥ እጁን አስገብቶ ቢሞክርም፣ ምርቱን ኮንትሮባንድ ከማድረግ የዘለለ ምንም የፈየደው ነገር የለም፡፡

ከዚህ ይልቅ ውሎና አዳራቸውን በሲሚንቶ ጥቁር ገበያ ውስጥ ያደረጉ ደላሎች ችግር እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጭምር በሲሚንቶ ንግድ ውስጥ እንዲሰማሩ ምክንያት መሆኑንም ይታማል፡፡

በሲሚንቶ ገበያ መንግሥት እጁን አስገብቶ ካባሰ ሰኋላ ምርቱ በነፃ ገበያ እንዲሸጥ መፍቀዱን ቢገልጽም፣ አንድ ከረጢት ሲሚንቶ ማግኘት ተራራን የመግፋት ያህል እየከበደ ነው።

ከሰሞኑም የጤፍና የስንዴ ምርት ላይ የታየው የዋጋ ንረት መንግሥት ለማረጋጋት እየሄደበት ያለው መንገድም የሲሚንቶን ፈለግ የተከተለ ነው፡፡ ለጤፍ ዋጋ መናር እየተናገሩ ያሉ ምክንያቶች በዋናነት የገበያ ሥርዓቱ ብልሽት የፈጠራቸው ስግብግብ ነጋዴዎች እንደሆኑ ቢነገርም፣ መንግሥት ወደ ክልሎች ገበያ ድረስ ዘልቆ በመግባት የዋጋ ተመን ማውጣቱ ሕገወጥ ነጋዴዎች እንደ አሸን እንዲፈሉ ምክንያት ሆኗል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ማኅበራት ሱቆች አማካይነት ጤፍ ለማኅበረሰቡ እየቀረበ መሆኑን የሚታወቅ ሲሆን፣ ይህም መንግሥት በዘላቂነት ችግሩን ከመፍታት ይልቅ የሚያባብስ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል፡፡

የጤፍ ዋጋ በሸማች ማኅበራት ቅናሽ ቢያሳይም በተለያዩ የገበያ ማዕከላት ግን ጣሪያ ነክቷል፡፡ የማያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል እንዲሉ ዘላቂነትና ለሁሉም ማኅበረሰብ ክፍል ተደራሽ የማይሆን የግብይት ሥርዓት ዘለቄታ የለውም፡፡ በስንዴ ላይም በተመሳሳይ ሁኔታ መንግሥት የዋጋ ተመን በማውጣት ምርቱን ከአርሶ አደሩ መሰብሰብ መጀመሩ የአገሪቱ የስንዴ ገበያ በመንግሥትና በነጋዴዎች እንዲሁም በነጋዴዎችና በዱቄት አምራቾች ግብግብ እየታመሠ ነው።

በስንዴ አምራችነት ከምትታወቀው ባሌ አርሶ አደሮች በ3,200 ብር የተሸመተ አንድ ኩንታል ስንዴ አዲስ አበባ ከተማ ላይ 7000 ብር ድረስ እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ይህም አርሶ አደሩ ተጠቃሚ ካለመሆኑ ባሻገር፣ የሸማቹን አቅም የተፈታተነ መሆኑ ዕሙን ነው፡፡ ከሁሉም የሚያሳዝነው ግን ዓመቱን ሙሉ ለፍቶ ፣ በሬዎቹን አድክሞ ፣ የአፈር ማዳበሪያ በብድር ገዝቶ ስንዴውን ያመረተው አርሶ አደር በኩንታል 3, 200 ብር ሲያገኝ፣ በመንግሥት በሚደጎም ነዳጅ የጭነት ተሽከርካሪ ይዞ አርሶ አደሩ መንደር የገባው ነጋዴ ምንም ሳይለፋ አርሶ አደሩ በእጥፍ የሚበልጥ ገቢ እያጋበሰ ነው። ይህ ሸማች ማህበረሰቡን ከመፈተኑ ዕኩል የአገሪቱ ገበያ ሥርዓት አልባ መሆኑን ግልጽ አድርጎ የሚያሳይ ነው።

ሰሞኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የስንዴ ግዥ አስተባባሪ ግብረ ኃይል በክልሉ የስንዴ ግብይት ሒደት ላይ የሚስተዋሉ ዋና ችግሮች ብሎ በዝርዝር ለይቷል፡፡

ቢሮው በክልሉ የስንዴ መግዣ ዋጋ 3‚800 እስከ 4‚300 የደረሰ መሆኑን በችግርነት ጠቅሶ፣ ለዋጋው መጨመር ምክንያት ነጋዴውና የዱቄት ፋብሪካ ባለቤቶች በክልሉ የሚያካሄዱት የስንዴ ግዥ መሆኑን አስቀምጧል፡፡ ለዚህም መፍትሔ ብሎ ያስቀመጠው በክልሉ ከሚገኙ ኅብረት ሥራ ማኅበራት በስተቀር ሌላ አካል ፣ ነጋዴም ሆነ ዱቄት ፋብሪካዎች የስንዴ ግብይት እንደይፈጽሙ የሚል ነው።

ከዚህም ባሻገር ስንዴ እንዲገበዩ የተፈቀደላቸው የኅብረት ሥራ ማህበራት ገንዘብ ሚኒስቴ በወሰነው የመግዣ ዋጋ ላይ አምስት በመቶ የትርፍ ህዳግ በመጨመር በ3‚350 ብር ብቻ ከአርሶ አደሩ እንዲገዙ ወስኗል።

ኅብረት ሥራ ማኅበራት ከአርሶ አደሩ ለሚገበዩት ስንዴ ገንዘብ እንዳይቸገሩ ተብሎም ከፌዴራል መንግሥት 1.3 ቢሊዮን ብር መላኩን ይገልጻል። በዚህም መሠረት በመንግሥት የሚደገፉ የኅብረት ሥራ ማኅበራት በመንግሥት በተተመነ ዋጋ የአርሶ አደሩን ስንዴ እየሸመቱ ነው።

የተሰጠውም ብር ለኅብረት ሥራ ዩኒየኖች ተደልድሎ መንግሥት በወሰነው የዋጋ ተመን መሠረት እየሸመቱ ይገኛል፡፡ ይህም አርሶ አደሩ ለለፋበትና ላቡን ጠብ አድርጎ ላመረተው ምርት በነፃነት ዋጋ መወሰን እንዳልቻለ የሚያሳይ ነው፡፡

ይህ የመንግሥት ውሳኔ በሌሎች ክልሎች ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፣ በዚህ የመንግሥት ጣልቃ ውሳኔ ሳቢያ የስንዴ ገበያው ተተራምሷል፣ የተትረፈረፈ ስንዴ ተመረተ ቢባልም የስንዴ ዋጋ በእጥፍ ጨምሯል፡፡ ስንዴ ወደ ውጭ ኤክስፖርት የሚደረገው የአገሪቱ የስንዴ ፍላጎት ተሟልቶ የተረፈው ብቻ እንደሚሆን መንግሥት ቃል ቢገባም፣ ቃሉ ሳይደርቅ ቃሉን አፍርሶ ለዓለም የምግብ ድርጅት እየሸጠ መሆኑንና ድርጅቱም ከመንግሥት የገዛውን ስንዴ በድርቅ እና በሌሎች ምክንያቶች ለተቸገሩ ኢትዮጵያውያን በዕርዳታ መልክ እንደሚያቀርብ ሰሞኑን አስታውቋል። በዚህም ምክንያት፣ የአገሪቱ የስንዴ ፍላጎት ከተሟላ በኋላ የተረፈው ስንዴ ለውጭ ገበያ ይቀርባል የሚለው ቃል መፍረሱ ግልጽ ሆኗል። ምክንያቱም የዓለም ምግብ ድርጅት ከኢትዮጵያ የገዛውንም ሆነ በኢትዮጵያ መጋዘኑ ያከማቸውን ስንዴ የከፋ ቀውስ ለገጠመው አጎራባች አገር ማኅበረሰብ የማቅረብ ዓለም አቀፋዊ መብት ያለው ተቋም ነው።

ይህ ዓይነቱ ያልተጠና ግብታዊ ውሳኔና ሥርዓት አልባ የገበያ መዋቅር ባለበት፣ አርሶ አደሩን ዳግም ስንዴ እንዲያመርት ማነሳሳት ቀላል አይሆንም።

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት