ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ያላትን ምንም ዓይነት ፍላጎት በማስፈራራትም ሆነ ሥጋት በመጫር ማሳካት እንደማትችል የኢትዮጵያ መንግሥት አስታወቀ።
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰሞኑት ላደረጉት ጠብ አጫሪ ንግግር የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሐሙስ ዕለት ባወጣው መግለጫ ምላሽ የሰጠ ሲሆን፣ ግብፅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በህዳሴ ግድቡ ላይ ያላትን ልዩነት ለመፍታት ሁሉንም አማራጮች እንደምትጠቀም መግለጿ ኃላፊነት የጎደለው ሕገወጥ አነጋገር በመሆኑ መቆም አለበት ብሏል።
ግብፅ በህዳሴ ግድቡ ላይ ያላትን ልዩነት በቅን ልቦናና በዓለም አቀፍ ሕግና መርሆዎችን በመከተል በአፍሪካ ኅብረት መሪነት በሚካሄደው የሦስትዮሽ ድርድር ካቀረበች ሰላማዊ መፍትሔ ላይ መድረስ እንደሚቻል የኢትዮጵያ መንግሥት እምነት እንዳለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አመልክቷል።
ከዚያ ውጪ ግን ኢትዮጵያን በማስፈራራትና ሥጋት በመፍጠር ምንም ዓይነት ፍላጎትን ማሳካት እንደማይቻል ግብፅ ልትገነዘብ ይገባል ሲል መግለጫው አሳስቧል።
ሁሉም የሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ አካላት ግብፅ ከሰሞኑ እያሰማች ባለው ጠብ አጫሪ የማስፈራሪያ ንግግር የዓለም አቀፍ ግንኙነት መርሆችን በግልጽ እየጣሰች መሆኑን እንዲገነዘቡም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ጥሪውን አስተላልፏል።
እንዲህ ያለው ማስፈራሪያና ሥጋት ጫሪ ንግግር የተባበሩት መንግሥታት ደርጅትንም ሆነ የአፍሪካ ኅብረት ማቋቋሚያ ቻርተር ድንጋጌዎች እንደሚጥስ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን በህዳሴ ግድቡ ላይ ልዩነት ያላቸው ግብፅና ሱዳን በአፍሪካ ኅብረት መድረክ እንደገና እንዲሳተፉና ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ልዩነት በድርድር እንዲፈቱ ጥሪ በድጋሚ ማድረጓን መግለጫው አመልክቷል።