Friday, March 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአፍሪካ ተማሪዎችን የምገባ ተጠቃሚነት ፈተና

አፍሪካ ተማሪዎችን የምገባ ተጠቃሚነት ፈተና

ቀን:

በአበበ ፍቅር

የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ባደጉና የተሻለ ገቢ ባላቸው አገሮች የሚተገበር ቢሆንም፣ ባላደጉትና ይልቁንስ ሕፃናት ተማሪዎች በምግብ እጦት ከትምህርት ገበታቸው በሚፈናቀሉበት አልያም ትምህርታቸውን በረሃብ ምክንያት በአግባቡ በማይከታተሉባቸው አገሮች አቅርቦቱ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡

ለችግሩ ሰፊ ሽፋንና ተደራሽነት አለመኖር እንዲሁም በከፊል አቅርቦት ለሚያገኙትም ተማሪዎች ቢሆን የተመጣጠነ ምግብ አለማቅረብ፣ ወጥነት አለመኖር፣ ተባብሮና ተደጋግፎ አለመሥራት በታዳጊ አገሮች የትምህርት ቤት የምገባ ሥርዓቱን የሚገዳደሩ ናቸው ተብለው ይነሳሉ፡፡

ችግሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ የአፍሪካ አገሮች ላይ ጎልቶ የሚታይ የአያሌ ሕፃናት ተማሪዎች ጉዳይ ነው፡፡ ብዙዎቹ የአፍሪካ መሪዎችና ባለድርሻ አካላት ችግሩን በየፊናቸው ለመፍታት ያደርጉት የነበረው ሩጫ ከችግሩ ስፋትና አንገብጋቢነት አንፃር አመርቂ ውጤትንና ዘለቄታዊ መፍትሔ ማስመዝገብ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2016  የ26ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በተካሄደበት ወቅት መንግሥታት ለትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም መመሪያንና ፖሊሲን በማፅደቅ ነበር የተለያዩት፡፡ በዚህም መንግሥታት ለትምህርት ቤት ምገባ ብለው ከሚበጅቱት ዓመታዊ በጀት በተጨማሪ ለጋሾችና አጋር ድርጅቶችን በማጠናከር በአኅጉሩ ከሚገኙ 54 አገሮች ውስጥ 30 ሚሊዮን ሕፃናትን በትምህርት ቤት የምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ ለማድረግ የጋራ አኅጉራዊ እንቅስቃሴ መጀመራቸው የሚታወስ ነው፡፡

የሕግ ማዕቀፎችን ማፅደቅ፣ ተቋማዊ አቅምን ማሻሻልና ነባር ፕሮግራሞችን ለማስፋፋት የማኅበረሰቡን ተሳትፎ ማነቃቃት ላይ መሥራት እንዳለባቸውና በቀጣይም ባለድርሻ አካላት የበለጠ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩበት የጋራ አቋምን ይዘውም ነበር ወደ ሥራ የገቡት፡፡

ብዙ ፈተናዎች እንደነበሩበት ቢነገርም እ.ኤ.አ. በ2019 ከ65 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት በመላው አፍሪካ የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ እንደነበሩ፣ ይህም እ.ኤ.አ. ከ2013  ከነበረው 38.4 ሚሊዮን በላይ ጭማሪ እንዳለው ኅብረቱ በተማሪዎች ምገባ ዙሪያ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ባካሄደው ስብሰባ ገልጿል፡፡

ኅብረቱ በጥሩ ሁኔታ የተነደፉ የትምህርት ቤት የምገባ መርሐ ግብሮች በአራት ጠቃሚ ዘርፎች ማለትም በትምህርት፣ በሥነ ምግብ፣ በማኅበራዊ ጥበቃና በአካባቢ ግብር ላይ ሁሉም ወደ ሰው ካፒታል ዕድገትና ዘላቂ ልማት እየተሸጋገሩ መምጣታቸውንም ጠቁሟል፡፡

ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓትና የተመቻቸ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን የሚያኙ ተማሪዎች ውጤታማ፣ ለአገርና አኅጉር ብሎም ለዓለም የሚተርፍ መሆናቸው ቢታወቅም፣ በአፍሪካ ውስጥ ከ60 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሕፃናት አሁንም የትምህር ቤት ምገባ ፕሮግራም ሳያገኙ የከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡

ሁሉንም የአፍሪካ ሕፃናት ተማሪዎች ለመመገብ ደግሞ በዓመት 3.8 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) እንዲሁም የአፍሪካ ተወካዮች በተገኙበት መድረክ፣ በኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ደረጃ አመርቂ የሚባል ውጤትን ብታሳይም፣ በአገሪቱ የተንሰራፋው ግጭት፣ ድርቅ፣ የምግብ አቅርቦትና ሌሎች ችግሮች የትምህርት ቤት ምገባ ተደራሽ እንዳይሆን ማድረጋቸው ተነስቷል፡፡

በዚህም በርካታ ሕፃናት በትምህርት ቤት መዋል ሲገባቸው ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ ይሁን እንጂ በአዲስ አበባ ባሉ ትምህርት ቤቶች ያለው የምገባ መርሐ ግብር ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች ምሳሌ እንደሚሆን ከንቲባ አዳነች ተናግረዋል፡፡

በመዲናዋ ለተማሪዎች ምገባ 4.6 ሚሊዮን ብር ተበጀቶ 700 ሺሕ ተማሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ፕሮግራሙ ከአራት ዓመት በፊት የተጀመረ ሲሆን፣ በወቅቱ 17 ሺሕ ገደማ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ተደራሽ ያደረገ እንደነበር አንስተው፣ ጅምሩን በማስፋፋት በከተማዋ ባሉ ሁሉም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 700 ሺሕ ተማሪዎችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉንና ለ16 ሺሕ እናቶች የሥራ ዕድልን መፈጠሩን ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ በርካታ ተፈጥሮአዊና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ትምህርት ጥራት ላይ አደጋ ደቅነው መቆየታቸውንና ችግሮችን ለመቅረፍ የትምህርት ቤት ምገባ እንደ አንድ ሥልት እንደተጠቀሙበት ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) ገልጸዋል፡፡

‹‹ከፍተኛ ጥራት ያለውን ትምህርት ማቅረብና በሰው ኃይል መዋዕለነዋይ በማፍሰስ ጠንካራ አኅጉር መፍጠር ተግዳሮቶችን ለመፍታት ይረዳናል፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት አሥር ዓመታት ጥራት ያለው ትምህርት ለማቅረብ ብዙ ርቀትን ብትጓዝም፣ ጥቂት የማይባሉ ታዳጊዎች በግጭት፣ በድርቅና በምግብ እጥረት ከትምህርት ቤት ውጪ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ይህም ዜጎች ከአገራቸው በፍትሐዊነት ሊያገኙ የሚገባቸውን ጥቅም አሳጥቷቸዋል  ሲሉ አክለዋል፡፡

ፍትሐዊና ጥራት ያለው ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ የተሻለ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ያሉት ብርሃኑ (ፕሮፌሰር)፣ ይህንን እውን ለማድረግ ትምህርት ሚኒስቴር በአሥር ዓመት ፍኖት ካርታውና በፖሊሲ ደረጃ እየሠራበት ይገኛል ብለዋል፡፡

ይህ ፖሊሲ በ2030 በአንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ሁሉም ተማሪዎች ቢያንስ በቀን አንዴ የመመገብ ዕቅድን የያየዘ ነው፡፡

የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ከአኅጉራዊ የትምህርት ስትራቴጂና ግብርና ጋር በመቀናጀት ከፍተኛ የሆነ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ እንዳለው የተናገሩት የአፍሪካ ኅብረት የትምህርት፣ የሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽ ኮሚሽነር መሐመድ በኤልሆሲን ናቸው፡፡

እንደሳቸው ገለጻ፣ የትምህርት ቤቶች የምገባ መርሐ ግብር ገበያን ለማረጋጋትና ለማስተዋወቅ የሚረዳ ሲሆን፣ የእሴት ሰንሰለቱም ኢኮኖሚያዊ ትርፍ የሚያስገኝና ለዘላቂ ልማት በር ከፋች ነው ብለዋል፡፡

ኮሚሽነሩ አክለውም፣ ገበያውንና ኢኮኖሚውን ከማስተዋወቅ በተጨማሪ በቤት ውስጥ የሚጀመረው የትምህርት ቤት ምገባ የእሴት ሰንሰለቶች ለዘላቂ ልማት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንደሚያስገኝ አመላክተዋል፡፡

መርሐ ግብሩ የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ዓላማን የሚያጎለብት ሲሆን፣ ይህም በአፍሪካ ያለውን የንግድ ልውውጥ የሚያሳድግ ነው ተብሏል፡፡

ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ካለፈው አንድ ዓመት ተኩል ወዲህ የአገር ውስጥ ፋይናንስ በ15 በመቶ ጨምሯል ሲሉ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዳይሬክተር ከርመን ባርቦን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የትምህርት ምገባ ፕሮግራምን ለመተግበር በየዓመቱ 85 ሚሊዮን ዶላር በመመደብ ላይ መሆኑን ሰምተናል ብለዋል ዳይሬክተሯ፡፡

ይህን ሓሳብ በማጠናከር መንግሥት ለአገር አቀፍ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም በየዓመቱ 85 ሚሊዮን ዶላር ከአገር ውስጥ በጀቱ መመደቡ ተደራሽነትንና ትኩረት መስጠቱን የሚያመላክትና በአፍሪካም አርአያነት ያለው ተግባር መሆኑን አክለዋል፡፡

ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አሁናዊ የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ከመዲናዋ ካሉ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ያልዘለለ ነው በማለት ብዙዎች ያነሳሉ፡፡ በተለይ ግጭቶችና ድርቅ ባለባቸው አካባቢዎች የምገባ ፕሮግራሙ ተደራሽ ባለመሆኑ በርካታ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለመከታተል ከባድ እንደሆነባቸው ይናገራሉ፡፡

ረጂ ድርጅቶች የሚያደርጉት ድጋፍ የሚያበረታታ ቢሆንም፣ ከአንድ ዓመትና ከሁለት ዓመት የዘለለ ርቀትን መጓዝ ሲያቅታቸው ይስተዋላል፡፡ መንግሥትም እስከ 2030 ተግባራዊ አደርገዋለሁ ያለውለ አገር አቀፍ የተማሪዎች ምገባ መተግበር አለበት የሚሉ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...