የታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥና ታክስ ነፃ እንዲሆኑ ሲሠራበት የነበረውን መመርያ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ከዚህ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ሊያነሳው መሆኑ ተገለጸ፡፡
ከሁለት ዓመታት በፊት ወጥቶ የነበረውና ባለፈው ዓመት የተሻሻለው መመርያ፣ በታክሲ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ባለንብረቶች ከቀረጥና ታክስ ነፃ አዳዲስ ተሽከርካሪዎች እንዲያስገቡ ይፈቅዳል፡፡
በዚህም አሮጌ ተሽከርካሪዎችን በመተካት ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ፣ ለቱሪዝም መስፋፋት ምቹ ሁኔታን እንዲፈጥሩና በአገር ውስጥ ተገጣጣሚ ተሽከርካሪዎች እንዲስፋፋ ዓላማ ይዞ የወጣው መመርያ፣ በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ፀድቆ የተዘጋጀውን የአንድ ገጽ መመርያ ይሽረዋል፡፡
የመመሪያውን መሰረዝ አስፈላጊነት በሚመለከት ሪፖርተር የገንዘብ ሚኒስቴር የሥራ ክፍል ኃላፊዎችን ለመጠየቅ በተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
የሚሰረዘው መመርያ የታክሲ ባለንብረቶች ማኅበራትና የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች በሚያስመጧቸውና በሚገጣጥሟቸው ተሽከርካሪዎች ላይ ነፃ የታክስና ቀረጥ ታሪፍ ዕድል በመስጠት ተጠቃሚ ያደርጋቸው ነበር፡፡
ተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ያላቸው ፋብሪካዎች ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል የተገነጣጠሉ ተሽከርካሪዎችን ሲያስመጡ ከሚያገኟቸው ጥቅሞች መካከል፣ የታክስና የቀረጥ ክፍያዎችን በቅድሚያ ከፍሎ በ30 ቀን ውስጥ የሚገጣጥሙዋቸው ተሽከርካሪዎች ለተጠቃሚ እንደሚተላለፍ ማረጋገጫ ከቀረበ፣ የከፈሏቸው የቀረጥና የታክስ ወጪ እንደሚመለስ ያዛል፡፡ በተጨማሪም እነዚህን ተሽከርካሪዎች አስገብተው በጉምሩክ መጋዘን ውስጥ ካለክፍያ ማስቀመጥ አንደኛው የሚያገኙት ጥቅም ነው፡፡
የታክሲ ባለንብረቶች ማኅበራት አሮጌ ተሽከርካሪዎቻቸውን ለመተካት ወይም አዲስ ለመግዛት ይህን ዕድል የሚጠቀሙበት ሲሆን፣ የክልልና የከተማ መስተዳድሮች ማኅበራቱ ለሚጠይቋቸው የታክስ ነፃ ዕድል ዕውቅና መስጠት ይኖርባቸው ነበር፡፡
የሚኒስቴሩ ኃላፊዎች መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሚኒስቴሩ የሰረዘውን መመርያ በሌላ ይተካ፣ አልያም የታክሲ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ድርጅቶች በዚህ ዕድል መጠቀምን አስቁመው እንደሆነ የታወቀ ነገር የለም፡፡