- ክቡር ሚኒስትር ዕርምጃ ከመውሰዳችን በፊት አንድ ነገር ለማጣራት ብዬ ነው የደወልኩት።
- እሺ ምንን በተመለከተ ነው?
- የቴሌኮም ኩባንያዎችን በተመለከተ ነው።
- የቴሌኮም ኩባንያዎች ምን?
- የቴሌኮም ኩባንያዎች የሞባይል ቀፎ እንዲሸጡ በሕግ ተፈቅዶላቸዋል?
- ቴሌኮም ኩባንያዎች የሞባይል ቀፎ እንዲሸጡ የሚፈቅድ ሕግ ያለ አይመስለኝም። ግን ደግሞ በአንድ ነገር እርገጠኛ ነኝ።
- በምን ክቡር ሚኒስትር?
- እንዳይሸጡ የሚከለክል ሕግ አለመኖሩን!
- ስለዚህ መሸጥ ይችላሉ ማለትዎ ነው?
- አላልኩም፡፡
- ታዲያ ምን እያሉኝ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- የሚከለክል ሕግ እንደሌለ እርግጠኛ ነኝ ነው ያልኩት።
- በእኛ ባደረግነው ማጣራት ደግሞ የሞባይል ቀፎ እንዲሸጡ የሚፈቅድ ሕግ የለም። ስለዚህ…
- እ… ስለዚህ ምን?
- የሚከለክል ሕግ ከሌለ እንደተፈቀደ ይቆጠራል ማለት እንችላለን ማለት ነው?
- ከሕግ ትርጓሜ አኳያ ከተመለከትነው እንደዚያ ማለት ነው። ግን ለምንድነው ማጣራት የፈለጋችሁት?
- በዚህ ሥራ ፈቃድ ያወጡ አስመጪዎች እያሉ አንድ የቴሌኮም ኩባንያ ሰሞኑን ውድ ስልኮችን አስመጥቶ ለገበያ እያስተዋወቀ ስለሆነ ነው።
- ውድ ስልኮችን ስትል ምን ያህል የሚያወጡ ናቸው?
- ትንሹ ዋጋ 95,000 ብር ነው።
- ትልቁ ዋጋስ?
- ትልቁ ዋጋ 140,000 ነው።
- የትኛው የቴሌኮም ኩባንያ ነው?
- የእኛው ነው።
- ነው? ገባኝ፣ ገባኝ!
- ምን ገባዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ለማን ሊያቀርብ እንደሆነ፡፡
- ለማን ሊያቀርብ ነው?
- ለከተማ አስተዳደሩ።
- የትኛው ከተማ አስተዳደር?
- ለአመራሮቹ የ140,000 ብር ስልክ እንዲገዛ የወሰነው አስተዳደር።
- ለአመራሩ በጥቅማ ጥቅም መልክ እንዲሰጥ ነው የተወሰነው ክቡር ሚኒስትር?
- አዎ። እንደዚያ ነው የተባለው።
- የጥቅማ ጥቅም ውሳኔ መባሉ ግን ትክክል አይመስለኝም።
- ታዲያ ውሳኔው ምን መባል ነበረበት?
- ጋላክሲ ኤስ 23!
- ኪኪኪኪ… የአስተዳደሩን ውሳኔ እንደዚያ ካልክ የቴሌኮም ኩባንያውን ውሳኔም ምን ልትለው ነው?
- የድርሻዬን!
[የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ በስንዴ ምርት ግዥ ላይ ግር ያላቸውን ለማጥራት ለፌዴራሉ አቻቸው ጋ ስልክ ደወሉ]
- በመኸር ወቅት የተሰበሰበው ስንዴ ለገበያ የሚቀርብበትን መንገድ የተመለከተ መመርያ ከገንዘብ ሚኒስቴር ደርሶን ነበር።
- እሺ፡፡
- እርስዎ ደግሞ ሰሞኑን ለሚዲያ የተናገሩትና ማሳሰቢያ አዘል መግለጫ አለ።
- እሺ፡፡
- እርስዎ የሰጡት ማሳሰቢያና ከገንዘብ ሚኒስቴር የደረሰን መመርያ የሚጣረሱ በመሆናቸው ነገሩን ለማጥራት ብዬ ነው።
- ከገንዘብ ሚኒስቴር የደረሳችሁ መመርያ ምን ይላል?
- የተመረተውን ስንዴ መግዛት የሚችሉት ከመንግሥት ጋር በትብብር የሚሠሩ ማኅበራትና ዩኒየኖች ብቻ ናቸው ይላል።
- ትክክል ነው።
- ማኅበራትና ዩኒየኖቹ ስንዴ መግዣ እንዳይቸገሩም ለክልሉ 1.3 ቢሊዮን ብር መላኩን ይገልጻል።
- አዎ። ለሁሉም ሰንዴ አምራች ክልሎች በጀት መመደቡን አውቃለሁ፡፡
- የደረሰን መመርያ የስንዴ መሰብሰቢያ ዋጋንም ያካተተ ነው።
- መሰብሰቢያ ማለት?
- አርሶ አደሩ የትርፍ ህዳግን ጨምሮ ስንዴ የሚሸጥበት ከፍተኛ ዋጋ ብር 3,200 መሆኑን አሳውቆናል።
- ትክክል ነው።
- እኛም በዚህ መሠረት ማንኛውም ዱቄት ፋብሪካና ነጋዴ ስንዴ እንዳይገዛ አግደናል። ምክንያቱም የዩኒየኖቹ የስንዴ ፍጆታ እንዳይጎድል በማሰብም።
- ትክክል ነው፣ ምክንያቱም የዩኒየኖቹ የስንዴ ፍጆታ መሟላት አለበት።
- ነገር ግን እርስዎ ሰሞኑን የሰጡት መግለጫ ችግር ፈጥሮብናል።
- የትኛው መግለጫ?
- አርሶ አደሩ ከ3,200 ብር በላይ የሚገዛው ካገኘ ስንዴውን መሸጥ ይችላል፣ የከለከለው የለም ብለው የተናገሩት።
- እሱን የተናገርኩት የዩኒየኖቹ የስንዴ ፍጆታ ለማስተጓጎል አይደለም።
- ታዲያ ለምንድነው?
- ለሚዲያ ፍጆታ!