በአበበ ፍቅር
‹‹ታላቅ ዕሳቤዎች›› የተሰኘ፣ ኢትዮጵያዊ ይዘት ያለውና በብዙዎች ዘንድ የአስተሳሰብ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል የተባለና ኢትዮጵያውያንን ወጣቶች ከዓለም ወጣቶች ጋር በዕውቀትና በአመለካከት ተወዳዳሪ ያደርጋል የተባለ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር ሊቀርብ መሆኑ ተገለጸ፡፡
መርሐ ግብሩ በባላገሩ ቴሌቪዥን በሳምንት አንድ ቀን ለአንድ ሰዓት ያህል ለተመልካች የሚቀርብ መሆኑን የመርሐ ግብሩ ዋና አዘጋጅ መምህር ዘበነ ለማ (ፕሮፌሰር)፣ መጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ወጣቱ ትውልድ ከአውሮፓና ከአፍሪካ እንዲሁም ከሌሎች አገሮች ወጣቶች ጋር በዕውቀትና በአመለካከት ተወዳዳሪ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀና መርሐ ግብሩ በወጣቶች ዘንድ ተጨባጭ የሆነ የአስተሳሰብ ለውጥ የሚያመጣ ነው ብለዋል፡፡ የፕሮግራሙ ዋና አዘጋጅ መምህር ዘበነ ለማ (ፐሮፌሰር)፣ መርሐ ግብሩን በማስመልከት ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ‹‹ታላቅ ዕሳቤዎች›› አራት ዋና ዋና ነጥቦችን መሠረት አድርጎ የሚሰጥ የቴሌቪዥን ፕሮግራም መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
‹‹አንቃኢ›› የሚቀሰቅስ፣ ‹‹አንቃሂ›› አዳዲስ ሐሳቦችን እንዲመነጩ ማስቻል፣ ባለ ራዕይና ‹‹አንፀሮ›› ሐሳቦችን፣ ነገሮችን በጥልቀትና በአስተውሎት የሚመረምር ትውልድን ለመቅረፅ ያለመ ፕሮግራም ነው ብለዋል፡፡
ሁሉንም ማኅበረሰብ ታሳቢ ያደረገ ይሆን ዘንድ በመረሐ ግብሩ ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው አስተምህሮቶች እንደማይገቡ የገለጹት መምህር ዘበነ (ፕሮፌሰር)፣ የታላላቅ ሰዎች አስተምህሮቶችና ተሞክሮዎች ይገባሉ ብለዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት አሰጣጥ ዘዴዎች የሚፈተሹበት የአርሶ አደሮችና የነጋዴዎችን የኑሮ ሁኔታ የሚዳስስ ፕሮግራሞች እንደሚቀርቡ አብራርተዋል፡፡
በባላገሩ ቴሌቪዥን በየሳምንቱ ከሚቀርበው መርሐ ግብር በተጨማሪ ‹‹የታላቅ ዕሳቤዎች›› አስተምህሮቶች በመጽሐፍና በልዩ ልዩ ሥልጠናዎች ተደራሽ እንደሚሆኑ ዋና አዘጋጁ ተናግረዋል፡፡
ፕሮግራሙ በሳይንስ፣ በፍልስፍና፣ በማኅበራዊ ዘርፍ የሚያተኩር ሲሆን በተለይ ደግሞ የሳይኮሎጂ፣ የአንትሮፖሎጂና የፊሎዞፊል ጥናቶች ሁሉንም ማኅበረሰብ ማዕከል በማድረግ ይቀርባሉ ተብሏል፡፡