በአገኘሁት ቁጥር በጣም የሚያስደምመኝ አንድ መለስተኛ የአዕምሮ ሁከት ያለበት ጎረቤቴ ነው፡፡ ይህ ሰው የሚኖረው ከታናሽ ወንድሙ ጋር ሲሆን፣ ከአርባ ምናምን ዓመታት በፊት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአራተኛ ዓመት የፍልስፍና ተማሪ ነበር፡፡ በዘመነ ደርግ በነበረው የቀይና የነጭ ሽብር ፍጅት ጊዜ ሕይወቱ ተርፎ፣ በማዕከላዊ ምርመራ ፍዳቸውን ካዩ የዘመኑ ወጣቶች መካከል አንዱ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ በማዕከላዊ ምርመራ የማሰቃያ ክፍሎች ውስጥ በደረሰበት ቶርቸር ለአካላዊና ለአዕምሮአዊ ጉዳት የተዳረገው ይህ ሰው፣ አሁን የአፍሪካ ኅብረት ዘመናዊ ሕንፃ ተንጣሎ በቆመበት ከርቸሌ በሚባለው እስር ቤት ለስምንት ዓመታት ማቋል፡፡
ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን የኢሕአፓና የመኢሶን፣ እንዲሁም የደርግ ትልልቅ የሚባሉ ሰዎችን አንድ በአንድ ታሪካቸውን ሲዘረዝርና በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲተነትን አፍ ያስከፍታል፡፡ በመሀል ዘብረቅ የሚያደርጋቸው ነገሮችም አሉት፡፡ ጤነኛ ሆኖ በርካታ ነገሮችን ሲያነሳ ደግሞ ይህ ሰው የሚናገረው ምናለበት ተቀርፆ ወደ ጽሑፍ ቢቀየር እላለሁ፡፡ እኔ በበኩሌ ምናልባት ከሕይወት ተፈራ ‹‹ታወር ኢን ዘ ስካይ›› እና ከታደለች ኃይለ ሚካኤል (አምባሳደር) ‹‹ዳኛው ማነው?›› በሚሉ ርዕሶች ከተጻፉት መጻሕፍት በስተቀር፣ የዚህን ሰው ያህል ሚዛናዊና አስተዋይ የዚያን ዘመንን ታሪክ የሚተርክ አላየሁም ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡ ይህ ሰው ተቀርፆ ቢያንስ ድምፁ እንዲቀመጥ ቢደረግ ብዬ ለወንድሙ (ታዋቂ ሐኪም ነው) ሐሳብ ባቀርብለትም፣ ‹‹መልሰን እዚያ ታሪክ ውስጥ ብንከተው ዕድሜውን ከማሳጠር ውጪ አይጠቅምም፡፡ ደስ ሲለው ያውራ፣ አንተ ከቻልክ ማስታወሻ ያዝ ወይም በድብቅ ቅረፀው እንጂ አትገፋፋው…›› ስላለኝ ቀስ እያልኩ ለትውልድ የሚሆን ነገር እያስወራሁት ነው፡፡
ከቀድሞው ታሪኩ ላስወጣችሁና ይህንን ወንድሜን አሁን ስላለው የአገራችን ሁኔታ ምን እንደሚሰማው ስጠይቀው፣ ‹‹በዚህ ዓለም ላይ ምንም አዲስ ነገር የለም፡፡ ድሮ ገባሪ የነበረው ዛሬ አስገባሪ ለመሆን ቢያምረው አይግረምህ፡፡ ትናንት የአለቆቹን ሳምሶናይት ይዞ ይከተል የነበረ አሽከር ጊዜ አግኝቶ ቦታ ሲደላደልለት፣ እሱም የእጅ ቦርሳውን ወይም ካፖርቱን የሚሸከምለት አሽከር መፈለጉ አይቀሬ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የበዳይና የተበዳይ ትርክት የሚጦዘው ለምን እንደሆነ ሊገባህ ይገባል፡፡ ሕዝቡን ከዳር እስከ ዳር ተመልከተው፡፡ ሁሌም እንደ ኩሬ ውኃ ረግቶ ነው የሚኖረው፡፡ ነገር ግን ጥቂት ብልጣ ብልጦች የሚፈልጉትን ነገር ለማሳካት ሲፈልጉ ረግቶ ያለውን ኩሬ ይነካኩታል፡፡ በራሳቸው ትርክት ውስጥ በመክተት ያልበላውን ያሳክኩታል፡፡ በተለይ ወጣቱን ግንፍል ስሜቱን በዘዴ በመቀስቀስ ልክ እኛ የማናውቀውን ርዕዮተ ዓለም ተጠምቀንበት አገር እንዳተራመስነው ለዓላማቸው ስኬት ይጠቀሙበታል…›› ብሎኝ ፈገግ አለ፡፡
‹‹እኛ ሶሻሊዝም ኢትዮጵያን የምድር ገነት ያደርጋል ብለን ኢንተርናሲዮናልን ዘምረን ከዓለም ኮሙዩኒስቶች ጋር እንዳበርነው ሁሉ፣ ዛሬ ደግሞ ኢትዮጵያዊ የሚባለው ማንነት፣ አፍሪካዊነትና ዓለም አቀፋዊነት እየጠፉ ብሔርተኝነት እየገነነ ያለው፡፡ ይኼ አዲስ ነገር አይምሰልህ፡፡ በእኛ ዘመን እኛ ኢትዮጵያን በአፍሪካ የሶሺሊዝም ኮከብ ለማድረግ ስንፈጋ፣ የስታሊንን ፈለግ የተከተሉ ብሔርተኞች ደግሞ የሄዱበትን ርቀትና ያመጡብንን መዓት ታውቀዋለህ፡፡ እኔ የኢሕአፓ አባል የሆንኩት አገሬ በዓለም ሀብታምና ሥልጡን እንድትሆን እንጂ፣ በብሔር ተከፋፍላ የማንም መጫወቻና መቀለጃ እንድትሆን አልነበረም፡፡ በጣም በርካታ ስህተቶችን ብንፈጽምም አሁንም ድረስ ብዙዎቻችን ለአገራችን ያለን ፍቅር የተለወጠ አይመስለኝም ብዬ አስባለሁ…›› በማለት አሁንም ለአፍታ ዝም አለ፡፡
አንድ የሚከነክነኝ ነገር ስላለ፣ ‹‹ያለፈው ትውልድ የሚባለው እንኳን በሩቁ በራሱ ታሪክ የማይግባበው ለምንድነው?›› በማለት ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ ‹‹ቅድም ምን አልኩህ? በዚህ ዓለም ምንም አዲስ ነገር የለም ነው ያልኩህ፡፡ ከድሮ ጀምሮ ታሪካችን የተመሠረተው በአብዛኛው በውሸት ላይ ነው፡፡ የተሳሳተ ታሪክ ሲጋት የኖረ ትውልድ ራሱም መልሶ የተሳሳተ ታሪክ ቢያስተላልፍ አይግረምህ፡፡ በዘመነ ደርግ በተፈጸመ ታሪክ ላይ የሚጻፉትን ሳነብ፣ በጣት ከሚቆጠሩት በስተቀር አብዛኞቹ በውሸት የተሞሉ ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ እኔ የማውቀው የኢሕአፓ ታሪክ ውስጥ ብዙዎቹ የፈጸሙት ሸፍጥ ያሳቅቀኛል…›› ካለ በኋላ፣ ‹‹ሌላው ቀርቶ እኮ ዓለም በሚያውቀው በዓድዋ ድል ላይ እንኳን እየተደረገ ያለውን መሰሪነት አትታዘብም እንዴ? በመርህ አልባ ፖለቲካ ታሪክን ማዛባት፣ ትውልዱን ውሸት መጋት፣ ማደናገርና የሌለን እንዳለ አድርጎ በማቅረብ ማስመሰል የዘመኑ ሌላው ድራማ እየሆነ ነው…›› ብሎኝ የቀረበለትን ቡና በተመስጦ ውስጥ ሆኖ መጠጣት ጀመረ፡፡
ከእንዲህ ዓይነቱ ወጣ ገብ ነገር ውስጥ ለመውጣት ምን ያስፈልግ እንደሆነ ላቀረብኩለት ጥያቄ የሰጠኝ ምላሽ፣ ‹‹ለእያንዳንዱ ጅማሬ ፍፃሜ እንዳለው ሁሉ፣ እያንዳንዱ ፍፃሜም የራሱ መጀመሪያ ነበረው፡፡ እያንዳንዱ ትውልድ የራሱ የሆኑ ፈተናዎች አሉት፡፡ አንዳንዶቹ ፈተናዎች በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ሒደት ሊቃለሉ ይችላሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላው ይሸጋገራሉ፡፡ ትውልዱ በራሱ ጊዜ የሚፈታቸው ሲኖሩት ወደ ሌላ ትውልድ የሚያስተላልፋቸው አሉ፡፡ የእኛም ችግሮች ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የመጡ ስለሆኑ፣ የምንችላቸውን ማቃለል የማንችላቸውን ደግሞ ወደ መጪው ማሸጋገር ግዴታችን ነው፡፡ እዚህ ላይ ዋናው ቁምነገር ባለፉት አወዛጋቢ ታሪኮቻችን ላይ ዕድሜ ልካችንን ከምንነታረክ፣ የራሳችንን አኩሪ ታሪኮች ሠርተን ለመጪው ትውልዳችን በጎ ነገሮችን ለማቆየት ጥረት ብናደርግ በምድርም በሰማይም የሚጠቅመን ይመስለኛል፡፡ የአሁኑ ትውልድ ከፈተናዎቹ በላይ ያሉትን መልካም አጋጣሚዎች ቢጠቀምባቸው፣ እንኳን ለኢትዮጵያ አገራችን ለአፍሪካ የሚተርፍ በረከት ይኖረው ነበር…›› የሚል ነበር፡፡
ይህ ለረጅም ዓመታት የአዕምሮ ሁከት የሚያስቸግረው ወገናችን ይህንን የመሰለ አስደማሚ ዕይታና ምክረ ሐሳብ ማቅረብ ከቻለ፣ እኛ ጤነኛ የምንባለው ምን ነክቶን ነው አገራችንን የደም ምድር ለማድረግ የምንንፈራገጠው? ለምን ይሆን በደንታ ቢሶችና በመሰሪዎች ሴራ እየተታለልን አገራችንን ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ አዘቅቱ የምንገፋት? ምን ነክቶን ይሆን መሰሪዎችን በየቀኑ በሚያዘጋጁልን ወጥመድ ውስጥ እየወደቅን የእነሱን ከንቱ አጀንዳዎች የምናግበሰብሰው? በፓን አፍሪካኒዝም ዕሳቤ ከአፍሪካውያን ወንድሞችና እህቶች ጋር አብረን ማደግ ሲገባን፣ በብሔር እየተከፋፈልን እርስ በርስ ለመፋጀት ለምን እናደባለን? ከመጠን ባለፈ ራስ ወዳድነት ሕዝባችንን እየበዘበዝንና ፍትሕ ነፍገን እያስለቀስን፣ የምናፈራው ሀብትም ሆነ ሥልጣን ተከትሎን ወደ መቃብራችን ይመጣል ወይ? ለማንኛውም ፈጣሪ ልቦናውን ይስጠን፡፡
(ዘውድዓለም ነገኦ፣ ከሰሚት)