በሔኖክ ፀጋዬ
ሞገስ ዘውዱ የተባሉ ጸሐፊ በባለፈው ሳምንት ዕትም፣ ‹‹የብሔርተኝነት ምንነትና መገለጫዎች ሲዳሰሱ (ክፍል አንድ)›› በሚል ርዕስ ያቀረቡትን ትንታኔ ለመመልከት ሞክሬያለሁ፡፡ በጥቅሉ ትንታኔው የተዛባና አሳሳች መልዕክት የሚሰጥ ብያኔና ትርጓሜ ያለውና እርስ በርሱ የሚጣረስ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ይህም የሆነበት ዋነኛ ምክንያት በመሠረታዊነት ጸሐፊው የተነሱበትን ቃል ብያኔና ትርጓሜ ሲሰጡ መሳሳት የፈጠረው ነው፡፡ በመሆኑም ሙሉ በሙሉ ያቀረቡትን ትንታኔ አልተቀበልኩትም፡፡
እንደ አገር ጎጠኛ ፖለቲከኞች የፈጠሩትን ይህን ዓይነት ችግርና ስህተቶች እኛም እንደ ሕዝብ/ዜጋ ከማረም ይልቅ፣ ስህተቱን ወርሰንና ተላምደነው እስካሁን ተጉዘናል፡፡ ለዚህም የየግላችን ሚና አስተዋጽኦ አለው፡፡ ሁሌም ጎጠኛ ፖለቲከኞች በባህሪያቸው አገራዊ የሚሏቸውን ስያሜዎች፣ ዕሳቤዎች፣ መገለጫዎች፣ ወዘተ. የጋራ ግማዶች እንዲኖሩ አይፈልጉም፡፡ በመሆኑም እነዚህን ግማዶችን ወይ ያጠፏቸዋል ወይ ያዛቡታል ወይም ይክዱዋቸዋል፡፡ ብቻ ባገኙት አማራጭ ሥልት ቢያንስ ቢያንስ ከአገራዊ ደረጃ ጎትተው ለማውረድና ከእነሱ የዝቅታ ደረጃ አቻ ለማድረግ ይሠራሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ እንደ ቃል በጎጠኛ ፖለቲከኞች ወለድ ከተዛቡ ብያኔና ትርጓሜዎች አንዱ ‹‹ብሔር›› እና ‹‹ብሔርተኛ›› የሚለው ቃል ነው፡፡
፩. ብሔርና ብሔርተኛ ትርጓሜ
ቃል የፊደላት ስብስብ ሆኖ ልናስተላልፈው የፈለግነውን ሐሳብ የሚሸከም የሐሳብ ወካይ መግለጫ ነው፡፡ ቃል የማይታይ፣ የማይዳሰስ፣ በጆሮ ብቻ የሚደመጥ ሳይሆን ቋንቋ ትምህርታዊ በመሆኑና ቃል ደግሞ የቋንቋ አንድ መዋቅር በመሆኑ በፊደላት አማካይነት ይታያል፡፡ በተጨማሪም ቃል ከትርጉም ሰጪ መዋቅርነት አንፃር ሲታይ የነገር ሁሉ መጀመርያ ነው ማለት ይቻላል፡፡
በመጀመርያ ‹‹ብሔር›› የሚለው የግዕዝ ቃል ሲሆን፣ ትርጓሜውም ‹‹አገር›› ማለት ነው፡፡ እንዲሁም ‹‹ብሔር›› ከሚለው ውልድ የሆነው ‹‹ብሔራዊ›› የሚለው ቃል ትርጓሜው ‹‹አገራዊ›› የሚል ሲሆን፣ አገራችን ኢትዮጵያ እስካሁን ቃሉን ‹‹ብሔራዊ መዝሙር፣ ብሔራዊ ደኅንነት፣ ብሔራዊ ኮሚቴ፣ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን፣ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት፣ ብሔራዊ ሙዚየም፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ…›› ወዘተ. የመሳሰሉትን ተቋማትና አደረጃጀቶች በአገር አቀፍ ደረጃ መሆናቸውን በሚገልጽ መንገድ ለመግለጽ ቃሉን በስም/በስያሜ ጭምር ስትጠቀምና እየተጠቀመች ትገኛለች፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ቃሉ በጎጠኛ ፖለቲከኞችም በክልል ደረጃ የክልሎችን አስተዳደር ብሔራዊ በሚል ያለ ቦታው ስያሜውን በመጠቀም የተዛባ ትርጉም እንዲሰጥ ተደርጎም ተሰይሟል (ለምሳሌ ለመጥቀስ ‹‹የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት›› በሚል ስያሜ ተሰይሟል)፡፡ ይህንንና መሰል ስያሜዎች እንደ ሕዝብ አሁን ላለንበት ‹‹ብሔር›› የሚለውን ቃል ከቋንቋ ጋር አጣብቀን እንድናይና የተዛባ ብያኔና ትርጓሜ እንድንሰጥ ዋነኛ ሚና ተጫውቷል፡፡
‹‹ብሔርተኛ›› የሚለው ቃል በመሠረቱ ብሔር ከሚለው ቃል ውልድ ቃል ሲሆን፣ በተጨማሪም በቅፅል መደብ የሚመደብና ገላጭ ቃል ነው፡፡ ምንም እንኳን በአማርኛ መዝገበ ቃላት ይህ ነው ተብሎ የሚቀመጥ ትርጓሜ ባይኖረውም፣ ከወላጅ ቃሉ ተነስተን አገር ወዳድ ወይም አገር የሚያስቀድም የሚል ትርጓሜ ልንሰጥ እንችላለን፡፡ በተጨማሪም አገር የሌለው አካል ብሔርተኛ ሊባል ወይም ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን ብሔርተኛ የሚለውን ቃል በአገራችን በስፋት በተሳሳተው የጎጠኛ ፖለቲከኞች ውልድ ብያኔና ትርጓሜ እንደ ሕዝብ ጭምር እየተጠቀምንበት እንገኛለን፡፡
በተጓዳኝ ገልጾ ለማለፍ ያህል ‹‹ኅብረ ብሔራዊ›› ወይም ‹‹ኅብረ ብሔር››ን ለአገሮች ስብስብ ወይም ለአኅጉራት ወይም ላለንባት ዓለም ገላጭ ትርጓሜ አድርገን ቃሉን ልንጠቀምበት እንችላለን እንጂ፣ ለአንድ አገር ‹‹ኅብረ ብሔራዊ›› ወይም ‹‹ኅብረ ብሔር››ን በገላጭነት ትርጓሜ ልንጠቀም አንችልም፡፡ በተጨማሪም ‹‹ንዑስ ብሔር›› የሚባል ነገር የለም፡፡ ከጎጠኛ ፖለቲከኞች ውልድ ዕሳቤ የመጣ እንጂ፡፡
፪. የቃላት ትርጓሜ መዛባት የሚያመጣው ጠንቅ
እንደ አገር በምንጠቀምበት የመግባቢያ ቋንቋችን ላይ ይህን ዓይነት የተዛቡ ብያኔዎችና ትርጓሜዎች በሰፉና በተጠናከሩ ቁጥር እንደ ሕዝብ ተነጋግረን/ተወያይተን የመግባባት ዕድላችንም በዚያው መጠን እየጠበበና እየቀጨጨ ይሄዳል፡፡ ይህም የማኅበረሰብ ቁርሾ ከመፍጠሩም አልፎ ለእርስ በርስ ጦርነት የመዳረግና አገር የማፍረስ መሠረት ይጥላል፡፡ በተለይ አገራችን ኢትዮጵያ ካለችበት ሁኔታ (የጎጥ ፖለቲካ) አንፃር እንዲህ ዓይነት የተዛባ ብያኔና ትርጓሜ ላይ ተመሥርቶ አገራዊና ፖለቲካዊ ትንታኔ መስጠት ደግሞ በእሳት ላይ ነዳጅ የማርከፍከፍ ያህል ነው፡፡
፫. መንጠቅ፣ ማዛባት፣ ማውረድ፣ መካድና ማጥፋት. . .
ማንኛውም ጎጠኛ በተለይም ጎጠኛ ፖለቲከኛ አገራዊ የሆኑ ማናቸውንም መገለጫዎችና ግመዶች መንጠቅ፣ ማዛባት፣ ጎትቶ ማውረድ፣ መካድና ማጥፋት፣ ወዘተ. ዋነኛ የሥራው መገለጫው ነው፡፡ ይህም ያለ ገደብ በተገኘው አጋጣሚና ዕድል ሁሉ የሚሠራ ነው፡፡ የጎጠኛ ጉልበትና አቅም እንዲሁም ብዛት በጨመረ ቁጥር አገራዊ መገለጫዎች በፍጥነት የመደብዘዝና የመጥፋት፣ እንዲሁም አገራዊ ግማዶች በፍጥነት የመበጣጠስና የመጥፋት አደጋ ይጋረጥባቸዋል፡፡
የማስፈጸሚያ ሥራዎቻቸውም ሐሰተኛ ትርክት መፍጠር፣ በተጠቂነት ስሜት ሌላው የአጥቂነት ስሜት እንዲሰማውና ማሸማቀቅ፣ ኢሳይንሳዊ ልማዶችና ኢአማኝነት ማንሰራፋት፣ ብሔርተኞችን በማጥላላትና የግብር ሥራቸው ከሆነው በተቃራኒው በመፈረጅ ማዳከም ማጥፋት፣ እውነትን መካድ፣ ወዘተ. የመሳሰሉት ናቸው፡፡
በጸሐፊው ጽሑፍ ውስጥ ካየኋቸው የተዛቡና እርስ በርስ የሚጋጩ ሐሳች መካከል ለመጥቀስ ያህል፣ ብሔር (Nation) ብለው ካስቀመጡ/ከገለጹ በኋላ፣ ‹‹በጋራ የባህል ማንነት ላይ የጋራ ፖለቲካዊ ዕጣ ፈንታ ሲጨመር የፖለቲካ ማኅበረሰብ (Nation) ይወለዳል›› ይላሉ፡፡ እንዲሁም የትግል ሥልቶችን ሲያብራሩ፣ ‹‹የጋራ ፖለቲካ ማኅበረሰብ ሳይፈጠር ብሔርተኝነት ስለማይኖር፣ ቢሞከርም ስለማያብብ›› በማለት የ‹‹ብሔርተኝነት››ን ምንነት ሲገልጹ ደግሞ፣ ‹‹ብሔርተኛ ለመባል የራስ አገር ግንባታ ግዴታ አይደለም (It Is Not A Mandatory Definitional Element)›› ይሉናል፡፡
ለወደፊታችን
ብሔር ወይም ብሔርተኛ የሚለውን ቃል እንዲሁም ሌሎች የተዛቡ ቃላትን በመለየትና ትክክለኛ ብያኔና ትርጓሜውን በመገንዘብ ለትክክለኛው ዕሳቤ መጠቀም፣ እንዲሁም የጎጠኛ ፖለቲከኞች የፈጠራ ብያኔን ካለመቀበል/ካለመጠቀም ጀምሮ የየራሳችንን ሚና እንድንወጣ በዚሁ አጋጣሚ ለመላ ኢትዮጵያውያን ወንድም እህቶቼ ጥሪ ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡ አገርን መጠበቅ ከዚህ ዓይነት ትንሽ ከሚመስሉ አገራዊ የቋንቋ ብያኔና ትርጓሜዎችን መጠበቅና ማስጠበቅ ጭምር ነው፡፡ በብሔርተኞችና በጎጠኞች መካከልም ከሚደረጉ ወሳኝ ትግሎችም እንደ ማንኛውም ተፎካካሪ የሥልጣን/የኃይልና የገንዘብ የመቆጣጠር ትግል ነው!!!
አገር እንድትቀጥል ለህልውና ትግል ብቻ ሳይሆን ብሔርተኝነት ለአገር ልማት፣ ዕድገትና ለማይቋረጠው አገረ መንግሥት ግንባታም ወሳኝ ሚና የሚጫወቱና የሚያስፈልጉ በመሆናቸው፣ ብሔርተኞች በአገር አቀፍ ደረጃና መጠን መጎልበትና መጠንከር እንዲሁም መብዛት ይኖርባቸዋል፡፡ አንድ አገር ብሔርተኞች ባሏት መጠን የወደፊት ዕጣ ፈንታዋ ይወሰናል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
መውጫ
ጸሐፊው ባቀረቡት ጽሑፍ ውስጥ ያሉኝ ልዩነቶች ብዙ ቢሆኑም፣ በብሔርና በብሔርተኝነት ትርጓሜ ላይ አተኩሬ መከተቤን ማሳወቅ እወዳለሁ፡፡ ቀሪ ልዩነቶቼን በይደር አስቀምጫለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው henokinside@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡