Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናመንግሥት ከጦርነቱ ለማገገም በመጭዎቹ አምስት ዓመታት 20 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል አለ

መንግሥት ከጦርነቱ ለማገገም በመጭዎቹ አምስት ዓመታት 20 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል አለ

ቀን:

  • በጦርነቱ የተሳተፉ 250 ሺሕ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋምና ወደ ኅብረተሰቡ ለመቀላቀል ሥራ ተጀምሯል

መንግሥት ለሁለት ዓመታት ያህል ከተካሄደው ጦርነት ለማገገምና በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ለድኅረ ግጭት መልሶ ግንባታ 20 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው ገለጸ፡፡

የገንዘብ ሚኒስተሩ አቶ አህመድ ሺዴ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ጉብኝት ካደረጉት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ በጦርነቱ ማግሥት የመልሶ ማቋቋም ሥራ ከአገሪቱ የውስጥ ፋይናንስ ምንጭና በዓለም ባንክ ድጋፍ መተግበር ቢጀምርም በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ በነበረው ጦርነት፣ በድርቅ፣ በአንበጣ መንጋና በኮቪድ 19 ወረርሽኝ የተነሳ 20 ሚሊዮን ዜጎች ለዕርዳታ ጠባቂነት እንደተዳረጉ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት በተከሰተ የዝናብ እጥረት ለ40 ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ መከሰቱን አስታውቀዋል፡፡

- Advertisement -

አቶ አህመድ ከውጭ አገሮችና ድርጅቶች የሚመጣው የልማት አጋርነት ድጋፍ መቀነስ ችግሩን እንዳባባሰው አስረድተው፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጉብኝት የኢትዮጵያን የልማት አቅም ሙሉ በሙሉ ይከፍታል ብለዋል፡፡

በብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አማካይነት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ የነበሩ ተዋጊዎችን መልሶ ማቋቋምና ወደ ማኅበረሰቡ የመቀላቀል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ያብራሩት የገንዘብ ሚኒስትሩ፣ ሥራው የሰላም ሒደቱን በሚያግዝ መንገድ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡ አቶ አህመድ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ሁለቱ አገሮች ቁልፍ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የተሻለ ግንኙነት ለመፍጠር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበከሉላቸው፣ መንግሥታቸው ባለፉት አራት ዓመታት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጨምሮ ለሰብዓዊ ዕርዳታ የሚውል ሦስት ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ መስጠቱን ተናግረዋል፡፡  

ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው 13 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የሚውል ተጨማሪ 331 ሚሊዮን ዶላር አገራቸው ለመስጠት ቃል መግባቷን ይፋ አድርገዋል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሳቢያ ለተፈጠረው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት፣ እ.ኤ.አ. በ2022 ብቻ 1.7 ቢሊዮን ዶላር ከአሜሪካ መንግሥት ዕርዳታ መገኘቱን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የአሜሪካው የውጭ ጉደይ ሚኒስትር ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ በሰሜን ጦርነት በተፈጠረው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠያቂነት እንዲረጋገጥና ሁሉን አቀፍ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ እንዲተገበር ጠይቀዋል፡፡ ሚኒስትሩ አክለውም በኦሮሚያ ክልል ያለው ሁኔታ እንዳሳሰባቸው ገልጸው፣ ችግሩ በንግግር እንዲፈታ መጠየቃቸው ታውቋል፡፡

አንቶኒዮ ብሊንከን የጠቅላይ ሚኒስትሩን የደኅንነት አማካሪና የፌዴራል መንግሥትን ዋና ተደራዳሪ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር)፣ እንዲሁም የሕወሓት ዋና  ተደራዳሪ አቶ ጌታቸው ረዳን እንዳነጋገሩ ተገልጿል፡፡

ተደራዳሪዎቹ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የመመሥረትን አስፈላጊነትና የሚኖረውን ሚና ገልጸው በቀጣይ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ፣ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ እንዲተገበርና የሰላም ሁኔታው እንዲረጋገጥ ከስምምነት መድረሳቸው ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንደገለጹላቸው ተጠቁሟል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በትግራይ ክልል እየተካሄደ ባለው የሰላም ስምምነት ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን መፍትሔ ያገኙ ዘንድ፣ ሴቶችን ያሳተፈ ውሳኔ እንዲተላለፍ እንደጠየቁ ተገልጿል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም (አምባሳደር) ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጉብኝት የሁለቱ አገሮች ወደ ተሻለ ደረጃ መሸጋገሩን የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ቃል አቀባዩ ሲያብራሩ፣ ‹‹አገሮቹ በመከባበር፣ በመፈላለግና አንዱ ከሌላው ጋር ተባብሮ በመሥራት ላይ የሚያተኩር ግንኙነት አላቸው፤›› ብለው፣ ይህንን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ከመግባባት የተደረሰ መሆኑንና በአሜሪካ የተሰጠው ሰብዓዊ ዕርዳታ የዚህ መገለጫ መሆኑን አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...