በገለታ ገብረ ወልድ
አገራችን አሁን የምትገኝበት ፖለቲካ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ብዙም የሚያስደስት አይመስለኝም፡፡ እውነት ለመናገር በለውጥ ጅማሮው ሰሞን የነበረው የብዙኃኑ ዜጋ ተስፋም እንደ ጉም እየበነነ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የአገራችን ምጣኔ ሀብት በእርስ በርስ ሁከትና ግጭት፣ በኮሮና ወረርሽኝ ጫናና በለየለት ጦርነት ከመመታቱ ባሻገር፣ የኑሮ ውድነትና ተረጂነት ይበልጥ ጎድተውታል፡፡ ከእነ ጉድለቱ ተጀማምሮ የነበረው ፈጣን ልማትም ግለቱን ጠብቆ እየሄደ እንዳልሆነ የታወቀ ነው፡፡
ከእንዲህ ያለው ሥጋት ተነጋግሮና ተጋግዞ ለመውጣት እንዳይቻል ደግሞ የብሔር ውዝግብ፣ የሃይማኖት ሽኩቻና የፖለቲካ ስግብግብነት ሊያባላን ጫፍ የደረሰ መስሏል፡፡ መደማመጡም በጥላቻና መካረር ተበርዟል፡፡ ለዚህም ነው የወገኖቻችን ሞት፣ ስቃይና መከራ ብሎም መፈናቀልና ተስፋ መቁረጥ በሰብዓዊነት መሥፈርት እጅግም ሲያሳዝነንና ለመደጋገፍ ሲያነሳሳን የማይታየው፡፡ ወቅታዊው የቦረናና አካባቢው የድርቅ አደጋም የገጠመው አንዱ ፈተና ይኼው ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚትዎሮሎጂ ኤጀንሲ ከወራት በፊት ይፋ ያደረገው መረጃ እንደ የሚያመለክተው ከ1900 እስከ 2014 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ዓመታት 29 ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ ኤልኒኖ ድርቅ አስከትሏል። ከኤልኒኖ በተጨማሪም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት 30 ዓመታት ተጨማሪ የድርቅ አደጋዎች በአገሪቱ ላይ ተከስተዋል። ባለፉት 32 ዓመታት ውስጥም ቢሆን ድርቅና ተያያዥ አደጋዎች የአገራችን ሥጋት ሆነው ያለፉበት ጊዜ ትንሽ አይደለም፡፡
በኢሕአዴግ 27 ዓመታት የአገዛዝ ምዕራፎች እንኳን እንደ አገር ትግሉ ከድህነት ጋር ነው እየተባለ ከተረጅነት ያልወጡ በአሥር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በየዓመቱ ለችግር ይጋለጡ ነበር። አሁን ደግሞ ትግሉ ከብሔርተኝነት፣ ከሰላም ዕጦትና ከአክራሪነት ወይም ከጥራዝ ነጠቅነት ጭምር ጋር እንደ መሆኑ አደጋውን ይበልጥ አስፈሪ ማድረጉ አይቀርም፡፡ በየከተማው ያልታየውና የተድበሰበሰው ድህነትና ችግርም እየተጠራቀመ አደጋ መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡
የፌዴራል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኤጀንሲ ኮሚሽን ባወጣው የቅርብ ጊዜ መረጃ በግጭትና ሥጋት ከሚፈናቀለው ሌላ፣ በአሁኑ ወቅት ከስምንት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ፈላጊ መሆናቸውን አስታውቋል። ከወራት ወዲህ በኦሮሚያ ክልል ቦረናና አካባቢው ተባብሶ ከታየው ድርቅ አኳያ ደግሞ ይህ አኃዝ ከፍ ሊል እንደሚችል በርካቶች ተናግረዋል።
ይህ አኃዝ በራሱ ከፍተኛ ሲሆን በቀጣይ በሶማሌ ክልል ድርቁ ተባብሶ ሊቀጥል እንደሚችልም ግምታዊ ትንተና አለ፡፡ በተለይ ከቦረና ዞን ጋር የሚዋሰነው ዳዋ ዞን ከ7‚000 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች ያሉት ሲሆን፣ ለሦስት ዓመታት አካባቢው በአጋጠመው ድርቅ እንስሳቱ ሙሉ በሙሉ አልቀው በድርቅ የተጎዱ በርካታ ዜጎችም ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን የዞኑ መስተዳድር ሰሞኑን መናገሩን በዚሁ ጋዜጣ ተዘግቧል፡፡
ከሶማሌ ክልል (ባለፈው ዓመት በ11 ዞኖች ከአንድ ሚሊዮን በላይ የቁም እንስሳት በድርቅ ማለቃቸውን ልብ ይሏል) በተጨማሪ በአፋር ክልል ድርቁ ሊከፋ እንደሚችል ግምቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በደቡብ ኦሞ ሐመር ወረዳ አካባቢም የከፋ ሥጋት ማንዣበቡ አይዘነጋም፡፡ በኦሮሚያ ክልል (በአሁኑ ወቅት ብቻ ከአራት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለረሃብ ሥጋት የተጋለጠበት ክልል ነው)፣ በአማራ ክልልም ተጨማሪ የድርቅ ሥጋት ማንዣበቡ አይታበልም፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ የሰላም ዕጦቱና መናቆሩ ተባብሶ ያለው ደግሞ በእነዚሁ አካባቢዎች መሆኑ ነገሩን እንዳያባብሰው ተሠግቷል፡፡
በመሠረቱ ድህነትን፣ ረሃብንም ሆነ ድርቅን ለመቋቋምና ለመታገል አስፈላጊውና ቀዳሚው ጉዳይ ሥራና የሥራ ተነሳሽነት መፍጠር ብቻ ነው። ሰው በአገሩ በነፃነት ተንቀሳቅሶና በሰላም ወጥቶ ገብቶ መሥራት ካልቻለ ደግሞ ሥራ ሥራ ማለት አይቻልም፡፡ ቁጠባው፣ መተባበሩና ፈጠራን ማሳደግ መቻሉ የሚመጣው ደግሞ በኋላ ነው፡፡ ስለሆነም ድርቅና ድህነትን ለመግታት ጠላታችን ያለው እዚሁ እጉያችን ሥር ነው ብሎ በአንድነት ከመነሳት ውጭ አማራጭ ሊኖር አይችልም። የትኞቹም ችግሮች ዘርና ሃይማኖት ለይተው አይመጡም፡፡ ያለንን ሀብት በአግባቡ ሳንጠቀም፣ ለመጠፋፋት ስንሻኮት ተራ በተራ ያጠቁን እንደሆን እንጂ አንዱ ተቸግሮ ሌላው ሊተርፍ አይችልም፡፡ ስለዚህ እንደ መንግሥት ብቻ ሳይሆን እንደ ሕዝብም መንቃት ያስፈልጋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገራችን ሌሎች ብዙ ችግሮች ቢኖሩብንም፣ ድህነት ከሁሉም የከፋ ጠላት ነው። ይህች አገር የኢትዮጵያዊያን የጋራ ቤታቸው በመሆኗ በሚገጥማቸው የጋራ ጠላት ላይ ልዩነቶቻቸው ትዝ ሊላቸው አይገባም፡፡ በኢፍትሐዊነት የሌላውን ድርሻ ጭምር ለማግበስበስ ከመመኘት ይልቅ፣ እጅ እግርን ከዶማና አካፋ ጋር ማስተሳሰርና በጎደለበት ካለበት ላይ የመሙላት የመቻቻልና የመደጋገፍ ዘመቻ ነው የሚያስፈልገን። የቀንድ ከብት ሀብት ምንጭ የሆነውን የቦረናና አካባቢው አደጋንም ሆነ ሌላውን መታደግ የምንችለው በዚሁ መደጋገፍ ብቻ ነውና፡፡
ለዚህ ግን ቅድሚያ ጥላቻና ጽንፈኝነትን መቅረፍና መደማመጥ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ዘመን ከመጠን በላይ ኢትዮጵያዊነትን የሚሸረሽሩ ብዙ አስቸጋሪ ነገሮች አሉ፡፡ የትናንቱን የሕዝባችንን የአገር ፍቅርና ታላቅ የአርበኝነት ስሜት የሚያደበዝዙ፣ ከአገራዊ አንድነት ይልቅ ማንነት ላይ ብቻ በመንጠልጠል ግራ ተጋብተው ግራ የሚያጋቡ ፖለቲከኞችና አንቂ ተብዬዎች ሞልተዋል፡፡ የመንግሥት አቋምና የትግል ሥልት ግልጽ አለመሆኑም በአገር ግንባታው ላይ ጥርጣሬ አጭሯል፡፡
አለመታደል ሆኖብን እንጂ ያውም ከእነዚያ ሁሉ ፈተናዎች በኋላ ኢትዮጵያዊነት ፍቅር፣ ታጋሽነት፣ አርቆ አስተዋይነት፣ ርህራሔ፣ ጀግንነት፣ መከባበር፣ ወዘተ. ያሉበት ትልቅ የጋራ እሴት መሆኑ ከቶም ሊዘነጋ ባልተገባ ነበር፡፡ ይህች አገር ከዚህ በኋላ በዓለም ፊት ልትዋረድ ከሆነ ድህነትን ማሸነፍ ካቃታት ብቻ ነው ብሎ የሚነሳ መንግሥትና ትውልድም ሊገነባ ግድ የሚል ሆኗል።
በአገርና በኢትዮጵያዊነት ቀልድ የለም፡፡ ኢትዮጵያዊነት መከበር አለበት ሲባል ለአገራቸው ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ የሚያደርጉ፣ በክፉ ጊዜ ደራሽ የሆኑና እንደ አያት ቅድመ አያቶቻቸው ለአገራቸው ቀናዒ የሆኑ ዜጎች ያስፈልጉናል ማለት ነው፡፡ ለዘመናት በላይዋ ላይ ሲጋልቡ ከኖሩት ድህነት፣ በሽታ፣ ማይምነት፣ ኋላቀርነትና ተስፋ መቁረጥ ጋር ተፋላሚ የሚሆኑ ዜጎች ያስፈልጉናል ማለት ነው። ግን ይኼን በጎ እሳቤ እንዴት እናምጣው ብሎ መጨነቅና ለለውጥ መነሳሳት ያስፈልጋል፣ የግድም ነው፡፡
በአሁኑ አካሄድ መንግሥት የተያያዘውን የለውጥ ጅምርም ሆነ አገር የማረጋጋት ሥራ ብሎም የፀረ ድህነት ዘመቻ እየተፈታተኑ ከሚገኙ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች መካከል ድርቅ የመጀመርያውን ረድፍ እየያዘ መምጣቱ አይቀርም። ስለሆነም ለፖለቲካ ትርፍ ብቻ ሲባል ከሚደረጉ ኋላቀር አስተሳሰቦችና አንድም ዕርምጃ ከማያራምዱ ድርጊቶች በመላቀቅ በመፍትሔው ላይ መሥራትና ለጊዜውም ቢሆን መደጋገፍ ዋነኛው ሥራችን መሆን ነው ያለበት፡፡
ድርቅን እንደ አገር በአንድ ጊዜ ጨርሰን ማስወገድ ባይቻለን እንኳ፣ ከውቅያኖሶች ሙቀት መጨመር ጋር ተያይዞ የሚመጣን ክስተትና ተያያዥ ችግሮችን መቋቋም የምንችለው ለአየር ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት ስንችል ብቻ ነው፡፡
የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ዳፋውን ያሳረፈው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ድህነት ጎጆውን በሠራባቸው አገሮች ላይ ሲሆን፣ በተለይ ኢኮኖሚያቸውን በግብርና ላይ በመሠረቱ አገሮች ላይ መሆኑን ዓለም በተገነዘበበት ሰዓት ወደ መፍትሔው መሮጥ እንጂ፣ ለፖለቲካ ትርፍ አቃቂር ማውጣት ኋላቀር ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን ሌላኛው ጠላትነት ነው።
ስለሆነም የቤት ሥራችንን በሚገባ መሥራትና በተለይም የሞላለት ላልሞላለት ሦስቴ የሚበላ አንዱን ባዶ ቤት ለሆነው በማገዝ፣ ይህንን ክፉ አጋጣሚ ማለፍ ወሳኙና ቁልፉ ተግባራችን ሊሆን ይገባዋል። ኢትዮጵያዊነትን ማቀንቀንም በእንዲህ ዓይነት ፈተናዎች የሚገለጽ እንጂ ባዶ ትምክህት ሊሆን አይገባም። አሁን በተያዘው የብሔር ውዝግብና መራኮት ግን ረዥም ርቀት መሄድ የሚቻል አይሆንም፡፡ በተለይ እንደ መንግሥት ትኩረት የሚሰጠውን ቁምነገር መለየት ከተቻለ ዙሪያው ገደል መሆኑ አይቀርም፡፡
አሁን በኦሮሚያና የደቡብ ቆላማ አካባቢዎች በርካታ እንስሳትን ለዕልቂት የዳረገውን በድርቅ ምክንያት የተከሰተውን የውኃ እጥረትም ሆነ የእንስሳት መኖ፣ እንዲሁ ተጋግዞና ተደጋግፎ መሻገር ይገባል። ለድርቅ ምክንያት የሆነን ኤልኒኖ የድንገቴ ዝናብ ምክንያት መሆኑም ይጠበቃልና የውኃ ማጠራቀሚያ ኩሬዎችን ተረባርቦ መቆፈርም እንዲሁ። በዚህ ረገድ ሁሉም መንግሥታዊ ተቋማት ከላይ እስከ ታችና የሚመለከታቸው የረድኤት ድርጅቶች መረባረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ከሁሉ በላይ ግን ለዘላቂ መፍትሔው ኅብረተሰቡ ከመንግሥት ጋር በመቀናጀት በአካባቢ ጥበቃ ሥራ ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሆኖ እንዲገኝ ማድረጉ ላይ ነው። ድንገቴውን ዝናብ ተከትሎ በጎርፍ የሚጠቁ አካባቢዎችን ሥጋት ለመቀነስና ለድርቅ አካባቢ የሚሆንን ማካካሻ ለማትረፍ የእርጥበት ዕቀባ ሥራም ቁልፍ ተግባር መሆን አለበት። ለታይታ ሳይሆን ለውጤት የግድ፡፡
ድርቅ በተደጋጋሚ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች ላይ ዛሬም ዋናው ችግር የግብርና ሥራው ኋላቀር ከመሆኑ ጋር የተያያዘ መሆኑም መረሳት የለበትም፡፡ ይህ ደግሞ በየጊዜው ከአየር ንብረት መዛባት ጋር ተያይዞ የሚገጥሙንን ችግሮች በአስተማማኝ ሁኔታ ለመቋቋም ይረዳል፡፡ ሕዝቡን ከድህነት የሚያላቅቅ በሒደትም የበለፀገ አገር ለመገንባት የሚያስችልና የግብርና ልማትን የሚያፋጥን ፖሊሲና ስትራቴጂ እንደ አገር ከልሶ መረባረብም ግድ ይላል፡፡
መንግሥት ለግብርናና ለገጠር ልማት ሥራዎችና ለገጠሩ ኅብረተሰብ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ መገኘቱ የማይተበል ሀቅ ቢሆንም፣ በመንግሥት ዕቅድና ፍላጎት ልክ ዛሬም ሥራዎች እየተከናወኑ አይመስልም። የግብርናና የገጠር ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂው ያለንን የልማት አቅም ማለትም ሰፊ ጉልበት፣ መሬትና ውኃ ውስን ካፒታል በቁጠባ ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑን መዘንጋት ለእንዲህ ያለ አደጋ ከሚያጋልጡን ምክንያቶች መካከል አንዱ መሆኑን ተገንዝቦ በአቅጣጫው አግባብ መሥራት ያስፈልጋል።
የልማት አቅሞቹን የማነቃነቅና ውጤታማ ተሞክሮዎችን እየቀመሩ የማስፋት ሥራ ማከናወን ዘላቂነት ያለው የድርቅ መፍትሔ ነው፡፡ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት፣ የግብዓትና ሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂዎች አቅርቦት እየተሻሻለና ለእንስሳትና ለሰው የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ሽፋንና ተደራሽነት እየጨመረ መምጣቱን ታሳቢ ያደረገ የአኗኗር፣ የአመራረትና የአረባብ ዘይቤንም ጭምር መቀየር ያስፈልጋል፡፡
እስካሁን ባለው ሁኔታ በበልግ ወቅት የሚጠበቀው የዝናብ ሥርጭት የሚጠበቀውን ያህል አይደለም፡፡ በዚህም በበልግ ዝናብ አምራች የሆኑ አካባቢዎች የምርት መቀነስ እንደ ሚጠብቃቸው በመገመቱ፣ በድርቅ የተመቱትን አካባቢዎች ይበልጥ ሥጋት ውስጥ እንደ ከተታቸው ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት የወጡ ሪፖርቶች ይፋ አድርገዋል፡፡ በዚህ ሳቢያ በድርቅ የተመቱ የአርብቶ አደር አካባቢዎች የማገገም ተስፋቸውን ጥያቄ ውስጥ እንደ ከተተው የሚያመለክቱት ደግሞ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ የትንበያ መረጃዎች ነበሩ፡፡
በበልግ ዝናብ በመታገዝ ከሚያመርቱ አካባቢዎች መካከል የደቡብና የደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ክፍሎች በአብዛኛውም የደቡብ ሶማሌ ክልል፣ በኦሮሚያ የቦረና ቆላማ አካባቢዎች፣ የጉጂና የባሌ ዞኖች፣ እንዲሁም የደቡብና የአፋር ክልሎች እንደ አዲስ ባገረሸው ድርቅ ተጎጂ መሆናቸው ሲታወቅ፣ ከየካቲት አጋማሽ እስከ ግንቦት ወር በሚኖረው የበልግ ወቅት የሚያገኙት ዝናብ ደካማ እንደሚሆን በመገመቱ፣ የማገገም ዕድላቸውን አሳሳቢ ያደረገው ስለመሆኑም መረጃዎቹ አመልክተዋል፡፡
በእነዚህ አካባቢዎች እንደሚኖር የሚጠበቀው ደካማ የዝናብ ሥርጭት፣ ከሚጠበቀውና መደበኛ ከነበረው ዝናብም ያነሰ እንደሚሆን የሚያመላክቱት መረጃዎች ለበልግ ሰብሎች ታስቦ የሚደረገውን የመሬት ዝግጅትም ሆነ የሰብል መዝራት ተግባር በእጅጉ እንደሚጎዳው ይጠቅሳሉ ባለሙያዎቹ፡፡ የውኃ አቅርቦትንና እርጥበትን በመቀነስ በሚያሳድረው ተፅዕኖ ሳቢያም ዜጎች ለምግብ እጥረትና ለተመጣጠነ ምግብ ዕጦት እንዲዳረጉ ምክንያት በመሆኑ፣ ቀድሞውንም በድርቅ የተጎዱትን ይበልጥ ጉዳት ላይ እንዳይጥላቸው ሥጋት ፈጥሯል፡፡
በመሆኑም መንግሥት እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ዘንድሮም ለተረጂዎች የሚያስፈልጉትን የምግብ እህል፣ አልሚ ምግብና ዘይትን ጨምሮ ሌሎችንም ቁሳቁሶች በቀዳሚነት በራስ አቅምና በሕዝብ ተሳትፎ ማቅረብ አለበት። ለእንስሳት ሀብቱም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ለሕይወት አድን ሥራ መረባረብ ግድ የሚለው ሆኗል። የራስን ድርሻ ሳይወጡ ሌላውን ድረሱልኝ ማለትና በማያዋጣው የውዝግብ ትርክት ጊዜን ማባከን ግን ከታሪክ ተጠያቂነት አያድንም፡፡
የአሁኑን ካለፉት ዓመታት ለየት የሚያደርገው የድርቁ አጠቃላይ አዝማሚያ የእንስሳት ሕይወትን በስፋት ሊቀጥፍ የሚችል መሆኑ ነው። ይህን ችግር ለመቅረፍ ደግሞ የመኖ አቅርቦት እየተዘጋጀ ሲሆን፣ እንስሳቱም ለገበያ እንዲቀርቡ እየተደረገ መሆኑን በተለይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሲገልጽ ተደምጧል፡፡ ሙከራው መጠንከር አለበት፡፡ በተለይ ደግሞ እንስሳቱን መኖ ወዳለባቸው አካባቢዎች ከማጓጓዝ ጀምሮ መኖ ያላቸው ክልሎችና አጎራባች ዞኖች የሕዝብ ለሕዝብ ድጋፍ በማድረግ፣ ድርቁን በጊዜያዊነት ለመቋቋም ሲደረግ የቆየው የቀደመው ጥረት መቀጠል አለበት።
አሁን የሰላምና መረጋጋቱ ሁኔታ ሌላ ሥጋት ቢሆንም ድርቅን በዘላቂነት ለመቋቋም የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችና በተሞክሮነት ሊወሰዱ የሚገባቸው ተግባራት እየተከናወኑ ካሉባቸው አካባቢዎች ኦሮሚያ በቀዳሚነት ይጠቀስ ነበር። የኦሮሚያ ክልል ባሌና ምዕራብ አርሲ ዞኖችን ሥነ ምኅዳር ለመጠበቅ ሲተገበር የቆየው ሼር የተሰኘ ፕሮጀክት 12 ሚሊዮን የአካባቢ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማደረጉን ከሰማን ገና አሥር ዓመታት እንኳን አልተቆጠሩም። ይህን ማስፋት ለምን አልተቻለም ነው ዋናው ቁምነገር፡፡
በወቅቱ የፕሮጀክቱ ዓላማ እየጨመረ የመጣው የሕዝብ ብዛት በባሌ አካባቢ ሥነ ምኅዳር ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት በጥናት በመለየት የመፍትሔ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱ ማድረግና የአካባቢውን ነዋሪዎች የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ነው። ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ ከአውሮፓ ኅብረት የተገኘ 5.5 ሚሊዮን ዩሮ ተመድቦ የነበረ ሲሆን፣ በ40 ወራት ለማጠናቀቅ ነበር የታቀደው። ውሾን ያነሳ ውሾ ሆኖ የቀረ ቢሆንም፡፡
ሌላው እንዲህ ያለውን የድርቅ አደጋ በዘላቂነት ለመቋቋምና ለመቀነስ በአየር ትንበያ ላይ ያተኮረ ሥራ ማከናወን እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ልሂቃን ሲናገሩ የመቆየታቸው እውነታ ነው። የኢጋድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ፣ ‹‹በአፍሪካ ቀንድ እ.ኤ.አ. በ2016/17 ለደረሰው አስከፊ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ መስጠት›› በሚል መሪ ሐሳብ አዲስ አበባ ላይ ባደረገው ጉባዔ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) አባል አገሮች የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ አሁን እያደረጉት ካለው እንቅስቃሴ በተጨማሪ፣ የአየር ትንበያን መሠረት በማድርግ መሥራት ይኖርባቸዋል የሚለው ሐሳብ ገኖ መውጣቱም የሚዘነጋ አልነበረም። ለዚህም ትኩረት መስጠት ያሻል፡፡
የኢጋድ አባል አገሮች የድርቅና ረሃብ ችግር ለመቀነስ ከየአገሩ የሚቲዎሮሎጂ ድርጅቶች የሚሰጠውን መረጃ በመቀበል ከባለድርሻ አካላት ጋር መሥራት ይኖርባቸዋል የሚለው ምክረ ሐሳብ መቼም ቢሆን ሊጣል አይችልም (መረጃዎች እንደሚያሳዩት በ2010/11 በአፍሪካ ቀንድ 13 ሚሊዮን ዜጎች በድርቅ የተጠቁ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር በማሻቀብ በ2016/17 ወደ 17 ሚሊዮን ደርሷል)፡፡ አሁን በምንገኝበት የ2022/23 የምርት ዘመንም ቁጥሩ ወደ 22 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ ይኼ ደግሞ በአካባቢው መሻሻል ሳይሆን የድርቅና የድህነት መባባስን አመላካች ነው፡፡
በአጠቃላይ በሽኩቻ ላይ ድርቅ በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ መሆኑን ተገንዝቦ፣ ከምንም ሆነ ከየትኛውም ጉዳይ በላይ ሕዝብ ለማዳን መረባረብ ይገባል እላለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፣ ጽሑፉ የጸሐፊውን የግል አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡