Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትከኬንያውያን አትሌቶች ፉክክር በላይ በመለማመጃ ዕጦት እየተፈተነ የሚገኘው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ

ከኬንያውያን አትሌቶች ፉክክር በላይ በመለማመጃ ዕጦት እየተፈተነ የሚገኘው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ

ቀን:

የዓለም በርካታ ዕውቅ ጸሐፊያን ለምን የሁለቱ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች አትሌቶች ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ሊቆጣጠሩ ቻሉ? ሲሉ በመጣጥፋቸውና በመጽሐፎቻቸው በመጠየቅ ይጀምራሉ፡፡ በብሔራዊ የሕክምና ቤተ መጻሕፍት (National Library of Medicine) ገጽ ላይ፣ ‹‹የኬንያና የኢትዮጵያን የርቀት ሯጮች ምን አጎበዛቸው?›› በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረበው ራንዳል ኤል ዊልበር የተለያዩ ማሳያዎችን አስቀምጧል፡፡

በዋኛነት ከተዘረዘሩት ስምንት ማሳያዎች መካካል የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች፣ የጄኔቲክ ቅድመ ዝንባሌ፣ በለጋ ዕድሜያቸው በእግር በመሮጣቸው ምክንያት የሚያዳብሩት ከፍተኛ የኦክስጂን አቅም፣ ባህላዊ የአመጋገብ ሥርዓታቸው፣ በከፍታ ቦታ መለማመዳቸው፣ እንዲሁም በኢኮኖሚ ለመበልፀግ ያላቸው ተነሳሽነት በቀዳሚነት ተቀምጠዋል፡፡

በጥናቱም መሠረት በተለይ ሁለቱ አገሮች እ.ኤ.አ. በ1968 የሜክሲኮ ኦሊምፒክ ጨዋታ በመካከለኛ ርቀት፣ በረዥም ርቀት እንዲሁም በማራቶን ውድድሮች በበላይነት መቆጣጠራቸውን ይጠቅሳል፡፡ ከዚያ ጊዜ በኋላም የሁለቱ አገሮች አትሌቶች በዓለም ሻምፒዮና፣ በኦሊምፒክ እንዲሁም በተለያዩ የግል ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በአሸናፊነት በማጠናቀቅ የአገራቸውን እንዲሁም የራሳቸውን የታሪክ አሻራ በማኖር ዛሬም ድረስ ዘልቀዋል፡፡  

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በተለይ አትሌቶቹ የአገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ከማውለብለብ በዘለለ፣ በግል ወደ ቢዝነስ በመግባት የአገር ኢኮኖሚን ማቅናት በመቻል ለተተኪው ትውልድ ሳይቀር በቅብብሎሽ ምሳሌነታቸውን ማስመስከር ችለዋል፡፡

በአንፃሩ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይ በኢትዮጵያ አትሌቶች ልምምድ ማድረግ የሚችሉበት ሥፍራን እያጡ በመምጣታቸው፣ ስፖርቱ እየደበዘዘ እንዲመጣ ዳርጎታል፡፡ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ለኬንያው ኔሽን ጋዜጣ አስተያየቱን የሰነዘረው ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ ሁለቱ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች አትሌቲክስን ታሳቢ ያደረገ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች ግንባታ ማከናወን እንደሚገባቸው ጥሪ አቅርቧል፡፡

እንደ ኃይሌ አስተያየት ከሆነ እነዚህ በረዥም ርቀቱ የሚታወቁ አገሮች መሠረታዊ የሆነ የልምምድ ሥፍራ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በኬንያ የአትሌቶች መፍለቂያ በሆነችው ኤልዶሬት ከተማ የሚገኘው የኪፕቾጊ ኬይኖ ስታዲየም እ.ኤ.አ. በ2012 ጀምሮ ዕድሳት ቢጀመርም እስካሁን መጠናቀቅ አለመቻሉን እንደ ምሳሌነት አንስቷል፡፡

‹‹የአትሌቲክስ የልምምድ ግብዓት በተለይ ምቹ የልምምድ ትራክ ለአትሌቶች ቁልፍ ከመሆኑ ባሻገር፣ ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን አትሌቶችን ታዋቂ እንዲሆኑ ያደረጋቸው መሠረታዊ ነገር ነው፤›› በማለት ኃይሌ አስተያየቱን ሰንዝሯል፡፡

ኃይሌ በርካታ የአውሮፓ አትሌቶች ኬንያና ኢትዮጵያ መጥተው ልምምድ መሥራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጾ፣ ምን ዓይነት መሠረተ ልማት ነው ልናቀርብላቸው የምንችለው? ሲል ይጠይቃል፡፡

‹‹በርካታ የውጭ ዜጎች አንድም ለሽርሽር፣ አንድም ልምምድ ለማድረግ ወደ እኛ የመምጣት ፍላጎት አላቸው፡፡ እኛ ግን በቂ የመለማመጃ ሥፍራ አለን ወይ?›› በማለት ኃይሌ ጥያቄውን ያክላል፡፡

በዚህም መሠረት መንግሥት አትሌቲክሱ ያለውን አቅምና ያለበትን ሁኔታ ተረድቶ የአትሌቲክስ መሠረተ ልማትን ሟሟላት እንደሚገባው ኃይሌ ያነሳል፡፡

በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች የኢትዮጵያና የኬንያ እንዲሁም የዑጋንዳ አትሌቶች በረዥም ርቀቱ መጉላታቸውን ተከትሎ፣ እነዚህ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በርቀቱ ላይ ያላቸውን የበላይነት ይዘው መቀጠል እንደሚገባቸው ኃይሌ አሳስቧል፡፡

ምንም እንኳን ኢትዮጵያና ኬንያ በአትሌቲክስ በተለይም በረዥም ርቀቱ ስማቸው ከፍ ብሎ የሚነሳ ቢሆንም፣ ኬንያ ከኢትዮጵያ በተሻለ መልኩ የአትሌቲክስ መሠረተ ልማት አላት፡፡ ኬንያ በተለያዩ ከተሞቿ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች እንዲሁም የስፖርት ማዕከል ባለቤት ናት፡፡ ከቅርብ ዓመት በፊት የዓለም ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮናን ማስተናገድ ችላለች፡፡

በአንፃሩ ኢትዮጵያ በረዥም ርቀቱ ከኬንያ ጋር ስሟ የሚነሳ አገር ብትሆንም አትሌቶች ልምምድ ማድረጊያ ሥፍራ ካጡ ሰነባብተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ዝግጅት ለማድረግ አትሌቶች በሱሉልታ የሚገኘውን ባለቤትነቱ የቀነኒሳ በቀለ በሆነው የመሮጫ ትራክ በየቀኑ እየከፈሉ ልምምድ ለማድረግ ተገደዋል፡፡ ይህም ክለቦችን እንዲሁም አትሌቶችን ለከፋ ወጪ እየዳረጋቸው እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ከርሟል፡፡

የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህርና በዓለም አትሌቲክስ አንደኛ ደረጃ የአሠልጣኞች ኢንስትራክተር የሆኑት አቶ አድማሱ ሳጂ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ አትሌቶች ለዚህ ችግር መጋለጣቸው በአትሌቶች ላይ ከፍተኛ ጫናን እየፈጠረ ነው፡፡

‹‹አብዛኛውን ጊዜ ልምምድ የሚያደርግ አትሌት ለከፍተኛ ወጪ ተዳርጓል፡፡ ስንቱ አትሌት አቅም ኖሮት እየከፈለ ልምምድ ያደርጋል የሚለው በራሱ ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ የልምምድ ሥፍራ ባለመኖሩ አትሌቶችን ከፍተኛ ጫና ውስጥ ከቷል፤›› ሲሉ አቶ አድማሱ ይናገራሉ፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም በርካታ አትሌቶች በአቅራቢያቸው የልምምድ ሥፍራ ባለመኖሩ፣ ለረዥም ሰዓት በትራንስፖርት በማሳለፍ ለእንግልት እንደሚዳረጉ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያውያን አትሌቶች የመሮጫ ትራክ ማጣት ከኬንያ አንፃር ሲታይ አሳሳቢ ነው፡፡ በኬንያ በርካታ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ተቋማት እንዲሁም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ማናጀሮች ከትመው እየሠሩ እንደሚገኙ አቶ አድማሱ ይጠቅሳሉ፡፡

መንግሥት አትሌቲክስ በኢኮኖሚ፣ በፖሊቲካ እንዲሁም በማኅበራዊ መስክ ያለውን ፋይዳ ተገንዝቦ የተለያዩ የማዘውተሪያ ሥፍራዎች መገንባት እንዳለበት ያስታውሳሉ፡፡

‹‹አትሌቲክስ እንደሌሎች የንግድ ዘርፎች ከአገር ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ሳያስፈልገው፣ ከውጭ ወደ አገር ቤት የውጭ ምንዛሪን የሚያመጣ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ዘርፉ ያለውን አገራዊ ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት ችግሩን መፍታት ይኖርበታል፤›› በማለት አቶ አድማሱ ያክላሉ፡፡

በአንፃሩ ኬንያ በናይሮቢ ዓለም አቀፍ ስፖርት ማዕከልና ናያዮ የተሰኘ ብሔራዊ ስታዲየም ቢኖራትም፣ ተጨማሪ ዓለም አቀፍ ውድድር ለማስተናገድ ዕድሏን አለመጠቀሟ ይነሳል፡፡ በተለይ ኬንያ የ2025 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ለማሰናዳት ውድድር ውስጥ ባለመግባቷ ዕድሉ ለቶኪዮ ዳግም መሰጠቱ የሚያስቆጭ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...