በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)
‹‹እኔ ግን የእነዛን ሁሉ ክርስቲያኖች ደም በከንቱ መፍሰሱን እያየሁ ድል አደረግኩ ብዬ ደስ አይለኝም…›› (ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከዓድዋ ድል በኋላ ለአውሮፓውያን መንግሥታት ከጻፉት ደብዳቤ የተቀነጨበ)፡፡
- እንደ መንደርደሪያ
ባለፉት ሁለት ዓመታት ‘በፌዴራል መንግሥቱ’ እና ‘በሕወሓት’ በኩል የተደረገውን መቶ ሺሕዎች ያለቁበትን የእርስ በርስ ጦርነት ለመዘገብ ግንባር ላይ የሰነበተ በአንድ የግል መገናኛ ብዙኃን ላይ ተቀጥሮ ይሠራ የነበረ ጋዜጠኛ ወዳጄ፣ የጦርነቱ ክፉ ዳፋ መልሶ መላልሶ የጎበኛቸው ወለዬዎች ስለእነዚያ ‘ክፉ ቀናት!’ እንዲህ መቀኘታቸውን አጫወተኝ፡፡
‘‘አንተ ቃሉ መጀን
ኧረ ጦሳ መጀን
ኧረ አዝዋ መጀን
ኧረ ወሎ መጀን
… እኮ ምን ይዋጠን
እውነት ምን ይበጀን…!?
ሲተኮስ ተወልደን ሲተኮስ አረጀን!
በንጉሥ ተፋጀን!
በአብዮት ተፋጀን!
ለኢያሱ ተዋግተን!
ለተፈሪ ሞተን!
በሕወሓት ጃጀን!
እውነት ምን ይበጀን…!?
ኧረ ጢጣ መጀን
ቧንቧ ውኃ መጀን
ሆጤ ሜዳ መጀን…
… ይኼው ጫት ታቅፈን
ፍቅርን ብለን አርፈን
ከኒህ ነጃሳዎች…!
የአህመድ ዓሊ ልጅ
ለውጥ ብሎ አፋጀን!!’’
- ፀፀትና ሐዘኔታ የሌለን ስለ ለምን ሆንን…?!
ባሳለፍነው ሳምንት ዕለተ-ንበትን በተለያዩ ምክንያቶች በአገራችን ኢትዮጵያ ከሚኖሩ የውጭ አገር ሰዎች ጋር አንድ የትውውቅ ፕሮግራም ላይ ተገኝቼ ነበርኩ፡፡ እናም በዚህ ዝግጅት ላይ ከአገረ ቱርክ ከመጣ አንድ ጎልማሳ ጋር የትውውቅ ወግ ጀመርን፡፡ ይህ በመዲናችን አዲስ አበባ በግል ቢዝነስ ላይ የተሰማራ ጎልማሳ ስሙንና ከቱርክ የመጣ መሆኑን ነግሮኝ ከተዋወቅን በኋላ፣ አንገቱን ዝቅ አድርጎ ፀፀትና ሐዘኔታ በተሞላበት ዓይነት ስሜት ውስጥ ሆኖ እንዲህ አለኝ፡፡
‘‘አገሬ ቱርክ በአገራችሁ በተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት የድሮን ሽያጭ በማድረጓና ስለተፈጠረው ሞት፣ ዕልቂትና መፈናቀል ከልብ ማዘኔን ልገልጽልህ እወዳለሁ…’’ ብሎኝ ከጥቂት የዝምታ አፍታ በኋላ ወደ ሌላ የጨዋታችን ርዕስ ተሸጋገረ፡፡
የዚህ ቱርካዊ የፀፀትና የይቅርታ መንፈስ የተላበሰ ንግግሩ በመብረቅ የተመታሁ ያህል ነበር ያስደነገጠኝ፡፡ እናም ራሴን እንዲህ ለመጠየቅ ተገደድኩ፡፡ ለሺሕ ዘመናት የዘለቀ ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ባህልና ሥልጣኔ ያለን ሕዝቦች ነን የምንል እኛ እንደ ምን በዚህ ልክ ከሰብዓዊነት ልዕልና፣ ከሞራል ሕግ፣ ከሃይማኖት የይቅርታ አስተምህሮ ልንጎድል ቻልን… ለመሆኑ መንግሥትም ሆነ እኛስ እንደ ሕዝብ እስከ መቼ ይሆን ለፀፀትና ለይቅርታ የጨከነ እኩይ ማንነትን ይዘን የምንዘልቀው… የሚል ጥያቄ አዕምሮዬን ሰቅዞ ያዘው፡፡
ላለፉት ሁለት ዓመታት ባደርግነው የእርስ በርስ ጦርነት በታሪካችን ከውጭ ወራሪ ኃይሎችም ሆነ እርስ በርሳችን ባደረግናቸው ጦርነቶች ከደረሰው ዕልቂት፣ ሞት፣ መፈናቀል፣ ስደት፣ ወዘተ. አንፃር አቻና ተወዳዳሪ ያለው አይደለም፡፡ ከሃይማኖት አባት እስከ አገር ሽማግሌ፣ ከአፈ ነቢብ እስከ ምሁራን፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ በሆንበት በዚህ የእርስ በርስ ዘግናኝ ጦርነት የደረሰው ዕልቂት (ገና ባይረጋገጥም በዚህ ጦርነት አንድ ሚሊዮን የሚያህል ሕዝብ ለሞት መዳረጉ ይነገራል)፣ መፈናቀል፣ የመሠረተ ልማት ውድመት… በአጠቃላይ ሰብዓዊና ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሱ ከምንገምተው በላይ ነው፡፡
አንድ ገጠመኜን አብነት ልጥቀስ፡፡ በምሠራበት መሥሪያ ቤት በጥበቃ ሥራ ተቀጥሮ የሚሠራ አንድ ኢትዮጵያዊ የቀድሞ ወታደር ነበር፡፡ ይህ የመሥሪያ ቤታችን ባልደረባ ከሁለት ዓመት በፊት መንግሥት ያወጀውን “የህልውና ዘመቻ ጥሪ” ተቀብሎ ወደ ሰሜን ግንባር ዘምቶ ነበር። ይሁን እንጂ ከጥቂት ወራት በፊት ይህ ኢትዮጵያዊ ወገናችን በሰሜን ግንባር እስከ ወዲያኛው መቅረቱን የሚያስረግጥ የሞቱ መርዶ ለሚስቱና ለሰባት ዓመት ልጁ ተነገረ።
ገና በሰላሳዎቹ መጀመርያ የምትገኘው ሚስቱ እርሟን/ሐዘኗን ከጎረቤት፣ ከዘመድ ወዳጆች ጋር ካወጣች በኋላ መቼም ሕይወት ይቀጥላልና ያለ አባት የቀረውን ልጇን ለማሳደግ ስትል ከመርግ ከከበደው የአገራችን ኑሮ ጋር ትግሏን ቀጠለች። ቀድሞ በባለቤቷ ገቢ ትተዳደር የነበረችው ይህች ሴት አሁን ብቻዋን ኑሮን መጋፈጡ አልሆንላት አለ። እናም የዚህችን ሴት ችግር የተመለከተው መሥሪያ ቤታችን ቀድሞ ባለቤቷ በጥበቃ ሥራ ሲሠራ ይከፈለው የነበረውን የወር ደመወዝ ታሳቢ ሆኖ እየተከፈላት በፅዳት ሠራተኝነት ቀጠራት።
ታዲያ ባለፈው ሰሞን ትምህርት ቤት ዝግ በመሆኑ ይህች ከላይ እስከ ታች ጥቁር ከል የለበሰች ሴት ለሥራ ወደ መሥሪያ ቤታችን ስትመጣ ልጇን ቤት ብቻውን መተው ባለመቻሏ ወደ ሥራ ቦታ ይዛው መምጣት ትጀምራለች፡፡ ታዲያ ይህ ልጅ መቼም ልጅ ነውና የቢሯችን ሕንፃ አካባቢ መሯሯጥና መጫወት በማዘውተሩ ከአንዳንድ ሰዎች ቅሬታ መቅረብ ጀመረ። ታዲያ ይህን ጉዳይ ምን መፍትሔ መስጠት ይቻል ይሆን? በሚል ያነጋገርናት የልጁ እናት በዕንባና በሰቀቀን ሆና እንዲህ አለችን፡፡
‹‹… ልጄን ምን ላድርገው…?! ቤት ጥዬው እንዳልመጣ ቤቱ ውስጥ ሰው የለ… ምን ትመክሩኛላችሁ… አይ ዕድሌ፣ እስቲ ፍረዱኝ ያለ አባት የቀረውን ልጄን ምን ላድርገው…?!›› ብላ አንገቷን ደፍታ መንሰቅሰቅ ጀመረች፡፡
‘‘ያለ አባት የቀረውን ልጄን ምን ላድርገው…?!’’ ይህ ልብን በሐዘን የሚሰብር ምሬትና ሰቆቃ በዚህ ጦርነት ወላጆቻቸውን ያጡ የበርካታ ኢትዮጵያውያን ሕፃናት ዕጣ ፈንታ ነው፡፡ ይኼ መራርና አሳዛኝ እውነታ በዚህ ጦርነት ባላቸውን፣ አባታቸውን፣ ወንድሞቻቸውን፣ እህቶቻቸውን ያጡ የብዙዎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ከመርግ የከበደ መከራቸውና ሰቀቀናቸው ማሳያ ነው።
ወደ ቀደመ ሐሳቤ ስመለስም ይህንን ዓለም በአግራሞትና በድንጋጤ እጁን በአፉ ላይ እንዲጭን ያደረገው የእርስ በርስ ጦርነት በአፍሪካ ኅብረት፣ በአሜሪካና በሌሎች የውጭ አገሮች ግፊትና ጫና በንግግርና በሰላማዊ ድርድር ይቋጭ ዘንድ ከተደረገ በኋላ፣ በሁለቱም ወገን የፀፀትና የሐዘን ስሜት ሳይሆን ያየነው የተገላቢጦሽ “ድሉ የእኛ ነው!!” ወደ የሚል ፉክክርና ብሽሽቅ፣ እንዲሁም የድል የአበባ ጉንጉን ወደ መሸላለም ነበር የተገባው። በዚህ ጦርነት ስለደረሰው ከፍተኛ የሆነ ዕልቂት፣ ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መፀፀቱንና ሐዘኑን የገለጸ አንድም የመንግሥት ባለሥልጣን አላየሁም፣ አልሰማሁም።
እንዲያው የሆነስ ሆነና እንዴት ነው ወደ እዚህ ዓይነቱ የሞራል ውድቀት/ልሽቀትና ደንታ ቢስነት የተሸጋገርነው። ለገዛ አገራችን፣ ለገዛ ሕዝባችን በመግቢያዬ ላይ ያነሳሁትን የባዕዱን ቱርካዊ ያህል ፀፀትና ርህራሔን ስለምን አጣን…?! ይህን ከመንግሥት እስከ የሃይማኖት ተቋሞቻችን፣ እንዲሁም እያንዳንዳችን ቆም ብለን ራሳችንን መጠየቅ ያለብን የጊዜው ጥያቄ ነው።
- ለመውጫ ያህል
ታሪካችንን ስንፈትሽ ከዓድዋው ጦርነት ድል በኋላ አፄ ምኒልክ ለአውሮፓ መንግሥታት በጻፉት ደብዳቤ እንዲህ ነበር ያሏቸው፡፡
‹‹… ጦርነት ይቅር ብላቸው እምቢ ብለው በጥጋባቸው ዓድዋ ላይ ድል ሆኑ፡፡ እኔ ግን የእነዚያ ሁሉ ክርስቲያኖች ደም በከንቱ መፍሰሱን እያየሁ ድል አደረግኩ ብዬ ደስ አይለኝም…›› በማለት የኢትዮጵያዊነትን የሞራል የበላይነትንና ሰው የመሆን ከፍ ያለ የመንፈስ ልዕልናቸውን ለተቀረው ዓለም አሳይተውበታል፡፡
ታዲያ እንዴት ነው ከመቶ ዓመታት በኋላ ለባዕድ እንኳን ባይተርፍ እንዴት እርስ በርሳችን ለተገዳደልንበት፣ ምድሪቱን ኢትዮጵያን አኬልዳማ/የደም ምድር ላደረግንበት፣ የብዙዎችን ሕይወትና ኑሮ ክፉኛ ላመሰቃቀልንበት፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናትን ወላጅ አልባና ተስፋ አልባ ላደረግንበት ጦርነት/ዘግናኝ ዕልቂት ጥቂት እንኳን እንጥፍጣፊ መፀፀት፣ ሐዘንና ኃፍረትን እንደምንና ስለምን አጣን!?
እናም… በእርግጥም ላለፉት ሁለት ዓመታት ያደረግነው የእርስ በርስ ጦርነት የኢትዮጵያ አንድነት መሠረትና ዋልታ የሆኑ ሕዝቦችን ደም ያቃባ፣ ኢትዮጵያን ወደኋላ የመለሰና በብዙ የከሰርንበት እንዲሁም መንግሥትም ሆነ እኛም እንደ ኢትዮጵያዊ ልናፍርበት፣ ከልብ ልንፀፀትበትና ይቅርታ ልንጠይቅበት/ልንጠያየቅበት የሚገባን ጦርነት ነው፡፡
ሰላም ለኢትዮጵያ!!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል fikirbefikir@gmail.com አድራሻ ማግኘት ይቻላል፡፡