Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርሆድና የሆድ ነገር

ሆድና የሆድ ነገር

ቀን:

(ክፍል አምስት)

በጀማል ሙሐመድ ኃይሌ (ዶ/ር)

ሲበሉ የላኩት…”

እናት ለቤተሰቡ ቁርስ አቀረበች፡፡ አባት፣ ልጆችና እሷም ጭምር መሶቡን ከበቡ፡፡ ገና መብላት እንደ ጀመሩ፣ አቶ አባት ለእርሻ ሥራ ከሠፈራቸው ገበሬ ለመዋስ ያሰበው ዕቃ (መጫኛ) ትዝ አለው፡፡ ሌላ ሰው እንዳይቀድመው ስለሠጋ ከሌሎቹ ከፍ ያለውንና ስምንት ዓመት አካባቢ የሆነውን ልጁን ላከው፡፡ ልጅም እየሮጠ ሄደ – ሐሳቡ ከኋላው ከቀረው ምግብ ጋር እንደ ተንጠለጠለ፣ ትንሽዬ ልቡ ወደ ኋላ እየሸፈተች፣ ቀጫጭን እግሮቹ ወደ ፊት እየሮጡ፣ ከተላከበት ቤት ደረሰ፡፡ በአጋጣሚ እነሱም ቁርሳቸውን እየበሉ ነው፡፡

ሰክ ብሎ ገባ፣ ዓይኑ በበኩሉ እየበሉት ካሉት ገንፎ ላይ ሄዶ ችክል!

የቤቱ በር ክፍት ስለሆነ ብቻ ዘው ብሎ መግባቱ አንሶ፣ ከምግባቸው ላይ በማፍጠጡ የተናደደው አባወራ “ምን ሁነህ ነው?”

“ተልኬ ነው፡፡”

“ማን ነው የላከህ?” መልሶ ጠየቀው፡፡ 

“አባቴ!”

“ምን ብሎ ላከህ?”

“ገንፎ ላክልኝ፡፡”

“ምን?”

“ገንፎ ላክልኝ፡፡”…

ባልና ሚስት ለቅፅበት ተያዩ፣ በቅፅበትም ተግባቡ… ይኼ ሲበሉ የላኩት፣ ይኼ ሥርዓተ ቢስ መቀጣት አለበት… (“ሲበሉ የላኩት” የሚለውን ወይ ከላኪዎቹ  (ከወላጁ) ወይም ከተላከላቸው ጋር አዛመዱት፡፡)

አቶ ባል “ና” በማለት ልጁን ወደ ቤቱ ምሰሶ አስጠጋው፡፡ ከዚያም ምሰሶውን በእጆቹ አቅፎ እንዲቆም አደረገ፡፡ ወይዘሮ ሚስት ወጪት (የሸክላ ሳህን) ላይ ካለውና ገና ትኩስ ከሆነው ገንፎ፣ ባገነፋችበት እንጨት ዛቅ አድርጋ አመጣች፡፡ አቶ ልጅ ምሰሶውን እንዳቀፈ እጆቹን እንዲዘረጋ ታዘዘ፡፡ ትነቱ የሚትለጎለጎውን ገንፎ ከእጆቹ ላይ አደረገችው፡፡ “ብላው ወይም ይዘኸው ሂድ” ተባለ፡፡ ለመብላትም ሆነ ይዞ ለመሄድ እጆቹ የምሰሶውን ዕቅፍ መልቀቅ አለባቸው፡፡ ያ ከሆነ ደግሞ የያዘው ገንፎ መሬት ላይ ይወድቃል፡፡ እርግጥ ነው እያቃጠለው ነው፡፡ ግን እንዴት ብሎ ገንፎውን መሬት ላይ ይጥላል? ኋላ ቢገረፍስ?… አንዱንም ማድረግ አልቻለም… ይኼ “ሲበሉ የላኩት” የሆነ ልጅ፣ ሁለተኛ እንዳይለምደው ሆኖ ተቀጣ ማለት ነው…

ይኼን ለጋ ልጅ ለቅጣት የዳረገው፣ ረሃብ ወይም ምግብ የፈለገ ሆዱ ነው፡፡ ሆዱ አካሉን እንዳይቆጣጠር አድረገው፡፡ እናም እግሩ ወደ ሰዎቹ ቤት ዘው ብሎ ገባ፣ ዓይኑ ተወርውሮ ከገንፎው ላይ ተቸከለ፡፡ ሆዱ አንደበቱን እንዳይቆጣጠር አድረገው፡፡ “መጫኛ ላክልኝ” በማለት ፈንታ “ገንፎ ላክልኝ” ብሎ እንዲናገር አደረገው…

አቶ ሆድ ልጁን ለቅጣትም ሆነ ለውርደት የዳረገው፣ ሕፃን በመሆኑ ከመሰለን ተሳስተናል፡፡ ከሆድ “ተንኮል” እና “ሴራ” የሚያመልጥ አለ ለማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ እስቲ የሚከተለውን አብነት እንይ፡-

የጫጉላ ጊዜውን ካሳለፈ ጥቂት ወራትን ብቻ ያስቆጠረ የገጠር ወጣት፣ “ሙሽሪት” በጣም እንደ ወደዳት ስላወቀች ነው መሰል፣ “ወላጆቼ ናፈቁኝ፣ ወስደህ አሳየኝ” እያለች ጨቀጨቀችው፣ መቆሚያ መቀመጫ አሳጣቸው፡፡ እናም አማቶቹን ሊጠይቅ ይሄዳል ሚስቱን ይዞ፡፡ የአማቾቹ ቤት ሩቅ ከመሆኑም በላይ የተጓዙት በእግራቸው ስለሆነ፣ በጣም ደክመውና ተርበው ጭምር ከቦታው ይደርሳሉ ፀሐይዋ ልክ ጥልም ስትል፡፡

የጥቁሩ እንግዳ የአማቻቸው መምጣት ዱብ-ዕዳ የሆነባቸው የልጅቷ ቤተሰቦች፣ አማቻቸውን የሚመጥን ምግብ ለማዘጋጀት ሽር-ጉድ ማለቱን ተያያዙት፡፡ ወ/ሮ ሚስት የሽር-ጉዱ አካል ስለሆነች፣ ረሃቡ ብዙም አልተሰማትም ወይም ችላዋለች፡፡ አቶ አማች ግን ረሃቡን መቋቋም አልቻለም፡፡ ከምድጃው ዳር ላይ የተቀመጠ ቶፋ አለ፡፡ እቤት እንደ ገቡ የአሹቅ (ከተቆላ በኋላ የተቀቀለ ባቄላ) ሽታ አውዶታል… ሰው ዘወር እስከ ሚልለት ጠበቀና ቶፋውን ከፈተው፡፡ ዠርግግ ብሎ ከቶፋው ውስጥ “የተኛውን” አሹቅ ሲያይ፣ ምራቁ አፉን ሞላው፡፡ ቶሎ ብሎ እጁን ከተተ እፍስ አድርጎ፣ ይህ ባይቻል ዘገን አድርጎ አፉ ውስጥ ከከተተ በኋላ፣ የለበሰውን ጋቢ አፍንጫው ላይ ጣል አድርጎ አሹቁን ሊያመሽክ፡፡

ሆኖም እንዳሰበው አልሆነም፡፡ እጁ፣ የዘገነውን አሹቅ ይዞ ይቅርና ትቶም አልወጣ አለ፡፡ ዘው ብሎ የገባ እጁ፣ በልመናም ሊወጣ አልቻለም፡፡ በብርዳማው ምሽት በላብ ታጠበ፡፡ ከቶፋው ለማውጣት ትግሉን ያላቆመ ቢሆንም፣ ወጣ-ገባ ሲሉ እንዳያዩት ቶፋ የተሸከመ እጁን ከጋቢው ውስጥ አደረገ፡፡ ጋሼ ቶፋ የጋቢን ሙቀት ተካፋይ ሆነ፡፡

አቶ የትናንት ሙሽራ እጁን ከቶፋ እስር ቤት ለማስለቀቅ “ይጠቅሙኛል” ያላቸውን ዘዴዎች ሁሉ ሞከረ፣ አልተሳካም፡፡ ቶፋው ካልተሰበረ፣ እጁ ነፃ ሊወጣ አይችልም፡፡ ይኼ ደግሞ እንዴት ይታሰባል ለዚያውም ከትኩስ አማቾቹ ቤት!? ወይስ ቶሎ ሰባብሮ እጁን ነፃ ካወጣ በኋላ፣ አሹቁንም፣ የቶፋውን ስብርባሪም ሙልጭ አድርጎ በመጠራረግ፣ ሳያዩት ወዲያ ከጓዳ ውስጥ ይጣለው? ከዚያ “ቶፋውሳ!”፣ “ኧረ ቶፋው የት ገባ?” እያሉ ሲጯጯሁ፣ “ያሽካነናት ቶፋ አሹቅ ይዛ ጠፋች” ብሎ በተረት ይመልስላቸው? ይኼን ቢል ማን ያምነዋል?…

ብዙም ሳይቆይ ከደጅ የቆዩትም፣ ምግብ ዝግጅት ላይ የነበሩትም የቤተሰቡ አባላት ወደ ቤት ገቡ፡፡ ማእዱ ቀረበ፣ የእጅ ውኃ መጣና እንዲታጠብ ተጠየቀ…”ጋሼ እጅህን ታጠብ!” ወደ ሚስቱ አገር የመጣው በህልሙ መሰለው… አዋራጅ የሆነ ረሃብ የሞደሞደው በህልሙ መሰለው… አሹቅ ሲሰርቅ፣ በቶፋ ጠባብ አፍ እጅ ከፍንጅ የተያዘው በህልሙ መሰለው… ቶፋ ውስጥ የተወሸቀ እጁን በጋቢው ሥር የደበቀው በህልሙ መሰለው… “እጅህን ታጠብ” የተባለው በህልሙ መሰለው… ሁሉም ነገር በህልሙ መሰለው… “ያሽካነናት ቶፋ አሹቅ ይዛ ጠፋች” የተባለው ዛሬ ቢሆን ተመኘ…

አስታጣቢው በድጋሚ፣ ድምፁን ትንሽ ሞቅ አድርጎ፣ “ጋሼ እጅህን ታጠብ!”

ከህልም ስካረ ምኞቱ ተመለሰ፡፡ ከንቱ ምኞት እንጂ፣ ምንም ህልም የለም ብቻ ሳይሆን ማምለጫም የለም፡፡ በየት፣ ወደ የት ይኬዳል? ወይ በኖ ወይ ተኖ መጥፋት የለ ነገር… የላቦቹ እንክብሎች በጀርባው መሀል ተንኳለው ሲሄዱ ተሰማው…

ለሦስተኛ ጊዜ፣ አስታጣቢው ድምፁን ይበልጥ ሞቅ አድርጎ “ጋሼ እጅህን ታጠብ  እንጂ!”

ቶፋ የተሸከመ እጁን መንጠቅ አድርጎ አወጣ፣ ወደ ላይ በመጠኑ ጓን አደረገ፣ ከዚያም፣ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፡-

“ከተናገረ አያባራ አፋቸው፣

ከያዘ አይለቅ ቶፋቸው፡፡”

በመቀጠልም ያጓነውን ቶፋ ከመደቡ ጫፍ ጋር አላተመው፡፡ ቶፋውም፣ አሹቁም ብትንትኑ ወጥቶ እርፍ…

ይህን ሁሉ ጣጣ ያመጣው የአንድ ቶፋ አሹቅ ነው ወይም ከአንድ ቶፋ ውስጥ ሊዘገን የነበረ አንድ ቢበዛ ሦስት እፍኝ አሹቅ፡፡ የሆድ ነገር እንዲህ ነው፡፡ አማችን አዋርዶ፣ አማትን እስከ ማሳፈር ይደርሳል፡፡ አሹቅ በማኅበራዊ ግንኙነት ውስጥ ይህን ያህል ችግር የፈጠረ፣ ደረጃው ወደ ሥጋ ቢያድግ ምን ሊያስከትል ኖሯል? ከአሹቅ ወደ ሥጋ እንሸጋገር…

ሴትየዋ ወንድም አላት፡፡ በግ ወይም ፍየል ባረደ ቁጥር፣ ምግብ ሲቀርብ ዕድሜውን ሙሉ አንድም ጊዜ ሳይሳሳት የሚሰጣት የሥጋ ብልት አንድና አንድ ነው – “ታለአይሰጥ” የሚባል :: ታለአይሰጥ ምንድነው? (የቃሉ ጥሬ ትርጉም፣ “እያለው የማይሰጥ” ማለት ነው፡፡) ታለአይሰጥ የወገብ ሥጋ ነው በአራት አቅጣጫ የጎን አጥንትን የመሰሉ፣ ሆኖም በጣም አጫጭር አጥንቶች ያሉት ነው፡፡ በጣዕም በኩል አይታማም፣ እንዲያውም ጥሩ ጣዕም ካላቸው የሥጋ ብልቶች አንዱ ነው፡፡ ሆኖም ሁለት መሠረታዊ ችግሮች አሉበት አንዱ ከራሱ ተፈጥሮ የሚመነጭ ነው፣ ታለአይሰጥ የያዘውን ሥጋ በቀላሉ ማግኘትና መብላት አስቸጋሪ ነው፣ እነዚያ በአራት አቅጣጫ የተጎዳኙት አጥንቶች አጥር ሆነው ያስቸግራሉ፡፡ ለተመጋቢው ፈተና ናቸው፡፡ ተመጋቢው፣ ሥጋውን በጣቱና በጥፍሩ ጭምር እየታገለና እየነጨ ብጥቅጣቂ ሥጋዎችን በማውጣት መብላት ይኖርበታል፡፡ በዚህ መንገድ የሚበላ ሥጋ ሊያጠግብ ቀርቶ፣ አምሮትን አይመልስም፡፡

የታለአይሰጥ ሥጋ የሚበላን ሰው፣ ጎድን፣ ቅልጥም ወይም ፍሪምባ ደርሶት በጥርሱ ጋጥ-ጋጥ፣ ገሽለጥ-ገሽለጥ እያደረገ አፉን ሞልቶ፣ የሥጋውን ለዛ እያጣጣመ ከሚበላና የሥጋ አምሮቱን ጭምር ከሚያረካ ሰው ጋር በዓይነ ህሊናችን እናወዳድር ልዩነታቸው የሰማይና የምደር! 

ሁለተኛው ደካማ ጎኑ ቴክኒካል ነው፡፡ አራጁ የሽንጡ ሥጋ በደንብ እንዲወጣ ካደረገ (ቀደም ባለው ጊዜ ብልትን ጠብቆ ማረድ ከፍተኛ ዋጋ እንደ ሚሰጠው ሳይዘነጋ)፣ ታለአይሰጥ በቂ ሥጋ ከአጥንቱ ጋር የመያዝ ዕድሉ ዝቅተኛ ነው…

ይህ ለእህቱ የታለአይሰጥ ሥጋ ሲሰጥ የኖረ ሰው፣ አንድ ዕለት ይሞታል፡፡ ለቀስተኛው ሙሾ እያወረደ ነው ዘመናዊ ሳይሆን፣ ጥንታዊ ሙሾ… “ዘመናዊው” ሙሾ ቪዲዮ ከመቀረፅም አልፎ፣ በሞንታርቦ የድምፅ ማጉያ እስከ መታጀብ መድረሱ ይሰማል፡፡ ሟች ከተቀበረ ከቀናት በኋላ፣ የሟች ቤተሰቦች ከሳሎን ቁጭ ብለው የለቅሶውን ሒደት ቀርፆ ያስቀረውን ቪዲዮ እያዩ እንደ ገና ያለቅሳሉ ለቅሶ ለሟች ይጠቅመው ይመስል፡፡ ከሁሉ በላይ አስገራሚውና የከፋው ነገር ግን የለቅሶ ታዳሚውን “የለቅሶ ሥራ አፈጻጸም” መገምገሚያ ማድረጋቸው፡፡ ፊልሙን እያዩ ለለቅሶው ታዳሚዎች በተለይም ለሚያውቋቸው ሰዎች “ነጥብ”ና “ደረጃ” ይሰጣሉ፡፡ በአጋጣሚ ሊያውቁት ያልቻሉት ሰው በተለየ ሁኔታ ጥሩ አፈጻጸም ካሳየ፣ ማንነቱን ለማወቅ ብዙ ጥረት ያደርጋሉ፣ የለቅሶ ባለውለታ መሆኑ ነው፡፡

ከሁሉ የከፋው ግን በቅሬታ መዝገብ ላይ የሚያሠፍሯቸውና ጥርሳቸውን የሚነክሱባቸው ሰዎች የመኖራቸው ጉዳይ ነው በተለይ ለሟች ቅርበት ያላቸው ሆነው ዝም ብለው ቆመው ወይም ተቀምጠው፣ በተለይም ደግሞ በአጋጣሚ ሲስቁ ወይም ፈገግ ሲሉ ከታዩ አለቀላቸው፡፡ ሟች ከመሬት ውስጥ ሆኖ፣ ሥጋው የሚበሰብስበትና ወደ አፈርነት የሚቀየርበትን ሒደት ጀምሮ፣ ምድር ላይ ያሉ የነገ ሟቾች፣ “ነግ በ‘እኔ”ን ረስተው፣ ለሟች በማይጠቅመው ሙሾና እየዬ ምድር ላይ ሲጣሉ፣ ቂም ሲያያዙ፣ አብሮነታቸውን ሲያጨልሙ… የጤና ነው አያስብልም?… ሞንታርቦውም ሆነ ፊልሙ የሰውን ልጅ ግብዝነትና ትዕቢት ከማሳየት የራቀ ፋይዳቸው የቱ ጋ’ ነው ያለው?…

ወደ ጥንቱ ሙሾ ስንመለስ ባለታለአይሰጧ ከለቀስተኛው መሀል ገባችና ማልቀስ ጀመረች፡፡ በመሀልም ድምጿን ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፡-

ታለአይሰጥ ሥጋ – ዘወር በል ከፊቴ

ባሏ ሙቶባታል – ላላቅሳት ላይቴ፡፡

ይህ ግጥም ሟች ወንድሟ ይሰጣት የነበረው የታለአይሰጥ ሥጋ ከፊቷ ድቅን እያለ በወጉ እንዳታለቅስ ያስቸገራት መሆኑን ብቻ ሳይሆን፣ ማዕድ ቀርቦ ወንድሟ ለቤተሰቡ ሥጋ ሲያድል ያደርስባት የነበረውን “ዘመን” የፈጀ ጭቆና አደባባይ አሰጣችው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፣ የሞተ ወንድሟን፣ አስክሬኑ መሬት ሥር ሊወተፍ፣ አፈር ሊጫነው የሰዓት ወይም የደቂቃዎች ዕድሜ የቀረውን ወንድሟን ድብን አድርጋ ተበቀለችው ለሕዝብ በማሳጣት፡፡ ሟች ወንድሟን “ወንድሜ” ብላ

ማልቀስ ያለመፈለጓ ነገር ከሁሉም የከፋው ነው፡፡ ይህ ሁሉ ከምን መጣ? ከሆድ! ከእነ ተረቱ “የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል” አይደል የሚባለው? ሊለወጥ የሚችልበት ዕድል ከተዘጋም በኋላ ቢሆን፣ ሆድ-ሆዷን ከሚቆርጣት ፍርጥ አድርጋ መናገሯ ነው፡፡ የሆድ ጣጣው ብዙ ነው ስላችሁ … (በክፍል ስድስት እንገናኝ)

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻ jemalmohammed99@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...