Friday, March 31, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለሚቀጥለው ዓመት የነዳጅ ፍጆታ ግዥ ለመፈጸም አራት ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተባለ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለ2016 በጀት ዓመት የነዳጅ ፍጆታ 212 ቢሊዮን ብር ወይም ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ፣ ግዥውን ለመፈጸምም የጨረታ ሒደት መጀመሩ ታውቋል።

ለቀጣዩ ዓመት የነዳጅ ግዥ አሁን ላይ ታሳቢ የተደረገው ወጪ አራት ቢሊዮን ዶላር በቀጣይ ወራት ሊከሰት በሚችል ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ መለዋወጥ ከፍ አልያም ዝቅ ሊል እንደሚችል የኢትዮጵያ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ለሪፖርተር አስታውቋል፡፡

የድርጅቱ የነዳጅ አቅርቦትና ሽያጭ መምርያ ኃላፊ አቶ ዓባይነህ አወል እንደተናገሩት፣ የቀጣዩ ዓመት ነዳጅ ፍላጎት አራት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሲሆን፣ የዘንደሮ በጀት ዓመት አጠቃላይ የነዳጅ ፍላጎት ደግሞ 3.8 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነው። በመሆኑም የቀጣዩ ዓመት የነዳጅ ፍላጎት ከ2015 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር የ200‚000 ሜትሪክ ቶን ጭማሪ ይኖረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አጠቃላይ የነዳጅ አቅርቦት በየዓመቱ በአማካይ በአሥር በመቶ የሚጨምር ቢሆንም የቀጣዩ በጀት ዓመት የነዳጅ አቅርቦት የአምስት በመቶ ብቻ ጭማሪ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ለ2016 በጀት ዓመት ለሚቀርበው አራት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ 212 ቢሊዮን ብር ወይም አራት ቢሊዮን ዶላር ወጪ ይዳረጋል ተብሎ መታቀዱን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

አክለውም፣ ከአጠቀላይ የነዳጅ ግዥው ውስጥ 45 በመቶ የሚሆነው ናፍጣ መሆኑን፣ የተቀረው ደግሞ ቤንዚን፣ የአውሮፕላን ነዳጅና ሌሎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ 

ሪፖርተር ባገኘው ሌላ መረጃ 3.8 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የ2015 በጀት ዓመት የነዳጅ ፍጆታን ለማቅረብ 164 ቢሊዮን ብር ወይም ሦስት ቢሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጓል። 

በመሆኑም የቀጣዩ ዓመት የነዳጅ ግዥ ወጪ ከ2015 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር የ48 ቢሊዮን ብር ወይም አንድ ቢሊዮን ዶላር ገደማ ጭማሪ እንደሚኖረው ለመረዳት ይቻላል፡፡ 

አቶ ዓባይነህ እንደሚሉት፣ ለ2016 የነዳጅ ግዥ አራት ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ቢቀመጥም፣ በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ መቀያየርና በምንዛሪ ለውጥ ምክንያት ሊጨምር ወይም ሊቀንስ እንደሚችል ጠቁመዋል።

ለ2015 በጀት ዓመት የነዳጅ ፍጆታ 164 ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ዓመታዊ የነዳጅ ፍላጎት መጠን ከ3.8 እና ከአራት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሳያልፍ ዓመታዊ ወጪዋ ግን ከዓመት ዓመት እያደገ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ። 

ለአብነት ያህል ከሁለት ዓመት በፊት 3.8 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ለመግዛት 2.8 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገ ሲሆን፣ ቀደም ባሉት ዓመታት ለተመሳሳይ መጠን ይወጣ የነበረው ሁለት ቢሊዮን ዶላር ነበር።

ለቀጣዩ ዓመት ከሚያስፈልገው ናፍጣ ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን እስከ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የሚሆን በጨረታ ከዓለም አቀፍ ከቅራቢዎች እንደሚገዛ ኃላፊው አስረድተዋል። ተመሳሳይ መጠን ያለው ናፍጣ ደግሞ ያለ ጨረታ ከኩዌት እንደሚገዛ ለማወቅ ተችሏል።

ቀደም ሲል በኢትይጵያና በኩዌት መንግሥት መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረት ኩዌት ፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን 50 በመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያ የናፍጣ አንዲሁም 75 በመቶ የሚሆነውን ዓመታዊ የአውሮፕላን ነዳጅ ፍላጎት ያቀርባል።

የተቀረው 50 በመቶ የናፍጣ ፍላጎትና 25 በመቶ የአውሮፖላን ነዳጅ ከዓለም አቀፍ አቅራቢዎች በጨረታ የሚገዛ ነው። አቶ ዓባይነት እንደገለጹት፣ ለ2016 በጀት ዓመት በዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የሚቀርበውን ናፍጣ ለመግዛት ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶ በሂደት ላይ ይገኛል።

የቀጣዩ ዓመት የቤንዚን ፍጆታ ከ760‚000 እስከ 860‚000 ሜትሪክ ቶን ይሆናል ተብሎ በዕቅድ መያዙንና የናፍጣም ሆነ የቤንዚን ግዥው በሁለት ዙር ወይም በየስድስት ወሩ ሊፈጸም እንደሚችል ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያና በሱዳን መንግስት መካካከል በተደረሰ ስምምነት መሠረት ከዓመታዊ የኢትዮጵያ የቤንዚን ፍላጎት ውስጥ 40 በመቶ የሚሆነው ላለፉት ዓመታት ያለ ጨረታ ሱዳን ሲቀርብ የነበረ ሲሆን፣ የተቀረው 60 በመቶ ቤንዚን ደግሞ በጨረታ ከዓለም አቀፍ አቅራቢዎች የሚገዛ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች